ቅድመ-ታሪክ
ሰሜን ሸዋ ኤፍራታና ግድም ያፈራችው ዘነበ ልጅነቱን እንደ እኩዮች ሲቦርቅ አሳልፏል:: ከቀዬው ባልንጀሮቹ ጋር መልካም የሚባል ጊዜ ነበረው::ሜዳ እየዋለ፣የከብቶች ጭራን እየተከተለ ክረምት ከበጋን ገፍቷል :: ከፍ ሲል ወላጅ እናቱ አዲስ አበባ ዘለቁ::ብቻቸውን አልነበሩም :: ገና አፉን በወጉ ያልፈታ ህጻን ልጃቸውን አስከትለዋል::
ዘነበ የአንደበቱን መኮላተፍ፣የልጅነቱን ማማር ያዩ ሁሉ ወደዱት :: ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የሆኑት እናት አዲስ አበባ እንደከተሙ ከብዘዎች ተግባቡ::ውሎ አድሮም ኑሮን ለመግፋትና ልጃቸውን ለማሳደግ መተዳደሪያቸውን ፈለጉ:: ከተማዋ ለእሳቸውና ለህጻኑ ጉሮሮ አልነፈገቻቸውም:: በጉልበታቸው ድካም፣ በላባቸው ወዝ እያደሩ ልጃቸውን ማሳደግ ያዙ ::
የዕለት ጉርስ ሞልቶ የሃሳብ ሲደርስ ለነገ ማሰብ ግድ ነው:: የሆድ ነገር ጊዜ አይሰጥም:: አንዱ ቀዳዳ ሲደፈን ሌላው ደግሞ ይተካል::የዘነበ እናትም ዛሬን በልተው ሲያድሩ ስለመጪው ቀን ያልማሉ::የትንሹ ልጃቸው ምቾት፣ የእሳቸው በጤና ውሎ ማደርና ሌላም ጉዳይ ያሳስባቸዋል ::
አዲስ አበባን ብዙዎች ለኑሮ ይመርጧታል::በርካቶች ህይወታቸው በከተማዋ ማዕድ ጣፍጧል::ጥቂት የማይባሉት ከገጠር ወጥተው ከተሜ ለመሆን አፍታ አልፈጀባቸውም::ከእነዚህ መሀል ለቁጥር የሚያዳግቱ ያሰቡት ተሳክቶ ሕይወታቸውን ለውጠዋል::ለሰዎች መኖር ያስፈልጋል ከሚባለው የበዛውን አሟልተውም ወፍራም ስም ካላቸው ረድፍ ተቆጥረዋል::
እነዚህ ሰዎች እዚህ እስኪደርሱ በበርካታ ውጣውረድ ያልፋሉ:: በርካቶች ከተማዋን ሲረግጡ የመኖሪያ ቤት ችግርን በተለየ ፈተና ሊጋፈጡት ግድ ነው:: በአዲስ አበባ ለጎን ማረፊያ ከተገኘ ሌላው ችግር ዕዳው ገብስ ነው የሚባልላት አገር ነች ::
ይህን የሚያውቁ አንዳንዶች ከከተማዋ ፈቀቅ ብለው የ‹‹ጨረቃ›› የሚባሉ ቤቶችን ይቀይሳሉ::አንዱ ሌላውን እየተከተለ፣ ሌላውም ሌላ ወገኑን እየሳበ ስፍራውን በደቦ ይቀይራል:: ተቃዋሚ ከጠፋ የላስቲክ ቤቱ በእንጨት፣ የእንጨቱም በብሎኬት ይተካል:: አጥር የሌላቸው ቀስበቀስ ወሰናቸው ይከበራል:: ቤቶቹ መብራት ከውሃ ገብቶላቸው እስከ መከራየት አንዳንዴም በጥሩ ዋጋ እስከመሸጥ ይደርሳሉ::
እነዚህ ቤቶች ውሎ አድሮ መንደር ይሆናሉ:: ደምቀውም ነዋሪን ያበረክታሉ:: በዓመታት ቆይታም የሰፈር ስያሜ ተችሯቸው ህገወጥ ተብለው ሊፈርሱ አልያም ህጋዊ ሆነው ሊቀጥሉ የዕድላቸውን ይሞክራሉ ::ይህ እውነት ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ አዲስ አበባ በሚመጡና በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ጭምር የተለመደ ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል::
የዘነበ እናት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ወገኖች ለመመደብ አቅሙ የላቸውም::ይህን ይሞክሩ ዘንድም ‹‹አለንሽ›› ባይ ዘመድ አላገኙም::ልጃቸውን ይዘው እንደአቅም በሚከፈሉ ጥቂት የኪራይ ቤቶች ዞረዋል:: እንግድነታቸውን ያስረሳቸው የጣሊያን ሰፈርና አካባቢው ከልጃቸው ጋር በሰላም አውሎ ያሳድራቸዋል::
ድንገቴው ዕድል
ከዕለታት በአንዱ ቀን ወይዘሮዋ ካልታሰበ ዕድል ጋር ተገጣጠሙ:: ቀሪ ዘመናቸውን በእፎይታ ይኖሩበት ዘንድ የቀበሌ ቤት እንዳገኙ ተነገራቸው:: ለእሳቸው ታላቅ የሚባል የምስራች ሆነ ::ይህኔ የዘነበ እናት ያለፈውን ችግር ረስተው ስለነገው ህይወት በታላቅ ተስፋ ተሞሉ::ደግመው ደጋግመው ይህን ላደረገ ፈጣሪያቸው ምስጋና አቀረቡ:: ብዙዎች በመኖሪያ ቤት እጦት በሚቸገሩባት ከተማ በአነስተኛ ዋጋ ቤት ማግኘት ለእሳቸው ተአምር ነበር::
ወይዘሮዋ መለስ ብለው ስለልጃቸው ነገ አሰቡ ::ከዚህ በኋላ ትንሹ ዘነበ ትምህርት ቤት ገብቶ ቀለም ይቆጥራል::በዕውቀት በልጽጎም ለራሱና ለእሳቸው ጭምር ይተርፋል:: አገር ቤት ሳለ የቀለም ሀሁን አላየም::ልጅነቱን ባሳለፈበት ቀዬ ቦርቆ ከመዋል የዘለለ ዕጣፈንታ አልነበረውም::
የኤፍራታዋ ወይዘሮ አሁን የጣሊያን ሰፈር ነዋሪ ለመሆን ጓዛቸውን ሸክፈዋል:: የተሰጣቸውን ቤትም ተረክበዋል::ቤቱ አሮጌና ደሳሳ ቢጤ ነው:: ወለሉ እምብዛም እግርን የሚያላውስ አይደለም::እናትና ልጅ ከሙሉ ጓዛቸው ጋር ሲይዙት ደግሞ በእጅጉ ይጨናነቃል::
ለችግሩ መፍትሄ አልጠፋም:: ከጠባቡ አንድ ክፍል ወደ ጣራው ዘለግ ብሎ ባለ መወጣጫ የቆጥ ክፍል ተቀየሰ::በዚህ ክፍል አልጋ ተዘርግቶ ፍራሽ ተጣለበት::ሁለመናው ተሰናድቶም ጥሩ መኝታ ቤት ወጣው:: የታችኛው ክፍልም ቀሪ ኮተቶችን በሆዱ አጭቆ የሳሎን ስያሜ ተቸረው ::
የእናትና ልጅ ህይወት በምድርና ፎቅ መሰል ቤት ውስጥ ቀጠለ::ሁሉን እንደ መልኩ አሳዳሪዋ አዲስ አበባ ሁለቱን ነፍሶች ከነበሩበት አውጥታ ከአካባቢው አቆራኘቻቸው:: ዘነበና እናቱ የጣሊያን ሰፈር ነዋሪዎች መሆናቸውን አረጋገጡ::
ቀለም ቆጠራ
ለዘነበ አዲስ አበባ ትምህርት አልነፈገችውም::እንደ እኩዮቹ የቀለም ሀሁን ይቆጥር ዘንድ መንገዱን አሳየችው::ከአቻዎቹ ጋር ትምህርትቤት ውሎ ሲመለስ እናቱ በደስታ ተሞሉ::ስለነገው ህይወት አንድ እርምጃ ማከሉን አስበውም ታላቅ ተስፋ ጣሉበት::በትምህርቱ የበረታው ታዳጊ ክፍሎችን በጽናት ተሻገረ::
አንደኛ ደረጃን ሲያጠናቅቅ ወደቀጣዩ ደረጃ ለመጓዝ እርግጠኛ ነበር::ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን አልፎ እስረኛ ላይ ሲደርሰም ጥንካሬው አብሮት ነበር::እሱና እናቱ ኑሯቸው እምብዛም በመሆኑ ገቢያቸው አነስተኛ ነው::ዛሬን ጠግበው ቢያድሩ ስለነገው ማሰብ ግድ ይላቸዋል::ተሯሩጠው አዳሪዋ ሴት አንዳንዴ እጅ ያጥራቸዋል::
እንዲህ በሆነ ጊዜ ጎናቸውን የሚደግፉት ከቆጡ በታች ያለውን የሳሎን ወለል አከራይተው በሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ ነው::ሳሎኑ በቂ የሚባል ስፋት የለውም::ያም ሆኖ ግን የአቅሙን ያህል ተከራይቶ ገቢ ያመጣል::
በዚህ ሳሎን ዓመታትን የተጋሩት አዛውንቱ በቀለ ከወለሉ ጎናቸውን አሳርፈው ቀናትን ተሻግረዋል::ሰውየው ልጆች እንዳላቸው ቢወራም ለአንድም ቀን ‹‹አባታችን›› ሲሉ ሲጠይቋቸው አልታዩም:: ብቸኛው ሰው ዓመታትን በዝምታ ሲያልፉም ስለልጆች አውርተው አያውቁም::
ከልጆቻቸው መሀል ለአንደኛው እጃቸው ባገኘ ጊዜ የአቅማቸውን ያደርጋሉ::ልጁ አባቱ ጣሊያን ሰፈር በኪራይ ስለመኖራቸው ያውቃል::ከራርሞ ሲያገኛቸው ግን ቤታቸውን ስለማየት አያነሳም :: እሳቸውም ቢሆኑ እንደ አባት ‹‹ቤቴን ላሳይህ›› ማለትን አያስቡም::
በጣሊያን ሰፈር ቤቶች መሀል ከቆመች ደሳሳ ጣራ ስር የሶትዮሽ ህይወት ቀጥሏል::እናትና ልጅ ከፎቅ መሰል ቆጥ ላይ ፣አዛውንቱ በቀለም ከእነሱ በታች ካለች ሳሎን መሰል ወለል አንጥፈው ሌሊቱን ያነጋሉ ::በቀለ ወር ሲደርስ የሚከፍሉትን አንድ መቶ ሃምሳ ብር ጊዜውን ጠብቀው ይሰጣሉ ::ለጓዳቸው ቀዳዳ የሚሹት ወይዘሮም የተሰጣቸውን ብር ከሌላ ጋር አብቃቅተው ስለነገው ያስባሉ::
አሁን ዘነበ የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል :: እናቱ በቅርብ ባይኖሩም እንደትናንቱ ኑሮን ለመግፋት ትግሉን አላቋረጠም::ከቆጡ ላይ አድሮ ሲወጣ ከወለሉ የሳር ፍራሽ አንጥፈው የሚያድሩትን አዛውንት ያያቸዋል:: አመታትን በደባልነት ያሳለፉት በቀለም ከቆጥ ማደሪያው ወርዶ በእሳቸው ጥግ የሚራመደውን ወጣት ኮቴ እያደመጡ በዓይናቸው ይሸኙታል::ይህ እውነት ላለፉት አስርት ዓመታት በተለመደው መልኩ ቀጥሏል::
ዘነበ የእናቱ በቅርብ ያለመኖር የህይወት አቅጣጫውን አልቀየረም::እንደትናንቱ ትምህርት ቤት ውሎ ይመለሳል፤ እንደቀድሞውም ወር ጠብቆ ከአዛውንቱ ተከራይ ገንዘብ ይቀበላል :: ይህ ገንዘብ ለእሱ መተዳደሪያው ሆኖለታል:: ሽማግሌው እስካሉ ገንዘቡ አይቀርም :: እሳቸው ገንዘቡን እስከከፈሉም የመኖር መብታቸው ይጠበቃል::
የቀን ክፉ
ለሊቱ ተጋምሷል:: ከጣሊያን ሰፈር ነዋሪዎች አብዛኞቹ በከባድ ዕንቅልፍ ውስጥ ናቸው::የነዘነበ ቤት በር ጥርቅም ብሎ ከተዘጋ ሰአታት ተቆረዋል::ሽማግሌው በቀለ ጎናቸው ከማረፉ የሚጀምሩት ማንኮራፋት ደምቆ እየተሰማ ነው::
ከቆጡ ማደሪያ ጋደም ያለው ዘነበ ግን ዕንቅልፍ በአይኑ አልዞረም::ሆዱን በእጁ ጥርቅም አድርጎ በአልጋው ዙሪያ ይንቆራጠጣል:: እንደዋዛ የጀመረው ቁርጠት ፋታ እየሰጠው አይደለም::ደጋግሞ እያሰቃየ በላብ አስምጦታል::ጥቂት ቆይቶ ዘነበ አንዳች ሀይል ሲያጣድፈው ተሰማው:: ሊይዘው ሊመልሰው ሞከረ:: አልቻለም::
የቆጡን መወጣጫ ይዞ በፍጥነት ወደ ወለሉ ተንደረደረ፤ ሽማግሌውን በጨረፍታ አያቸው::ከሳር ፍራሻቸው ላይ ባደረጉት አሮጌ ብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ዕንቅልፍ ጥሏቸዋል:: እንደምንም አልፏቸው ከአንድ ስፍራ ቁጢጥ አለ::ያጣድፈው የነበረው ሀይል ከሆዱ አፈትልኮ ሲወጣ ሰላም ተሰማው :: ‹‹እፎይ…›› አለ::
ያሰበውን ሲጨርስ አዛውንቱን ዳግመኛ አያቸው :: ካሉበት ንቅንቅ አላሉም:: ከእሳቸው ቅርበት የተወውን ነውር መለስ ብሎ ማየት አልፈለገም። በነበረበት ትቶ ተራምዷቸው አለፈና በቆጡ መሰላል ተራመደ:: ከአልጋው እንዳረፈ ዕንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደው::
ወፎች ሲንጫጩ ሽማግሌው ከዕንቅልፋቸው ነቁ። የለበሱትን የሌት ልብስ ከላያቸው አንስተውም ለመውጣት ተዘጋጁ::ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ዓይናቸው በአንድ ጉዳይ ተሳበ፤ ከመኝታቸው አጠገብ የሆነውን ባዩ ጊዜም በሀዘን አንገታቸውን ደፉ::
በትካዜ ጥቂት ቆይተው በሩን ከፍተው ወደውጭ ዘለቁ:: አዝነዋል::ከመንገድ ያገኟቸው አንዳንዶች ፊታቸውን አይተው ምክንያቱን ጠየቋቸው:: አቶ በቀለ ፊታቸውን ሳይፈቱ የሆነውን ሁሉ ተናገሩ::ስለእማኝነቱም ሰዎቹን ከቤት ወስደው ማስረጃውን ‹‹እነሆ›› ሲሉ አሳዩ::
ጉዳዩን የሰሙና ያዩ ሰዎች በአንድ ጀምበር ወሬውን በመንደሩ አዳረሱት። ዘነበ በአዛውንቱ ራስጌ ላይ የፈጸመውን ድርጊት እየተቀባበሉም አዳመቁት::እውነቱን የሰሙ ጓደኞቹ ወሬውን ትምህርት ቤት ለማድረስ አልዘገዩም::አጋጣሚው ሳቅና ስላቅን ፈጠረ::ዘነበን ያዩ ሁሉ እጃቸውን ቀስረው ተሳለቁ::አፋቸውን ሸብበው አንሿከኩ::
ይህ ፈተና የደረሰበት ዘነበ በወሬው ብዛት አንገቱን ደፋ :: በነጻነት ለመራመድ ተሳቀቀ::ትምህርት ቤት ሲሄድና ሲመለስ እግሮቹ መርገጫ እስኪያጡ ግራ ገባው:: ሰፈር ለመዋል፣ ትምህርት ለመማር አዳገተው::ይህ ሁሉ መነሻ ደባሉ ሽማግሌ መሆናቸውን ሲያውቅ በአቶ በቀለ ላይ ቂም ያዘ ::ወደቆጥ ማደሪያው ሲወጣና ሲወርድ ጥርሱን እየነከሰ በዛቻና ማስፈራራት ቀን ቆጠረ::
ሰኔ 10 ቀን 2006 ዓ.ም
አቶ በቀለና ተማሪው ዘነበ በየፊናቸው ከዋሉበት ተመልሰው በቤታቸው ደርሰዋል::ሰአቱ ጊዜ ቢሆንም ሁለቱም በየማደሪያቸው ጎናቸውን አሳርፈዋል::ዘነበ አሁንም ቂሙን አልረሳም::መክረሚያውን በጓደኞቹ፣በትምህርት ቤትና በመንደሩ ነዋሪ የደረሰበት ስም መጥፋት እየከነከነው ነው::ለዚህ ሁሉ ስብራት ምክንያት የሆኑት አዛውንት ዛሬም አብረውት ይኖራሉ:: አሁንም ባያቸው ቁጥር ይናደዳል፤ ይበሽቃል::
የዛሬው ምሽት ሁኔታው ግን ከሌሎች ቀናት ተለይቷል:: ከዚህ በኋላ እሳቸውን ባየ ጊዜ እራሱን መጎዳት እንደሌለበትና አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ወስኗል::ይህን ሲያስብ ‹‹በል አድርገው ›› የሚል ሀይል ሞገተው::ይህን ሀይል እንደዋዛ ሊመልሰው አልፈለገም:: ውስጡን ከፍቶ የትኩሳቱን ስር አስነካው፣ ስሜቱን አስደመጠው፣ቁጭት ንዴቱን አሳየው::ስሜቱና ነባር ውስጠቱ በአንዴ ተናበው ተስማሙ፤ወዲያው ከነበረበት ተነስቶ በቆጡ መሰላል ቁልቁል ተንደረደረ ::
አዛውንቱ በእጁ ላይ ያለውን ትልቅ ጩቤ ሲያዩ በድንጋጤ ጩኸት ጀመሩ::‹‹ልጄ አትግደለኝ፣ተወኝ፣ተወኝ፣ አያሉ ተማጸኑ:: ዘነበ ጩኸት ተማጽኖውን አልሰማም። አጠገባቸው ሲደርስ ንዴት ያዘው ::ያለፈው ወሬና የስሙ መጥፋት ታሪክ ውል አለበት::ይህኔ ደጋግሞ ግራና ቀኝ ጎናቸውን ወጋቸው::መልሶ ልባቸው ላይ ሰነዘረ :: አልሳታቸውም::ሁሉን ፈጽሞ ሮጦ ወጣ::
ሽማግሌው በቁመታቸው ተዘረሩ::ደማቸው እየፈሰሰ በተዳከመ ድምጽ ለእርዳታ ተጣሩ::ጩኸታቸውን የሰሙ ጎረቤቶች ሲሮጡ ደረሱ::መጎዳታቸውን እንዳዩ ታክሲ ይዘው ሆስፒታል አደረሷቸው::የገቡበት ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላካቸው::
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀሉ መፈጸም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ በጩቤ ተወግተው ጉዳት የደረሰባቸው ሰው ዘንድ ቀርቦ ቃላቸውን ተቀበለ::ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ የአቶ በቀለ ህይወት ማለፉ ተሰማ:: ፖሊስ አስቀድሞ በያዘው መረጃ ተጠርጣሪውን ለማግኘት ክትትሉን ቀጠለ::ጉዳዩን በምርመራ የያዘው ረዳት ኢንስፔክተር ታፈሰ ዘበርጋ በፋይል ቁጥር 948/06 በተከፈተው ዶሴ የዕለት ሁኔታዎችን እያሰፈረ ቆየ::
ፖሊስ ተፈላጊውን ወጣት አላጣውም::እግር በእግር ተከታትሎ በቁጥጥር ስር አዋለው::ሙሉ ቃሉን ሲቀበል ድርጊቱን በቂም በቀል ተነሳሳቶ ስለመፈጸሙ አመነ::የሰጠውን ቃል በእማኝነት መዝግቦ ለህግ ይቀርብ ዘንድ ለዓቃቤ ህግ አስተላለፈ::
ውሳኔ
ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የአራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆን ብሎ ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሰውን ወጣት ጉዳይ ለመዳኘት በቀጠሮው ተገኝቷል::ዕለቱ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት እንደመሆኑ በርከት ያሉ ሰዎች ታድመዋል::ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በፈጸመው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኝነቱን በማረጋገጡ ‹‹ይገባዋል›› ያለውን የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ታሳቢ ይሆን ዘንድ በይኗል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
መልካምስራ አፈወርቅ