ታማሚው ከሕመማቸው ፋታ ያገኙ ዘንድ ሆስፒታል ደርሰዋል:: የእለቱ ተረኛ ዶክተር በስራ ላይ ናቸው:: ሌሎች ታካሚዎችን ሸኝተው በተራቸው ወደ ምርመራ ክፍል እንዲገቡ አዘዙ:: ታካሚው ሳል ያጣድፋቸዋል::ምናቸውን እንደሚሰማቸውና እንደሚያማቸው ለማስረዳትም ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ ይል ነበር:: ወባ እንደያዘው ሰው ይንቀጠቀጣሉ:: ቁርጥማት እንደሚያማቸውም ተናገሩ:: ዶክተሩ የሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትራቸውን ከታማሚው ብብት በማስጠጋት የሰውነታቸውን ሙቀት ፈተሹ:: ታማሚው ሙቀታቸውም ከፍ ብሏል::ዶክተሩም ጥርጣሬያቸው ከፍ አለ፤ስጋትም አደረባቸው::
ዶክተሩ ቀና ብለው ትንፋሻቸውን ሳብ አድርገው ምልክቶቹን ደግመው አስታወሱ:: ወደ የትኞቹ በሽታዎች ሊቀራረቡ እንደሚችሉም አሰቡ:: ሳል፣ብርድ ብርድ ማለት፣ሙቀት መጨመር፣ቁርጥማት እኒህ ታማሚ ላይ መስተዋላቸው ምን ሊሆን ይችላል? ጥያቄውን የሚያቀርቡት ለራሳቸው ነበር:: ወባ?፣ ቲቪ(ሳንባ ምች)?፣ ታይፎይድ?፣ ማጅራት ገትር?፣ኮሮና? …ወዘተ::
ዶክተሩ ደጋግመው አሰቡ:: የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በየእለቱ የሚያሳየው መጨመር ታወሳቸው:: ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው ተግባራቸውን እየተወጡ ስለመሆናቸው ራሳቸውን ፈተሹ:: ምልክቶቹ የበርካታ በሽታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም በማሰብ ውስጣቸውን አረጋጉት:: እርግጠኛ መሆን እንደማይቻልም ለራሳቸው ነገሩት:: ምክንያቱም በመገመት ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደማይቻል የሙያቸው ሥነምግባር ጽኑ ክልከላ የሚዘነጋቸው አይደለም:: የበሽተኛውን ሕመም ለይተው ሊያረጋግጡ ወደሚችሉባቸው ክፍሎች በማዘዝ ናሙናዎች እንዲሰጡና ውጤት ሲደርስላቸውም ይዘው እንዲመጡ ነግረው ከሌሎች ታካሚዎች ጋር መደበኛ ስራቸውን ቀጠሉ::
የዚህ አይነት ምልክቶች በታማሚ ላይ ሲስተዋሉ በርካታ በሽታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ቢጠራጠሩም ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ስጋት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ባለሙያዎች እስኪያረጋግጡ ድረስ ጥርጣሬዎች ያድሩባቸዋል:: አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አገልግሎት ለመስጠት ራሳቸውን ያዘጋጃሉ:: የሕክምና ባለሙያዎቹ እርስበርስ በመወያየትም አስፈላጊ የመገልገያ ቁሳቁሶችን ዝግጁ አድርገው ሊጠባበቁ ይችላሉ:: ይሄ የሚሆነው አንድም ኢትዮጵያን ጨምሮ የመላው ዓለም ስጋት የሆነው ኮሮና ወረርሽኝ ቫይረስ በበሽተኛው ላይ ስለመኖሩ ከመለየቱ በፊት በሚፈጠሩ የንክኪ ሂደቶች በሽታው ወደሌሎች ታካሚዎች እና አገልግሎት ወደሚሰጡት የሕክምና ባለሙያዎች እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሲባል ነው::ሁለትም ኮሮና ቫይረስ መሆኑ ከተለየ ወደተዘጋጀላቸው የሕክምና አገልግሎት መስጫ በመውሰድ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ስለሚረዳም ጭምር ነው::
የታማሚው የምርመራ ውጤት ተጠቃልሎ ደርሷል:: ባለሙያዎቹ ሰብሰብ ብለው ተነጋገሩ::ማረጋገጥ የሚገባቸውን ጉዳዮችም ደጋግመው በማጤን በራጂ ማሽኖቻቸው አረጋገጡ:: በውጤቱ መሰረትም ታማሚው በቲቪ በ(ሳንባ ምች) በሽታ መጠቃቱ ተለይቷል:: አስፈላጊውን መድሐኒትና ክትትል ወደሚያገኝበት ክፍል ገብቷል::
የዚህ አይነት ሁኔታዎችና ገጠመኞች በተለያዩ የአገሪቱ ጤና ተቋማት ሊገጥሙ እንደሚችሉ የሚታመን ቢሆንም ጽሑፉ የተዘጋጀው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በአማራ ቴሌቪዥን ሰኔ ወር መጀመሪያ ሳምንት የቀረበ ፕሮግራምን መነሻ በማድረግ ነው:: የባለሙያዎችን አስተያየትም ለማካተት ተሞክሯል:: በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምልክቶች ከሌሎች በሽታዎች ጋር የሚኖረው ተመሳሳይነት፣ የሕክምና ተቋማት ተግባራቸውን እንዴት አጣጥመው መሄድ እንደሚገባቸው፣ ባለሙያዎች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች፣ ታካሚዎች በበሽታዎች ምልክት መመሳሰል መደናገጥም ሆነ መታለል እንደማይገባቸውና ሕክምና ተቋማት በመምጣት ሊታከሙ እንደሚገባቸው ግንዛቤ በሚፈጥር መልክ ተሰናድቷል:: የአዲስ ዘመኗ ማህደረ ጤና አምድ እንዲህ አሰናድታ ለአንባቢያን እንካችሁ ብላለች::
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምልክቶች ከሌሎች በሽታዎች ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ይኖረው ይሆን? በአማራ ክልል ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ጥላሁን ቢራራ እንዳሉት በጤና ሚኒስቴር ደረጃም ሆነ በጤና ተቋማት ደረጃ የተያዙት አቋሞች ከኮሮናም በላይ ሌሎች ተያያዥ ሕመሞች የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ ስለሆኑ ከኮሮና መከላከሉ እኩል ማስኬድ እንዲቻል ተደርጓል:: ለሁሉም በሽታዎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል::
አንድ ሙቀት ያለው ታማሚ ሲመጣ ባለሙያዎቹም ሊደናገጡ አይገባቸውም:: ኮሮና ሊሆን ይችላል በሚል መፍራትና መሸሽ ሳይሆን የሙያው ስነ ምግባር በሚያዘው ልክ ተንከባክቦ አስፈላጊውን ሕክምና መስጠት አስፈላጊ ነው:: በታካሚው በኩልም አንድ ትኩሳት የሚያስከትል በሽታ በያዘው ቁጥር ኮሮና ሊሆን ይችላል በሚል ስጋትና ለይቶ ማቆያ ሊያስገቡኝ ይችላሉ በሚል ስጋት በቤት ውስጥ መደበቁ ተገቢ አይሆንም:: ምክንያቱም ሙቀት የሚያስከትለው በሽታ ኮሮና ብቻ ሳይሆን ወባ፣ ታይፎይድ፣ ማጅራት ገትር፣ቲቪ እና ሌሎቹም ሊሆኑ ይችላሉ:: በዚህ የተነሳ በቶሎ አገግሞ ለሥራ መመለስ ይቸግራል::ሕይወትን ማጣትም ሊኖር ይችላል:: ከፍርሃትና ከሽሽት በመላቀቅ ወደጤና ተቋማት መሄድና ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ይኖርባቸዋል::
ከኮሮና ወረርሽኝ ራሳቸውን ለመከላከልም በባለሙያዎች የተቀመጡ ምክሮችን መተግበር አለባቸው:: ማስክ መልበስ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ እጅን በሳሙናና በውሃ ቶሎቶሎ መታጠብ፣ ከአላስፈላጊ ንክኪና እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ መከላከል ይችላሉ:: ገዳይ ከሆነው የወባ በሽታም ዛንዚራ፣ አጎበር በመጠቀም፣ በአካባቢቸው ያቆሩ የውሃ ኩሬዎችን በማጽዳትና በማፋሰስ መከላከል ይኖርባቸዋል:: ቲቪ (የሳንባ ምች) ያለበት ሰው ሳል አለው፤ ብርድብርድ ይለዋል፤ ሙቀት አለው፤ ቁርጥማት ይኖርበታል:: ስለዚህ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ይመሳሰላል:: የዚህ አይነት ሁኔታ ሲገጥም በሽታው በሕክምና ምርመራ እስኪለይ ድረስ ፍርሃትና መሸበር ውስጥ ባለሙያዎችም ሆኑ ታካሚዎች እንዲሁም አስታማሚዎች ሊፈጠርባቸው እንደማይገባ ዶክተሩ ተናግረዋል::
በአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ወረርሽኝ ማጥፋና መከላከል አማካሪ አቶ አማረ ደስታ በበኩላቸው የበርካታ በሽታዎች ምልክቶች ከኮሮና ቫይረስ ጋር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊመሳሰሉ ይችላሉ:: ነገር ግን ወደ ሕክምና ተቋማት ሳይሄዱ ይሄ በሽታ ነው በሚል መድሃኒት ገዝቶ መውሰድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው:: ታማሚው ተመርምሮ በሽታውን በማወቅ ሊታከም ይገባል::
ለምሳሌ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት ስለታየበት ወባ ነው ማት አይቻልም:: ሌላ በሽታ ሊሆን ይችላል:: የወባ ዝርያዎችም ቢሆኑ የተለያዩ በመሆናቸው ተመርምሮ አይነቱን በመለየት ሊያድን የሚችለውን መድሐኒት ለይቶ መውሰድ አስፈላጊ ነው:: ሰዎች ያን ሳያደርጉ መድሐኒቱ አላድነኝ እስከማለት እንደሚደርሱ ተናግረዋል:: ወባና ተመሳሳይ በሽታዎች መከላከል ላይ ከተሰራ የሚቀረፉ ካልተሰራ ግን በከፍተኛ ደረጃ የሰው ሕይወት የሚቀጥፉና አምራቹን ኃይል የሚጎዱ በሽታዎች ናቸው::
በ2012 ዓ.ም በአማራ ክልል 112 ወረዳዎች ላይ የወባ ወረርሽኝ ተከስቷል:: የተጠቂው ቁጥር ከአምናው 71 ከመቶ በላይ ጨምሯል:: የተከሰተ ሲሆን የኬሚካል ርጭት በባሰባቸው 26 ብቻ ተካናውኗል::ስለዚህ ማህበረሰቡ ከኬሚካል እኩል ጥቅም ያለውን አጎበር በመጠቀም ራሱንና ቤተሰቡን ከወባ መከላከል ይኖርበታል:: በመሆኑም የወባ ወረርሽኙም በመጨመሩ እና የኮሮና ወረርሽኙም በመስፋፋቱ ሕብረተሰቡ ነቅቶ ሊከላከል ይገባል:: የበሽታዎቹ ምልክቶች በአብዛኛው ተመሳሳይ በመሆናቸው ፈጥኖ ወደሕክምና ተቋማት በመሄድ መታከምና መከላከል አለበት:: ይህ ከሆነ ከምርት ስራ ተግባሩ ሊስተጓጎል እንደማይችልም ገልጸዋል::
በአጠቃላይ በአገሪቱ የኮሮና ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ገዳይ በሽታዎች ይገኛሉ:: ብዙዎቹም የሚያሳዩት ምልክት ከኮሮና ጋር ይመሳሰላል:: ስለዚህ በሽታውን በምርመራ ሳያውቁት በስጋትና በፍራቻ ለሌላ ተጨማሪ ችግር መጋለጥ ተገቢ አይደለም:: ኮሮናም ሆነ ወባ ታክመው ሙሉ በሙሉ ከዳኑ በኋላ መልሰው ሊያገረሹ ይችላሉ:: ስለዚህ በተገቢው የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር ሰምቶ በመተግበር መከላከል አስፈላጊ ነው::
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ሙሐመድ ሁሴን