ስለ ሴቶች እኩልነት ብቃት፣ እምቅ ክህሎት ብዙ ተብሏል። በተግባር ይህን ብቃታቸውን እንዲያወጡ እየተሰጠ ያለው እድል ግን ዳዴ ከማለት የዘለለ አይደለም።በአንጻሩ አጋጣሚው ሲፈጠርና አንዳንዴም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ማህበረሰቡ ለወንዶች ብሎ ባስቀመጣቸው ቦታዎች ሴቶች አስደናቂ ውጤቶችን ሲያስመዘግቡ ይታያሉ። ይሄም ሆኖ ዛሬም ድረስ እከሊት ለዚህ ቦታ ታጨች ፣ተሾመች ሲባል ትችል ይሆን? ትወጣው ይሆን? የሚል ጥያቄ ሲነሳ በስፋት ይደመጣል። ይሄ ለምን ሆነ ስንል ያነጋገርናቸው የሴቶች ማህበራት አመራሮች የሚከተለውን አጋርተውናል።
«ወንዶች ብቃት አላቸው የሚለው አስተሳሰብ መደበኛ እንደሆነ ሁሉ በዚህ ዘመን የሴቶቹ ብቃት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ምክንያት የለም። ሴቶች አንድ የማህበረሰብ አባል ናቸው፤ የዚህ ብሔር የዚህ ሀይማኖት ተከታዮች ብቃት አላቸው ወይንስ የላቸውም ተብሎ እንደማይጠየቅ ሁሉ ለሴቶቹም ጥያቄው መቅረብ የለበትም። ትችል ይሆን ብሎ መጠየቅ በራሱ ተገቢ አይደለም።» ሲሉ አስተያየታቸውን ያካፈሉን የሴታዊት የጾታ እኩልነት ንቅናቄ መስራች ዶክተር ስኂን ተፈራ ናቸው። ዶክተር ስኂን እንደሚሉት እንዲህ አይነቱ ለወንዱ ሳይቀርብ ለሴቷ የሚነሳ የብቃት ማረጋገጫ የስጋት ጥያቄ ከመነሻው ምክንያታዊ ያልሆነ ግን በስፋት የሚታይ ስህተት ነው። እምነት ማጣትና ጥርጥሬ ደግሞ በወንዶች ብቻ ሳይሆን በራሳቸው በሴቶችም በስፋት ሲንጸባረቅ ይስተዋላል።
ከዚህ ባለፈም ስልጣን መያዝና በውሳኔ ሰጪነት መቀመጥ ለሴቶች መታየት ያለበት እንደመብት ጥያቄ ነው። በየትኛውም ሀገር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከህዝብ ብዛቱ ከሀምሳ በመቶ በላይ ሴቶች ናቸው።ይሄንን በኢትዮጵያ በህብረተሰብ ደረጃ ብናየው በሀገሪቱ ካለው ትልቁ ብሄርም በላይ ቁጥር ያለው ነው። የብሄር መብት ተብሎ ለበርካታ አመታት ህዝብ ሲታገልበት ኖሯል፤የፆታ እኩልነትም ከዚህ አይለይም። በመሆኑም የዚህን የህብረተሰብ ክፍል ጥያቄ ሳይመልሱ ስለዲሞክራሲና መልካም አስተዳደርና እኩልነት ማውራት የሚታሰብ አይደለም። ይሄ በልግስና የሚሰጥ ሳይሆን እስካሁን ሲጠየቅ የነበረውን የእኩልነት መብት የመመለስ ጉዳይ ነው።
የሴቶች ተሳትፎ በቁጥር ብቻ ሳይሆን እድሉን ሲያገኙ በተግባርም ውጤታማ የሆኑባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ሩቅ ሳንጓዝ ከህወሓት ታጋዮች መካከል 30 በመቶ ሴቶች ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በጦርነቱ ከውጊያ እስከ አመራር ተሰማርተው ከወንድ እኩል ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል። ይሄ በቁጥር ትንሽ ቢሆንም እጋጣሚውን ያገኙት በየትውልዱ ሲፈጽሙት የነበረ ተግባር ነው። ነገር ግን በሀገራችን ቤተሰብ ከማስተዳደር ሀገር እስከ መምራት የደረሱ ሴቶች እየታዩ እንኳ ዛሬም የትችል ይሆን አስተሳሰብ መኖሩ የሚያስገርም ነው። ባደጉት ሀገራት አሜሪካን ጨምሮ በግል ኩባንያዎች እንደ ኮካ ኮላና ማይክሮ ሶፍት ባሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ሳይቀር በከፍተኛ የስልጣን ደረጃ የተቀመጡ በርካታ መሪ ሴቶች መኖራቸውን ማየት ይቻላል። የዚህ አይነቱ ልምድ በሀገራችን የተስፋፋ አይደለም።
ችግሩ ደግሞ ከቋንቋ አጠቃቀማችን ይጀምራል፤ ብዙ ጊዜ ሴቶችን ማብቃት ሲባል ይደመጣል። ማነው አብቂ ማነውስ የሚበቃው። ይሄ ትልቅ ስህተት ነው። ከመሰረቱ ጀምሮ እኩል እድል እየተሰጠ ሴት ልጆች እንዲያድጉ ቢደረግ የሚመጣ ክፍተት አልነበረም። ማብቃት የሚለው አገላለጽ ልግስና የማድረግ ያህል ነው። በልግስና የተሰጠና የሚደረግ ነገር ደግሞ የሚወሰድ የሚነሳ ይሆናል። መታየት ያለበት ግን እንደ እኩልነት መብት ነው። ለሴቶች እንዘንላቸው፣ እንተባበራቸው በሚል መንፈስ ሳይሆን የግድ መደረግ ስላለበት ነው። ይህም ማለት መንግስት ለብሄሮች ለሃይማኖቾች የሰጠው መብት ለማብቃትና በሀዘኔታ ሳይሆን ያንን መብት ማግኘት ስላለባቸው ነው።
ከዚህ አንፃር ያሉትም ህጎች ክፍተቶች ስላሉባቸው ሊፈተሹ ይገባል። ለምሳሌ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ ለብቻ የወጣ ህግ የለም። እንደተለየ ወንጀል እየታየም አይደለም። አሁን ባለው የህግ ማእቀፍ መዳኘት የለበትም የሚያደርሰው የተለየ ጉዳት ነው። በአሲድ ጉዳት ማድረስ እንደማንኛውም አካል ማጉደል ነው የሚታየው። በወቅቱ ህጉ ሲወጣ ይሄ ጥፋት አልነበረ ይሆናል። ነገርግን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መስተካከል ነበረበት። እንዲሁም ሌሎቹ ህጎች ለወንዶች የቆሙ ናቸው።
ሴት ልጅ በሰላም ወጥታ የማትገባና የማትማር ከሆነ ፤ ጥቃትና ፆታዊ ትንኮሳ ሲደርስባት ከለላ የማታገኝ ከሆነ ወደ ትልቅ መሪነት የምትሄድበት መንገድ ይዘጋል ማለት ነው። ይሄ እንዲስተካከል ማድረግ የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄን መመለስ ነው። በአንፃሩ ይሄ መንገድ ሲስተካከል እነሱም ከማንም ባላነሰ ለትልቅ ቦታ ይደርሳሉ፤ የሚሰጣቸውንም ሀላፊነት ከማንም በተሻለ መወጣት ይችላሉ። ከዚህ ሌላ ማብቃትና ድጋፍ አያስፈልግም። ይሄ ደግሞ የመንግስትና የህብረተሰቡም የግዴታ ስራ እንጂ ችሮታ አይደለም። በወቅቱ ከለላ ባይሰጣቸው ግማሹን የህብረተሰብ ክፍል ማሰናከል ነው። ለእድገትም ቢሆን ሀምሳ በመቶ ህዝቡን ሳይዙ መንቀሳቀስ እግርን አስሮ ለመሮጥ እንደመሞከር ነው። አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ሲሰሩ የሚፈጠር ስህተትም ተለይቶ ጎልቶ ሊታይ የሚገባው አይደለም፤ ያልተሳተ፣ የማይሳሳት ወንድ የለም።
በአሁኑ ወቅት ሴቶች በኢትዮጵያ ታሪክ በውሳኔ ሰጪነት ያላቸው ድርሻ እየጎላ መጥቷል። ለውጡ መታየት ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ከሌላው ጊዜ በተሻለ ጅማሮው አለ። ሴቶች በትልልቅ የስልጣን ደረጃ መሾማቸው በገጠርም በከተማም ላሉ ጥሩና አበረታች ነው። ነገር ግን የህይወታቸውን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር እታች ድረስ የሚወርዱ ሌሎች በርካታ ስራዎች በየደረጃው ይጠበቃሉ። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በሴቶች ላይ ያለውን ግራ አስተያየት ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም ማስወገድ አለባቸው። የተጀመሩት ስራዎች ከግብ የሚደርሱት ውስጣችን ያለውን የወንድን የበላይነት የሴትን አትችልም መናድ ስንችል ነው ይላሉ።
በተመሳሳይ የሴቶች የቢዝነስ ማህበር የቦርድ አባል እጩ ዶክተር ሲያሜ አንለይ በበኩላቸው የተጀመረው ለሴቶች እድሉን የማመቻቸት ስራ ወደታችም መውረድ እንዳለበት ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚገልጹት አሁን እየታየ ያለው እንቅስቃሴ በፌዴራል መንግስት የተገደበ ነው ይሄ በክልል በዞንና በወረዳም ሊቀጥል ይገባል። ሴቶች ብልሀተኞች ናቸው ከጉልበት ከሀይል ይልቅ ነገሮችን በብልሀት የመፍታት አቅም አላቸው። ከሰዎች ጋር በቀላሉ የመግባባት ተሰጥኦ ስላላቸውም የመሪነት ቦታ ቢሰጣቸው ኃላፊነትን መቀበል ብቻ ሳይሆን የተሻለ ፈጻሚ መሆን ይችላሉ። በመሆኑም በየትኛውም የስልጣን ደረጃ የግል ተቋማትን ጨምሮ በሴቶች ላይ እምነት በመጣል እንዲሰሩ መፍቀድ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ሴቶች እንደማንኛውም ህዝብ በየትኛውም የሀገራቸው ጉዳይ ውሳኔ የመስጠት መብት አላቸው ይሄ አሁን እንዳየነው ሀገርን መምራትንም ያካትታል። በተለይ ሰላም ለማወርድ ሴቶች ሰፊ ሚና መጫወት የሚችሉ ቢሆንም በተደጋጋሚ በሀገራችን የምናየው ችግር ሲፈጠር በየአዳራሹ ተጠርተው ልጆቻችሁን ያዙ ጠብቁ ሰብስቡ ሲባል ብቻ ነው። ነገር ግን ሰላም ሲደፈርስ ብቻ ሳይሆን ችግር እንዳይከሰት በሚሰሩ ስራዎችም ቢሳተፉ ብዙ ገንቢና ጠቃሚ ሀሳብ ማፍለቅ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ አሁን የተጀመረው አይነት ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በሙሉ ወንዶች ናቸው ይሄ የሆነው ሴት ጠፍቶ ሳይሆን እምነት ስለሌለ ነው። በመሆኑም በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ የወሰዱት አይነት ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ በየደረጃው መውሰድ ይፈልጋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግስት ያለውን የፖለሲ፣ የህግ ትግበራና የማህበራት ተደራሽነት ከሴቶችም መካከል የተለያያ መሆኑን በመረዳት እንደየ ነባራዊው ሁኔታ ማስተካከል አለበት። የሁሉም ሴቶች ችግር አንድ አይነት አይደለም ድርብ ድርብርብ ችግር ያለባቸው ሴቶች አሉ። ለምሳሌ በከተማ ያሉ ሴቶች ጠለፋ ያለ እድሜ ጋብቻና የመሳሰሉት ዋና ስጋት አይሆኑባቸውም በአንጻሩ በገጠር ያሉ ሴቶች ሌሎቹን ጥቃቶች ጨምሮ እነዚህ ችግሮች በስፋት ሲገጥሟቸው ይስተዋላል። ይሄ ደግሞ ከክልል ክልልም ይለያያል በታዳጊ ክልል የደሃ ልጅ የሆኑ ሴቶች ደግሞ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደራርበው ይወድቁባቸዋል። የሚቀረጸው ፖሊሲና ህግ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት የሚቋቋሙትም ማህበራት ተደራሽነታቸው በተመሳሳይ የሴቶቹን ችግር የለዩ ሊሆን ይገባል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠንካራ የሴት ማህበራት እንቅስቃሴ የሚታየው በከተሞች ነው። ፖሊሲ ሲቀረጽ ህግ ሲወጣ ከላይ ወደታች ሲሆን በትክክል ችግሩን የማየት አቅሙ ይዳከማል በመሆኑም በዝርዝር የእያንዳንዱን አካባቢ በመለየት ከላይ ወደታች የሚወጣበት አካሄድም ሊዘረጋ ይገባል።
ሴቶችን ለትልቅ ቦታ ለማድረስ የሚሰራው ስራ ደግሞ ከልጅነታቸው መጀመር አለበት። ሴት ልጆችን ስናሳድግ መሆን ትችያለሽ ማድረግ፣ መስራት፣ መማር ትችያለሽ እያልን መሆን አለበት እንጂ አሁን በስፋት እንደሚስተዋለው ጥሩ ሚስት እንዲሆኑ ብቻ እያደረግን መሆን የለበትም። እንደ ማህበረሰብ ሴት ልጅ ተምራ የት ትደርሳለች የሚል ማህበረሰብ ነው ያለን አባባላችንን በማስወገድ ከዚያ በላይ ራሳቸውን በትልቅ ቦታ ማስቀመጥ እንዲያስቡ፤ እንዲሰሩ አድርገን እያነጽን ማሳደግ ይጠበቅብናል።
በትምህርት ቤትም በመምህራን በጓደኞቻቸው ራሳቸውን በትንሽ ነገር ወስነው ገድበው እንዳይኖሩ ማድረግ ይጠበቃል። የትምህርት መምሪያ መጽሀፍትም የሴት ስራን ሲያስቀምጥ የሚሰጠው ምሳሌ መሪ፣ ዶክተር ና የመሳሰሉትን ለወንድ ብቻ የተሰጡ የሚመስሉትን ማካተት አለበት ይሄ እያደጉ ሲመጡ ትልቅ ሀይል ይሰጣቸዋል።። በተለይ በሀይማኖት ስፍራ ሴቶች ሄደው እንዲገለገሉ ብቻ ነው የሚደረገው በእምነት ተቋማት የእነሱ አስተዋጽኦ አይታይም ለምሳሌ የሀይማኖት እናት የሚባል የለም። ከላይ የተቀመጡት እኩልነትን የሚያስተምሩ አካሄዶች ደግሞ ከትምህርት ቤት በተጨማሪ በሚድያው በፊልምና ሌሎች የኪነጥበብ መስኮችም በስፋት ሊኬድባቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ