በያዝነው ወር የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ባልተጠበቀ ሁኔታ በአንድ ነጥብ ስድስት ከመቶ እንደሚወድቅ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ መተንበዩ ይታወሳል። በተለይም ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ አሁን አፍሪካ ለምትገኝበት የፋይናንስ ቀውስ ቁልፍ የሆኑ የኤክስፖርት ገበያዎች መቀዛቀዝ እንዲሁም ወረርሽኙን ለመግታት ተግባራዊ በሆኑ የእገዳ እርምጃዎች በቀጥታ ተጋላጭ የሆኑ የኢኮኖሚ መስኮች መቋረጥ ምክንያት አፍሪካ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የከፋ ሁኔታ ውስጥ መውደቋ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል። ይህንኑ ቀጣዩ አስፈሪ ሁኔታን በመተንበይ እንደ አይኤምኤፍ፣ የዓለም ባንክ፣ እንደ ፈረንሣይ ያሉ ሉዓላዊ ሀገራትና እንደ ብሩኪንግስ የመሳሰሉ የምርምር ተቋማት እና ባጠቃላይ ቁልፍ የሚባሉ ባለድርሻ አካላት ባስቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድህረ ኮቪድን የኢኮኖሚ ማገገምን ለማበረታታት የእዳ ስረዛ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። በርግጥም በሚያዚያ ወር አጋማሽ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ባወጣው መግለጫ ለ25 ድሃ ሀገራት 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት የ6ወር የእዳ ስረዛ ማድረጉን አስታውቋል። ከነዚህ አገራት መካከል አስራ ዘጠኙ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን የአይኤምኤፍ መግለጫ ይጠቁማል።
እንግዲህ ይህን በሚያክል ግዙፍ እና በርካታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተዋናዮች የተካፈሉበት የእዳ ስረዛ መርሐ ግብር ውስጥ የቻይና መንግሥትን ያላሳተፈ ማንኛውም ጥረት የአፍሪካ ሀገራት ለዘርፉ ብዙ ችግር መጋለጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። አዎን እርግጥ ነው ቤይጂንግ ለመላው ድሀ የአፍሪካ ሀገራት እንደ ብቸኛ አበዳሪ ባለሟል ነው የምትታየው። “የኢዮቤልዩ የእዳ ስረዛ ዘመቻ” የተሰኘውና ለታዳጊ አገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግ የሚንቀሳቀሱ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ተቋማት ጥምረት እንዳስታወቀው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2018 ወዲህ ብቻ 20 በመቶ የሚሸፍነው አጠቃላይ የአፍሪካ መንግሥታት የብድር እዳ ምንጩ ከቻይና ነው። አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ከእነዚህ የአፍሪካውያን የብድር ግዙፍነት በመነሳት ለአፍሪካውያን መደረግ ስላለበት የእዳ ስረዛ ወይም ቅነሳ ዙሪያ ቻይና ትልቁን ድርሻ መያዝ እንደሚገባት አጥብቀው ይከራከራሉ። ሌላው ቀርቶ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ማንዋ ይልማ ፕሮን ቻይና ለአፍሪካ አገራት የዕዳ ቅነሣ ማድረግ እንዳለባት ጥሪ አድርገዋል።
እስከአሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቻይና ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ራስዋን ቆጥባለች። ይህንኑ አቋሟን ይፋ እንድታደርግ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ድርጅት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት የተሰጠው ምላሽ “የአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ችግር ምንጭ እጅግ ውስብስብነትና የእያንዳንዱ ተበዳሪ አገራት የእዳ ዝርዝር መረጃ የሚለያይ ከመሆኑ ጋር ታያይዞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንዳንድ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአፍሪካ ሀገራት የእዳ ስረዛ መርሐ ግብሮችን በኛ በኩል ተግባራዊ እንድናደርግ ጥሩ ማስተላለፋቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ይህንኑ እውን የምናደርግበት አቅጣጫ ለማጥናት ፍቃደኝነቱም ዝግጁነቱም አለን” ማለቱን ዘግቧል።
በሚያዝያ ወር አጋማሽ የቡድን 20 አገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮችና የባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ የቻይናው የፋይናንስ ሚኒስትር ሚስተር ሊዩ ኪን በሰጡት አስተያየት ቻይና በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚደረገውን የእዳ እፎይታ ጥረት እንደምትደግፍ እና በቡድን 20 አገራት በተደረሰበት የጋራ መግባቢያ መሰረት የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ገልጸዋል።
በመሆኑም ቻይና ይህንን ግዙፍ የአፍሪካ የእዳ ውዝፍን በተመለከተ በቀጣይ የምትወስደው አቋም ምን ይመስላል የሚለው ነጥብ በሂደት የሚታይ ይሆናል። ቢያንስ ግን እንደ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ አባልነቷ በዚህ ዓለም አቀፋዊ የጋራ የእዳ ስረዛ ጥረት ውስጥ ተሳታፊ መሆኗ ምንም ጥርጥር
የለውም። ይሁን እንጂ በተናጠል የምትወስደው የእዳ ስረዛ አካሄድ የሚኖር አይመስልም በተለይም አፍሪካ ከቻይና ከተበደረችው እጅግ የሚበዛው ጊዜያዊ ብድር እና የንግድ ብድሮች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ልትወስድ ከምትችላቸው እርምጃዎች መካከል ቀጥተኛ የእዳ ስረዛ ከማድረግ ይልቅ ክፍያ ጊዜውን ማራዘም፣ የአከፋፈል ስርዓቱን መከለስ እና የእዳ ወይም ሃብት ልውውጥ ስልት ልትከተል ትችላለች።
እዳ ስንል የትኛውን ማለታችን ነው?
እዚህ ላይ ቻይና የምታደርገውን ወይም ልታደርግ የምትችለውን የእዳ ስረዛ መርሐ ግብር በተመለከተ የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ የትኛው የእዳ ዓይነት የሚለው ጉዳይ ነው። ለደሃና ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት ዜሮ የወለድ ምጣኔ ስረዛን ማድረግ ቻይና ዘንድ ቋሚ ባህል እየሆነ መጥቷል። በ2005 (እኤአ) ቻይና አስር ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የዜሮ የወለድ ምጣኔ ብድር መሰረዟን አስታውቃ ነበር። በ 2009 ዓመተ ምህረትም የዚህ አይነት 150 ብድሮችን ከ32 የአፍሪካ ሀገራት ላይ መሰረዟንም እንዲሁ አስታውቃለች። በ2018 ዓመተ ምህረት የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከቻይና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ካላቸው ታዳጊ አገራት ላይ ሁሉንም የበይነ መንግስታት የዜሮ የወለድ ምጣኔ ብድሮችን መሰረዛቸውን በተመሳሳይ ይፋ ማድረጋቸውን እናስታውሳለን።
ነገር ግን ይህ የዜሮ የወለድ የምጣኔ ብድር አፍሪካውያን ከቻይና ከተበደሩት አጠቃላይ የብድር መጠን በጣም ትንሹን ድርሻ የሚሸፍን ነው። ከ2000 እስከ 2017 ዓመተ ምህረት ድረስ ቻይና ለአፍሪካ መንግሥታትና ለየሀገራቱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አንድ መቶ አርባ ሦስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት የብድር አቅርቦት ሰጥታለች።
ከእነዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የብድር አይነት የዋስትና ብድር፣ ክሬዲት ላይን እና የልማት ፋይናንሲንግ የተሰኙ ዘርፎች ናቸው። በተመሳሳይ በ2015 ዓ.ም. በቻይና-አፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ ቻይና ለአፍሪካ ቃል ከገባችው 60 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር አቅርቦት ውስጥ 70 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ከፍ ሲል የተጠቀሱት የብድር ዘርፎች ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዜሮ የወለድ ምጣኔ ብድር ዘጠኝ በመቶውን ብቻ ነው የሚሸፍነው። እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የአፍሪካ መንግሥታት የቻይናን ለጋስነት ነጋ ጠባ ለምን እንደሚያጠምቁን ልብ ማለት የሚቻለው።
በ2018 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካና የአበዳሪያችን ቻይና የጋራ መድረክ ላይም በተመሳሳይ ስድሳ ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ከገባችው ግማሽ ያህሉ በክሬዲት ላይን እና በልማት ፋይናንሲንግ መስክ የሚሰጥ ሲሆን በእርዳታና በዜሮ የወለድ ምጣኔ ብድር መስክ ለመስጠት የተያዘው የገንዘብ መጠን ከአጠቃላዩ 60 ቢሊዮን 25 ከመቶውን ብቻ ነበር። እንግዲህ ይህን የቻይና የብድር አሰጣጥ ባህል መለስ ብለን ከቃኘን ዛሬ ላይ የሚኖራት አቋምም ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እናም ዕዳውን ሰርዤላችኋለሁ ካለችን ያለጥርጥር የዜሮ ወለድ መጠን ብድር ማለቷን ሳናንገራግር መቀበል አለብን ማለት ነው።
እንደአበዳሪ ሀገር ሆነን ካሰብን መቼም ለወለድ አልባ ብድር ቻይና ያሳየችውን ቸርነት በዋስትና ብድር እና በሌሎችም የብድር ዘርፎች ላይ ልቧ ይራራል ብሎ ማሰብ የዋህነት መሆኑን መካድ አይቻልም። ምክንያቱም ከብድሩ ግዙፍ መሆንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ እንዲሁም ለአፍሪካ እንኳ ላድርግ ብትል ይህንኑ ተከትሎ ሌሎች አካባቢዎችም የሚያነሱትን ተመሳሳይ ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ ስለሚሆንባት እና ለተበዳሪ የአፍሪካ ሀገራትም የሚኖረው አንድምታ ጭምር በዋና ዋናዎቹ የብድር ዘርፎች ላይ ቻይና ልታደርግ የምትችለው የእዳ ስረዛ ቢያንስ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የማይጠበቅ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። እናም ወገኔ የቻይና ለጋስነት ማለት እንደ የጀርባ ስጋ ነው። ስትግጥ ብትውል ትርፉ መጋጋጥ ነው።
የእዳ ስረዛውስ?
እንግዲህ የቻይና-አፍሪካን ወዳጅነት ስንቃኝ የዓለማችን ሁለተኛ የምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነችው የሩቅ ምስራቅ ኤሽያዊት ሀገር አፍሪካን እንዴት
ትታደጋት ይሆን ብለን መጠየቃችን አይቀርም። በዚያ ረገድ ለአፍሪካ የእዳ ምህረት በማድረግ እፎይ ማሰኘት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፤ ብቸኛው ባይሆንም። ደሃ የአፍሪካ መንግሥታትና አገራት ሁሉንም እዳ ምሬያችኋለሁ ቢባሉ ምንኛ በተደሰቱ ነበር። ቻይና ግን ቆቅ ናት። ላይ ላዩን ለአፍሪካ የእዳ ስረዛ እንዲደረግ እኛም እንፈልጋለን ትበል እንጂ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያት ውስንነቶች እንዳሉባት ግልጽ ነው። ይሁንና ሌሎች የብድር ዘርፎች ላይ ለአፍሪካ አገራት የእዳ ስረዛ ለማድረግ እምብዛም ፍላጎት የላትም። በአፍሪካ ካላት የብድር ውዝፍ ትልቅነት አንፃር ሙሉ በሙሉ መሰረዙ ባይቻላት እና በከፊል የእዳ ስረዛ ለማድረግ ብታስብ ቀድሞውኑ በወረርሽኙ ምክንያት እየተቀዛቀዘ የመጣው የኢኮኖሚ እድገቷ እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ካላት የንግድ ጦርነት አንጻር ስረዛው ቻይናን ለከፋ የፋይናንስ ቀውስ እንደሚዳርጋት ነው የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪዎች የሚናገሩት።
ከተሞክሮ እንደምንረዳው አሁን ላይ ቻይና ለአፍሪካ የእዳ ስረዛ ታድርግ ቢባል እንኳ እንዲሁ በደምሳሳው ሳይሆን የእያንዳንዱን የአፍሪካ አገራት ጉዳይ በተናጠል በማየት የእዳ ስረዛውን የምናስተናግድበት የነፍስ ወከፍ ስትራቴጂዎችን እና መንገዶችን ልትከተል እንደምትችል የቻይና ተንታኞች ይስማሙበታል። በርግጥም ወደ ኋላ መለስ ብለን የቻይና-አፍሪካን የብድር ጋብቻ ስንመለከት እንደምንረዳው ቻይና እንደው ለይስሙላ የእዳ ስረዛ አድርጌያለሁ ከማለት ይልቅ የእዳ ቅነሳ፣ የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘምን፣ የድጋሚ ብድር አቅርቦትና የእዳ ክለሳ የመሳሰሉ አማራጮችን ለተበዳሪ የአፍሪካ አገራትና በሌሎችም አካባቢዎች ተግባራዊ ስታደርግ እንደነበር ማየት ይቻላል።
ከዚህ አንፃር ለምሳሌ የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 ኢትዮጵያ ያለባትን እዳ ለመቀነስ ተስማምታ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለፈጀው የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ የሚውል ብድር መፍቀድ እና አጠቃላይ ለሀገሪቱ የሰጠችውን ብድር የመክፈያ ጊዜ ለተጨማሪ ሃያ ዓመታት ማዘግየቷን በስምምነቱ ወቅት ማካተቷን የቻይና መንግሥት አስታውቆ እንደነበር እናስታውሳለን።
በአፍሪካ አብዛኛው ሀገራት ጋር የብድር ጋብቻ ውስጥ እንደገባች የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ረገድ ጋና፣ ዛምቢያ እና አንጎላ ትላልቆቹ ተበዳሪዎች ናቸው። ይሁንና አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን ተበዳሪ ሀገራት ጋራ የምትከተለው የእዳ ስረዛም ሆነ ማቅለያ እስትራቴጂ ብዙም ግልጽነት እንደሌለው የፖለቲካ ምሁራን ይተቻሉ።
እርዳታ
ሌሎች አበዳሪዎች በተመሳሳይ ተግባራዊ ሳያደርጉ ቻይና ብቻዋን የምትተገብረው የእዳ ስረዛ ፍትሃዊ እና አዋጭ ተደርጎ አይታይም። በዚህ ጉዳይ ላይ ቻይና በርግጠኝነት ለአፍሪካም ሆነ ለሌሎች ተበዳሪ አገራት የእዳ ስረዛ ለማድረግ በሚል ከተቀረው የዓለም ማህበረሰብ ተነጥላ መቆም አትፈልግም።
እርግጥ ነው ከአጠቃላይ የአፍሪካ የእዳ መጠን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ሴክተር በቅደም ተከተል የ35 በመቶ ና የ32 ፐርሰንት የባለቤትነት ድርሻ ሆኖ ሳለ ቻይና ብቸኛዋ ትልቋ አበዳሪ እንዳልሆነች ትጠቁማለች። የእርሷ ድርሻ 20 በመቶ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ። ከዚህ ተነስተን ጉዳዩን ስናጤነው ቻይና ልትከተል የምትችለው የብድር እፎይታ ማዕቀፍ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች አበዳሪ አካላት ጋር የሚወሰድ የጋራ አቋም እንጂ ብቻዋን የምትወስደው ተናጠላዊ አመራር እንዳልሆነ የማያሻማ እውነታ ነው። በጉዳዩ ከማንኛውም መንግሥት ቀድማ በመመጻደቅ ዝናዋን ማጣት አትፈልግም። ነገር ግን የምታበረክተው አስተዋጽኦ መጠን እና ደረጃ ከአማካኝ ያልፋል ተብሎ አይታሰብም። በተለይ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ግፊት አኳያ አጠንክራ ልትሄድበት አትችልም የሚለው ግምት ከሚኖረው ተጨባጭ አንድምታ አኳያ።
የሆነው ሆኖ ከፍ ሲል የተጠቀሱት ነጥቦች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ የሚወስደውን እርምጃ በተለይም አበዳሪ አካላትን የጋራ ምክክርና ቅንጅት አስፈላጊነት በእጅጉ ያመላክታሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ