በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሕንድ ተማሪዎች ትምህርት ለመቅሰም መላውን ዓለም ያዳርሳሉ። የዛሬን አያድርገውና በትምህርት ዕድል የውጭ ጉዞ የቪዛ አገልግሎት ለማግኘት በዚህ ሰዓት በየኤምባሲዎች ተኮልኩለው ማየት የተለመደ እንደነበር ይነገራል። ዛሬ ግን ያን ማድረግ አልተቻለም። ዓለም በኮሮና ተናግታለች፤መልኳንም ቀይራለች።
ወረርሽኙም ቢኖር፣ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ‹‹ኦን ላይን›› ትምህርታችሁን መከታተል ትችላላችሁ ሲሉ የትምህርት ዕድለኞችን እየጋበዙ ይገኛሉ። ነገር ግን ይሄን አማራጭ ብዙዎቹ የተቀበሉት አይመስልም። ትምህርታቸውን ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ያገባደዱት ካልሆኑ በስተቀር አዲስ ጀማሪዎቹ በ‹‹አካል ካልሆነማ.. ›› ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቦታል። ይሄን ማንሳታችን እንዲሁ አይምሰላችሁ። የትምህርት መልክ በኢትዮጵያም ተቀይሯልና ነው።
ከዚህ ቀደም እንደ አማራጭ ወይም እንደቅንጦት ይቆጠሩ የሚመስሉት በቴክኖሎጂ ላይ ሙሉ ለሙሉ የተመሰረቱ የማስተማር ሂደቶች አሁን ላይ አስገዳጅ መልክ እየያዙ መምጣት ጀምረዋል፤ በቂ አለመሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ።
በሌላ በኩል የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ማከናወን እና በቴክኖሎጂ ማዘመን የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሥራቸው ዋና አካል ተደርጎ የተቀመጠ ነበር። ከዚያም አለፍ ሲል እያንዳንዱ መምህር በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ቢበዛ ያለገደብ ጥናትና ምርምር ማከናወን እንደሚገባው አሠራሩ ያስገድድ ነበር። እነዚህን ሁኔታዎች በመተግበርና በማስተግበር በኩል ከፍተኛ ውስንነቶች ነበሩ፤ በዚህ ረገድ አሁን ላይ መጠነኛ መነቃቃቶች እየተስተዋሉ መሆኑን መጥቀስ ያስፈልጋል።
የኮሮና ወረርሽኙ አንድም እክል ሁለትም ዕድል ይዞ የመጣ ይመስላል። የገጽ ለገጽ ትምህርት እክል ቢገጥመውም ለቴክኖሎጂና ለጥናትና ምርምር ዕድል ይዞላቸው እንደመጣ ይነገራል። ለማህበረሰባቸው ችግሮች በጥናትና ምርምር የተደገፉ ምላሾች ለመስጠት ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በተመሳሳይም ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን መፍትሄዎች እንዲያፈልቁ በመስራት ላይ እንደሆነ መጥቀስ ይቻላል።
የላቀ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውንና በዓለም አቀፍ ወረርሽኙ ምክንያት አገሪቱ ለተጋረጡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ሊያስገኙ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮች በመምረጥ ሳምንታዊ የምሁራን የውይይት መድረኮች መፈጠራቸው ሊለመድ የሚገባው እንደሆነም ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፤ ይስማሙበታልም። በመድረኮቹም ምሁራን ሐሳባቸውን አቅርበው አስተያየት ይቀበሉባቸዋል። ለችግሮች መፍትሄም በጋራ ይፈልጉባቸዋል።
እየተከናወኑ ከሚገኙ ዘርፉን ከሚያግዙና በቴክኖሎጂ ከተደገፉ የጥናትና የምርምር ሥራዎች መካከል ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር እየተላመዱ የትምህርት አሰጣጡን በ ‹‹ዲጂታላይዜሽን›› ማከናወን እንደሚቻል ልምድ የተገኘበት ነው። የ‹‹ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በዘመነ ኮቪድ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ አሁን ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ የሚገመግምና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላከተ ውይይት በቅርቡ ተካሂዷል።
ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ግብዓት ለማሰባሰብ ዓላማ ማድረጉን የሚገልጹት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ የውይይት መድረኩ የዓለም አቀፍና የአህጉር አቀፍ ተሞክሮዎች የቀረቡበት እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ቢኖርም በ‹‹ዲጂታላይዜሽን›› ትምህርት መቀጠል እንደሚቻልና ለዚህም ብዙ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ግንዛቤ ማግኘት ተችሏል። ከዚህ በፊት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ዓለም አቀፍ አሠራሮች የተቀሰሙበት እንደሆነም ይገልጻሉ። የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናቀ ኤጀንሲዎችም የኮቪድ 19 ወረርሽኙን በመቋቋም እንዴት ተግባሮቻቸውን ማስቀጠል እንዳለባቸው አቅጣጫ ያመላከተ መሆኑም ተነስቷል።
ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በቅንጅት ‹‹የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገራዊና ዓለምአቀፋዊ ደህንነት ላይ ያለው ተጽዕኖ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ፍሬያማ ውይይት አድርጓል። ፍሬያማ ከሚያሰኙት ጉዳዮች መካከልም ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስቀድሞ በቴክኖሎጂዎች መሰብሰብ መቻሉ በተጨባጭ ግብዓት እንዲገኝ የሚያግዝ በመሆኑ ነው። ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተነስተው አገራዊ መፍትሄዎች ተመላክተዋል። ቴክኖሎጂን በምን አግባብ ለችግሮቹ በመፍትሄነት መጠቀም እንደሚቻል ግንዛቤ የተፈጠረበት እንደሆነም ተገልጿል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ፣ በተለያዩ ዘርፎች የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች በመረዳትና ሳይንሳዊ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማስቀመጥ በወረርሽኙ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ መቀነስና መቆጣጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ ለማገዝ አላማ ማድረጉም ተገልጿል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት በጥምረት በመሆን በዘርፉ ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን በመስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣትም መክረው ወደ ተግባር ገብተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የምርምር ሥነምግባር ሥልጠና መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ የቴክኖሎጂ ተቋማት ተቀራርበው በመነጋገርና ዘርፉን በማስተሳሰር የጋራ ስትራቴጂና ፕሮግራሞችን መቀየስ ይገባል። በዚህም ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን የተሻሻለ ብሔራዊና ተቋማዊ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስችል ተናግረዋል። በተልዕኮና በአሠራር የሚገናኙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት በጥምረት በመሆን በዘርፉ ችግር ፈቺ የሆኑ፣ በጥናትና ምርምር ላይ የተደገፉ ሥራዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያሉት።
በማህበረሰቡ ዘንድ በወረርሽኙ የተነሳ የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት ለተቸገሩና ማሟላት ለተሳናቸው ሰዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በገንዘባቸው ከሚያደርጉት የዘወትር ድጋፍ በዘለለ ምርምሮች ላይ ማተኮራቸው ይስተዋላል።
ወረርሽኙ በስፋት የሚከሰትባቸውን ሁኔታዎች መመከት የሚያስችሉ ምላሾች እየሰጡም ነው። በርካታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ወረርሽኙ በንክኪ ምክንያት የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ማስቀረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሰርተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለአቅራቢያቸው የአስተዳደር አካላት ማበርከት ችለዋል። ለሕሙማኑ ማረፊያ የሚሆኑ አልጋዎችን በአጭር ጊዜ በማምረትም አጋርነታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። ዘመናዊ የከተማ ግብርና አሠራር በምርምሮች እንዲታገዝም በቅርበት በመደገፍ ላይ ይገኛሉ።
ዩኒቨርሲቲዎች በኮሮና ወረርሽኙ ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ተማሪዎቻቸውን ትምህርት ለማስቀጠል በ‹‹ኦን ላይን›› የማስተማሪያ መጽሐፍት፣ አሳይመንቶች፣ፈተናዎችንና አስፈላጊ ግብዓቶችን ሲያደርሱ ቆይተዋል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመፍጠር የኢ-ዩኒቨርሲቲ ለመቀላቀል ርዥምም ርቀት መሄዱን መግለጹ ይታወሳል።ብዙ አሠራሩን የሚያቀላጥፉ ‹‹ሶፍት ዌሮች›› በመስራትና በማስተሳሰር የዶክትሬት መመረቂያ ጥናታዊ ምርምሮች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በምስለ ትይዩ (ቨርችዋል) በተሳካ መንገድ እንዲቀርቡ ማድረግ አስችሎታል።
ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ የሚሆኑ የጽዳት ቁሳቁሶች፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ አልባሳት ከማምረት ባለፈ ለክትባት የሚያግዙ መድኃኒቶች ምርምር ላይ እየተሳተፉ እንደሆነም እየተገለጸ ነው። ለዚህ ደግሞ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ሙሐመድ ሁሴን