አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ የትግል አማራጭን መጠቀም እንዳለበቻው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች አስታወቁ።
የመድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ሰላማዊ የትግል መንገድ አዋጭ ነው፤ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የፓለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ተስማምተው ከመጡ በኋላ ሀሳባቸውን እየቀየሩ የማይገባ ተግባር ውስጥ መግባት የለባቸውም። ለአገሪቱ የሚጠቅማትም ሀሳባቸውንና ፍላጎታቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ ብቻ ነው።
ከመንግስት ጋር በመደራደር ወደ አገር ውስጥ የገቡት አካላት ስምምነት ተጥሶብናል በሚል ማኩረፋቸውን ጠቅሰው፣ መንግስት በበኩሉ ምንም አይነት ስምምነት አለማድረጉን እንደሚገልጽ ፕሮፌሰር በየነ ተናግረዋል፡፡ ከሁለቱም ወገን ያለውን ማወቅ ብንችል አንድ ፍርድ እንሰጥ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
በአገሪቷ መጻኢ እድል ላይ ተገቢ ያልሆነ ስምምነት ተሰጥቶም ከሆነ የተስማማው አካል ተወቃሽ ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ተስማምተናል የሚሉት አካላትም ተጨባጭ ባልሆነና በመረጃነት ሊቀርብ የሚችል ነገር ከሌላቸው ህዝቡን ግራ ከማጋባት መቆጠብ እንዳለባቸው፣ አገሪቷንም ትርምስ ውስጥ መክተት እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።
መንግስትም የገባው ቃል ካለ ለህዝቡ እንዲሁም ለእኛ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ ማድረግ አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ከዚህ በኋላም በደምና በህይወት የሚከፈል መስዋዕትነት እንደማያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው ፓርቲዎች ለውጡን በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንቅስቃሴያቸውን ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ተበታትነው ያሉ ፓርቲዎች አቋማቸውን በማቀራረብ በአንድ ተሰባስበው ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሌንጮ ገለጻ ፤ሰላማዊ ትግል ከምንም በላይ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፤ አሁን እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴም መቆም ይኖርበታል፡፡ ፓርቲዎች እንደ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ምዝገባቸውን አከናውነው የአገሪቱ ህግና ደንብ በሚፈቅደው ልክ በመንቀሳቀስ ደጋፊዎቻቸውን ማሰባሰብና ራሳቸውን እንደ ጥሩ አማራጭ አደርገው ማቅረብ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።
«በሰላም አገሬ ገብቼ ትግሌን እቀጥላለሁ ብሎ ከገቡ በኋላ የትጥቅ ትግልን አማራጭ ማድረግ የሚያስኬድ አይደለም›› ያሉት አቶ ሌንጮ፣ የትጥቅ ትግል ለአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንደማይጠቅም መረዳት ያስፈልጋል» ብለዋል።
አንዳንዶች ስምምነታችን አልተሟላም በማለት አላስፈላጊ ውጊያ ውስጥ ገብተዋል ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ይህ ግን ግልጽ አይደለም የተስማማው አካልም ቃል ገብቶ ተፈጻሚ ያላደረገው ካለ ሊታወቅ ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ሰራዊት ይዞ ገብቶ በአንድ ሉአዋላዊ አገር ላይ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ጠቅሰው፣ ሰላማዊ ትግሉን መያዙ እንደሚጠቅም አብራርተዋል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው ጉባኤ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በዝርዝር ገምግሞ በማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚቻል አቋም መያዛቸውን አድንቋል፡፡
አንዳንዶች ግን ጽንፈኝነትን በመስበክ የህዝቦችን አንድነት በመሸርሸርና የህግ የበላይነትን ባለማክበር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ እነዚህ ወገኖ ከዚህ ተግባራቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡ በውይይት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
በእፀገነት አክሊሉ