የዓመቱ ‹‹ምራት›› (ባለተረኞች መዘምራን ወይም ተረኛ አድባር) የነበረው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መዘምራን የቅዱስ ያሬድን ‹‹አጫብር›› ዜማ እያሰሙ ናቸው። የ‹‹ምራት›› ባለተረኞቹ በዓመቱ የጥምቀት ቀን ለማሸብሸብና ማህሌት ለመቆም፣ ቅዳሴ ለመቀደስና ሌላውንም የቤተክርስቲያን ሥርዓት ለመፈጸም ኃላፊነት የተጣለባቸው ገዳማትና አድባራት ናቸው። ተረኞቹም «ወረደ ወልድ ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም» እያሉ በደስታና በሰላም እግዚአብሔር ወልድ ወደ መጠመቂያ ወረደ የሚለውን የጥምቀትን ወረብ ያስተጋባሉ።
ሴቶች እና ወንዶች ተቀላቅለው በሚያሳዩት የ‹‹አጫብር›› ትርኢት መቋሚያቸው ከወዲያ ወዲህ ሲል ይታያል። ጥዑም ዜማ ነበር፤ ምክንያቱም በጸናጽል እና በከበሮ አልፎ አልፎም በጭብጫቦ የታጀበው ነፍስን የሚያለመልመው ዜማ የታዳሚውን ቀልብ ሰቅዞ መያዝ አልተሳነውም። በወዲያኛው ማዶ ደግሞ አንድ ሜትር የሚደርሱ በገናዎችን የያዙ ወጣቶች በባህላዊ ልብስ አጊጠው በተርታ ቦታቸውን ያዙ። ነጭ ከጥቁሩ ህጻን ካዋቂው ከሚርመሰመስበት በጃንሜዳ ላይ ነኝ። በጥለታማ የአገር ባህል ልብሳቸው አጊጠው የሚታዩ እናቶች ደምቀዋል። አዛውንቶች ጭራ ይዘው ግርማ ሞገሳቸውን ለዓለም ያሳያሉ። እኛም የበዓሉን ኩነት ለመመልከት እዛው የጥምቀተ ባህሩን አቅራቢያ ተገኝተናል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ አራተኛ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አምስተኛ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በቦታው ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ ሁለት የአንድ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ለጥምቀት በዓል በአንድነት ሲገኙ ይህ ለመጀመሪያ ነው። ጥር 11 ቀን2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ጃንሜዳ የጎረፈው እና እዛው ያደረው እና ምዕመንም የባህረ ጥምቀቱን መባረክ እየተጠባበቀ ነው። ጳጳሳቱ ባርከው ህዝቡን የተባረከውን ፀበል መርጨት ሲጀምሩ ታዳሚው ለመጸበል እየተጋፋ ፊቱን እና መላ ሰውነቱን ያስመታል። ይህን እያደረገ የማይረሳ ትውስታ በአዕምሮው ቀርጾ ይቀራል። ሁኔታው የሳባቸው የተለያዩ አገር ዜጎች ጭምር ደግሞ በካሜራቸው ያገኙትን ሁሉ ውብ ነገር ለትውስታ ማስቀረታቸውን ተያይዘውታል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ስለአብሮነት እና መተሳሰብ መሰረት ያደረገ መልዕክታቸውን አስተላለፉ። እርሳቸው እንደ ተናገሩት፤ መለያየት በመላም ዓለም ላይ እየጠና የመጣ ችግር መሆኑ የሚካድ አይደለም። እኛ ከሌላው የተለየን ነን የሚሉ ሲጎዱ እንጂ ሲጠቀሙ አልታዩም። በመሆኑም አንተ ትብስ አንቺ ትብስ ብሎ መኖር ያስፈልጋል። ለሰው ልጅ ከሰው የበለጠ ፍጡር የለምና መፋቀር ለነገ አይባልም።
«ወንዝና ተራራ ሰው ሊጠቀምባቸው እንጂ ሊለያይባቸው አልተፈጠሩም» ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ፤ «በሃጢያት ምክንያት በተፈጠረው የነገድ፤ የጎሳ እና የብሔር ልዩነት ምክንያት በመለያየት እንዳንጎዳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንተ የዚህ አገር ነህ አንተ የዚያ ተባብለን ውጣ አንተ ግባ የምንባባልበት ሁኔታ ከየት መጣ?፤ የነበረው የመከባበር ባህላችንስ ከየት ጠፋ? የቆየ የመተሳሰብ ባህላችን የተወደደ ነውና ልናከብረው ይገባል » የሚል ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
እንደ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ ከሆነ፤ የእየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ተከትለን ከሄድን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማክበርና መቀበል ይገባል። አንድነት እንጂ ተለያይቶ ውበትም፤ ድመቀትም የለም። በኃይለ ቃላት ውርወራ መጎናተል ትቶ በአንድነት በመተሳሰር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል። የሰዎች መፈናቀል፣ መገደል እና መሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልናቆመው ይገባል። ወጣቶችም የአባቶችን ምክር በመስማት ጥሩ ሥነ ምግባራቸውን ማስቀጠል አለባቸው።
የባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳሁን ደግሞ ወደ መድረክ ብቅ ብለው ንግግር ማድረግ ጀመሩ። «ይህ ቀን ትህትናና ፍቅር የተገለጠበት ቀን ነው። በመሆኑም ይህን የአንድነትና የትህትና መልዕክት ወስደን እና ተላብሰን መኖር ይገባናል። እንደ ጥምቀት ያሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶቻችንን እንደለበስነው ሸማ ደምቀን እንድንታይባቸው መጣር ይኖርብናል» በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እንደ ዶክተር ሒሩት ገለጻ፣ በሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በመላው ህዝብ በጎ ፈቃድ እና ተሳትፎ ለአሁኑ ዘመን የደረሱ በርካታ ባህላዊ እሴቶች በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ጥምቀትም የዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ኩነቱ በተጠበቀ መንገድ ይቀጥላል። በሌላ በኩል የዘንድሮው በዓል እንደተለመደው ሁሉ እንግዶችን በሰላምና በፍቅር የመቀበል ልምዱ የተጠናከረበት መሆኑን መመስከር ይቻላል። ይህ የእንግዳ ተቀባይነት ሥነሥርዓት መቀጠል ያለበት በጎ ሥራ ነው።
«የየአካባቢው ወጣቶችም በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከናወን ያሳዩት ጥንካሬ የሚደነቅ ነውና ከጎናቸው መሆናችንን በመግለጽ ምስጋና አቀርባለሁ» ያሉት ዶክተር ሒሩት፤ የወጣቱን ሥነምግባር አወድሰዋል። በመጨረሻም መጪው ዘመን የአስተሳሰብ እና የሥራ እመርታ የምናስመዘግብበት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸው ንግግራቸው ቋጭተዋል።
ከህንድ አዲስ አበባ ድረስ 3 ሺ950 ኪሎ ሜትሮችን አቋረጠው ለበዓሉ የደረሱት የማላንካራ ኦርቶዶክስ ወይም የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተወካይ ደግሞ ህንዳዊው አቡነ ጆሰሁ ማር ኒቆዲሞስ ናቸው። የቤተክርስ ቲያናቸው ጳጳስ ብጹህ አቡነ ባሲሎስ ማርቶማ ፓውሎስን መልዕክት አስተላ ልፈዋል። በመልክታቸውም የኢትዮጵያ እና የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ግንኙነት እንዳላቸው ያወሳሉ።
«እንደዚህ ያለ ሰፊ ህዝብ የሚሳተፍበት እና ትልቅ ክብረበዓል በየትኛውም ዓለም አይገኝም» በማለት ለጥምቀት አከባበር አድናቆታቸውን የሰጡት ህንዳዊው ጳጳስ ልዩ ፌስቲቫል በመሆኑ ሁልጊዜም ሲያስታውሱት እንደሚኖሩ ይገልጻሉ። ለእርሳቸው እና ለልዑካቸው በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ጥሩ መስተንግዶ በማመስገን የኢትዮጵያውያን አቀባበል እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።
የመድረክ ንግግሮች እንዳበቁ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች ከድንኳን አንስተው መንቀሳቀስ የጀመሩትን ታቦታት ፊት ጸሎት አድርሰው ጉዞ ተጀመረ። ሁሉም በየፊናው የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑን ታቦታት በእልልታ እና በዝማሬ እያጀበ በአምስቱም የጃንሜዳ በሮች መውጫቸውን አደረገ። በየመንገዱ ቀይ ምንጣፍ ያዘጋጁ ወጣቶች ሥርዓት ባለው ወግ ጥምቀትን አስተናብረውና የአባት እና የእናት ምርቃት ተችረው በዓሉ ተጠናቀቀ።
የቀጣዩ ዓመት የምራት ባለተረኞች ወይም «አንሺዎች» የሆኑት ደግሞ የበዓታ ለማርያም የታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም ካህናትና መዘምራን ናቸው። በቀጣዩ ዓመት በሰላም ያገናኘን የተባለ ሁሉ የአንሺዎቹን አጫብር ወረብን ለመታደም ከመዲሁ ሊናፍቅ ይችላል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ጌትነት ተስፋማርያም