“የአርብቶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት ለአገራዊ አንድነት” በሚል መልዕክት ዘንድሮ ለ17ኛው ጊዜ የኦሮሚያ አርብቶ አደሮች ቀን ከጥር 11 ቀን እስከ 13/2011 በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ በመከበር ላይ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ ጠቢባ ሃሰን፣ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፣ የክልሉ አርብቶ አደር አካባቢ ልማት አስተባባሪ ልማት ኮሚሸን ኮሙሽነር አቶ ሊበን አደሬና እንዲሁም ከሰባት የኦሮሚያ ዞኖች የተወከሉ አርብቶ አደሮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የአርብቶ አደሩ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን እንዲሁም አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድዋ በቦረና ዞን ያቤሎ እና ዱብሉቅ አካባቢ ያሉ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 290 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም አስመርቀዋል።
ከተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል በ44 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት በያቤሎ ወረዳ ጊዶ ያቤሎ ቀበሌ የተገነባውን 1.5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚችለው የመስኖ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከ200 ሄክታር በላይ በመስኖ ማልማት የሚያስችልና 400 አባወራዎችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። እንዲሁም በ246 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ከድብሉቅንና ዲሎ ከተማዎችን የሚያገናኘው የ85 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድም ይገኝበታል።
በተጨማሪም ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በያቤሎ ከተማ በ51 ሚሊዮን ብር .የተገነባውን የያቤሎ ከተማ አውቶቢስ መናሃሪያንም አስመርቀዋል።
የሶስት ቀናት ቆይታ የተያዘለት ይህ መርሃ ግብር ባለፉት ሁለት ቀናት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳዩ የመስክ ጉብኙቶች እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን የአካባቢው ህብረተሰብ ያሳተፈ ውይይቶችም በመካሄድ ላይ ናቸው።
በእያሱ መሰለ