ወሩ ግንቦት ወቅቱ ደግሞ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቁ የረመዳን ፆም ተጠናቆ በዓሉ የሚከበርበት ቀን ላይ እንገኛለን። በዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ ላይም ይህን ታላቅ በዓል ምክንያት በማድረግ ስለ አንድ ጉዳይ በስፋት ለመዳሰስ ፈቅደናል።
ነገሩ እንዲህ ነው። የእምነቱ ተከታዮች አምላካቸውን በልዩ ልዩ መልኩ ያመሰግኑታል፤ ያመልኩታል። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ በከበሮ በሚታጀብ መንዙማ ስነ ስርዓት የሚከናወነው ነው። የእስልምና እምነት ተከታዮች በመደበኛው ጊዜ በተለያዩ የምስጋና መልዕክት ባላቸው የተለያዩ ስርዓቶች አምልኮታቸውን ይፈፅማሉ። ለዚህ እንዲረዳቸው የዜማ መሳሪያ ሲጠቀሙም ይስተዋላል።
በአንዳንድ ልዩ ክብረ በዓላት ላይ ደግሞ ጥበባዊ የማመስገኛ ዘይቤው ለየት ብሎና መንገዱን ቀይሮ እናስተውላለን። ለምሳሌ ያህልም በዚህ በያዝነው ወቅት ከባድ እራስን የመግዛት፣ የማምለክና ከዓለማዊው ጩኸት የመራቅ ጊዜ ነው። በመሆኑም አምላካቸውን (አላህ)ን የሚያስቡበት ለምስጋና የሚጠቀሙበት የዜማ ስልት መንዙማ ይሆናል።
መንዙማ በእርግጥ በሌሎችም የፆም እና አዘቦት ቀናቶች ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም በረመዳን ጊዜ ግን በልዩ ሁኔታ ሰፊውን ቦታ ይይዛል። መነሻችን ላይ ጠቆም አድርገን እንዳለፍነው ለዛሬ በዝርዝር የሚከተሉትን ጉዳዮች እንመለከታለን፤ መንዙማ በረመዳን ወቅት ለምን ጥቅም ላይ ይውላል? ጥበባዊና ሃይማኖታዊው ፋይዳው ምን ይመስላል? መንዙማን ለአምልኮ ስርዓት መጠቀም መቼ ተጀመረ? ዜማው በየትኛው የዜማ እቃ ጋር ተደምሮ ይቀርባል ? የግጥሞቹ መልክቶችስ ምን ይመስላሉ? የሚሉትን እናነሳለን።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም አገር አቀፍ የመንዙማ ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ወቅት ደግሞ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ አባቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ተገኝተው ነበር።
በወቅቱ ‹‹የመንዙማ ግጥምና ዜማ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ በማቅረብ ሰፊ ማብራሪያ የሰጠው የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪና ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ነበር። ይህን ግብዣ ያደረገለት ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነበር፡፡ ለዛሬ መንዙማ በተመለከተ ይዘንላችሁ ለምንቀርበው ማብራሪያ ሰፊውን ድርሻ በመውሰድ የፅሑፋችን ማጠንኛ የሆኑ ሃሳቦችን አቀብሎናል። የእስልምና እምነትን በተመለከተ ለምንፈልገው ማብራሪያ በተለያዩ ጊዜያቶች በድምፅም ሆነ በኢሜል አድራሻ በፅሑፍ ለሚልክልን ሰነድ በቅድሚያ ልናመሰግነው እንወዳለን።
መንዙማ ምንድን ነው?
የእስልምና ጉዳይ ተመራማሪው ‹‹መንዙማ›› የዓረብኛ ቃል ሲሆን የተገኘውም ነዞመ፣ ከተሰኘው ሥርወ ቃል እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ ትርጉሙም አዘጋጀ፣ አደረጀ፣ ትክክለኛ ቦታ ላይ አስቀመጠ፣ አስተካከለ፣ ተስተካከለ፣ አልሺዕር የሚል ቃል ሲጨመርበት ነዞም አልሺዕር ግጥም መደርደር፣ መግጠም፣ ቃላትን፣ ሐረጎችን፣ ስንኞችን በትክክለኛ ቦታቸው ማስቀመጥ መደርደር እንደሆነም ይገልፃል፡፡ ኢንተዞመ፣ ተነዞመ፣ ተናዞመ፣ ሲሆን ደግሞ አዘገጃጀት፣ አደረጃጀት፣ አደራደር የሚል ስሜት ይሰጣል ይላል፡፡ ተንዚሙል ሺዕር ሲሆን ግጥምና ቅኔ የግጥምን ሥነ ጽሑፋዊ ውበት በተከተለ ሥልት፣ ሥርዓት፣ አካሄድ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ፣ መደርደር፣ ለወጣለት ዜማ ወይም ለሚወጣለት ዜማ እንዲሆን አድርጎ መድረስ የሚል አንድምታ አለው ይለናል፡፡
‹‹መንዙማ ከሌላው ግጥም የሚለየው ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ግጥም በመሆኑ ነው›› በማለትም እስከአሁን ሲነገር የነበረው የመንዙማ ትርጉም በዚህ የሚተካ ከሆነ ዜማውንና ግጥሙን፣ እንዲሁም ውዝዋዜውንና የምት መሣሪያውን የሚያጠቃልል ገላጭ ስም ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል ይለናል፡፡
መንዙማ ከግጥምና ከዜማ አንፃር
የጥናቱ ፀሐፊ ተመራማሪ አቶ ተሾመ ብርሃኑ ‹‹መንዙማ ከግጥምና ከዜማ አኳያ ሲፈተሽ የተደረሰው በየትኛው ዘመን ነበር? ወይም የትኛውን ዘመን ያንፀባርቃል? ዘመን አይሽሬ ነው ወይስ የአንድ ዘመን ብቻ እያሉ መተንተን ሊጠይቅ ይችላል›› በማለት በምሳሌነት
«እንዴት አደርክ ብለው እንዴት አደርክ አለኝ
አልሃምዱሊላሂ ሊቀር ነው መሰለኝ» የሚል እንጉርጉሮ ቢገጥመን የትኛውን ጊዜ እንደሚያንፀባርቅ መገመት ይቻላል እያለ አመክንዮውን ያስቀምጣል፡፡
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ መንዙማ ከዘመኑ ጋር የሚያድግ፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነት የሚጎለምስ ስለሆነ ግጥም በወዲያኛዎቹ አያቶቻችን ዘመን፣ ግጥም በአባቶቻችን ዘመንና ግጥም በእኛ ዘመን ብሎ መተንተን ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 70 ዓመት ገደማ ሐጂ ባደረገበት ጊዜ መካንና መዲናን ዓይቶ የድንጋይና የአሸዋው ክምር፣ ስለአነስተኛዎቹ የመኖሪያ ቤቶች፣ ፅዳት ስለጎደላቸው ምግብ ቤቶች፣ ስለዓረብ ምጽዋት ፈላጊዎች፣ ስለተላላፊ በሽታዎች ቢቃኝ፣ በዚህ ዘመን የሚቃኘው ደግሞ ስለፎቆቹና መንገዶቹ ውበት፣ ስለመብራቱና በመብራት ስለተሠሩት ውብ ጌጦች፣ ስለመኪኖችና ስለሌሎች አስገራሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊጽፍ ይችላል፡፡
ግጥምና ዜማ እንዳይሰበሩ
ጋዜጠኛና የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪው ተሾመ፤ ከመንዙማ ጋር ግጥምና ዜማ አብረው የሚኖሩ ሲሆን ገጣሚዎቹና ዜማ አውጪዎቹም በሚያውቁት፣ በታያቸው፣ በበራላቸው፣ በተረዳቸው መንገድ ሐሳብ የሚያመነጩና የሚያዜሙ ሲሆኑ የግጥምና የዜማ ደራሲዎቹም ዘመን አይሽሬ ሥራ ሊያበረክቱ እንደሚችሉት ሁሉ ለጊዜው አንጎራጉረው የሚተውት ሊሆን ይችላል ይለናል፡፡
‹‹ከመንዙማ ግጥምና ዜማ ጋር የሚነሳው ዋናው ቁም ነገር ደራሲዎቹ እነማን ናቸው? ከየት ናቸው? በኅብረተሰቡ የነበራቸው ወይም ያላቸው የላቀ ደረጃ እስከ ምን ድረስ ነው?›› የሚለው አቶ ተሾመ፤ ከዚህም በተጨማሪ በግልጽም ሆነ በረቀቀና በጠለቀ ምስጢራዊ መንገድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው? ጥልቀቱና ምጥቀቱ ምን ያህል ነው? ቅርፁ ምን ያህል ማራኪ በሆነ ውበት ይዘቱን ገልጾታል? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል በማለት የተጠቀሱትን ጥብቅ ጥያቄዎች ማንሳት እንደሚያስፈልግ ይነግረናል፡፡
ተመራማሪው አቶ ተሾመ ጥናቱን በሚሠራበት ወቅት ሼክ ኑረዳኢም አወል ከሐሸንጌ (ደቡብ ትግራይ) አስረድቶኛል ብሎ ባስቀመጠው ሃሳብ ላይ እንደሚያነሳው፤ መንዙማ ጥንታዊ የፈጣሪ ማመስገኛ፣ የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ማወደሻ፣ የፈጣሪ አሀድነትን ማስተማሪያ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በሰሜን ኢትዮጵያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የንጉሥ (ወሎ) ሙጃሂዱ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ፣ ቀጥሎም የአና ሸኾች እንደሚመጡ፣ ከአናም ወደ ዳና፣ ከዳና ወደ ጫሌና ወደ ሌሎች እንደ ተዛመተ አስ ቀምጧል፡፡
የወንድሙ ልጅ መሐመድ ዓረብ ዓብዱራህማንም ደግሞ፤ በራያ መንዙማ የሚደረሰውም ሆነ የሚዜመው በመርህ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ እንደጠቀሰለት አንስቶ በተለይ በአና ወጣት ዓሊሞች ትክክለኛውን አቅጣጫ ተከትለው እንዲጓዙ የሼኮች ክትትል ይደረግ እንደነበረ፣ ነገር ግን ጉዳዩ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር እንደሚያስፈልገው እንደነገረው በጥናቱ ላይ አስፍሯል፡፡
ይህ ተመራማሪ በሰሜኑና በማዕከላዊው የአገራችን ክፍል ስለመንዙማ ሲነሳ ከ200 ዓመት ያልበለጠ ታሪክ ስለሚጠቀስ ተጨማሪ ጥናቶችን አጥንቶ ወደ ትክክለኛው ዘመን መድረስ እስከሚቻል ድረስ ባሉት ላይ ማተኮር የግድ እንደሚሆንም ይነግረናል፡፡
ይህም ሆኖ የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የሐረሪ መንዙማ ታሪክ መኖሩና ከአናም ሆነ ከዳና ሊቀድም እንደሚችል ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የባሌና የአርሲው ሰይድ ኑርሁሴን እስከአሁን ድረስ ውብ በሆነ ዜማና ውዝዋዜ መቅረቡ ምስክር መሆኑን በምክንያትነት ያነሳል፡፡
የዓረብኛ «መንዙማ›› ምንጮች»
‹‹የዓረብኛ መንዙማዎች መሠረታቸው ፈጣሪን ከማመስገን ከማወደስ፣ ለፈጣሪና ለነብዩ መሐመድ (ሱዓወ) ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት ከመግለጽ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው›› የሚለን ጋዜጠኛና ተመራማሪ ተሾመ፤ ወደ ፈጣሪ የሚወስዱት መንገዶች ከቁጥር በላይ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ይላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሀቅ መረጃ ሳይንስ የሆነው ሱፍያ በውስጡም ተጓዡ ለጉዞው የሚያስፈልጉትን ምግብ፣ ብርሃንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሲሆኑ መድረሻ ወደቦቹም መንፈሳዊ ሥርዓቶቹ ማለትም ጠሪቃዎቹ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ እነሱንም ከዚህ እንደሚከተለው በሁለት በመክፈል የበለጠ ያብራራቸዋል።
የሀቅ መንገዶችም በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሲከፈሉ፣ የመጀመርያው ተጓዡ ከመጓዙ በፊት የሚሰጠው ወይም የሚማረው ነው፡፡ ይህም ትምህርት ትንሽ መብላት፣ ትንሽ መጠጣት፣ ትንሽ መተኛት፣ ዚክርን ማብዛትና አስፈላጊ ካልሆኑ ማኅበራዊ ግንኙነቶች መገታትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዚክሮቹም ሰባት ሲሆኑ አንዱ ከፈጣሪ (ከአላህ) በስተቀር ሌላ የለም፤ ፈጣሪ፣ እርሱ፣ ሀቁ፣ ዘለዓለማዊው፣ የተብቃቃው የሚሉት ናቸው፡፡
እነዚህን የፈጣሪ ስሞች ደጋግሞ በማውሳት ሰባት የመንፈስ ደረጃዎችን ያልፋል፡፡ ሰባት የመንፈስ ደረጃዎች እርኩስ መንፈስ አዛዥ፣ ራስን የማውገዝ መንፈስ፣ የዕረፍት መንፈስ፣ የፍስሐ መንፈስ፣ የመንፃት ማለትም እንከን የለሽ የመሆን መንፈስ ናቸው፡፡ ይህንን መንገድ የሚከተሉት ሁሉንም ነገር ዓለማዊ ነገር ሁሉ ትቶ ሸሪዓው በሚፈቅደው መሠረት መሪዎቻቸውን ወይም አስተማሪዎቻቸውን እየተከተሉ በፈጣሪ ፍቅር ማለትም በዓሽቅ ተሞልቶ ወደ ሀቅ መጓዝ ነው፡፡
ዓሽቅ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘና ፍፁም የሆነ ፍቅር ውበት ወይም አካላዊ ወዘና ሲሆን፣ ሱፊዎች እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ፍቅር የሚሰጡት ለዘለዓለማዊው ንጉሥ፣ ለግርማዊነቱና በግርማዊነቱ ለሚገለጽ ውበቱ ነው፡፡
ሙላ ጃሚዕ የተባለ ሰው ስለፈጣሪ አስገራሚና አስደናቂ ውበት ሲገልጽ፣ ‹‹የግብፅ ሴቶች የዩሴፍን ውበት ሲመለከቱ ከመደነቃቸው የተነሳ ይዘውት በነበረው ሳንጃ እጃቸውን ከቆረጡ፣ ጌታ ሆይ ያንተን ግሩም ድንቅ ውበት ቢመለከቱ ኖሮ በያዙት ሳንጃ ልባቸውን ይሰነጥቁ ነበር፤›› ብሏል፡፡ ይህም ከፍተኛ ዓይነት ውበትና ፍቅርን (ዓሽቅን) ይፈነጥቃል፡፡
መውጫ
ደራሲ፣ተመራማሪና ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሃኑ መንዙማ መጠናት፣ መተንተንና መታወቅ ያለበት የኢትዮጵያ ረቂቅ ቅርስ ነው ይላል፡፡ መንዙማ ከተደረሰበት፣ ከተዜመበት፣ ከተማሩበት፣ ከደረሱበትና ከደራሲያኑ ጋር የተሰናሰለ መሆኑን በመጠቆምም ከተጨባጭ የኢትዮጵያ ቅርስ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባ ይመክራል፡፡ በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ አገራዊ ሀብት ትኩረት ማድረጋቸው የሚመሠገን መሆኑን ጠቅሶ ወደፊትም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ጥልቅ ጥናት ማድረግና ጥናቱን ማሳተም ያስፈልጋል የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ‹‹ኢስላሚክ ቱሪዝምን በማስፋፋት የአገር ልማት አጋር ማድረግ ይቻላል›› በማለት ሃሳቡን ይደመድማል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር