(መጨረሻ ክፍል)
(መጨረሻ ክፍል)
ሮዛ ሆስፒታል ልጅዋ ጋር ሆና ስልክዋ ጠራ የደወለው ባለቤትዋ ነበር። በላይ እሰጥሀለው ብሎት የነበረው ለልጃቸው ማሳካሚያ የሚሆን ገንዘብ ምክንያት ፈጥሮ እንደማይሰጠው እንደነገረው ሲያረዳት ተስፋዋ ተሟጠጠ። አልጋ ላይ በጀርባው ተንጋሎ አይኖቹን የሚያንከራትተው ልጅዋን እያየች የእናትነት አንጀትዋ አላስችል ሲላት ለማልቀስ ክፍሉን ለቃ ወጣች። አምርራ አለቀሰች፤ የምታደርገው ጨንቋታል አይንዋ እያየ ልጅዋን ለማጣት እየተቃረበች መሆኑን ተረዳች።
ከቆይታ በኋላ የእጇ ስልክ ተጣራ በላይ ነበር። ስለ ልጅዋ ጠየቃት እጅግ መታመሙን ነገረችው። ፍላጎቱ የስዋ ተስፋ መቁረጥ ማየትና እጅ መስጠትዋን መመልከት ነበርና ለፍላጎቱ መቃረብዋን እጅጉን በሚመኝ ተስፋ ደጋግሞ ጥያቄ አነሳ። “ልጅሽን ማሳከሙን አትፈልጊውም? እያየሽው ሊሞት አይገባም። ምን አታልቂ ነገር ምነው ቃሌን ልጠብቅ ብለሽ…” ይሄኔ አልቻለችም አቋረጠቸው። ሳትፈልገው የሚገባውን ለመነገር ተጣደፈች።
“አንተ ሰው አይደለህም አውሬ ነህ። ጓደኛዬ ብሎ የቀረበልህን ለእድገትህ በሚማስን ባልንጀራህ ላይ የምታደባ እርኩስ ነህ።” ሰውነትዋ እየተንቀጠቀጠ ንግግርዋን ቀጠለች። “ በልጆችህ እናት መማገጥህ ሳያንስ በልጄ መታመም ሰበብ ደካማነቴን አይተህ ስጋዊ ፍላጎትህን ለመሙላት የምታስብ ድንጋይ ነህ። ሁለተኛ በዚህ መልክ አንዳች ሙከራ አደርጋለሁ ብትል በጓደኛህ ብቻ አይደለም በሚስትህ ፊት ሙከራህን ሁሉ እውነታው አውጥቼ አዋርድሀለሁ።” ብላ ጆሮው ላይ ስልኩን ዘጋችው።
በላይ እጅግ ተናደደ ንዴቱ የሚያደርገውን አሳጣው። መኪናውን አስነስቶ ሁሌም ወደ ሚያዘወትርበት ባር አቀና። የቀረበለትን መጠጥ ደጋግሞ እየተጎነጨ ፍላጎቱን ያኮላሸው የስድብ ናዳ ደጋግሞ ማሰብ ያዘ። ስልኩ ደጋግሞ ይጠራል። ባለቤቱ ናት። ማንሳት ፈፅሞ አልፈለገም። ደጋግማ ደወለች፤ አይቶ ምላሽ ሳይሰጥ ድምፁን አጥፍቶ ጠረጴዛው ላይ አኖረው።
ከቆይታ በኋላ በተለየ ድምፅ ወደ ስልኩ የገባው የፅሁፍ መልዕክት ከተቀመጠበት አፈናጥሮ አስነሳው። በተደጋጋሚ ስትደውል ምላሽ አልሰጥ ያላት ባለቤቱ ነበረች ምልዕክቱን የላከችለት። ልጁ ላይ የመኪና አደጋ እንደደረሰበትና ያሉበት ሆስፒታል ነገረችው። በሩጫ ከነበረበት ባር አፈትልኮ ወጥቶ መኪና ውስጥ ገባ አንድ አስተናጋጅ ተከታትሎ “ሂሳብ አልከፈሉም ጌታው” አለው፤ በላይ ድንጋጤ በቀላቀለው ችኮላ ረስቶ የነበረውን የመጠጥ ሂሳብ ከፍሎ ወደ ፊት አፈተለከ።
በአንድ ከፍተኛ ሆስፒታል ውስጥ ባለቤቱ በእንባ ርሳ አገኛት። “ልጄ እንዴት ነው? አሁን ምን አደረጉለት?” በማለት አንዴ የማይመለሱ ብዙ ጥያቄዎችን አከታተለላት። “ድንገተኛ ክፍል ውስጥ አስገብተው እያከሙት ነው በጣም ሰግቻለው ልጄ በጣም ተጎድቷል።” ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ባልዋ ላይ ተጠመጠመች።
ወደ ድንገተኛ ክፍል አመራ። ስለ ልጁ አንዲትን ነርስ አስቁሞ ሲጠይቅ እንዲረጋጋና ህክምና ላይ መሆኑ ነገረችው። ብዙም ሳይቆይ ቅድም ያናገራት ነርስ ወደ በላይና ባለቤቱ በመቅረብ “ልጃችሁ እየታከመ ነው፤ ደህና ነው ለክፉ አይሰጠውም። ነገር ግን ብዙ ደም ፈሶታል ለዚያ ደግሞ ደም ያስፈልገዋል። ከሁለት አንዳችሁ መስጠት ይኖርባችኋል።” ነርስዋ ንግግርዋን ሳትገታ በላይ ላቦራቶሪው የት እንደሆነ ጠይቆ ወደዚያው አመራ።
በላይ ከማይወዳት ሚስቱ ያገኛቸው ልጆቹን ይወዳቸዋል። ሚስቱን ሳይፈታት የመቆየቱ ሚስጥር ሁለቱ ልጆቹ ናቸው። አሁን አደጋ የደረሰበት ልጁ ደግሞ እጅግ የሚወደው ነው። ምንም እንዲሆንበት ፈፅሞ አይፈልግም። ልጁ የፈሰሰው ደም ከፍተኛ በመሆኑ ከሆስፒታሉ ደም ባንክ ለልጁ የሚሆን ደም ተወስዶ እንደሚሰጥና ለዚያ ምትክ እንደሆነ ተነግሮት አስፈላጊውን ምርመራ ካደረገ በኋላ ደም ሰጠ። ልጁ በሁለተኛው ቀን ጤንነቱ እየተሻለ በመሄዱ መናገር ቻለ። በላይ ልጁ ያለበት ክፍል ውስጥ ሳለ አንዲት የህክምና ባለሙያ ገብታ ዶክተሩ ሊያናግረው እንደሚፈልግ ነገረችው።
ከዶከተሩ የጠበቀው ስለልጁ መስማትን ነበር። ነገር ግን ፍፁም ባልጠበቀው መልኩ የሰጠው ደም ሲመረመር ያገኙት ውጤት መነሻ አድርጎ ስለራሱ ጤና አንዳንድ ጥያቄዎች ሲያቀርብለት ግራ ተጋባ። ጤና ምርመራ በድጋሚ ማድረግ እንዳለበትም ነገረው። እጅጉን ተደናገጠ። ድጋሚ ተመረመረ።
ልጁ ተሽሎት እቤት ቢመለስም የበላይ ውጤት ግን ያልተጠበቀ ነበር። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በላይ ያላንኳኳው ሆስፒታል ያላማከረው ልዩ ስፔሻሊስት ሀኪም አልነበረም። ነገር ግን የሚሰማው ተመሳሳይ ውጤት ነበር። በደሙ ውስጥ የተገኘው የደም ካንሰር እጅጉን የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱንና ቀድሞ መታከም ባለማቻሉ ወይም ባለማወቁ መዳን የማይችልበት ደረጃ መድረሱ ነው። በተቻለው መጠን እረፍት ማድረግ እንደሚጠበቅበት ምን አልባትም እዚህ ምድር ላይ የሚቆይበት ጊዜ የረዘመ እንደማይሆን ሀኪሞች ደጋግመው ነገሩት።
ልበ ደንዳናው በላይ በሰማው መርዶ ዓለም አስጠላችው። ስለ ሰው ብዙ ያሴር በሰዎች ላይ ተረማምዶ ለራሱ ምኞት መሳካት ይሮጥ የነበረው ሩጫ መገታቱን ተገነዘበ። በብርቱ ሀዘን ተዋጠ። ለሰዎች ቀና ሆኖ የማያውቀው በላይ በህይወት ዘመኑ የሰራችው ክፉ ነገሮች ገዝፈው ታዩት። በዙሪያው ያሉ ሰዎች ላይ ያደረጋቸው ተገቢ ያለሆኑ ክፉ ተግባራት እያንዳንዱ ታዩት። ኤልያስን ደጋግሞ አሰበው።
ስራ ቦታው ከሄደ ቀናት አልፈዋል። ኤልያስ ሁሉንም ሸፍኖ ይሰራል። ድርጅቱን እየመራለት ቆየ። ዛሬ እቤት ለብርቱ ጉዳይ እንደሚፈልገው ነግሮ እቤት አስጠርቶታል። ለመጀመሪያ ጊዜ ጓደኛውን ኤልያስ በቀናነት ተመለከተው። ጓደኛው ላይ የሰራውን ክፉ ተግባር ፊት ለፊቱ ሲያየው እጅግ ገዘፈበት።ፀፀት ተሰማው። የሰራበትን በደል ባይክስ እንኳን የተጨነቀበትና ህይወቱን የሚገራለትን አንድ ነገር ለማድረግ አስቦ ነበር ያስጠራው።
ኤልያስ የጓደኛውን ሁኔታ በማየት ስለተፈጠረው ነገር ጠየቀው። በላይ የጤናው ሁኔታ ዘርዝሮ ነገረው። ልበ ቀናው ኤልያስ ስለጓደኛው እጅግ በጣም አዘነ። ስለወዳጁ አነባ። ካቀረቀረበት ቀና ሲል እጁ ዘርግቶ እየሰጠው ያለ ወረቀት ላይ አይኑ አረፈ። በእንባ የራሱ አይኖቹን እየጠራረገ “ምንድ ነው በላይ” በማለት ጥያቄ አቀረበ። በላይ እንዲቀበለው አመለከተው።
ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የተፃፈበት ቼክ። ኤልያስ “ምን ላድርገው ስራ…” ብሎ ጠየቀ። ኖ.. ይሄ አንተ እስከዛሬ እኔ ጋር ያቆየኸው ገንዘብ ነው። ልጅህ ታሟል መዳን እየቻለ በብር እጦት ነው ሆስፒታል ያለው። እሱን አሳክምበት። እንተም ሁሌ በዚህ መልክ መቆየት የለብህም እራስህን መለወጥ አለብህ ብሩ የአንተ ነው።” ኤልያስ ከበላይ የተሰጠውን ቼክ ያመነው ባንክ ሄዶ ብሩን ወደ እራሱ አካውንቱ ካዞረው በኋላ ነበር። ከዚያን ክንፍ አውጥቶ መብረር ልጁና ሚስቱ ጋር መድረስን ተመኘ። የተጨነቀቸው ባለቤቱ ከጭንቀትዋ ሊገላግል ልጁን፤ የአብራኩን ክፋይ ማሳከሚያ ብር ማግኘቱ ሊነግራት ቸኩሎ። ተጣደፈ። ተፈፀመ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ተገኝ ብሩ