ዘመናዊ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ፀጉር ሲያደንቁ ይስተዋላሉ። ፀጉራቸውን ለመስተካከል(ለመሠራት) ሲሯሯጡም እናያለን። በፀጉር አምሮና ተውቦ ለመገኘት ሁሉም እንደየአቅሙ ሲሟሟት ይታያል። ግን ለምንድነው ሰዎች ፀጉራቸውን የሚንከባከቡት? ለፀጉር የሚጠፋው ገንዘብና ጊዜ ቀላል ነው? ነጋ ጠባ ፀጉር እያደገ፣ እየተስተካከለ፣ እየተበጠረ የሚኖር መሆኑ አያናድድም? ያለማቋረጥ የሚያድግ ፀጉር ባለቤት በመሆን ረገድ፣ የሰው ልጅ ብቸኛ ፍጡር ነው። እኮ ለምን?
ከአንድ ሁለት ዓመት ወዲህ ፀጉርን በሚመለከት ሳይንሳዊ አመለካከቶች እየተንፀባረቁ ናቸው። እንደሚባለው ከሰው በስተቀር ሌሎች ፍጡራን አንዴ ፀጉር ከተላበሱ በኋላ ዕድገቱ ይቆማል። የእኛ ፀጉር ግን ሲሻው ዕድሜ ልክ ሲያድግ፣ ሲመዘዝ ይባጃል። ለምንድነው የሰው ፀጉር ያለማቋረጥ ለማደግ የቻለው? በእንክብካቤ ብዛት ወይስ በተፈጥሮ? ለዚህ አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት ይከብድ ይሆናል።
በደንብ የሚታወቀው ሁለት ዓይነት ፀጉር ያለን መሆኑ። ዋነኛው የጭንቅላት፣ የቅንድብና የሽፋሽፍት፣ ሌላው በሌሎች የሰራ አካላታችን የሚገኙት ናቸው። እነዚህም እንደየሰዉ ዕድሜ፣ ፆታና ተፈጥሮ ይብዛ ይነስ እንጂ የብሽሽት፣ የብብትና የጢምንም ጨማምሮ ዘጠኝና አስር ዓይነት ይሆናሉ። በትከሻ ላይ ዝቅ ብሎ አምሮ የሚታየውም ሆነ በእግር ጣቶች ላይ የምትበቅለዋ ስስ የሆነች ፀጉር፣ ሁሉም እስከሚረግፉ እኩል ይበቅላሉ። በወር ከአንድ እስከ 1 ነጥብ 5 አፅቅ (ሳንቲ ሜትር) የበቀለ ፀጉር አድጎ ሲያበቃ ይረግፋል። የፀጉር ዕድገት ጊዜም እንደ ፀጉሩ ዓይነት ይለያያል፣ ርዝመቱም በዚያው ይወሰናል። ለምሳሌ የእግር ፀጉር ዕድገቱን በሁለት ወራት ያቋርጣል፣ የብብት ፀጉር ለስድስት ወራት፣ የራስ ፀጉር ግን ያለማቋረጥ ዕድገቱ ከስድስት ዓመት በላይ ይዘልቃል።
እጅግም የማይታወቀው የፀጉራችን አስተዳደግ ስልተ ምስጢሩ ሲሆን ወደፊት ግን የሚደረስበት ይሆናል። ለመሆኑ መቼ ነው የሰው ልጆች የራስ ፀጉር በማያቋርጥ ሁኔታ ማደግ የጀመረው? ተብሎ ሲጠየቅ የዛሬ 240 ሺ ዓመታት፣ የሰው ልጅ እሳት ማቀጣጠል ከጀመረበት ጊዜ በኋላ ነው ይባላል። እናም ከብርድ መከላከያ ብልሃት እስካገኘበት ጊዜ ድረስ በፀጉሩ ላይ የዓይነትም ሆነ የመጠን ለውጥ ማስከተሉና፣ በለውጡም የማይፈለግ ቦታ የበቀለ ፀጉር ከጊዜ ወደ ጊዜ መርገፉና መሳሳቱ የዝግመት ለውጥ ሀቅ እንደሆነ ይታሰባል።
የፀጉር መሳሳት በበኩሉ አያሌ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም አለመዘንጋት ይገባል። ይኸውም ፀጉር ውስጥ ተደብቀውና ተራብተው በሽታ አምጪ የሆኑ ተባዮችን መቀነሱ፣ ከአስቸጋሪው የጫካ ኑሮ ወደ ሜዳማ፣ ሙቀታማና ወደ ባህር አካባቢዎች ሲጠጋ ከፀሐይ ከሚከላከልበት የራስ ፀጉር በስተቀር፣ ራሱን ለማቀዝቀዝ የፀጉሩ ከቀድሞው መቀነስ ላብ በብዛት ለማመንጨት ረድቶታል። በዚያ ላይ የሰው ልጅ ፀጉሩ እያነሰ በሄደና፣ ለስላሳ ቆዳ በኖረው ቁጥር ይበልጥ ለፍቅር እየተፈላለገ፣ ባለ አናሳ ፀጉሮቹ እየተራቡ፣ ፀጉራሞቹ በብዛት እየቀነሱ እንደሄዱ ይገመታል።
ስለ ፀጉራችን ለምን እንጨነቃለን?
በርካታ ሰዎች የፀጉራቸውን ሁኔታ በመስተዋት እያዩ በየቀኑ ብዙ ሰዓት ያሳልፋሉ። ስለ ፀጉር ማሰብ ወንድ ሴት የማይል ከመሆንም በላይ ትልቅ ጭንቀት የሚፈጥርበት ጊዜም አለ።
ስለ ፀጉርህ ሁኔታዎች ምን እንወቅ?
በራስ ቅል ላይ በአማካይ 100,000 የሚደርሱ ፀጉሮች እንዳሉ ይገመታል። አንድ ነጠላ ፀጉር የሚያድገው ዕድሜ ልክ ሳይሆን ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ይረግፍና ከጥቂት የሽግግር ጊዜ በኋላ ከዚያው ቀዳዳ አዲስ ፀጉር መብቀል ይጀምራል። አንድ ነጠላ ፀጉር የራሱ የሆነ የአስተዳደግ ኡደት አለው። በዚህ ኡደት ምክንያት ምንም ዓይነት የፀጉር ችግር ከሌለበት ሰው እንኳን በእያንዳንዱ ቀን ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ ፀጉሮች ይረግፋሉ።
የፀጉር ቀለም የሚለያየው በምን ምክንያት ነው?
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ በማለት ያብራራል። ‹‹የፀጉር ቀለም በአብዛኛው የሚወሰነው ሜላኒን የተባለው ጥቁር ቡናማ ቀለም ባለው ስርጭትና መጠን ነው›› ሜላኒን በፀጉር፣ በቆዳና በዓይን ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ቀለም ነው። የቀለሙ መጠን በጨመረ መጠን ፀጉርም ጠቆር እያለ ይሄዳል። የሜላኒን መጠን እያነሰ ሲሄድ ደግሞ የፀጉር ቀለም ከጥቁር ወደ ቡናማነት ወይም ወደ ቢጫነት ያደላ ይሆናል። ፀጉር ምንም ሜላኒን ከሌለው ግን ሙሉ በሙሉ ነጭ ይሆናል። ከፎረፎር ሌላ ብዙዎችን የሚያሳስባቸው የፀጉር መርገፍ አለዚያም የፀጉር መሸበት ነው።
የፀጉር አስተዳደግ
የፀጉራችን አስተዳደግ የራሱ ዑደት አለው። ፀጉር የማደጊያ፣ የመሸጋገሪያና የማረፊያ ጊዜ አለው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ በማለት ያብራራል። ‹‹ፀጉር በማረፊያ ጊዜ ማደጉን ያቆማል። በዚህ ጊዜ አሮጌው ፀጉር የማደጊያው ጊዜ እስኪ ደርስ ድረስ በስሩ ላይ እንዳለ ይቆያል። በማደጊያ ጊዜ አሮጌው ፀጉር ይረግፍና አዲስ ፀጉር ከስር ይወጣል። ‹‹በማንኛውም ወቅት ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚደርስ ፀጉር በዕድገት ላይ ሲሆን ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው በማረፊያ፣ በመቶ የሚሆነው በመሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ይሆናል።
ፀጉርህ ሸብቷል?
ሽበት ብዙውን ጊዜ የእርጅና እና የአረጋዊነት ምልክት ተደርጎ ይታያል። እርግጥ ነው፣ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ፀጉር ይሸብታል። ይሁን እንጂ ሽበት የሚመጣው በእርጅና ምክንያት ብቻ አይደለም። ሽበት ጠቆር ያለ ፀጉር ባላቸው ላይ ጎልቶ የሚታይ ይሁን እንጂ ፆታም ሆነ የፀጉር ቀለም አይመርጥም።
አንዳንዶች በመሸበታቸው ምክንያት ከዕድሜያቸው በላይ ያረጁ መስለው ሊታዩና ይህም አሳሳቢ ሊሆንባቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ባለመሸበታቸው ምክንያት ትክክለኛው ዕድሜያቸውና መልካቸው አለመመሳሰሉ የሚያሳስባቸው ሰዎችም አይጠፉም።
ፀጉር ከሸበተ ሞተ ማለት አይደለም። እርግጥ ነው በዓይን የሚታየው ውጪያዊ የፀጉር ክፍል በድን ነው። የእያንዳንዱ ፀጉር ስር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ህይወት ያለው የፀጉር ክፍል ይህ ብቻ ነው። የፀጉር ስር እንደ ፀጉር ፋብሪካ ሆኖ ያገለግላል። በስሩ ውስጥ ያሉት ሌሎች በብዛት ተራብተው ፀጉር ሲፈጠር የቀለም ሴሎች የሚሠሩትን ሜላኒን ይቀባል። በዚህም የተነሳ የቀለም ሴሎች ሜላኒን መሥራት ካቆሙ ፀጉር ነጭ ይሆናል።
የቀለም ሴሎች በድንገት ሜላኒን መሥራታቸውን የሚያቆሙት ለምን እንደሆነ ማንም የማያውቅ የለም። በዚህም ምክንያት ለሽበት የሚሆን አስተማማኝ መድሃኒት ሊገኝ አልተቻለም። በተጨማሪም ሥራቸውን አቁመው የነበሩ የቀለም ሴሎች እንደገና መሥራት ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተደርሶበታል።
አንዳንዶች ሜላኒን እንደመወጋት ያሉትን አዳዲስ ህክምናዎች ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ፀጉራቸውን ቀለም ይቀባሉ። ይህም ቢሆን ዛሬ የመጣ ልማድ አይደለም። የጥንቶቹ ግሪካውያንና ሮማውያን ፀጉራቸውን ቀለም ይቀበሉ ነበር። የጥንት ግብፃውያን በበሬ ደም ፀጉራቸውን ያቀልሙ ነበር።
ይሁን እንጂ በየጊዜው ቀለም መቀባት ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ የአንዳንዶችን ቆዳ ሊያስቆጣ ወይም ሊያቆስል ይችላል። ሽበትን በቀለም ማጥቆር ብንወስንም መቀባትን ለማቆም የምንፈልግበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ከስር የሚያድገውን ሽበት መሸሸግ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ሽበት በአዎንታዊ ጎኑ የሚያምርና ከዚህ በፊት ያልነበረህን ግርማ ሞገስ የሚያስገኝልን ሊሆን ይችላል።
የፀጉር መሳሳትና ራስ በራነት
ሌላው የተለመደ የፀጉር ችግር የፀጉር መሳሳትና ራሰ በራነት ነው። እነዚህም ችግሮች ቢሆኑ ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። በጥንቷ ግብፅ ለራሰ በራነት ከአንበሳ፣ ከጉማሬ፣ ከአዞ፣ ከድመት ከእባብና ከዝይ ስብ የተቀመመ መድሃኒት ይሰጥ ነበር። በዛሬው ጊዜ ራስ በራነትንና የፀጉር መሳሳት ይከላከላሉ የሚባሉ በርካታ ሸቀጦች ሲኖሩ ለእነዚህ ሸቀጦች በየዓመቱ የሚፈሰው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው።
በራነት የሚጀምረው ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል ሲዛባ ነው። ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል በምግብ አለ መመጣጠን፣ ረዥም ጊዜ በሚቆይ ትኩሳት ወይም እንደ ቆዳ በሽታ ባሉ ምክንያት የተነሳ ሊዛባ ይችላል። በተጨማሪም የፀጉር አበቃቀል እንደ እርግዝና እና ልጅ መውለድ ባሉ ምክንያቶች ስለሚዛባ አዲስ ፀጉር መበቀል ከመጀመሩ በፊት ብዙ ፀጉር ሊረግፍ ይችላል። የፀጉሩን አስተዳደግ ያዛባው ምክንያት ሲወገድ ግን እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ ይቆምና ወደ መደበኛው ሁኔታ ይመለሳል።
ሌላው ዓይነት የፀጉር መርገፍ ደግሞ ላሽ ይባላል። ይህ ችግር በሚኖርበት ጊዜ በአንዱ አካባቢ ያለ በርካታ ፀጉር አንድ ጊዜ ይረግፋል። ላሽ የሚመጣው በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ በሚደርስ ቀውስ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር በቅርቡ የተደረጉ የህክምና ጥናቶች ያመለክታሉ።
በጣም የተለመደው የፀጉር መርገፍ በወንዶች ላይ የሚደርሰው የራሰ በራነት ዓይነት ነው። ከፊት ያለው ፀጉር ገባ ገባ በማለት ወይም መሀል አናት ላይ ሳሳ በማለት ይጀምርና ቀስ በቀስ እየተባባሰ ይሄዳል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የፀጉር እድገት የተዛባ ሆኖ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ጨርሶ ወደ ማቆም ይደርሳል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት ያብራራል- ‹‹በራነት በጀመረው አካባቢ በነበረው ረዥም፣ ጠንካራና ባለቀለም ፀጉር መብቀል ይጀምራል›› የፀጉር ዕድገት እየቀጠለ ሲሄድ እየሳሳና ዕድሜው እያጠረ ሄዶ ምንም ፀጉር ከማይበቅልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። ይህ የሚሆነው በዘር ውርሻና በወንዶች ሆርሞኖች ምክንያት ነው።
የወንዶች ራሰ በራን ከአፍላ የጉርምስና ዕድሜ አንስቶ ሊጀምር ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በ30ዎቹ ዓመት መገባደጃና በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ነው። እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ በብዙ ወንዶች ላይ የሚደርስ ቢሆንም መጠኑ ከዘር ወደ ዘርና ከግለሰብ ወደ ግለሰብ ይለያል። ያም ሆነ ይህ ለዚህ ችግር የተረጋገጠ መድሃኒት ማግኘት አልተቻለም። አንዳንዶች በራቸውን ለመሸፈን ሰው ሠራሽ ፀጉር ለማድረግ ወይም በቀዶ ህክምና ፀጉር ለማስተካከል ይመርጡ ይሆናል። ለተቀረው ፀጉር ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ፀጉር እንዳይረግፍ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
የአንድ ሰው ፀጉር አንዴ መሳሳት ከጀመረ ጨርሶ ይመለጣል ማለት አይደለም። ነጠላ ፀጉሮች በመቅጠናቸው ምክንያት ሳስቶ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ የፀጉር ውፍረት ምን ያህል ነው? አንድ ጥናት እዳመለከተው ከ50 እስከ 100 ማይክሮ ሊደርስ ይችላል። አንድ ሰው እያረጀ ሲሄድ ፀጉሩ ይቀጥናል። የጥቂት ማይክሮኖች መቀነስ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ 100 ሺ የሚያክሉ ፀጉሮች መኖራቸውን አትዘንጉ። ስለዚህ ነጠላ ፀጉሮች በትንሹ እንኳን ቢቀጥኑ በጠቅላላው የፀጉር ብዛት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ከፍተኛ ይሆናል።
ለፀጉር እንክብካቤ ማድረግ
ፀጉር በየወሩ 10 ሚሊ ሜትር ያህል ያድጋል። ፈጣን ዕድገት ካላቸው የሰውነት ክፍሎች አንዱ ነው። የሰውነት ፀጉሮች ዕድገት በሙሉ አንድ ላይ ቢጀመር በየቀኑ 20 ሜትር ያህል ያድጋል ማለት ነው።
ለሽበትና ለራስ በራነት ፍቱን የሆነ መድሃኒት ገና ያልተገኘ ቢሆንም ያለንን ፀጉር ለመንከባከብ ብዙ ልናደርግ የምንችለው ነገር አለ። በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብና የራስ ቅል በቂ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከመጠን በላይ ምግብ መቀነስ ወይም የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ሽበትና የፀጉር መሳሳት ሊያፋጥን ይችላል። አዘውትረን ፀጉራችንን መታጠብና የራስ ቅል ቆዳን በጥፍር ሳይቧጥጡ ጥሩ አድርጎ ማሸት ጥሩ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህን ለማድረግ የራስ ቅል ጥሩ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ያስችላል። ፀጉራችሁን በሳሙና ወይም በሻምፖ ከታጠባችሁ በኋላ ጥሩ አድርጋችሁ አለቅልቁት።
ፀጉራችሁን በኃይል አታበጥሩ። ፀጉራችሁ ረዥም ከሆነ መጀመሪያ ላይ ከስራ ጀምሮ እስከጫፍ አለማበጠር ጥሩ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ ፀጉራችሁን መሀል ላይ ይዛችሁ ጫፍ ጫፉን በማበጠር አፍታቱት። ቀጥላችሁ ከመሀል አንስታችሁ እስከ ጫፍ አበጥሩ። በመጨረሻም ፀጉራችሁን ወደታች ልቀቁትና ከስር እስከ ጫፍ አበጥሩት።
ፀጉራችሁ ሸብቶ ስታዩት ወይም ሲረግፍ ሊያሳስባችሁ ይችላል። ቢሆንም የፀጉራችሁ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ እናንተን የሚያሳስባችሁን ያህል ሌሎችን እንደሚያሳስብ አስታውሱ። ፀጉራችሁን ቀለም መቀባት፣ ሰው ሠራሽ ፀጉር ማድረግ ወይም ህክምና ማድረግ ተፈልጎ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ለእናንተ የተተወ ነው። የፀጉራችሁ ቀለም ምንም ዓይነት ይሁን ወይም ምንም ያህል ፀጉር ይኑራችሁ ዋና አስፈላጊው ነገር በንፅህናና በስርዓት መያዛችሁ ነው።
ምንጭ፡- ማህደረ ጤና ድረ ገጽ
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012