
መነሻ ሃሳብ
ስኬት እና ስኬታማነት አንድም፣ የተለያዩም ሆነው ይከሰታሉ። ይሄ ምናልባት እንደ ሁኔታው እና እንደ ዓውዱ የሚለያይበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ሆኖም፣ ስኬት የአንድን ጉዳይ ወይም ሁነት የዕለት ተዕለት መፈጸም፤ መከወን፤ ከዳር መድረስ፤ ከታሰበበት የማኖር፤… የመሳሰሉ ተግባር ተኮር መገለጫ ሆኖ ይታያል። በአንጻሩ ስኬታማነት፣ በአንድ ዓውድ ወይም ሁነት ውስጥ ተረማምዶ ወደ ሕልም ማማ የመድረስን ግለሰባዊ አልያም ቡድናዊ ወይም ማኅበረሰባዊ የዕለት ተዕለት ግብ መቺነትን የሚያመለክት ጽንሰ ሃሳብ ነው።
ከዚህ አንጻር እሳቤዎቹ የአድራጊና ተደራጊነት ተዛምዶ መከሰቻነታቸው ጎልቶ ይገለጻል። እናም ስኬት የአንድ ስኬታማ ሰው ወይም ቡድን፣ ወይም ማኅበረሰብ የድርጊት መገለጫ ዓውድ ሲሆን፤ ስኬታማነት ደግሞ የእነዚህ ስኬታማ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አልያም ሕዝቦች የሕልም ጫፍ የመድረስ መንገድና እውነትን የሚያነጽር ሆኖ እናገኘዋለን።
ይሄ የስኬት እና ስኬታማነት ቁርኝት ታዲያ፤ በሕልም እና ለሕልም በመኖር ውስጥ በሚገለጥ የተግባር ተጋድሎ በጽኑ መተሳሰርን የግድ ይላል። ይሄ ደግሞ እንደ ባለሕልሙ ግለሰብ፣ ቡድን አልያም ማኅበረሰብና ሕዝብ ጽናት የሚገልጽ ነው። ዛሬም በዚህ እሳቤ ውስጥ የኢትዮጵያን እና ሕልሞቿን ጉዳይ ሲሆን፤ ለዚህም ስለ ኢትዮጵያ ከፍታ ከማለም፤ ስለ ሕልሞቿም ጸንቶ ከመሥራት፤ በዚህ ሂደት ስለተገለጠ የስኬት መንገድ እና የቀጣይ የስኬቷ ማማ ላይ ለመድረስ ስለሚጠበቁ የቤት ሥራዎች ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ።
ለዚህ ደግሞ፣ እንደ ሀገር በተለይም ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በዋናነትም ባለፈው ዓመት የታሰቡ፤ ከሃሳብ ወደ ንድፍ የተለወጡ፤ ከንድፍ ወደ ተግባር የተቀየሩ እና በተግባር ተገልጠውም በስኬት መስመር መራመድ የጀመሩ ጥቂት ኹነትና ሁኔታዎችን ማዕከል በማድረግ ጉዳዬን አስጉዛለሁ።
ለጉዳዬ ማራመጃም እንደ ሀገር ወደ ስኬት እናመራለን ስንል መዳረሻን ከማወቅ፤ ሂደታዊ አቅምን ከመለየት (ድክመትን ለይቶ ማረም፣ ጥንካሬ አልቆ ከመጠበቅ)፤ የማይናወጥ ማንነት ከመገንባት (በተገኙ ውጤቶች ካለመኮፈስ፣ ለፈተናዎች እጅ ካለመስጠት/አለመዛል)፤ እንዲሁም ከአቃፊነትና ከአስተባባሪነት (የራስ አቅምን ብቻ ሳይሆን የሌሎችን አቅምና እውቀት ከመደመር) አኳያ የነበሩ ማሳያዎችን በመመልከት፤ ቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸውንም በመጠቆም ይሆናል።
መዳረሻን ማወቅ፣
እንደ ሀገር ከ2010ሩ ለውጥ ማግስት አንዱና አንኳር ጉዳይ ሆኖ የወጣው፤ የት ነበርን ዛሬ ላይ የት አለን፤ ነገስ ወደየት መድረስ እንፈልጋለን? የሚሉት ጉዳዮች፤ ትናንት፣ ዛሬንና ነገር አስተሳስረው የተገለጹበት ዓውድ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ ትናንት ታላቅና የሥልጣኔም ባለቤት እንደነበረች መረዳት ተችሏል። በለውጡ ሰሞን ላይ ደግሞ ከታላቅነቷ ሰገነት አሽቆልቁላ የድህነት፣ የኋላ ቀርነት፣ የልዩነትና ኅብረት ማጣት ማዕከል ሆና ስለመገለጧ ግንዛቤ ተይዟል።
ከዚህ ለመውጣት እና ወደቀደመ ከፍታዋ ለማድረስ ብሎም የኃያላን ኅብረት ውስጥ ለመቀላቀል (ኢትዮጵያን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ) የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሕልሞች በዘርፍ በዘርፋቸው ትልም ተተለመላቸው። ዓውድ ተፈጠረላቸው፤ ባለቤትም ተሰጣቸው። ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ሊያሻግሩ፤ በሁሉም መስክ ሊያበለፅጉ፤ በሁሉም መስክ ልዕልናዋን ሊመልሱ የሚችሉ ዕቅዶች፣ ስትራቴጂዎች፣ አሠራሮች ተሰናዱ።
“መደመር መንገዳችን፤ ብልፅግና መዳረሻችን!” ተብሎም፤ እንደ ሕዝብም፣ እንደ ሀገርም በኅብር የተሰባበሰ አንድነት፤ የተደመረ አቅምን ይዞ መጓዝ ተጀመረ። ከማያውቁን አይዶሎጂ ጥገኝነት ይልቅ የራስ ዕውቀትና መንገድ በመደመር እሳቤ ተሰድሮ ወደ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድጎ የሥራ ባህል ተደረገ። ይሄም ‘የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ’ እንዲሉት ብቻ ሳይሆን፤ በአንድና ሁለት መስኮች ላይ ተንጠልጥሎ የመጓዝ ሂደትን አስቀርቶ በዘርፈ ብዙ የልማትና እድገት ዕይታ ውስጥ እንዲገባ አደረገ።
ምክንያቱም፣ መንገድ የሆነው መደመር በእሳቤው፤ ‘ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ’ አይነት ነው። በዚህም ከአንድ ዘርፍ አቅምነት ይልቅ በግብርናውም፣ በማዕድኑም፣ በቱሪዝሙም፣ በኢንቨስትመንቱም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂውም ታግዞ መራመዱ የበለጠ አቅም እንደሚሆን ተለየ። ይሄውም በአስር ዓመት የልማት ግቦች ማሕቀፍ ተመላክቶ የሥራ መመሪያ ሆኖ ተዘጋጀ።
አለፍ ሲልም፣ የመደመር እሳቤው፣ ‘የመጣበትን የረሳ መዳረሻውን አያውቅም’ አይነት ነው። በዚህ መልኩም፣ የትናንት ወረቶችን እየቀመረ፤ የዛሬ አቅሞችን እየጨመረ፤ የነገ ሕልሞችን እያሰመረ መራመድን መርሆው አደረገ። ይሄ ደግሞ ትናንትናችን የችግር ብቻ ሳይሆን የስኬታማነት ዓውድም እንደነበር የተደራ ስለነበር፤ ችግሮችን በማረም እና መልካም ነገሮችን በመቀመር ዛሬ ላይ አቅምም እንዲሆኑ የማስቻል፤ የዛሬው የተደመረ አቅምም ለነገ መዳረሻችን የተሰመረው መስመር ላይ መራመድ በሚያስችል አግባብ የማዋቀር አቅምን የተላበሰ ነበር።
በዚህ መልኩም፣ መደመርን መንገድ ያደረገው ጉዞ፤ መዳረሻዬ ብልፅግና ነው በሚል ደምሳሳ እሳቤ የተቋጨ አልነበረም። ይልቁንም የኢትዮጵያን የብልፅግና መዳረሻ በጉልህ ያመላከተ ነበር። ለአብነትም፣ ራዕይ 2018-ኢትዮጵያን ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን ማሸጋገርን፤ ራዕይ 2023-ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌት የመሆንን፤ እንዲሁም ራዕይ 2040-ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ አርዓያ የሆነን ብልፅግና እውን የማድረግ የብልፅግና ሕልሞች መጥቀስ ይቻላል። በዚህ አግባብ ወደተቀመጠው ስኬት ለመድረስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነው፤ ከፍ ያለ ውጤትና ስኬትም የተገኘበትን እውነት መመልከት ይቻላል።
ሂደታዊ አቅምን መለየት
እነዚህ የሀገራዊ ብልፅግና ሕልሞች ለማሳካት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ አመርቂ ውጤቶችም ተገኝተዋል። ለምሳሌ፣ የነበሩ ችግሮችን በማረምና ወረቶችን በመቀመር ሂደት በተከናወነው ተግባር፤ ችግሮችን ማረም እና የጋራ መንገድን መተለም የሚያስችል የሀገራዊ ምክክር ዓውድ በመፍጠር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ወረቶችን በመቀመር ረገድም፤ ሰፋፊ የታሪክ ቅርሶች ተለይተው ሀገራዊ ከፍታን በሚያጎናጽፍ መልኩ ታድሰው ውበታቸውን መግለጥ ተችሏል። የግብርናውን ዘርፍ አስመንድጎ፤ ስንዴን ከመሸመት አውጥቷል፤ የቡና ኤክስፖርትን በአዲስ የውጤት ሰገነት ላይ አኑሯል።
አሁናዊ አቅምን ለይቶ ለቀጣዩ የጉዞ መስመር ጉልበት ከማድረግ አኳያም፣ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በገበታ ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባ ተነስቶ፤ በጎርጎራ፣ ኮይሻ እንዲሁም ወንጪና ደንዲ ድንቅ ስፍራዎችን ፈጥሮ፤ በትውልዱ መንገድ ከሶፍ ዑመር ዋሻ እስከ ገርዓልታ ተራሮች የተዘረጋ የቱሪዝም መስመርን መሥርቷል። በማዕድን ዘርፉ ዘልቆ እመርታዊ ለውጥን አስገኝቷል። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከትሞም ዲጂታላይዜሽንን ተክሏል። በሰው ሠራሽ አስተውሎት መስኩ ከራሷ አልፋ የአፍሪካ ኩራት የመሆን አቅምን አጎናጽፏታል። በኢትዮጵያ ታምርት እሳቤ ተጉዞም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ መስክ አነቃቅቷል።
በአንጻሩ፣ እዚህም እዚያም የሚታዩ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፤ በግለሰቦችና በቡድኖች የሚታዩ የአመለካከት ችግሮች፤ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር እንከኖች፤ የእውቀትና ክህሎት ክፍተቶች፤ ከቴክኖሎጂ እና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ፈተናዎች፤ ዛሬም ከስኬቱ ባሻገር የሚገለጡ እውነቶች ናቸው። በመሆኑም እነዚህን የስኬትም፣ የፈተናም ዓውዶች በልካቸው መረዳት፤ ስኬቶቹን አልቆ የማስቀጠል፤ ችግሮቹንም ለይቶ ማረም ከተቻለ፤ ጅምር ስኬቱን መድገም ብቻ ሳይሆን አልቆ ማስጓዝ ይቻላል።
የማይናወጥ ማንነት መገንባት
ቀደም ሲል የተጠቃቀሱ ስኬቶች እና ድክመቶች በልካቸው መታየት እንዳለባቸው እሙን ነው። ምክንያቱም፣ ስኬቶች ሁልጊዜም ሂደታዊ ናቸው። እነዚህ ሂደታዊ ስኬቶችን ታዲያ በልካቸው መገንዘብ እና የዛሬው ስኬት የነገው ስኬት መዳረሻ እንጂ መጨረሻ አለመሆኑን ካልተረዳን፤ በተገኘው ጅምር ስኬት መኩራራትና መኮፈስ እንጀምራለን። ይሄ ሲሆን ደግሞ ከትልቁ ስኬት ሳንደርስ በትንሿ ውጤት ተማርከን በአጭር እንቀራለን።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ዛሬ ላይ የሚታዩ ፈተናዎች እና እንቅፋቶች ለጊዜው ሊታገሉን ይችላሉ። ነገር ግን ይሄ ትግል ዘላቂ ሳይሆን ጊዜያዊ፤ ስኬቶቻችን እየተገለጡ በሄዱ ቁጥር ቀስ በቀስ እየተነነ የሚጠፋና የሚያልፍ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይሄን ስንገነዘብ ለችግሮቻችን የማንበረከክ፤ ለፈተናዎቻችን የማንሸነፍ፤ በጉዟችን ለሚገጥሙን ችግሮች ክንዳችን የማይዝል እንሆናለን። በመሆኑም፣ በስኬቶቻችን የማንዘናጋና የማንኮፈስ፤ በፈተናና ችግሮቻችንም ሸብረክ የማንልበትን የማይናወጥ ማንነት መገንባት ይጠበቅብናል። ይሄን ማንነት ገንዘባችን ስናደርግም ነው የነገ መዳረሻ ብለን ያስቀመጥነውን ሕልምና ራዕይ እውን ማድረግ የሚችል ልዕልናን የምንጎናጸፈው።
አቃፊነትና አስተባባሪነት
ይሄ የማይናወጥ ማንነትን የመገንባት ሂደት በራስ ላይ ብቻ ሊቆም የሚገባው አይደለም። ይልቁንም መንገድ በጋራ ሲሆን ቀና እንደሚሆን ሁሉ፤ የስኬት ጉዞም በኅብረትና መደመር ተቃኝቶ ሲመራ ነው ከሚፈለገው ከፍታ ላይ መድረስ የሚችለው። በመሆኑም ሥራዎች በራስ አቅም ብቻ ከከወኑት ከፍጻሜ እንደማይደ በመረዳት፤ ከቤትም ከጎረቤትም፣ ከአካባቢም ያለን አቅም ማስተባበር እና መደመር የግድ ይላል።
በዚህ መልኩ ተጉዘን በአረንጓዴ ዐሻራ እመርታዊ ውጤት አምጥተን አሳይተናል። በዚህ መልኩ ተጉዘን በምግብ ራስን የመቻል መንገድን ተልመን ለሌሎች አብነት ሆነናል። በዚህ መንገድ ተጉዘን በዲፕሎማሲው መስክ አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። በቀጣይም ይሄንኑ መንገድ ይዘን የባሕር በር ባለቤትነትን እውን እናደርጋለን። ሌሎች ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጥቅምና ፍላጎታችንንም እናሳካለን። በመሆኑም በመደመር መንገድ ስንጓዝ የራስን አቅም ብቻ ሳይሆን የሌሎችን አቅም እና እውቀት ደምሮ ወደ ብልፅግና መድረስ የሚያስችል ያልተቆራረጠ ስኬትን ማምጣት እንደሚቻል መገንዘብ የግድ ይሆናል።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ በዋናነትም ባለፈው በጀት ዓመት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከውና፤ ዘርፈ ብዙ ውጤትና ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ለአብነት፣ በኢኮኖሚው መስክ በግብርና፣ በፋይናንስ፣ በወጪ ንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እና ሌሎችም ከፍ ያለ ውጤት፤ የሚያድግ ስኬትም አግኝታለች። በማኅበራዊ መስክም ቢሆን ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎችን ከውናለች። በፖለቲካውም ቢሆን፣ አካታችነትና አሳታፊነትን ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን አግባብ ገልጣለች።
በሰላምና ፀጥታው ዘርፍም አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉበትን ምስክርነት የሰጠ ተግባርን ፈጽማለች። በውስጧ ያለውን ችግር ከማረምና ፈር ከማስያዝ ጀምራ፤ የሌሎች የሰላም አጋር መሆንም ችላለች። በዲፕሎማሲው መስክም እኩልነት እና ፍትሐዊነት የሰፈነባት ዓለም እንድትፈጠር፤ ዓለም ከአንድ ወገን ዘዋሪነት ወደ ባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲና ፖለቲካ ዓውድነት ሽግግር እንድታደርግ በተናጠልም፤ በጋራም እየተጋች ትገኛለች።
በጥቅሉም የነበረችበትን፣ ያለችበትን እና ልትደርስ ያሰበችበትን ቦታ በመለየት፤ ለዚህ የሚሆናትን የራሷንም ሆነ የሌሎች ተደማሪ አቅም በማጤን፤ ለዚህ የሚሆን አመቺ የአሠራር ሥርዓት በመፍጠርና በመተግበር ተራማጅ የስኬት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ስኬቶቿን እያጎላች፤ ፈተናዎቿንም ወደ ዕድል እየቀየረችም የብልፅግናዋን አይቀሬነት እየገለጠችም ነው። ይሁን እንጂ ይሄ ጅምር የቀጣዩ ጉዞ መሠረት እንጂ ሙሉ ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። በመሆኑም የቀጣዩ ጊዜ ስኬትን ከመግለጥ ባሻገር፤ ስኬቶችን መድገምን፣ አለፍ ሲልም አልቆ መፈጸምን የግድ የሚሉ ናቸው። ለዚህ ደግሞ በአቅምም፣ በሞራልም፣ በቁርጠኝነትም፣ በዕውቀትና ክህሎትም የተገቡ ሆኖ መገኘት የግድ ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከሰሞኑ የካቢኔ አባላቱን ሰብስበው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድና በገመገሙበት ወቅት፤ “በ2017 የሥራ ዘመን ትርጉም ያለው እና ለመጪው የ2018 የቀጠለ የእድገት ጉዞ ጠንካራ መሠረት የሚሆን እድገት ፈፅመናል። በዚህ መነሻም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጪው ዓመት ለትግበራ የተዘጋጀውን የ2018 የተሟላ የሁሉም ዘርፎች እቅድ እና ሀገራዊውን የልማት እቅድ ለመገምገም ተሰብስቧል።” ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት አፈጻጸም ኢትዮጵያ ማንሰራራት የጀመረችበት ነው። ምክንያቱም፣ አፈጻጸሙ እስከ አሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ከነበሩት አፈጻጸሞች ሁሉ በእጅጉ የላቀ ነው። የወጪ ንግድ ከእጥፍ በላይ ያደገበት፣ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት፣ የዋጋ ግሽበትም በግማሽ የቀነሰበት ነው። ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይሲቲ ዘርፎችም እጅጉን ተስፋ ሰጪ ውጤት አምጥተዋል። በ2018 በጀት ዓመትም ይህን አሻሽሎ መድገም እንዲቻል ጠንካራ አመራር ስለሚያስፈልግ ካቢኔው ይህን ተረድቶ በዕውቀት መምራት ይኖርበታል። ምክንያቱም ተጨባጭ ለውጥ የሚመጣው ይህ መልካም ጅማሮ መድገምና ማላቅ ሲቻል ስለመሆኑ ማብራሪያ አዘል ማሳሰቢያ ማስተላለፋቸውም ይሄንኑ የሚያጠናክር ሐቅ ነው።
ሰላም!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዐምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም