
እንደ እናቴ እታለምዬ ሞት ሁልጊዜ የእግር እሳት ሆኖ የሚያንገበግበኝ የኤርትራ መገንጠል ነው። ኤርትራንም ኤርትራውያንንም ማጣት በግል እንደደረሰብኝ ማጣት ነው የሚሰማኝ። ይህን የምለው ሰሞነኛ አጀንዳ ስለሆነ አለመሆኑም የቅርብ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ ያውቃሉ። ሕወሓትን አምርሬ የምቃወመው፤ እንደ አባቴ ገዳይ የማየው በኤርትራ መገንጠል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል ብዬ ስለማምን ነው። ብቸኛ ገዢ ለመሆን ኤርትራን የጦስ ዶሮ አድርጓታል። ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅሙ ሲል ስትራቴጂካዊ ዋጋ አስከፍሎናል ብዬ ስለማምን መቼም ይቅር አልለውም። ሆኖም ተጠያቂው እሱ ብቻ አይደለም።
የአጼ ኃይለሥላሴ ግብታዊ አካሄድ ማለትም በቂ ፖለቲካዊ ሥራ ሳይከናወን ማለትም ኮንፌዴሬሽኑን አፍርሰው ኤርትራን ማዋሀዳቸው፤ ገንጣይ አስገንጣዮችን በዲፕሎማሲያዊ በወታደራዊና በፖለቲካዊ ጥረት በእንጭጭ አለማስቀረታቸው፤ ደርግ ወደ አገዛዝ ከመጣ በኋላ ደግሞ በድርድር ለመፍታት ሀቀኛ ጥረት አለማድረጉ፤ ሕወሓት ለኤርትራ መገንጠል ከሻዕቢያ ጎን ሆኖ መዋጋቱ እና ወዲህ በትጥቅ ትግል ደርግን ማዳከሙ ኤርትራ እንድትገነጠል የአንበሳውን ድርሻ መጫወቱ ሁሌ እንደረገምሁት አለሁ።
ይባስ ብሎ ደርግ ከተገረሰሰ በኋላ ሻዕቢያ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሃሳቡን ትቶ ከሕወሓት ጋር ጥምር መንግሥት ለማቋቋም ፍላጎት ሲያሳይ ሕወሓት በተጠናወተው የትንሽነትና የጠቅላይነት አባዜ ሃሳቡን ውድቅ ከማድረግ አልፎ ሻዕቢያ የኤርትራ ሕዝብን የዘመናት ጥያቄ አደጋ ላይ ሊጥለው ነው የሚል ገገማ ፕሮፓጋንዳ በማራገብ ከሻዕቢያ በላይ ለኤርትራ ሕዝብ ተቋርቋሪ ሆኖ ከመገለጡ ባሻገር አዋክቦ ወደ ሕዝበ ውሳኔ እንዲገባ አድርጓል።
ይህ ሳያንስ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት መጠየቅና መደራደር እንደሚችል እየተነገረው ሕወሓት ግን ድንገት እጁ ላይ የወደቀችውን ኢትዮጵያን ለመግዛት ቋምጦና ጎምዥቶ ስለነበር ሀገር ሕዝብና የባሕር በር አሳጣን በማለት ዛሬ ድረስ ጥርሴን እነክስበታለሁ። ሞቼም አስከሬኔ ይቅር አይለውም። ከአጼ ምኒልክ እስከ ሕወሓት የተፈጸመ የስህተት ቅብብሎሽ ዛሬ 135 ሚሊዮን ሕዝብ የባሕር በር አልባ አደረገው።
ከዘፍጥረት ጀምሮ በሰሜንም በምሥራቅም የባሕር በር የነበራትን ሀገር መና አስቀሯት። ይች ታላቅ ሀገር በአንድ ወቅት የግዛቷ አካል የነበረችው ጅቡቲ እጅ ላይ ወድቃለች። ከ95 በመቶ በላይ ወጪና ገቢ ንግዳችን በእዚች ሀገር መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው። በእዚህ ደረጃ ኢትዮጵያ ጥገኛ ሆና ሉዓላዊ ሀገር ናት ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር መታበይ ነው። አሁን ጥያቄው ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋት ወይስ አያስፈልጋት የሚል አይደለም። ጥያቄው አሁን ያለው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጥያቄውን ለማንሳት ትክክለኛ ጊዜ ነው ወይ የሚል ነበር። መጀመሪያ የቤት ሥራችንን ብንከውን አይሻልም ወይ። እርቅን ሰላምንና አንድነትን እውን ማድረግ አይቀድምም ወይ። ይሁንና ይሄ ስጋት እንዳለ ሆኖ ጥያቄው በሀቀኛ ቁጭት የተነሳ ከሆነ በቁጥብነት with reservation እደግፈዋለሁ።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት የባሕር በር ካላገኘች ሀገር መሆን አትችልም መባሉ ትክክል ነው። ሀገሮች የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እንዲያከብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ሰኔ መገባደጃ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሲሰጡ ነው። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ሲያብራሩ፤ ‹‹ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር ናት፣ በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም። ሀገር መሆን መብቷ ነው።
ጂቡቲ ሉዓላዊ ሀገር ናት። ሶማሊያ ሉዓላዊ ሀገር ናት መከበር አለባት፣ ጥያቄ የለንም፤›› በማለት ካብራሩ በኋላ፣ ‹‹አብሮ ለመኖር ያለው ነገር ሰጥቶ መቀበል በመሆኑ ይህ መከበር አለበት›› ብለዋል። የባሕር በር የሚመጣው በገንዘብ ወይም በመሬት ልዋጭ ነው የሚለው ጉዳይ በንግግር መሆን አለበት ሲሉም ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።
እንደ ጸሐፊ ፌስቡክ ላይ ባጋራን አስተያየቱ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ጥያቄን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ የመዘዘው ለፖለቲካ ፍጆታ ነው በሚል ጉዳዩን ለማጣጣል የሚሞክሩ ወገኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች አጀንዳውን ከማጣጣል ባለፈ፣ የተሻለ አማራጭ መንገድ መኖሩን አይጠቁሙም። እንዳውም የአንዳንዶቹ አቋም ኢትዮጵያ የባሕር በር አያስፈልጋትም የሚል አንደምታ ያለው ነው። በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን በማጣቷ ስንብሰለሰል የቆየን ወገኖች አለን። ከእዚያም ባለፈ፣ ለወደብ ኪራይ የምናወጣውን በማስላት፣ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ እንዳጣንና ይህን ለልማት ብናውለው ኖሮ በሀገር ደረጃ የሚኖረውን ውጤት በማሰብ መቆጨታችን አልቀረም።
የባሕር በር ጉዳይ፣ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ፣ ከብሔራዊ ጸጥታና ደህንነት ጋር በተያያዘ ያለው አንደምታም ሰፊ ነው። የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት፣ ከቅርብና ከሩቅ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች የተጋለጡና፣ በሌሎች ሀገራት ዓይንም ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ የሌላቸው መሆናቸው እሙን ነው። በአጠቃላይ፣ የባሕር በር ጉዳይ፣ እጅግ አንገብጋቢና ስትራቴጂያዊ ነው። ቢሆንም፣ በወያኔ/ ኢህአዴግ ዘመን፣ ጥያቄው በመንግሥት ደረጃ አይነሳም ነበር። ይልቁንም እንደመንግሥት ፖሊሲ የተያዘው ጥያቄውን የሚያነሱ ወገኖችን በጦረኝነት መፈረጅና ማፈን ነበር። አሁን ደግሞ የተገላቢጦሽ በመንግሥት ደረጃ አጀንዳው ሲነሳ መንግሥትን በጦረኝነት የሚፈርጁ ቡድኖች አሉ። በእርግጥ፣ ትናንት በሥልጣን ላይ የነበሩና ከኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ቡድኖች፣ ዛሬ ላይ የመንግሥት ተቃዋሚ ናቸው።
ይህም ሆኖ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመሩትን መንግሥት መቃወም አንድ ነገር ነው። ከኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም በተጻራሪ መቆም ግን ሌላ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጥቅም መቆም የዐቢይን (ዶ/ር) መንግሥት መደገፍ ማለት አይደለም። ወይስ፣ አጀንዳው ዐቢይ (ዶ/ር) መንግሥት ስለተያዘ ብቻ ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ መቆም አለብን። ዐቢይ (ዶ/ር) መንግሥት የአካሄድ ችግርና የዲፕሎማሲ ክፍተት ካለበት ክፍተቶችን ማመላከትና ገንቢ ሃሳብ ማቅረብ የወግ ነው። ከእዚያም ባለፈ፣ አስፈላጊውን ቴክኒካል ድጋፍ መስጠት ተገቢ ነው። ከእዚያ ውጪ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ ያለውን ስትራቴጂያዊ አጀንዳ ለማደናቀፍ መሞከር ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ሲሉ እኝህ ጸሐፊ ያሳስባሉ።
“የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች፤” በሚል ርዕስ ለሚ ታደሰ ያስነበቡን መጣጥፍ ላጋራችሁ ወደድሁ። ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ሶማሊያን እና ጅቡቲን ያቀፈው እና በአፍሪካ አህጉር ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ዓይናቸውን የጣሉበት አካባቢ ነው። ቀደም ሲል ይህን አካባቢ ዋና ትኩረታቸው አድርገው የነበሩት እንደ አሜሪካ እና ቻይና ያሉ “ኃያላን” የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን የአፍሪካ ቀንድ ለአዳዲስ ተወዳዳሪዎች ወሳኝ የፉክክር ሜዳ ሆኗል። ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ኢራን እና ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞቻቸውን በአካባቢው ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዋና ቀጣናዊ ተዋናዮች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ እና ቱርክን ጨምሮ አስራ አንድ ሀገራት በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የጦር ኃይል ሰፈር አላቸው፤ እዚህ የመገኘታቸው ምክንያት እንደየሀገራቱ ይለያያል። ይሁንና የቅርብ ጊዜ ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች የአካባቢውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በማሳደጉ ቀይ ባሕር ታላቅ የኃይል ሽኩቻ ምህዋር መሆኑን ግልጽ ሆኗል። የቀይ ባሕር ተፈጥሮ 2250 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀይ ባሕር ኮሪዶር ሜዲትራኒያን ባሕርን እና ሕንድ ውቅያኖስን አልፎ ወደ እስያ የሚለየው ቁልፍ የውሃ መስመር ሲሆን፤ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የንግድ እንቅስቃሴ ይከናወንበታል።
ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በየዓመቱ በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል፤ የንግድ መስመሮቹ በዓለም ላይ ካሉት 10 እጅግ ስትራቴጂካዊ የውሃ መንገዶች ሁለቱን ማለትም በባሕሩ ደቡባዊ መግቢያ የሚገኘውን ባብ ኤል- ማንዳብ እና በሰሜን ግብጽ የሚገኘውን ስዊዝ ካናልን ያቋርጣሉ። ይህ የቀይ ባሕር አካባቢ በዘይትና በከበሩ ማዕድናት የበለጸገ ነው።
እንደ የማሪን ኢንሳይት (Marine Insight) በቀይ ባሕር ጠረፎች 10 ትላልቅ እና ሥራ የሚበዛባቸው ወደቦች አሉ። በቀይ ባሕር ዙሪያ ከሚገኙት ሥራ የሚበዛባቸው ወደቦች መካከል የጂዳ ወደብ አንዱ ሲሆን፤ በዓመት ወደ 52 ሚሊዮን ቶን ጭነት፣ 4 ሚሊዮን ኮንቴነሮችን (TEU) እና 275 ሺህ 700 መንገደኞችን ያጓጉዛል። በፖርት ሱዳን 8.6 ሚሊዮን ቶን ጭነት እና 431 ሺህ ኮንቴነሮች ይጓጓዛል። ሌላው ቀይ ባሕር ላይ የሚገኝ ወደብ የጂቡት ወደብ ሲሆን፤ ከ5.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና 293 ሺህ ኮንቴነሮች (TEU) በዓመት ይተላለፍበታል። በምፅዋ ወደብ ደግሞ በዓመት 826 ሺህ ቶን ጭነት ያልፋል።
ሌላኛው የሳዑዲ ዓረቢያ ንብረት የሆነው ያንቡ የንግድ ወደብ 1.8 ኪሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ በዓመት 13.5 ሚሊዮን ቶን ጭነት የሚያስተናግዱ 12 ማረፊያዎች እና 1 ሺህ 500 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ልዩ የመንገደኞች ተርሚናል አለው። የግብፅ ንብረት የሆነው ሳፋጋ ወደብ 100 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያለው ሲሆን፤ በዓመት ወደ 742 መርከቦችን በማስተናገድ 3.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና ከ876 ሺህ በላይ መንገደኞችን ያስተናግዳል።
የእስራኤሉ ኢላት ወደብ 2.1 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት 70 ሺህ መኪኖችን እና 50 ሺህ ኮንቴነርች በየዓመቱ ያልፉበታል። ሆዴዳ ወደብ የየመን ንብረት ነው፤ 1 ሚሊዮን ቶን የፔትሮሊየም ምርቶችን ጨምሮ 5.7 ሚሊዮን ቶን ጭነት ያስተናግዳል። የኤርትራው አሰብ ወደብ 1.2 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት፣ 32 ሺህ ኮንቴነሮችን(TEU) እና 1.3 ሚሊዮን ቶን ፈሳሽ ጭነት ይተላለፍበታል። የየመኑ ኤደን ወደብ በዓመት 2 ሺህ መርከቦች የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፤ 15.6 ሚሊዮን ቶን ጭነት፣ 380 ሺህ ኮንቴነሮች (TEUs) በእዚህ ይተላለፋሉ።
የባሕር በርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህም፣ ዓሳ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል። የእዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚያመለክተው ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በእዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተመላክቷል። አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ በባሕር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሐተታ የአፍሪካ ሀገራት የባሕር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባሕር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሶ፤ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ይደነግጋል። ኢትዮጵያ እና የባሕር በር ታሪካዊ ዳራ የጎን ስፋቱ ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር የማይበልጠውን እና ከመርሳ ፋጡማ ተነስቶ የትግራይን እና አፋርን ምድር እየታከከ ቁልቁል እስከ ራስ ዱሜራስ የሚወርደውን ቀጭን መሬት ያየ ሁሉ፤ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባሕር የሚያስወጣ መሬት እንዳይኖራት ሆን ብለው ያጠሩት አጥር መሆኑን ይረዳል።
ኢትዮጵያ ይህንን አጥር አፍርሳ ኤርትራን ለመቀላቀል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ጥያቄ ባቀረበችበትና ሙግት ባካሄደችው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ወቅት የባሕር በር እንድታገኝ የሚያስችል መሬት ተፈቅዶላት እንደነበረ ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) “አሰብ የማን ናት? (የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ)” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የወቅቱ ጥያቄ መላዋን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ማዋሃድ ስለነበር የተሰጣትን የባሕር በር የማግኘት አማራጭ አልተቀበለችውም ነበር።
ክርክሩ እና የዲፕሎማሲው ዘመቻ ፍሬ አፍርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ተወስኖ ኢትዮጵያም ዳግም የባሕር ጠረፍ ባለቤት ሆና ነበር። እንደ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) በወቅቱ የነበሩት መንግሥታት በፌዴሬሽኑ አያያዝ ላይ በተከታታይ በፈጸሙአቸው ስህተቶች ፌዴሬሽኑ ፈርሶ በተካሄደው ጦርነት ብዙ ደም ፈሶ ኤርትራ ነጻ ሀገር እንድትሆን በተፈቀደበት ወቅትም ኢትዮጵያ ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንዳታቀርብ በወቅቱ የነበሩት መሪዎቿ ተቃውመው ባዶ እጇን አስቀርተዋታል።
ቀይ ባሕር አካባቢ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች እና ቀጣይ የአካባቢው እጣ ፈንታ፤ ከላይ እንደተጠቀሰው አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በቀይ ባሕር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት ከመከታተል አልፎ የጦር ሰፈሮቻቸውን አቋቁመው በአካባቢው ያላቸውን ዓለም አቀፍ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ነው። እነዚህ ሀገራት አድማስ ተሻግረው እዚህ ሲገኙ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጥቀስ እና በአካባቢው ያለው ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ በዓለም ላይ ሊፈጥር ይችላል ያሉትን ቀውስ ምክንያት በመስጠት ነው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት መሠረት በቀይ ባሕር ዙሪያ ያለው የሕዝብ ብዛት እ.ኤ.አ 2050 ዓ.ም 343 ሚሊዮን ይደርሳል። አውሮፓን ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሩቅ ምሥራቅ ጋር የሚያገናኘው የቀይ ባሕር እና አንድ ሺህ ኪሜ ርዝመት ያለው የባሕሩ ክፍል ሰላሙ እንዲጠበቅ የአካባቢው ሀገራትን ተሳትፎ ይፈልጋል።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለ24 ዓመታት ያገለገሉት እና በአሁኑ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የዓረብ ማዕከል (Arab Center Washington DC) ተባባሪ ባልደረባ የሆኑት ቻርለስ ዱኔ እንደሚሉት፤ ቀይ ባሕር ወሳኝ የኢኮኖሚ የደም ቧንቧ ሲሆን፤ ተፈላጊነቱ በመጪዎቹ ዓመታትም ከእዚህ በላይ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። በጂኦፖለቲካዊ አገላለጽ፣ ምናልባት ከአሜሪካ እና አውሮፓ ፖሊሲ አውጪዎች ነባራዊ “የመካከለኛው ምሥራቅ” ትኩረት የበለጠ የተዋሃደ የፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ መታየት አለበት ይላሉ።
በአካባቢው ያለው የአፍሪካ ክፍል በመሠረተ ልማት እጥረት እና በምጣኔ ሀብት ዕድገት ኋላ ቀር ቢሆንም፤ የቀጣናው አቅም እያደገ እና የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ በቀይ ባሕር አካባቢ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ፍላጎት፣ የትጥቅ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እየሰፋ እንደሚሄድ ተንታኞች ይገልጻሉ። እነዚህን ዓለም አቀፍ ነባራዊ እና መጻኢ ሁኔታዎችን በመተንተን በእዚህ በቀይ ባሕር አካባቢ የሚያንዣብቡ ሀገራት ግን በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ላይ የምትገኘውን እና አካባቢውን አስተሳስሮ ለመያዝ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ያለችውን ኢትዮጵያን ይዘነጋሉ። ለአብነትም በሳዑዲ ዓረቢያ አስተባባሪነት የተመሠረተው “The Red Sea Forum/Alliance” የሚጠቀስ ነው። ስምንት ሀገራትን ያቀፈው እና እ.አ.አ በጥር 2020 በሳውዲ ዓረቢያ አንቀሳቃሽነት የተመሠረተው “The Red Sea Forum/Alliance” ሲቋቋም ኢትዮጵያን እና ሌሎች የጉዳዩን ባለቤቶች ማግለሉ ፍትሐዊ ካለመሆኑም በላይ የጥምረቱን ውጤታማነት ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባ እንደሆነም ይገለጻል።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፤ ይህም በዓለም የባሕር በር ከሌላቸው ሀገሮች ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር ያደርጋታል። በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 ሀገሮች የባሕር በር የሌላቸው ሲሆን፤ በእነዚህ ሀገራት ከሚኖረው አጠቃላይ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቀጣይ በአካባቢው ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ያካተተ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሥራት ምንም ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝባቸው ሕጋዊ መሠረቶች ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ሕጎች እና የአፍሪካ ኅብረት ድንጋጌዎች ኢትዮጵያንም የሚመለከቱ ናቸው። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የአፍሪካ ቀንድ ሲሆን፤ ይህም የጅቡቲ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የባሕር ዳርቻን ያጠቃልላል። በሱዳን እና በኬንያ በኩል ያለው መስመርም ሌላው የባሕር በርን ለመጠቀም የሚያስችላት አማራጭ መንገድ ነው። በሌላ አነጋገር የመንግሥቱ ድርጅት በ1982 ባወጣው የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 የተጠቀሰው ድንጋጌ፣ ከአንቀጽ 125 እስከ 132 የተገለጹት ድንጋጌዎች እና አንቀጽ 148 የኢትዮጵያን የባሕር መውጫ መብት የሚመለከቱ ናቸው።
በ1900፣ 1902 እና 1908 በኢትዮጵያ እና የኤርትራ ቅኝ ገዢ በነበረችው ጣሊያን መካከል የተደረጉት ስምምነቶች እና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት በ1964 የቅኝ ግዛት ውሎችን ማጽናቱ ለኢትዮጵያ የባሕር መውጫ መጥፋት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መምህሩ ዳምጠው ተሰማ “International Law and Ethiopia’s right access to the Sea outlet” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ጠቅሰዋል። ምሁሩ እነዚህ ስምምነቶች ቢኖሩም በሌላኛው ወገን በመጣሳቸው ሕጋዊ ተፈጻሚነት እንደሌላቸው በማስረጃ አስደግፈው አስቀምጠዋል።
ተመራማሪው ስምምነቶቹ ሕጋዊነት የሚያጡባቸውን መሠረቶች ሲጠቅሱም፤ ጣሊያን እ.አ.አ በ1935 ኢትዮጵያን ዳግም ስትወር የመጀመሪያውን ስምምነት መጣሷን ይገልጻሉ። በእዚህ ረገድ የቪየና የስምምነት ሕግ አንቀጽ 60 (1) የሁለትዮሽ ውልን በአንደኛው አካል መጣስ ሌላው አካል ለውሉ እንዳይገዛ እና ውሉን የጣሰውን አካል የመክሰስ መብት ይሰጠዋል።
በእዚህም መሠረት የ1900፣ 1902 እና የ1908 ስምምነቶች በሌላኛው አካል ስለተጣሰ ተፈጻሚነት እንደሌለው ኢትዮጵያ ተከራክራለች፤ ይህ ደግሞ የአልጀርሱንም ስምምነት ዋጋ ያሳጣዋል።ሁለተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1950ዎቹ ምክረ ሃሳብ እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ዳግም በኮንፌዴሬሽን መዋሀድ ‘የኢትዮጵያን የባሕር የማግኘት መብት’ ለመጠየቅ መሠረት ሊሆን የሚችል ስምምነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል መምህር ዳምጠው በጥናታዊ ጽሑፋቸው አመልክተዋል። እንደእዚህ ዓይነቶቹ ተጨባጭ እውነታዎች እና የዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች የአልጀርሱ ስምምነት ሕጋዊ መሠረት እንደገና እንዲገመገም ጥያቄ እንደሚያስነሳ ጠቁመዋል።
ሕጋዊ መሠረቶች በመነሳትም
ከአምስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሲመጣ በቅድሚያ ከተሠሩት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የባሕር ኃይል መመሥረት ነው። ከፈረንሳይ እስከ ዱባይ ለባሕር ኃይል ሥልጠና ድጋፍ በማፈላለግ የባሕር ኃይልን እንደገና ያደራጀችው ኢትዮጵያ፤ ከ27 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የባሕር ኃይል አድሚራል በመሾም ኃይሉን አጠናክራለች። ኢትዮጵያ የምታምነው የባሕር በርም ሆነ የቀይ ባሕር ጉዳይ ከኤርትራም፣ ከጂቡቲም፣ ከሶማሊያም፣ ከሱዳንም የገዘፈ የዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካል እና የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን ነው። የቀይ ባሕር ከሜዲትራኒያን ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ጫፍ፣ ከገልፍ እስከ አፍሪካ ቀንድ ያለውን አካባቢ የሚያካትት ነው። ስለሆነም ጉዳዩ በጥንቃቄ እና በሰጥቶ-መቀበል (Give-and-Take) መርህ የሚከናውን እንጂ ጦር በመስበቅ የሚደረግ አይደለም።
ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) እንደጠቀሱት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝባቸው ነባራዊ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው። የዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጠቀም በቅርቧ የሚገኘውን የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማስከበር፣
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደምትፈልገው ሁሉ የባሕር በር ያላቸው የአካባቢው ሀገራት የእርሻ መሬት እና ሌሎች የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ስላሉ እነዚህን በመለዋወጥ ሰጥቶ የመቀበል መርህን ተግባራዊ በማድረግ፣ሀገራቱ ወደቦቹን እኩል በማልማት የሚጠቀሙባቸውን ጣምራ ሉዓላዊነት (joint sovereignty) በመፍጠር በጋራ መጠቀም የሚሉት ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ አባላት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያም ከእነዚህ አማራጮች ውጪ የመሄድ ዓላማ የላትም።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም