አዲስ አበባ፡- በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና አካባቢው በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በወንጀሉ ጠንሳሽነትና ተሳታፊነት በተጠረጠሩት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እነ አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) አራት ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት የክስ መመስረቻ 13 ቀናት ፈቀደ፡፡
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና አካባቢው ብሄርን መሰረት በማድረግ ከሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጽሞ ብዙ ሰዎች በሞቱበት፣ በአካልና ንብረት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በወንጀሉ ጠንሳሽነትና ተሳታፊነት የተጠረጠሩት፤ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወይዘሮ ራህማ መሐመድ፣ የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አብዱራዛቅ ሳኒና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፈርሃን ጣሂር ናቸው፡፡
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ትናንት የቀረቡት ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ሲያካሂድ እንደሰነበተ ዓቃቤ ህግ አስታውሷል፡፡ የምርመራ መዝገቡን በሰው፣ በሰነድና በሌሎች ማስረጃዎች አደራጅቶ መዝገቡን ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም እንዳደረሰውም ጠቁሟል፡፡ ሆኖም ከቀረቡት በርካታ ማስረጃዎች አንጻር መዝገቡን መርምሮ ተገቢውን ክስ በመመስረት ለመደበኛ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የጊዜ እጥረት እንደገጠመው ጠቅሷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንን በመገንዘብ ግለሰቦቹ ከተጠረጠ ሩበት ድርጊትና ከደረሰው ከባድ ጉዳት አንጻር እንዲመለከተው አሳስቦ፤ በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 109/1 መሰረት የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ለችሎቱ አቤቱታ አቅርቧል፡፡
ግለሰቦቹ በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ብሄርን በመለየት የብዙ ሰዎች ህይወት ያለፈ በመሆኑ የሚቀርብባቸው ክስ ዋስትና ይከለክላል ያለው ዓቃቤ ህግ፤ ክስ እስኪቀርብ ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩለት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ዓቃቤ ህግ የጠየቀው የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ረጅም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ለአምስት ወራት ያህል በእስር የቆዩ በመሆናቸው ጊዜው እንዲያጥርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ለዓቃቤ ህግ የተሰጠው በምርመራ ሂደቱ ያልተሳተፈ ከሆነ መሆኑንም በመጠቆምም፤ በምርመራ ሂደቱ ዓቃቤ ህግ ከፖሊስ ጋር ተጣምሮ ሲሰራ በሰነበተበት ሁኔታ 15 ቀናት መፈቀድ የለበትም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ቢፈቀድ እንኳን አጭር ጊዜ እንዲሆንላቸውም ፍርድ ቤቱን አሳስበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ መዝገቡን ጥር ስምንት ቀን 2011 ዓ.ም ለዓቃቤ ህግ መላኩን፣ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ውስብስብና ከባድ መሆኑን፣ በምርመራ ሥራው ከፖሊስ ጋር ከተጣመሩት ዓቃቤ ህጎች በተጨማሪ ሌሎችም ዓቃቤ ህጎች ሊሳተፉበት እንደሚችሉ በመገመትና የጠራ ክስ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ታሳቢ በማድረግ ዓቃቤ ህግ መዝገቡን ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ የ13 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ በመፍቀድ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ አዟል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ዘላለም ግዛው