የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነቡ ተስፋዎች፣ የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊነት የምናይባቸው ተምሳሌቶች፣ ወላጅ ለፍቶ ደክሞ አሳድጐ ፍሬውን የሚያጭድባቸው ቡቃያዎች፣ ሀገር ከድህነቷ ቀንሳ ብዙ መዋዕለ ነዋይዋን ያፈሰሰችባቸው እምቡጦቿ ናቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች።
የሀገራችን መጻዒ ዕድልና ወድቀቷም ሆነ ብልጽግናዋ በእነዚህ ተማሪዎች እጅ ላይ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። መምህሩም ሆነ መሃንዲሱ፣ ሃኪሙም ሆነ ጂኦሎጂስቱ፣ አካውንታንቱም ሆነ ኢኮኖሚስቱ በአጠቃላይ ሀገር ለነገ ግንባታዋ የምትፈልገው አዲስ ደም የሚፈልቀው ከእነዚሁ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ነውና፡፡ ስለሆነም የዩኒቨርሲቲዎቻችንና የተማሪዎቻቸው ጤናማ መሆን የሀገር ጤና መሆን፤ መታመማቸው ደግሞ የሀገር ህመም ነው ብለን መደምደም እንችላለን። መቻቻልን፣ ጤናማ የሃሳብ ክርክርን፣ ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ከግጭት መቆጠብ፣ ዘረኝነትን መጠየፍና ለወገን አለኝታ መሆን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን ሁሌም የሚጠበቁ ተግባራት ናቸውና ተማሪዎቻችን ይኽንን ተግብረው ማየት የሁልጊዜ ምኞታችን ነው።
ይኽንን እውነት በመገንዘብም የ2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የትምህርት መጀመርን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት «የነገዋ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ሆናችሁ የምትወጡበትን የትምህርት ተቋም የግጭትና የጥላቻ መናኸሪያ ለማድረግ ተፍ ተፍ የሚሉ ካሉ በሰለጠነ መንገድ ገሥጿቸው፣ አርሟቸው፣ ተቃወሟቸው። ከልክ በላይ ከሄዱ ደግሞ ለተቋሙ አስተዳደር አባላትና ለጸጥታ አካላት አጋልጣችሁ ስጧቸው። እንደዚያ የሚያደርጉ ሰዎች የእናንተን ጣፋጭ የኮሌጅ ሕይወት ለማበላሸትና የሀገራችንን መጻኢ ዕድል ለማሰናከል የተሰለፉ ናቸውና ‹ልዩነታችን ውበታችን ነው› በሏቸው። ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ አሸንፋችሁ አሳዩዋቸው።» ብለው ነበር።
ደም የጠማቸውና በንጹሐን ተማሪዎች ዕልቂት ለውጡን በማደናቀፍ አገር ማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች ለጥፋት ዓላማቸው ማሳኪያ ዩኒቨርሲቲዎችን በምሽግነት እየተጠቀሙ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ እነዚሁ የጥፋት ኃይሎች አቅደውና ተዘጋጅተው በመሥራት በሌሎች ሃገሮች የተከሰቱ የእልቂት ፎቶዎችን በሶሻል ሚዲያ በመለጠፍ እንዲሁም ጥቃቅን የግለሰብ ግጭቶችን የብሄር መልክ በማላበስ ወዘተ ሰላማዊ የትምህርት ሂደት እንዲስተጓጐል፣ ንብረት እንዲወድምና መተኪያ የሌለው የንጹሐን ተማሪዎች ህይወት እንዲቀጠፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ደም አፍሳሽ ፍላጐታቸው ማብቂያ ስለሌለውም በአንዱ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን ችግር ወደሌላው በፍጥነት በማዛመት እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እንቅልፍ አጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ችግር ወደ ጐንደርና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የተዛመተበት ሁኔታ ነው፡፡
የጥፋት ኃይሎች ሥራ ሁሌም ውድመትና ዕልቂት ነውና በህግ አግባብ የእጃቸውን እስኪያገኙ ድረስ መልካቸውን እንደ እስስት እየለዋወጡ እዚህም እዚያም የእልቂት እሳት እንደሚለኩሱ የታወቀ ነው፡፡ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ግን ይኽንን ሴራ ማክሸፍ የሚቻለው ተማሪዎች የእነዚህን ኃይሎች ሰይጣናዊ ዕቅድ በሚገባ ተገንዝበው የጥፋት ተልዕኮ ፈፃሚም አስፈፃሚም ከመሆን ሲታቀቡ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ በግለሰብ ስሜት እየተነዱና የጠላትን አጀንዳ እየተቀበሉ መፈጸም ትርፉ ጸጸትና ውድቀት ብቻ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ባልተጨበጠና ዓላማ ቢስ ለሆነ ነገር ንጹሁን የወንድምና የእህትን ደም አፍስሶ በሰላም የሚኖር ህሊና ፈጽሞ ሊኖር አይችልም።
«አጠገባችሁ ያለው ተማሪ ወንድማችሁ እንደናንተው ከምስኪን ቤተሰብ የተገኘ ፣ ጭራሮ ለቅማ፣ ጠላ ሸጣ፣ ግፋ ቢል በጉሊት ችርቻሮ ወይም በመንግሥት ሥራ ከእጅ ወደአፍ ኑሮ የምትኖር የአንተኑ እናት የምትመስል እናት አለችው። እንዳንተው በእርሻ ፣ በመለስተኛ ንግድ ወይም በመንግሥት ሥራ የሚተዳደር አባት፣ እንዳንተው ነገ ተመርቀህ ለራስህና ለኔ ታሳልፍልኛለህ ብሎ ተስፋ የሚጥልበትና የሚያዝንለት ወገን ያለው ወገንህ ነው። እናም ማንም ከየትም ሆኖ በሚፈጥርልህ በውል እንኳ ተለይቶ በማይታወቅ ምክንያት አታጥቃው። እመነኝ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትርፍ አልባ ግጭት ደም ገብረህና ወንድምህን ገድለህ በፀፀት አለንጋ እየተገረፍህ ዕድሜህን ትማቅቃለህ። አሊያም ራስህ ሰለባ ሆነህ የራስህንና የወገንህን ህልም ታጨልማለህ።» የሚለው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታደሰ ቀነዓ መልዕክትም ሁሉም ሰው ቆም ብሎ ሊያስበውና የህይወት መርሁ ሊያደርገው የሚገባ ቅዱስ መልዕክት ነው፡፡
የተማሪ ወላጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጐች፣ የእምነት አባቶችና አባገዳዎችም ተማሪዎቹ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብርቅዬ ልጆች ናቸውና እነሱን በጋሻነት ተጠቅመው እርኩስ ዓላማቸውን ሊያሳኩ ከሚሠሩ ኃይሎች ራሳቸውን እንዲጠብቁና እርስ በርስ ተፋቅረው የጠላትን ዓላማ እንዲያከሽፉ አባታዊ ምክር መስጠት ይገባቸዋል። ይህ ጉዳይ ደስ ስላለን የምንፈጽመው ሳይሆን ታሪካዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ ዛሬ ነገ ሳይባል ተተግብሮ ሊታይ ይገባዋል፡፡
የአንድ መንግሥት አልፋና ኦሜጋ ተግባሩ የዜጐችን ደህንነት መጠበቅና በሰላም ወጥተው በሰላም መግባታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት አለመወጣት ትልቅ ኪሣራ ከማስከተሉም በላይ የህግ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም መንግሥት የዜጐች ደህንነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ህጋዊ አሠራርን ምክንያት በማድረግ ከመዘግየት ወጥቶ በፍጥነት መንቀሳቀስና በተለይም የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ዜጐችን ሰላምና ህይወት መጠበቅ ያለምንም ማንገራገር በፍጥነት ሊፈጽመው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ የነገ ተስፋዎቻችንን በጋሻነት በመጠቀም ሀገር ለማፍረስ እየተሠራ ያለውን ርኩስ ተግባር ጠንቅቀን ማወቅና የተጣለብንን ሀገራዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመፈጸም ሀገርን ከመፍረስ ትውልድን ከጥፋት ማዳን ወቅቱ ያቀረበልን የማይታለፍ የቤት ሥራ ነው እንላለን!