
የሕዝባችን የሁል ጊዜ ጥያቄ ሰላም እና ልማት ነው። ለአሁናዊው ዓለም የቀለሉ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በአግባቡ ለማሟላት፤ ዛሬን አሸንፎ ነገን በተስፋ ለመጠበቅ፤ ከዚያም በላይ የትውልድን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ጥያቄዎቹ ወሳኝ ናቸው። የእኛ ብቻ ሳይሆኑ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ማኅበረሰቦች የቅድሚያ ቅድሚያ ጥያቄዎች ናቸው።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ከመጣንበት ብዙ ውጣ ውረድ፤ በተለይም በየዘመኑ እያጋጠመን ከነበረው የሰላም እጦት እና የሰላም እጦቱ እያስከፈለን ካለው ያልተገባ ዋጋ አኳያ የሰላም ጥያቄ የሕዝባችንም አሁናዊ ትልቁ አጀንዳ ነው። የነገ ሕልውናችንም መሰረት ነው፤ አብዝተን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ልንጮኸበት የተገባ፤ ዘመናት የተሻገረ ሀገራዊ ፈተናችን ነው።
የሰላም እጦት በቀደሙት ዘመናት ከነበርንበት ትልቅ የስልጣኔ መንበር አውርዶ፤ ዛሬ ላይ በድህነት እና በኋላቀርነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ አሰልፎናል። ድህነትን እና ኋላቀርነትን አሸንፈን ለመውጣት በየዘመኑ ያደረግናቸውን ሀገራዊ ጥረቶችን አክሽፎብናል። ትውልድ በብዙ ተመኝቶ የጀመሯቸውን የለውጥ መነሳሳቶች ፍሬ እንዳያፈሩም አድርጓል።
በዘመናት ሄደት የሀገሪቱ ፖለቲካ ኃይል አምላኪ እንዲሆን በር ከፍቷል” ይዋጣልን የሚሉ” የፖለቲካ ሥልጣን በኃይል እና በኃይል ብቻ እንደሚገኝ አምነው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በስፋት እንዲወጡ፤ የፖለቲካ መድረኮቻችን ፉከራ እና ቀረርቶ የሚበዛባቸው፤ ስክነት እና መረጋጋት የጎደለባቸው እንዲሆኑ አድርጓል። መገዳደልን ባሕላዊ ጨወታ አድርገው የሚገምቱ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲፈጠሩም አግዟል።
ችግሩ ሀገር እና ሕዝብ ስለ ለውጥ እና ዕድገት ብዙ ተስፋ ባደረግንባቸው ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት እንኳን ሳይቀር፤ የለውጥ መነሳሳታችንን ለተጨማሪ ጦርነቶች እና ግጭቶች ዳርጓል። ከትናንት የግጭት ታሪኮቻችን ተምረን መታረም አለመቻላችን፤ ለዘመናት ለሀገራዊ የሰላም እጦታችን መቋጫ ማበጀት እንዳንችል ፈተና ሆኖብናል።
የሰላም እጦታችን ሁሉ እያለን በዓለም አቀፍ መድረክ የድሀ ድሀ አድርጎናል፤ ለለት ጉርሳችን ሳይቀር ጠባቂ እንድንሆን፤ ድህነት ፍጥረታዊ ዕጣ ፈንታችን የሆነ ያህል ተቀብለነው እንድንኖር ከማድረጉም በላይ ሠርተን በብዙ ማደግ እና መላቅ የምንችልበትን እድል አሳጥቶናል። በድህነት ድባቴ ውስጥ እያላዘንን ዘመናትን እንድንቆጥር አስገድዶን ኖሯል።
በሰላም እጦት የተሞላው የትናንት ታሪካችን ከግጭት/ከሰላም እጦት እናተርፋለን የሚሉ ግለሰቦችን እና ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ዘመን የተሻገሩ የወንድማማችነት፣ የአብሮነት እና የጉርብትና እሴቶቻችንን አደብዝዞታል። መግደል ብቻ ሳይሆን መሞትን አቅልሎ የሚያይ ተስፋው የተነጠቀ ትውልድ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ሰላም እና የሰላም አሴቶችን አሳንሰው የሚያዩ፤ ስለሰላም በብዙ መናገር የአቅመቢስነት መገለጫ አድርጉ የሚያስቡ፤ የሰላም ጥያቄ በመሰረታዊነት የልማት፣ የፍትህ እና የነጻነት ጥያቄ መሆኑን ለመቀበል የተከፈተ ልብ እና ቀና ሕሊና የሌላቸው፤ ሁሌም አመጽን የፖለቲካ መታገያ አቅም እድርጎ የሚወስዱ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
የሰላም እጦቱ፤ በግጭት ወቅት ስለሚጠፋው የሰው ሕይወትም ሆነ የሀገር ንብረት ምንም የማይሰማቸው፤ ስለተገለጠው ጥፋታቸው ከመጸጸት ይልቅ የቀራቸውን የጥፋት አማራጭ ለመጠቀም አብዝተው የሚተጉ፤ በሙታን እና በፍርስራሽ ላይ ቆመው የሚፎክሩ፤ ይህንንም ክብር አድርገው የሚመለከቱ ግለሰቦች እና ቡድኖችን ፈጥሯል።
ልዩነቶችን በማስፋት እና የልዩነት ትርክቶች በማጮኽ በሚፈጥሯቸው ማኅበረሰባዊ ትርምስምስ ውስጥ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት የሚተጉ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ጭር ሲል የማይወዱ፤ ከራሳቸው እና ከዘመናቸው ጋር ተጣልተው የሕዝብን የሰላም እና የልማት ጥያቄ በአደባባይ የሚቃወሙ፤ በዚህም ራሳቸውን የሕዝብ ተቆርቋሪ አድርገው የሚያዜሙ እንዲበዙ አድርጓል።
ከዚህ ዘመናት ከተሻገረ ሀገራዊ የሰላም እጦት እና እያስከፈለን ካለው ያልተገባ ዋጋ ለዘለቄታው ለመውጣት፤ እንደ ሕዝብ ስለ ሰላም በእውነት እና በእውቀት አብዝተን ልንጮህ፤ ከሰላም እጦታችን አትራፊ ሆነው ለመገኘት አደባባዮቻችንን የሞሉ የጥፋት ግለሰቦች እና ቡድኖችን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል። ከዚህ በላይ በሰላም እና የልማት ጥያቄያችን እንዲያላግጡ ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም