. ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት ሊጀምር ነው
አዳማ፡- የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የፋይናንስ አገልግሎት ሁሉን አቀፍና ደንበኛ ተኮር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ሰነድ አዘጋጅቶ ከእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ጋርም መክሯል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ትናንት በአዳማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው በፋይናንስ ዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ደንበኛ ተኮር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተግባሩ ውጤታማነት ይረዳው ዘንድም በገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ስራ ማህበራት አማካይነት የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎትን በሀገር ደረጃ ለማስጀመር በዘርፉ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው አካላት ጋር በመሆን የትግበራ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለጸ፤ የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት በተለያዩ አገራት በተለይም በሙስሊም አገራት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሃይማኖት አስተምህሮቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በተለያዩ የእስያ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ አገራት በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አገራት ዜጎቻቸው በአገራዊ ልማት ውስጥ ፍትሃዊ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን እንዲያረ ጋግጡ በማድረግ አገራዊ ሰላምና መረጋጋትን ለመገንባት እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
በኢትዮጵያ አገልግሎቱን የሚፈልግ የኅብረተ ሰብ ክፍል ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የፋይናንስ አገልግሎቱን ደንበኛ-ተኮር በማድረግ ለህብረተሰቡ ማቅረብ በመሆኑ፤ አንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት የአሰራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት አገልግሎቱን መስጠት ቢጀምሩም ዝርዝር ደንብና መመሪያ፣ የአሠራር ማኑዋል፣ አደረጃጀት፣ ተመጣጣኝ ዕውቀትና ክህሎት በዘርፉ ባለመኖሩ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚጠበቀው ደረጃና ጥራት ተደራሽ ማድረግ ሳይቻል ቆይቷል፡፡
የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት በዋናነት የእስልምና ሃይማኖት አስተምሮትን መነሻ ያደረገና የሸሪዓ ድንጋጌዎችን ተከትሎ የሚሰራ የፋይናንስ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት አቶ ኡስማን፤ ተግባሩም ሃይማኖታዊና ሰብዓዊ ዕሴቶችን በመገንባት የጋራ መረዳዳትንና መተሳሰብን በሰዎች መካከል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው ወደዚህ ተግባር መግባቱ አገልግሎቱን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባለው አደረጃጀቶች እንዲስፋፋና እንዲያድግ በማድረግ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበት ማግኘት እንደሚያስችለው፤ በቂ ፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት ተጠቃሚ ያልሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ለአርሶና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
በኤጀንሲው የፋይናንስ ሕብረት ሥራ ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዱፌራ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እየተሰጠ ቢሆንም፤ በተለይ ባንኮች አገልግሎቱን የሚሰጡት በአመዛኙ ለባለሃብትና ነጋዴው ነው፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶችም ቢሆኑ የሙስሊሙን ማህበረሰብ በተለየ መልኩ እያገለገሉ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኤጀንሲው ይሄን አገልግሎት ተግባራዊ ሲያደርግ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለውን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ቀደም ሲል አገልግሎቱን የማያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና የሙስሊሙ ማህበረሰብ በስፋት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ የነበረውን የፋይናንስ አገልግሎት ችግር ለማቃለል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
በወንድወሰን ሽመልስ