አዲስ አበባ፡- የ2011 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲሰራ 300ሺ ሥልጠና የወሰዱ ቀያሽ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከ13ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ከትናንት በስቲያ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴዎች ታግዞ ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ 300ሺ ቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና ወስደው ሥራውን ይመራሉ፤ ከ13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይሳተፍበታል፤ በሥራ ላይ ካሉት የግብርና ባለሙያዎችም ከ80 በመቶ በላይ ርብርብ ያደርጋሉ፤ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የእጅ መሳሪያዎችም ተዘጋጅተዋል፡፡
‹‹የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዋና ዓላማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በማከናወንና ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ በግለሰብና በአገር ደረጃ በምግብ ራስን መቻል ነው›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ መመሪያ ተዘጋጅቶለት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ችግርና በግጭት ምክንያት በሥራው ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ መሆኗና መሬት የሌላቸውን ወጣቶች በሥራው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ እስካሁን በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ከተገኙ ልምዶች መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡
የ2011 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል ደግሞ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀመር የሚኒስቴሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
አንተነህ ቸሬ