አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ሕዝብ ያጣውን አመኔታና የተቀዛቀዘውን ድጋፍ ወደነበረበት ለመመለስ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በራስ ሆቴል ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ምክክር ላይ እንደተናገሩት፤ ተከታታይና ታላላቅ ምክክሮችን በማካሄድ ጋዜጠኞች፣የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የተለያዩ አካላት ግድቡን በማስጎብኘት እንዲሁም የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የታጣውን የህዝብ አመኔታ ለመመለስና ለግንባታው ሲደረጉ የነበሩ ድጋፎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ስለግድቡ ህዝብ የሚፈልገውን መረጃ ለመስጠት ጽህፈት ቤቱ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ያለፈው ስህተት እንደማይደገም፣ ህዝብ ቅሬታ ቢሰማውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የራሱ መሆኑን ተገንዝቦ ቅሬታውን ትቶ ግድቡን ለማጠናቀቅ ተሳትፎውን የበለጠ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር የተወከሉት ዶክተር ዮሐንስ ግብረሥላሴ በሰጡት አስተያየት ዳያስፖራው ከሌላው ህብረተሰብ በበለጠ ውዥንብር ውስጥ መሆኑን ጠቁመው፣ያለውን እውነታ በድረገጽ በማሰራጨት ማሳወቅ እንደሚገባና ጽህፈት ቤቱ የጀመረውን በግልፅ የማሳወቅና ድጋፍ የማጠናከር ሥራ በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው፤ ማህበሩ ዳያስፖራው ለግንባታው አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አሊ ሱልጣን በበኩላቸው ግድቡን ካንዴም ሁለቴ የመጎብኘት ዕድል እንዳጋጠማቸው በማስታወስ፤የነበራቸውን ትልቅ ተስፋ በአጭር ጊዜ የሚያጨልም ነገር መፈጠሩ አሳዝኗቸው እንደነበር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ያለውን እውነታ ህዝብ እንዲያውቀው ተደርጎ ዳግም መነቃቃት መፈጠሩ እንዳስደሰታቸውና ከዚህ ቀደም ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በግድቡ ሥራ ላይ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር እንደሌለ ፣ 50 ዓመትና ከዛም በላይ እንዲያገለግል ተስፋ የተጣለበት ግድብ ላይ የተፈፀመው ስህተት በቶሎ ታርሞ የግንባታው ሥራ በአግባቡ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
የግድቡ የሲቪል ሥራ 82 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ቀሪውን ሥራ ለማጠናቀቅ በጊዜ ሰሌዳ በመመራትና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በወቅቱ በመፍታት ፍፃሜ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚሰራ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
ለምለም መንግሥቱ