በምድራችን የተፈጥሮም ሆነ የሰው ሰራሽ አደጋዎችና ወረርሽኞች ሲከሰቱ ከጥንት ጀምሮ በአብዛኛው የመሪዎች ተቀባይነት ከቀደመው ጊዜ እንደሚጨምር በዘረፉ የተጻፉ ድርሳናት ያመለክታሉ። እንደ ፒው/ Pew/ እና ጋሉፕ /Gallup/ ያሉ የሕዝብ አስተያየት ሰብሳቢ፣ አጥኝና ተንታኝ ተቋማትም ይሄን ጥሬ ሀቅ ያረጋግጣሉ። ከሀገር ቤት ብጀምር፤ አጤ ቴዎድሮስና አጤ ዩሐንስ የዙፋን ተቀናቃኞቻቸውን በኃይል ረተውም ሆነ አስገብረው ሲመለሱ እንደ ቱርክ፣ ግብፅና ጣሊያን ያሉ ተስፋፊዎችን ጉንደትና ጉራ፣ ዶጋሌ ላይ አሳፍረው በድል ሲመለሱ፤ በተለይ አጤ ምኒልክ ታላቁንና አንጸባራቂውን የአድዋ ድል መቀዳጀታቸውን ተከትሎ ዝናቸው ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ናኝቷል። ” ጓድ ” መንግስቱ እብሪተኛውንና ወራሪውን የዛድባሬ ጦር ድባቅ መምታቸውን ተከትሎ ለጊዜውም ቢሆን በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ጨምሯል። አጤውንና ኮምኒስቱን መሳ ለመሳ ማንሳቴ እንደ ታሪክ አጋጣሚ እንጂ እንደ ንፅፅር እንዳይቆጠርብኝ።
በተቃራኒው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ2ኛው የጣሊያን ወረራ መሸነፋቸው እና ወደ እንግሊዝ መሰደዳቸው በተቀባይነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
በ2ኛው የአለም ጦርነት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ሮዝቬልት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል፤ የቀዝቃዛውን ጦርነት በድል በማጠናቀቃቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን እና የእንግሊዟ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትርና ” ጠንካራዋ እመቤት “/ አይረን ሌዲ/ በመባል የሚታወቁት ማርጋሪት ታቸር፣ በመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በማስከተል ልጃቸው የሳዳምን የኩየት ወረራ ለመቀልበስ፣ የሳዳሟ ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ታጥቃለች በሚል በኋላም የመስከረም 1 ቀን የሽብር ጥቃት ተከትሎ አፍጋኒስታንን ጦርነት ባወጁ ጊዜ፤ የ2008ቱ የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላም ሳርስ ሲከሰት የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የሕዝባዊና አለማቀፋዊ ተቀባይነት ጨምሮ እንደነበር ድርሳናትና ዘገባዎች ያትታሉ።
የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ እያደረሰው ያለ ሁለንተናዊ ቀውስ እና በሰው ልጅ ህልውና ላይ የደቀነው አደጋ ግን ከፍ ብለን ከተመለከትናቸው የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎችና ወረርሽኞች በእጅጉ የበረታ መሆኑን ስንረዳ ከወቅቱ መሪዎች የተሻለ ስትራቴጂካዊ እይታ፣ ማስተዋልና ጥበብ የተሞላበት አመራር መስጠት እንደሚጠበቅ እንገነዘባለን። የመሪዎች ዋናው አላማ ዜጎቻቸውን ከእልቂት፣ ኢኮኖሚያቸውን ከወድቀት መታደግና ማህበራዊ ቀውስን መከላከል ነው። ይህን ተከትሎ የሚመጣውን ተቀባይነትና ” ፖለቲካዊ ፍጆታ ” የማወራረድ ፍላጎት ላለው ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ከተቆጣጠርን በኋላ ይደርሳል። ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረግ ግብግብ መሀል ማን ፖለቲካዊ ትርፍ እንዳስመዘገበና እንደከሰረ ስሌት ውስጥ መግባት የፖለቲከኝነትም ሆነ የጋዜጠኝነት ጨዋነት ነው። አንዳንድ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች እና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ገና ከአሁኑ ስለፖለቲካዊ ፍጆታ ሒሳብ ማወራረድ መጀመራቸው ሳያንስ መንግስትን ወረርሽኙን ለፖለቲካዊ ፍጆታ እያዋለው ነው በሚል መክሰስ ጀምረዋል። ይህ መናኛ ክስ ለህይወታቸው ሳይሰስቱ ሌት ተቀን እየደከሙ ያሉ አመራሮችን፣ የጤና ባለሙያዎችንና በጎ ፈቃደኞችን ሞራል መንካት ነው። ለመካሰስ፣ የወሮታ ሒሳብ ለማወራረድ ጊዜው ገና መሆኑን ለመገንዘብ ወረርሽኙ በሰው ልጅ ላይ የደቀነውን አደጋ መመልከት ይገባል።
ይህ መጣጥፍ እየጫጫርሁ ሳለ፣ በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የተሻገር ሲሆን፣ የሟቾች
ቁጥር ከ230 ሺህ በላይ ደርሷል። በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን ዘሏል።የሟቾች ቁጥርም ደግሞ ከ60 ሺህ ተሻግሯል። ወደ ሀገራችን ስንመጣም ገና በማለዳው 3 ሰዎችን በቫይረሱ ያጣን ሲሆን በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ወደ 130 የተጠጉ ሲሆን ያገገሙት ደግሞ 50 ደርሰዋል። ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጣጠር አኃዙ ተመስገን የሚያስብል ቢሆንም የከፋ ቀን ሊመጣ እንደሚችል አስቦ አበክሮ መዘጋጀቱና አለመዘናጋቱ የግድ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ፈዋሽ መድኃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት መሆኑ እና ሳይንቲስቶች ስለ ቫይረሱ ገና ብዙ ያልደረሱበትና ያልተገለጠላቸው ሚስጥር መኖሩ እንደ ዜጋ ይበልጥ ሊያስጨንቀን፣ ሊያሳስበንና በአንድነት ሊያቆመን ሲገባ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ መሀል ገብተን የፖለቲካዊ ፍጆታ ሒሳብ ለማወራረድ የምንታትር ከሆነ ከሰውነት ተራ ወጥተናል። የሚያሳዝነው አንዳንድ ሚዲያዎች እረፍት እየነሳቸው እያስጨነቃቸው ያለው ጉዳይ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ሳይሆን ከፖለቲካዊ ፍጆታው ማን አተረፈ? የሚለው ጥያቄ ነው።
የኮሮናቫይረስ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ከእፓኒሽ ፍሉ፣ ከ1ኛውና 2ኛው አለም ጦርነቶች፣ በ1930ዎች ወይም በቅርቡ ደግሞ እ.አ.አ በ2008/9 ከደረሰው የኢኮኖሚ መናጋት እና ከ2001 ዓ.ም የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በላይ መሆኑ በሰፈው እየተነገረ ነው። እንግዲህ ከፍ ብለን በአብነት ያነሳናቸውም ሆነ ያላነሳናቸው የሀገራችንም ሆኑ የውጭ መሪዎች ከኮቪድ – 19 ባነሱ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎችና ወረርሽኞች የተነሳ በሕዝባቸው ዘንድ ተቀባይነታቸው ከፍ ካለ የሰው ልጅ እና የአለማችን ህልውና ላይ የተደቀነውን አደገኛ ወረርሽኝ በግንባር ቀደምነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወደቀባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሌት ተቀን ለሚተጉ መሪዎች እውቅና ቢሰጥ፣ ተቀባይነታቸው ቢጨምር የቅድመና የድህረ ቀውስ ባህሪ እንጂ የእነሱ የእጅ ስራ ውጤት እንዳልሆነ ከወዲሁ ሊጤን ይገባል።
በሌላ በኩል ቀደም ባለ መጣጥፌ እንዳስነበብሁት ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ከባድ ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ እንደማይፈታ መረጃዎች አበክረው እየወጡ ነው። አይ ኤም ኤፍ በዚያ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፓርት የአለም ኢኮኖሚ ከ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ/ ግሬት ዴፕሬሽን/፤ እንዲሁም እ.አ.አ ከ2008 የኢኮኖሚ ቀውስ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አኮኖሚው 3 በመቶ ያሽቆለቁላል ሲል ሰግቷል። ከ6 በመቶ በላይ እድገት ይመዘገባል ተብሎ ተተንብዮ የነበረው ኢኮኖሚ ነው እንዲህ እየተንኮታኮተ ያለው። የወረርሽኙ በትር አፍሪካ ላይ በተለይ ሀገራችን ላይ የበረታ እንደሚሆን ለመገመት የግድ የጆሴፍ ስቲግሊትዝ ደቀ መዝሙር መሆንን አይጠይቅም። የአለም ጥቅል ምርት/ ጂ ዲ ፒ / የጃፓንና የጀርመን ድምር ኢኮኖሚ የሚያህል ማለትም በ9 ትሪሊዮን ዶላር ይቀንሳል ተብሎ ተሰግቷል።
የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚ ከ6 በመቶ በላይ፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ደግሞ ከ2 በመቶ በላይ ይቀንሳል ተብሎ ተተንብዯል።አሜሪካንን ጨምሮ የ170 ሀገራት የነፍስ ወከፍ ገቢ ይቀንሳል።የአሜሪካ ኢኮኖሚ በተያዘው ሩብ ዓመት በ4 ነጥብ 8 በመቶ ማሽቆልቆሉ አለምን ክው አድርጓል። እንዲሁም የአውሮፓ የነፍስ ወከፍ ገቢ 7 ነጥብ 5፣ በወረርሽኙ ክፉኛ የተመታችው ጣሊያን 9 ነጥበ 1 በመቶ ይቀንሳል። ይሁንና ድህረ ኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ መነቃቃቱ የተሳካ ቢሆን እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞ ወደ ነበረበት ቁመናው ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም። የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ/ ዩኒሴፍ/ወረርሽኙን ተከትሎ በመጋቢት ማብቂያ ባወጣው ጥናት የኢኮኖሚው እድገት በ1 በመቶ ሲቀንስ ከ14 እስከ
22 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለከፋ ድህነት ይዳረጋሉ። በወረርሽኙ ሳቢያ በሚከሰት የኢኮኖሚ ቀውስ ከድህነት ወለል የሚላቀቁ ሰዎች ቁጥር በ48 ሚሊዮን ይቀንሳል። በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ኮሚሽን /ዩ ኤን ኢሲኤ/ ይፋ ባደረገው ሌላ መረጃ የአፍሪካ ጥቅል ምርት በ3 ነጥበ 9 በመቶ ወይም በ70 ቢሊዮን ዶላር ያሽቆለቁላል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በ2 ነጥብ 9 ዝቅ ይላል ተብሎ ይሰጋል።
ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አለምን በተለይ ሀገራቸውን መታደግ የቻሉ መሪዎች በሕዝባቸው ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ቢጨምር ሊደንቀን አይገባም። አለም የምትሰራው እንዲህ ነውና። የጀርመን መራሔተ መንግስት አንጌላ መርኬል፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑዬል ማክሮን፣ የሲንጋፓር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ሔይሴን ሎውንግ፣ የታይዋን ፕሬዝዳንት ጻይ ኢግ – ዌን ገና ካሁኑ ተቀባይነታቸው እንደ ጨመረ የሕዝብ አስተያየት ጥናቶች እየገለጹ ነው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ገለልተኛ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ተቋም ባይኖረንም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እና የመንግስታቸው ተቀባይነት ቢጨምር የሚጠበቅ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። ከተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲም በዚህ ፈታኝ ሰዓት ለሀገሩ ለወገኑ ባበረከተው አስተዋጾ ተቀባይነቱን ከፍ ቢል ግር ሊለን ወይም ቡራ ከረዩ ሊያስብለን አይገባም። የኢዜማ አመራሮች እንደ ብልፅግና አመራሮች ደም በመለገሳቸው፤ ሕዝቡን ስለወረርሽኙ በማስተማራቸው ተቀባይነታቸው ቢጨምር ወረርሽኙን ለፓለቲካዊ ፍጆታ አውለውታል የምንል ከሆነ ይቅርታ ይደረግልኝና አይነ ጠባቦች ነን። ይሁንና ከላይ ለአብነት ያነሳኋቸው ሀገራት መሪዎችም ሆኑ የየብልፅግና ፓርቲም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ወይም ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ኮቪድ – 19 ለፖለቲካዊ ፍጆታ ሲሉ ተለማምነውና ጸልየው ያመጡት ወረርሽኝ ይመስል እንዲሁም ከልጅነት እስከ እውቀት ካላቸው ቅን፣ ሩህሩህና ደግ ሰብዕና በተለየ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ሲሉ ድንገት ተነስተው ያልነበረ ባህሪ እንዳሳዩ ተደርጎ የሚቀርብባቸው ክስ አመክንዮም ተጠየቅም የለውም። ፖለቲካዊ ፍጆታም ሆነ የተቀባይነት መጨመር የእሳቸው የእጅ ስራ አይደለምና።
እነዚህ ሚዲያዎችም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዳንድ አመራሮች ይህን ጉጭ አልፋ ክርክር ከማመንዠክ ይልቅ ስትራቴጂካዊ ጥያቄዎችንና ሀሳቦችን ቢያቀብሉ የአባት ነበር። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ሆነ ከከፊል የእንቅስቃሴ ገደቡ የተገኘውን ውጤት ቢጠይቁ ፣ የመከላከል ጥረቱን ጠንካራና ደካማ ጎኑን በአዎንታም ሆነ በአሉታ ቢተቹ፤ የምርመራውን፣ ማህበራዊ ፈቀቅታውን እና የአግልሎ ማቆያውን ተፈጻሚነት ቢሞግቱ፤ ፌዴራል ከክልሎች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ቢፈትሹ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል የተቀናጀና ፍትሐዊ እንደሆነ ቢመረምሩ፤ ሚዲያው የማብራራት ጋዜጠኝነትን ተጥቅሞ ለሕዝብ እያደረሰ ስላለው ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲሁም ሚዲያው እየሰጠ ያለው ሽፋን እንደተለመደው ከላይ ወደ ታች ነው ወይስ ከታች ወደ ላይ ነው ብለው ቢጠይቁ፤ የወረርሽኙን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ለመመከት መንግስት አበክሮ የቀየሰውን ስትራቴጅና የቀውስ አመራር አፈጻጸም በመፈተሽ፣ በመመርመር፣ በመተንተን መፍትሔ ቢያመላክቱ የፖለቲከኛ፣ የጋዜጠኛ ወጉ ነበር።
በነገራችን ላይ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስት የኖቨል ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርጉት አኩሪ ርብርብ እና እየሰጡት ያለ በሳል አመራር ውጤታማ ከሆነ ከፈጣሪ ጋር ውጤታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። የቻይናው የህክምና ልዑክ ግምገማ ያረጋገጠው ይሄንኑ
ነው። አውንታዊ ፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ ሲኖረው፤ አያድርገውና ካልተሳካ ደግሞ አሉታዊ ፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ እንደሚያስከትልም ልብ ሊባል ይገባል። ለዚህ ነው ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ለመከላከል ሕዝባቸውንና መንግስታቸውን አቀናጅተው በመምራት ወረርሽኙን በመከላከል ጉዳቱን መቀነስ የቻሉ ከፍ ብዬ በአርዓያነት ያነሳኋቸው መሪዎች ተቀባይነታቸው ሲጨምር በተቃራኒው ውጤታማ መሆን ያልቻሉት እንደ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ወዘተረፈ ያሉ ሀገራት መሪዎች ደግሞ ክፉኛ ከመተቸታቸው ባሻገር ቀጣይ የፖለቲካ ህይወታቸው ያጥራል ተብሎ የተሰጋው። ኮቪድ – 19 ለሀገር መሪዎች ባለሁለት ሰይፍ ተደርጎ የሚወሰደው ለዚህ ነው።
ዳሩ ግን የሰው ልጅ መንግስት የሚባል ተቋም መስርቶ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጥንተ ጊዜ አንስቶም ይሁን በአሶር ወይም በባቢሎን አልያም በፐርዥያ ወይም በሮማን አልያም በቤዛንታይን፣ በኦቶማን አገዛዞች ይሁን በ21ኛው መክዘ የመንግስት አሰራር ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ፣ ተለይቶ አያውቅም። ወደ ፊትም ከፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ ተነጣጥሎ ከቶ ሊታይ አይችልም። የቀድሞው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል መራሔ መንግስት ዮሽካ ፊሽከር ፤ ” The Politics of the Pandemic ” በሚል ርዕስ ” ፕሮጀክት ሲንዲኬት ” ላይ እንዳስነበቡን ወረርሽኙ የአለማችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ፣ አሰራር፣ የመንግስታትን ግንኙነት፣ የመንግስትን ቅርፅና ይዘት፣ አይዶሎጂ፣ ወዘተረፈ እንደሚገለባብጥ፣ እንደሚቀያይርና በአዲስ እንደሚበይን አበክረው አስጠንቅቀዋል።
እንደ መውጫ
የሀገራችን አንዳንድ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ወረርሽኙን ተከትሎ ሊመጡ ያሉትን የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ ቀውሶችን ከመመልከት ይልቅ ለጋዜጣና ለመፅሔት ማሻሻጫና የአድማጭ ተመልካች ቁጥር ለመጨመር፤ ተከታይና ጭፍራ ለማፍራት ሲሉ ሀሰተኛ፣ የተዛባና የተጣመመ መረጃን መንዛት ላይ ማተኮርን መርጠዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወረርሽኙን ለመከላከልና ይዞት እየመጣ ያለውን ቀውስ ለመከላከል ከፊት ሆነው መምራት፣ ንቅናቄ መፍጠርና ተከታይ ማፍራት የዕለት ተዕለት ስራቸው መሆኑ ሆን ብለው ትኩረት በመንፈግ፤ ወረርሽኙን ለፖለቲካ ፍጆታና ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ዋቄ ፈናን፣ እየሱስን ለምነው ያመጡት ይመስል፤ ቀደም እንዳሉት ገዥዎቻችንና ነጅዎቻችን ሳይሆን ከአንድ ሀቀኛ መሪ እንደሚጠበቅ ኃላፊነት በትህትና ዝቅ ብለው ለዜጋ ምሳሌና አርዓያ ለመሆን ከእነ ባለቤታቸው ዘይት፣ ዱቄትና የጽዳት እቃዎችን መሸከማቸው፣ ደም መለገሳቸው፤ ከንቲባ ታከለን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የፓርቲያቸው አመራሮች የእሳቸውን ፈለግ መከተላቸው እውቅና ማሰጠቱ ቢቀር በልኩ ሊመዘን ሲገባ በዚህ ፈታኝ ስዓት ከሕዝባቸው ጎን መሆናቸውን በተግባር፣ በምሳሌ ስለገለጹ ሊወቀሱ አይገባም። እደግመዋለሁ ወረርሽኙም ሆነ እሱን ተከትሎ የሚመጣው የተቀባይነትም ሆነ ፖለቲካዊ ፍጆታ የተፈጥሮም ሆነ የሰው ሰራሽ አደጋ፣ ወረርሽኝ ቅድመና ድህረ ቀውስ ባህሪ እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእጅ ስራ አይደለም።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ ይጠብቅ !
አሜን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com