.ምርጫ ቦርድ አላውቅም ብሏል
አዲስ አበባ:- በትግራይ ክልል የሚገኙ የምርጫ አካላት እና አስፈጻሚዎች እስከ ታችኛው የስልጣን እርከን ድረስ በህወሓት ሰዎች የተያዙ መሆናቸውን የዓረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ገለፁ።የህወሓት ሰዎች የምርጫ ጽህፈት ቤቱን እና ሌሎች ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ውስጥ ስለመኖራቸው እንደማያውቅ ምርጫ ቦርድ አመለከተ፡፡
ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ (ዓረና) ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የምርጫ ጊዜ መካሄድ እና አለመካሄድ ዋነኛ የፓርቲው ጉዳይ አይደለም። ዋናው ጉዳይ የምርጫ ሥርዓቱ ተስተካክሏል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። በትግራይ ክልል የሚገኘው የአስመራጩ አካል በአብዛኛው በህወሓት ሰዎች የተያዘ ነው።በ2012 ለሚደረግ ምርጫ እንቅፋት እንዳይሆን ማስተካከል ይገባል፡፡
እንደ አቶ አብርሃ ከሆነ፤ በመሆኑም በቀጣይ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ካስፈለገ የምርጫ ቦርዱ እስከታችኛው አካል ድረስ በገለልተኛ ሰዎች መተካት አለበት። በክልሉ የሚገኙ የምርጫ አካላት ራሳቸውን ከፓርቲ አባልነት ነጻ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ነጻነቱ እስከ ወረዳ እና ቀበሌዎች ድረስ መዝለቅ ይኖርበታል።
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ምርጫ ቦርድ የራሱ የሆነ ተቋማዊ ይዘት ያለው ነው። በመሆኑም በትግራይ ክልል ያሉ የምርጫ ተቋማት በህወሓት ሰዎች ተይዟል የሚለው አባባል ከተራ ውንጀላ የተለየ አይደለም።
በእርግጥ በጉዳዩ ላይ ምርጫ ቦርድ የበለጠ ቢናገር የተሻለ ይሆናል ያሉት አቶ ጌታቸው፣በኢትዮጵያ ያለው አንድ አገራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። ለዓረና ብቻ ተብሎ የሚቋቋም የምርጫ አካል ስለሌለ የህወሓት ሰዎች ተይዟል የሚለው አካሄድ ትክክል አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ በበኩላቸው በትግራይ ክልል የኢት ዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መኖሩን ገልጸዋል። የህወሓት ሰዎች የምርጫ ጽህፈት ቤቱን እና ሌሎች ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን ውስጥ ስለመኖራቸው እንደማያውቁ አመል ክተዋል።
ዓረና ፓርቲ ያነሳው የምርጫ አካላት በህወሓት ሰዎች ተይዘዋል የሚለውን ጉዳይ የበለጠ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ አስፈላጊውን መረጃ መስጠት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
በጌትነት ተስፋማርያም