በአንድ ወቅት አንድ የቦክስ ስፖርተኛ በልምምድ ጊዜ ጥሩ ብቃት ሲያሳይ ይቆይና ወደ ፍልሚያ ሲገባ ጨዋታውን እየተረታ ያጠናቅቃል። እናም አሰልጣኙ በአንድ ወገን ተጋጣሚውን ሲያይ እየፈራ እየመሰለው አይዞህ ብቻ ተረጋግተህ ተጫወት ካንተ በኪሎ የሚበልጡህንም ብትገጥም የማሸነፍ ብቃት አለህ፤ ደፋር ሁን እያለ በራስ መተማመኑን ለማዳበር ሲሰራ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተጋጣሚህን ዓይን ዓይኑን እየው ቡጢ ሲያርፍብህ ቶሎ ተስፋ አትቁረጥ አትደናገጥ በመከላከልም አትወሰን፣ ሁለት ጊዜ ከተከላከልክ ሦስተኛ መሰንዘር አለብህ። ስትመታው ደግሞ ፋታ አትስጠው ደጋግመው፤ ወዘተ እያለ ቴክኒካል ነገሮችንም ሲያስረዳው ቢቆይም ቦክሰኛው ውጤታማ መሆን አልቻለም።
አንድ የግጥሚያ ቀን አሰልጣኙ ባጋጣሚ ቦክሰኛው ቤት በጠዋት ሲሄድ ፑሽ አፕ እየሠራ ያገኘዋል። እናም ምን እያደረክ ነው ሲል በመገረም ይጠይቀዋል። ቦክሰኛውም ከልጅነቴ ጀምሬ በየቀኑ የማደርገው ነው፤ ምን አዲስ ነገር አለውና የጠዋት ስፖርቴን ላቁም ይለዋል። እኔ ከምሰጠህ ማሟሟቂያ ውጭ ለዚያውም በውድድር ወቅት እንዲህ አይነት አድካሚ ስፖርት መሥራት የለብህም እስካሁንም ከውጤት ያራቀህ ይሄ ነው። ከዚህ በኋላ እኔ ከምነግርህ ውጭ እንኳን ፑሽ አፕ በደረትህ ተኝተህ እንዳላገኝህ። ለካ እስካሁን ትንፋሽ እየጨረስክ ገብተህ ነው ፎጣ ስታስወረውረኝ የቆየኸው ብሎ በማስቆም በቀጣዩ ውድድር ውጤታማ ለመሆን ያበቃዋል። የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ እየተሰሩ ያሉ አንዳንድ ሥራዎችን ስመለከትም በተለያየ መንገድ ትንፋሽ እንዳንጨርስ የሚል ሐሳብ አጭረውብኛል።
የመጀመሪያው በቁሳቁስ አጠቃቀማችን በኩል የሚታየው አባካኝነት ነው። በዚህ ረገድ ሰሞኑን የገጠመኝን ላውጋችሁ። ከወደ ሃያ አራት ቀበሌ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ወደ አውቶብስ ተራ ጉዞ የጀመርኩት ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ነበር፤ ተጓዥ ለመሸኘት። ታዲያ ከሰፈሬ ብዙም ሳልርቅ አንድ እንደኛው ሻንጣ የተሸከመ ሰው ከፊት ለፊታችን ሲያዘግም አየሁ። ሰውየው የፊት ማስኩን ግጥም አድርጎ አስሮታል። እናም ለምን ስል ለራሴ ጥያቄ አነሳሁ። በመንገዱ ያለነው እኛና እሱ ብቻ ነን። በመካከላችን ደግሞ ያለማጋነን ከሃምሳ ሜትር ያላነሰ ክፍተት አለ። እንዲሁ እንደተከታተልን መገናኛ ደረስን እሱም እኔም አንድ ታክሲ ውስጥ ገብተን ወደ አውቶብስ ተራ አቀናን። በጉዞ ወቅት ማድረጉ ትክክል ነው። እኔም የአንገት ልብሴን አንገቴ ላይ ጠምጥሜ ነበር።
የዚሁ ቀን አመሻሽ ላይ ደግሞ አንድ ቪትዝ መኪና የያዘች ቆንጆ ወጣት ቤለር አካባቢ የመኪናውን አራት መስኮት ግጥም አድርጋ ዘግታ አፏን በጭንብሉ አፍናለች። ከኋላም ሆነ ከፊት ሌላ ተሳፋሪ አለመኖሩን ሳስተውል ጭምብሉ ከኮሮና ውጭ የምን መድሃኒት ይሆን የሚል ጥያቄ አጫረብኝ። ጭምብሉን ማን መቼ መጠቀም እንዳለበት በተደጋጋሚ በመደበኛውም በማህበራዊ ሚድያዎችም ሲነገር ቆይቷል። በዚህ መሰረት አንደኛ ለራሳችን መጠቀም እንኳ ቢያስፈልግ ካለብከነት እየተጠቀምን ለክፉ ቀን ብናስቀምጥ፤ በሁለተኛ ደረጃ እንደነዚህ ወገኖቼ ምንም ፋይዳ ሳይኖረው ስንገለገልበት እንደ ሀገር ለባለሙያዎችም ለህመምተኞችም እጥረት እንዳይገጥመን በተናጥል ልንቀርፈው የምንችለውን ችግር የህዝብ ችግር እንዳናደርገው እሰጋለሁ።
ሁለተኛው ትንፋሽ መጨረስ ደግሞ ወደ ገበያ የምናደርገው እሽቅድድም ነው። ይህኛው ደግሞ የኛ የተጠቃሚዎቹ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትንም ቁርጠኝት የሚመለከት ነው። እኔ በገበያ ጉዳይ ሁለት ምልከታ አለኝ። በመጀመሪያ ደረጃ የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ህሊናን መሸጥ ተገቢ ባይሆንም ነጋዴ አላማው ትርፍ ማግኘት በመሆኑ ባገኘው አጋጣሚ ዋጋ መጨመሩ አይቀርም። ስለዚህ ይህንን እየተከታተሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው። በዚህ ረገድ እስካሁን እንደ ሀገር የነበረንን ልምድ ስናየው በእኔ ግም ገማ ውጤታማ አይደለም። መንግሥት ደመወዝ ጨመረ ተብሎ የሸቀጦች ዋጋ ሁሉ ሲጨምር መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ወስዶ በወቅቱ ሲያስተካክል አልታየም። አንድ ሸቀጥ እጥረት ገጥሞ ዋጋው ከጨመረ በሌላ ጊዜ ምርቱ ተትረፍርፎም ቢመጣ እንኳ ዋጋው ከተሰቀለበት ሲወርድ አይታይም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲኖር የቆየ ማህበረሰብ አንዳች ነገር ተፈጠረ ሲባል ሥጋት ገብቶት በስፋት ለሽመታ ቢወጣ የሚደንቅ አይሆንም።
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በርካቶቻችን በአሉባልታ ወሬ እየተመራን ከጎዳና ላይ ነጋዴ እስከ ባለሱቅ ሲያጭበረብረን መኖሩን መዘንጋት የለብንም። በገና ለገና ዕቃ ሊጠፋ ነው ሊወደድ ነው እያልን ስንቱን ነጋዴ ካለ ዕቅዱ ሀብታም ስናደርገው ቆይተናል። አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ስለገዛ ብቻ በመደበኛው ገበያ ከሚሸጥበት በጨመረ ዋጋ ትክክለኛ (ኦርጅናል) ያልሆኑ ምርቶችንም ስንሸምት ነበር።
ከቀናት በፊት የአልኮልን አስፈላጊነት በማየት የተለያዩ ባዕድ ነገሮችን ሲቀላቅሉ የተያዙት አጭበርባሪዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይመስሉኛል። ምክንያቱም ሲቀላቅሉ በጥቆማ ባይያዙና ገበያ ይዘውት ቢወጡ መግዛታችን አይቀርምና። በዚህ ረገድ የሚደረጉት አንዳንዶቹ ሥራዎች ከኮረናው በፊት ሊያጠፉን የሚችሉ መሆናቸውን ብንገነዘብ ጥሩ ነው። እናም አነሰም በዛ የህክምና ባለሙያዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሚያወጧቸው መረጃዎች ቅድሚያ ጆሮ ብንሰጥ ነገን ለማየት እድሉን እንድናገኝ ይረዳናልም ብዬ አስባለሁ።
በሌላ አነጋገር ማንም ከመሬት እየተነሳ ሲያሰኘው የህክምና ዶክተር፤ ሲያሰኘው ፖለቲከኛ፤ ሲፈልግ ደግሞ ኢንጂነርና ሃያሲ እየሆነ የሚለቅልንን መረጃ ተቀብለን መደናበር ያለብን አይመስለኝም። ምክንያቱም አንዳንዱ የኮረና ቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ከሚያደረገው እንቅስቃሴ ባለፈ የራሱን ድብቅ አጀንዳ ይዞ ሃይማኖት ሊያስፋፋ ወይም የፖለቲካ ሀሳቡን ሊያራምድ የሚፈልግ ስለማይጠፋ መጠንቀቁ አይከፋም። በነገራችን ላይ በዚህ ረገድ በነጋ በጠባ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎችንና ትእዛዞችን በደፈናው የሚቃወሙት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። እናም ያገኘነውን የሚጠቅመንንም፤ የማይጠቅመንንም ስንሰበስብ ቆይተን ለስህተት እንዳንዳረግ እያላመጥን ብንውጥ መልዕክቴ ነው።
ሦስተኛው ትንፋሽ የመጨረሽ እሽቅድድማችን ደግሞ በማህበራዊ እንቅስቃሴያችንና በፍቅራችን የሚስተዋለው ነው። በእኔ እይታ ይህኛው ጠንከር ያለና ብዙ የሚያስከፍለንም ይመስለኛል። እንደ መግቢያም አንድ ምሽት ከአራት ኪሎ እስከ መገናኛ በእግሬ ስጓዝ ያስተዋልኩትን ላካፍላችሁ። የመጀመሪያ እይታዬን የሳበው ቤሌር አካባቢ በሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ነበር። ሜዳው ሰፊ በመሆኑ ሁለት ቦታ ላይ ትንንሽ ጎሎችን አስቀምጠው የሚጫቱ ሁለት ጥንድ ቡድኖችን አየሁ። በዚህ ሜዳ ላይ ከዚህ በፊትም ማታ ማታ ከሥራ መልስ ለጤናቸው ስፖርት የሚያዘወትሩ ወጣቶች እንዳሉ አውቃለሁ። በዚህ ወቅት ግን እንደዛ እያለከለኩና እያላባቸው ኳስ ተጋፍተው እየተናጠቁ ሲጫወቱ ማየቴ ለእኔ እንግዳ ነገር ሆኖብኛል።
እዚሁ ቦታ ላይ ሌላው የገረመኝ ነገር ጥቂት የማይባሉ ተመልካቾች በየዳርቻው ከመተቃቀፍ ባልተናነሰ ተጠጋግተው ድምጽ እያወጡ እየደገፉም እየተቃወሙም ይመለከቷቸው ነበር። ዓይኔን ከእነሱ ስመልስ አስፋልቱ ዳር የቆመች አንዲት ላዳ ታክሲ ውስጥ አራት ልጆች ሁለት ከኋላ ሁለት ከፊት ተቀምጠው የሞቀ ወሬ ይዘዋል ወሬያቸው ደግሞ ስለዚሁ መከረኛ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ነው። የፊታቸው ወዝና የምላሳቸው መንቀዠቀዠ ጫት ቅመው እንደመጡ ያሳብቃል። በእርግጥ የላዳው የኋላ በር ክፍት ነው። ግን እነዚህ ታክሲዎች በየቀኑ የተለያዩ ሰዎችን ማንቀሳቀሳቸው አይቀርም እናም ከመካከላቸው አንዱ … ብቻ ይቅር ፈጣሪ ይጠብቃቸው ብዬ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ሁለተኛ እይታዬን የሳበው ደግሞ እንግሊዝ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያለ አንድ ፑል ማጫወቻ ቤት ነው። ለመግባት አልደፈርኩም፤ ነገር ግን ስልክ እንደሚያወራ ሆኜ መንገዱ ዳር በመቆም በደንብ ቃኘኋቸው። የክፍሉ ስፋት አምስት ሜትር በአምስት ሜትር ቢሆን ነው። ግን ከአስር በላይ ወጣቶች ክፍሉን ሞልተውታል። እንግዲህ ልብ በሉ፤ ከክፍሉ ትልቁን ቦታ የያዘው የፑሉ ጠረጴዛ ነው። ዳርና ዳር የተቀመጡት ተመልካቾች ተቃቅፈው ዓይናቸውን ተጫዋቾቹ ላይ ተክለዋል። ሦስቱ ተጋጣሚዎች እየተቀያየሩ አንዴ አጭሯን፤ አንዴ ረጅሟን ዘንግ (ስቲክ) እየተቀባበሉ ይጫወታሉ። ሳኒታይዘር የሚለው ነገር በአካባቢው የለም። ምን አልባት በዘንግ ኳሱን ሲመቱ አዳልጦ አቅጣጫ እንዳያስትባቸው የሚቀቡት ፓውደር ካልጠበቃቸው። ከፑል ቤቱ አጠገብ ደግሞ በኮምፐርሳቶ በተለየች አንዲት በጣም ጠባብ ክፍል ውስጥ አራት ልጆች ጎን ለጎን እየተሻሹ ተቀምጠው በቴሌቪዠን መስኮት ላይ አፍጥጠው ፕቴይ ስቴሽን ጌም ይጫወታሉ። ቤቷ በጣም ጠባብ ከመሆኗ ባለፈ መስኮት የላትም። ይባስ ብሎ ከፊል በሯን በመጋረጃ ጋርደውታል።
በፍቅራችን ረገድ ደግሞ ሁለት ትልልቅ ሥጋቶች አሉኝ። አንዳንዶቻችን የኮሮና ቫይረስ የምናውቀውን ሰው የማይዘው አልያም ከምናውቀው ሰው እኛን የማይይዘን ይመስለናል። ትራንስፖርትና ሥራ ቦታችን ላይ ስንጠነቀቅ ቆይተን ሰፈራችን ስንደርስና ቤታችን ስንገባ ተጨባብጠን፣ ተሳሰምን አብረን እንበላለን፣ እንጠጣለን። በተመሳሳይ የሃይማኖት አባቶችን፤ ሽማግሌና አሮጊቶችን እንደ ልባችን እየጨበጥንና እየሳምን ሰላምታ እንሰጣቸዋለን። ህፃናትንም አቅፎ የመሳም ልምዳችን በነበረበት ነው። ይህን የምናደርጋው ደግሞ ግማሾቻችን በገና ለገና በይሉኝታ ተሸብበን ነው። አያድረግውና ከየመንደራችን ችግሩ ቢፈጠር ግን እንኳን ልንጨባበጥ ለቅሶ መድረስ መፍራታችን አይቀርም። እንኳን መተላለፊያው በበዛው በኮሮና ቫይረስ ይቅርና እከሌ በኤች. አይ.ቪ ሞተ ስንባል ሙሉ ቤተሰቡን ስናገል የኖርን መሆናችን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ለዚህ ነው ትንፋሽ እንዳንጨርስ ያልኩት። ታዲያ ሳይቃጠል በቅጠል፤ ሰነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል፣ ወዘተ … የምንላቸውን ብሂሎች ተከትለን በጊዜ መጠንቀቅ መጀመሩ አይበጅም ትላላችሁ?።
ከዚሁ ጋር በተያየዘ ሁለተኛው ሥጋቴ በሃይማኖት ተቋማት ያለው እንቅስቃሴና ክንዋኔ ነው። በዚህ ረገድ ጉዳዩ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ሁለት ነገሮችን ብቻ በደምሳሳው ለማለት እፈቅዳለሁ። አንደኛ የአብዛኛዎቻችን እንቅስቃሴ ፈጣሪያችንን ማምለክ ሳይሆን መፈታተን የሚመስል ነው። ሁለተኛ ደግሞ በሁሉም እምነት ተቋማት የእምነቱን አገልግሎት የሚሰጡት አባቶች፤ ሰባኪዎች ወዘተ… ፈንጠር ብለው ለብቻ በተዘጋጀላቸው ቦታ ሲሆን አምላኪው በምን ሁኔታ እንደሚታደም ለታዳሚና ለአንባቢ ልተወው። ነበር ከመባል አለ እንድንባል እኛም እንጠንቀቅ ፈጣሪም ይርዳን የመዝጊያ መልዕክቴ ነው !።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ