በሳይንሳዊ ስሙ ኮቪድ 19 በመባል የሚታወቀው የኮሮና ቫይረስ ድንገት ተከስቶ ዓለምን በከባድ ጭንቀትና ስጋት ወስጥ ከከተታት ወራት እየተቆጠሩ ነው።በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች በበሽታው ተጠቅተዋል ፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።
እስከአሁን ወረርሽኙን ለመግታት የሚያስችል ክትባትም ሆነ መድሀኒት አልተገኘለትም።ቫይረሱ ወደ ሀገራችን ከገባ አንድ ወር አስቆጥሯል።በዚህም ጊዜ ወስጥ 114 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው ፣ሦስት ሰዎች ሞተዋል። 16 የሚሆኑም ከበሽታው አገግመዋል።
መንግሥት ቫይረሱ በመላው ዓለም መስፋፋቱን ተከትሎ የተለዩ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ቫይረሱም ወደ ሀገር ወስጥ ከገባ በኋላም መላው ሕዝብ ስለበሽታው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እስከአሁን በመንግሥት በኩል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴና እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶች አዲስ ዘመን የአገር አቀፍ ኮቪድ 19 ዋና ግብረ ኃይል ኮሚቴ አባልና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለተለያዩ ጉዳዮች ድጋፍ ለማሰባሰብ በተቋቋመው አገር አቀፉ ግብረ ኃይል ኮሚቴ አባል እንደመሆንዎ የእስከአሁኑ እንቅስቃሴያችሁ እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ አዳነች፡- የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የዓለም ስጋት ሆኖ ሲሰማ የቆየ ነው።ይህ ችግር ደግሞ በዓለም በተወሰኑ አገሮች ብቻ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን ወደአገራችንም ከገባ አንድ ወር አስቆጥሯል።ልክ ምልክቱ ሊታይ አካባቢ በአገር አቀፍ ደረጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋማቸው እኔም የዚያ ኮሚቴ አንዷ አባል ሆኜ በመንቀሳቀስ ላይ እገኛለሁ።
በሽታን በመከላከል ሂደት ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የለይቶ ማቆያ ጉዳይ ነው። ለይቶ ማቆያ ላይ የሚደረገው ዝግጅት በተመለከተ ለይቶ ማቆያዎቻችን ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉና ለለይቶ ማቆያነት አስፈላጊው ግብዓት ያላቸውና የሌላቸው መሆናቸው ተለይቶ በጊዜ እንዲሠራና ቅድመ ዝግጅቱ እንዲከናወን ይደረጋል። ይህንን የሚሠራ ኮሚቴ አለ። ኮሚቴውን የማስተባብረው እኔ ነኝ ፤ ሌሎች ሚኒስትሮችም በአባልነት ተካተውበታል።
የወረርሽኙን ባህሪ በምናይበት ሰዓት በዓይነቱ ልዩ ነው።ይህ ቫይረስ በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ነው።ምንም እንኳ በዓለም ላይ አዲስ ክስተት ቢሆንም እንኳ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ካለን ባህል ጋር ሲታይ ፈታኝ የሆነ ባህሪ ያለው ነው።
እንደሚታወቀው የእኛ ባህል በአብዛኛው በአብሮነት የሚከናወን ነው።ኑሯቸውን የአንድነት ነው፤ ስንሠራም በእጅጉ ተቀራርበን ነው።አብሮ መብላቱም እንዲሁ የእኛው ባህል ነው።የቤተሰብ ቅርርብም ጥብቅ ነው።በዚህም የተነሳ ንኪኪያችንና ጥግግታችን ቁርኝታችንን በደንብ የሚያሳይ ነው።እንቅስቃሴያችንም አብሮነታችንን መሰረት ያደረገና በዚያም ላይ የዳበረ ነው።
ከዚህ አንጻር ይህንን እንዴት ማስፈጸም እንደሚቻል ጉዳይን ማሳወቅና የሕግ ማዕቀፉ እንዲኖረው የማድረግ ጉዳይ ሌላ ሥራ ነው።በብዛት በህግ ብቻ የምንፈታው ስላልሆነ እንዲዚህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ሰዓት ማህበረሰባችን በደንብ እንዲረዳው በባህሉ ወይም ደግሞ በእሴቱ የተመጣበት ሳይመስለው ከእዚያው ከእሴቱ ሳይወጣ ሳይጠጋጋ ፤ ግን ደግሞ ልብ ለልብ ተቀራርቦ ይህን ችግር ማለፍ የሚልቻበት አሠራር እደሚኖር የማሳወቅም ምራ ነው።
ሌላው ደግሞ በሽታው በባህሪ ብዙ የሥራ እንቅስቃሴን የሚገታ በርካታ ሥራዎችንም ያቀዛቀዘ እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚን የጎዳ ነው።የኢትዮጵያን ደግሞ በምናይበት ጊዜ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን ብዙ ማህበረሰብ አኗኗሩ በዕለት ጉርስ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይበልጥ የሚያናጋ ነው፤ ይህም ቁጥሩ ቀላል የሚባል ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ዜጎች ተሯሩጠው ሠርተው የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ላይ ተቀዛቅዟል። ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት የጀመርነው ግን አስቀድመን ነው።ስለዚህ ገቢ ማሰባሰብና ለተቸገሩ ወገኖቻችን መልሰን በመስጠት እነርሱ በቤት እንዲቆዩ ማስቻል ላይ ሥራ እየተሠራ ነው።ዝም ብሎ ብቻ መመሪያው ይህ ነው።እሱን ካልፈፀማችሁ ቅጣት አለ አሊያ ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ገዳይ ነው፤ እርሱን መከላከል ካልቻላችሁ ትሞታላችሁ በማለት ብቻ ማስፈራራት ሳይሆን እንዴትና በምን ዓይነት አግባብ ቤት መቆየት እንደሚችሉም ጎን ለጎን መፍትሔ በማስቀመጥ ነው ሁኔታዎችን ማስተካከል የሚያስፈልገው።ምንም እንኳ የሚያስፈልገውን ሙሉ ለሙሉ ማሟላት ባይቻልም በተወሰነ መልኩ በመደጎም አቅም መፍጠር ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ይህ ችግር በዚህ ሰዓት ይመጣብናል ብለን ያቀደነው ነገር ሳይሆን ዱብዳ የሆነ ጉዳይ ነው።ከዚህም የተነሳ ብዙ ሩጫ፣ ርብርብና መተባብርን በተለይ ደግሞ ችግሩን መረዳትና ቅንጅት በመፍጠሩ በኩል ሁላችንም አስተዋጽዖ እንድናደርግ የሚጠይቅ ሆኖ አግኝተነዋል።ወረርሽኙ ልክ ሌሎች አገሮች ላይ ሲከሰት ወደእኛ ሊመጣ እንደሚችል ማሳያዎች ሲመጡ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን የማድረግ ሥራ ነው ስንሠራ የቆየነው።
ከወረርሽኙ ባህሪ ጋር የተገናዘበ ሥራዎችን መሥራት ደግሞ የተጀመረው ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከኢትዮጵያዊ ባህልና ማንነት ጋር ሲነጻጸር ፈታኝ የሆነ በሽታ ስለሆነ ይህንኑ ከግምት በማስገባ ነው ዝግጅቱ የተጀመረው።እንደተጠረጠረውም አልቀረልንም፤ ችግሩ ወደእኛ ደርሷል።አስቀድመን ባንዘጋጅ ኖሮ ዛሬ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የሞት ቁጥርም ሆነ በቫይረሱ የተያዘው ሰው ቁጥር ይህ ብቻ ላይሆን ይችላል።ወረርሽኙ ወደህዝባችን ገብቶ ያልተጠበቀውን ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችል እንደነበረ ማሳያዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡-የመከላከል ሥራው እንደተጠበቀው እየሄደ እንዳልሆነ በአንዳንድ አካላት ይነሳል፤ አዲስ አበባ ላይ ብቻ በተወሰነ መልኩ የሚንፀባረቅ ቢሆንም ቸልተኝነቱ ግን አለ፤ ሌሎች አገሮች የታየው መዘናጋት አለና ከዚህ ጋር በተያያዘ ያስተዋሉት ነገር ምንድን ነው?
ወይዘሮ አዳነች፡- እንደ አንድ የኮሚቴ አባል የድጋፍ ኮሚቴ ውስጥ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ውስጥ እሳተፋለሁ፤ ቀን ስንሠራ ውለን ማታ ላይ ደግሞ በየቀኑ እንገመግማለን። ለለይቶ ማቆያ ተቋማትን እንፈልጋለን።በተጨማሪም ለማከሚያ የሚሆኑም እንደዚሁ የምንፈልጋቸው ስፍራዎች ናቸው።ለይቶ ማቆያ ሁለት ዓይነት ነው። በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ ህክምና የሚደረግበትና የተጠረጠሩትን ደግሞ ለይቶ ማቆያ እንደ ማለት ነውና ለዚህም ጭምር ቦታዎችን መፈለግ ግድ ይለን ነበርና በዚህ ዙሪያ ስንሠራ ነበር።ችግሩ ይመጣብናል ብለን ያሰብነው ባለመሆኑ በብዙ እንድንሮጥ ግድ ብሎናል። በዚህም ብዙዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ እያሳወቅንና እየቀሰቀስን የሚሠራ ሥራ ነው።
ከዚህ አንፃር ሲታይ እውነቱን ለመናገር የተደረገው ድጋፍ መልካም ነው የሚባል ነው።ብዙ አገሮች እኛ ዘንድ አይደርስም ሲሉና በሩቅም እየተመለከቱ ሲተቹ ተስተውለዋል።ነገር ግን ባላሰቡት ሁኔታ በቫይረሱ በመወረራቸው ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ ማየት ችለናል፤ ስልጣኔያቸው ደግሞ ከዚህ ወረርሽኝ እንዳላስጣላቸውም የአደባባይ ምስጢር ሆኗል። ገንዘባቸው፣ እውቀታቸው ብሎም ኃያልነታቸው አላዳናቸውም።በጣም በሚያሳዝንና ልብን በሚነካ ሁኔታ ለዕልቂት ተዳርገዋል።ይህ በአገራችን እንዳይከሰት ነው ሁላችንም እንደጋገፍ፤ ያለንን እንስጥ እያልን ያለነው።የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋል።ምክንያቱም ለለይቶ ማቆያ በሚል የተዘጋጀ ተቋም የለም፤
አዲስ ዘመን፡- በእስከአሁኑ በተቋምም ሆነ በሌሎች ድጋፎች ምን ያህል ነው ማግኘት የተቻለው?
ወይዘሮ አዳነች፡- አብዛኛው የመንግሥት ቢሆንም እንኳ እስካለፈው ዓርብ ድረስ ወደ 180 ተቋማት ለይተናል። መቶ የሚሆኑት የመንግሥት ተቋም ሲሆኑ 80 የሚሆኑት ደግሞ የግል ተቋማት ናቸው።ድጋፍ ከተደረጉት መካከል የማምለኪያ ቤተ ክርስትያኖች፣ ኮሌጆች፣ የግለሰብ መኖሪያዎችና የተለያዩ ሕንፃዎች ይገኙባቸዋል።ቀናነት በልጦባቸው ሕንፃዎቻቸውን አከራይተው ገንዘብ ያገኙበት የነበረውን ትተው ለዚህ ለድንገተኛ ወረርሽኝ ለይቶ ማቆያነት ይዋል ብለው ረድተውናል።ከዚህ አንጻር ሰታይ ርብርቡ ጥሩ ነው።
ሕንፃውን ብቻ ስለያዝን ምግብ አሊያ ልብስ መሆን አይችልም።የገንዘብና የሌሎችም ድጋፎች ደግሞ አስፈላጊዎች ናቸው።ሌሎች የንጽሕና መጠበቂያም የግድ የሚሉ ናቸው። ወረርሽኙ በባህሪው የሚፈልገው ብዙ ነገር ነው።ከዚህ አኳያ በምናይበት ጊዜ እንደ ሳሙና እና ሌሎች የንፅሕና መጠበቂያ እቃዎችን የለገሱ በርካቶች ናቸው።በገንዘብ ደረጃ እስከአሁን ድረስ በኮሚቴ በኩል 400 ሚሊዮን የሚደርስ ብር ተሰብስቧል።ከዚህ ጎን ለጎንም የእህልም የቁሳቁስ እና የሌሎችም ዓይነት ድጋፎች ተደርገዋል።የተደረገው ድጋፍ ሲደማመር የሚናቅ ሳይሆን የሚያስመሰግን ነው።
ከችግሩ ስፋት አንጻር የተሰበሰበው ገንዘብ በቂ ነው ማለት አይደለም።ችግሩን ለመሻገር የሚያስፈልገን ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነው። ምክንያቱም የወረርሽኙ ባህሪ ሰዎችን ቤት የሚያስቀምጥ ነው።በቤት ውስጥ ዕንዲቀመጡ የምናስገድዳቸው ዜጎቻችን ከብት ባለፈ ምግብ ይፈልጋሉ። የንጽሕና መጠበቂያ እቃዎች ያስፈልጓቸዋል።የምንሰጣቸው ምግቦችም በተቻለ መጠን የተመጣጠኑና ወረርሽኙን የመቋቋም ኃይላቸውን ከፍ ማድረግ የሚችሉ እንዲሆኑ ይጠበቃል።ከዚህ በተጨማሪም አልባሳት የሚፈልጉ አሉ።እነዚህን ከግምት በምናስገባበት ጊዜ የምንፈልገው ዕርዳታ ከፍ ያለ መሆኑን መረዳት እንችላለን።ከዚህ በመነሳትም የተደረገው ድጋፍ ትንሽ መሆኑን ለመናገር ድፍረት ይሰጠናል።
እዚህ ላይ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ወረርሽኙ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ለማስቆም ያለን ዋናው አማራጭ መከላከል ላይ ተግቶ መሥራት ነው።በሽታውን ለመከላከል ዋናው አቅማችን መጠንቀቅና መጠንቀቅ ብቻ ነው።በእርግጥም የእግዚአብሄር ኃይል እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኑን ለመከላከል የወጡ ህግና መመሪያዎችን በአግባቡ በመረዳት ራስን ለህጎቹና መመሪያዎች ማስገዛትና በታማኝነት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።ይህ ደግሞ ከሁሉም ዝጋ የሚጠበቅ ነው።ከአቅማችን በላይ የሆነውን ለእግዚአብሄር እንሰጠዋለን።በአቅማችን ሊደረግ የሚገባውን ግን መተግበር ይጠበቅብናል።
ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባና ከተስፋፋ በስልጣኔያቸውም ሆነ ባሏቸው ባለሙያ እነ ጣሊያን፣ አሜሪካና ሌሎችም አገራት ያልተቋቋሙት በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ የሚጠይቀውን ግብዓት እንኳ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ሆነው ሳለ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ይህን ወረርሽኝ እኛ ኢትዮጵያውያን እንቋቋመዋለን የሚል ትንታኔና አስተሳሰብ ውስጥ መግባት አንችልም።
እኛ የምንችለው በተቻለን ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግና ዛሬ ባለን መረዳዳት ነው።የተዘናጉ አገራት ምን እንዳጋጠማቸውና እያጋጠማቸው እንዳለ ለመረዳት የግድ የእያንዳንዳችንን ቤት ማንኳኳት አይጠበቅም።ትልቁ መድሃኒት በባለሙያዎች የሚነገሩ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ራስን ከቫይረሱ መከላከል ነው።
ገንዘባችንን ዛሬ ለዚህ ጉዳይ ካልተጠቀምንበት ወረርሽኙ ከገባ ምንም ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ትርጉም የለውም።ባንክ ውስጥ ያስቀመጥነው ገንዘብ ወረቀት ነው የሚሆነው።ዛሬ ብንገለገልበትና ወገኖቻችንን ረድተን ራሳችንንም የምንከላከል ከሆነ ነገ ሌላ ቀን ነውና እንሠራለን። ገንዘብ ተመልሶ የሚገኝ ነው፤ ህይወት ግን ተመልሶ አይገኝም። በአሁኑ ወቅት የተዋጣው ገንዘብ በቂ አይደለም ስንል ችግሩ ከሚጠይቀው በታች ነው ለማለት ነው።ገንዘብን ማከማቸት በራሱ ለእነ ጣሊያ፣ አሜሪካ፣ ስፔንና ሌሎችን እንዳልጠቀማቸው መረዳት ይቻላል።ከእኛ የተሻሉ ሀብታም ናቸው ብቻ ብሎ ማለፍ ሳይሆን ከእኛ የተራራቀ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ያሉ መሆናቸውም እውነት ነው።
እንዲህ ስል ኢኮኖሚያችን ዝቅተኛ ነውና ምንም ማድረግ አንችልም ለማለት ሳይሆን ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ወረርሽኙ ሳያጠቃን በመከላከል ብቻ ማምከን እንችላለን ለማለት ነው።እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን እልህ አለብን።አንድ ነገር ሊያጠቃን ነው የመጣው ብለን ካመንበት ጉዳዩ እንዳይደርስብን ብቻ ሳይሆን አሸንፈን ድልን ለመቀዳጀት በጣም ጠንካሮች ነን።ለዚህ ማሳያ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳየነውን ርብርብ እንዲሁም የዓደዋን ጦርነትና የተቀዳጀነውን ድል መለስ ብሎ ማየቱ ብቻ በቂ ነው።ምን ኖሮን ነው የህዳሴውን ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ ልናደርስ የቻለነው፤ ያለን ነገር ቢኖር ወኔ ነው።ያ ወኔ እና እልሃችን ከጎዶሏችን እንድንሰጥ ስላደረገን ነው አባይን እዚህ ደረጃ ላይ ልናደርሰው ያስቻለን።ዛሬም እንረዳዳ፣ እንስጥ ስንል ስለተረፈን ሳይሆን ከጉድለታችንም ቢሆን እናድርግ ለማለት ነው።ከጎደለብን ነገር መልሰን አጉድለን የምንረዳዳ ከሆነ ነገ ሌላ ቀን ነው።ተስፋ አለ፤ መኖር አለ፤ መኖር ካለ ደግሞ መሥራትና ማግኘት እንዲሁ ይኖራል።ዛሬ ላይ ያለን ገንዘብም ሆነ እውቀት የጋራችን ነው፤ የህዝባችን ነው ብለን መረዳዳትና ይህንን የጭንቅና የመከራ ሰዓት በጋራ መሻገር አለብን እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የየቀን የሥራ ውሏችሁን እየገመገማችሁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፤ በግምገማችሁ ጊዜ የየዕለት ተግዳሮት ሆነውብናል ብላችሁ የለያችኋቸው ችግሮች ይኖሩ ይሆን?
ወይዘሮ አዳነች፡- አዎ! ለይቶ ማቆያን እንደሚያስተባብር ኮሚቴ ሳንሳ የመጀመሪያው ተግዳሮት ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዜጎቻችን ሊመጡ ይችላሉ ብለን ከጠበቅነው በላይ ነው የሆነብን።ለዚህ ምክንያታችን ደግሞ አንደኛ አገራት በሮቻቸውን ዘግተዋል፤ ኢትዮጵያም እንዲሁ በሮቿን ዘግታለች።እንቅስቃዎች ተግትተዋል።የዚያን ያህል መንገደኛ ይመጣል የሚል ታሳቢ አላደረግንም ነበር።ነገር ግን ችግር ሲመጣ አገር ሊሆን የሚችለው የራስ አገር ነው።ከነችግሩም ቢሆን ተገን ሊሆን የሚችለው ዜጋ ነውና የራስ አገር ነው።ወደየትም ልትጥል የማትችለው እናት አገር ናት።ባልጠበቅነው ሁኔታ ዜጎቻችን ከየአገሩ ተገፍተዋል።ውጡልን ተብለዋል።በመሆኑም መጥተዋል።ከጠበቅነው በላይ ስለሆነ አንዱ ተግዳሮት ይህ ነው ማለት ይቻላል።
ሌላው ደግሞ የመጡበት ሁኔታ ጥንቃቄ የተሞላበት አይደለም።ስለዚህም እነሱን በለይቶ ማቆያ ማቆየት፣ ወጪያቸውን መሸፈን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ስነ ልቦናቸውን ጭምር ማከም የሚፈልግ ነው።ስነ ልቦናቸው ጭምር የተጎዱ ዜጎቻችን ሆነው ነው ያገኘናቸው።ለዚህ ያደረግነው በቂ ዝግጅት ባይኖርም ችግሩ ሲገጥመን ግን ገምግመን ምን ማድረግ እንዳለብን በመወያየት የስነ ልቦና ህክምና እና ምክርም ጭምር እንዲደረግላቸው የማድረግ ሥራ እያከናወንን ነው፤ ተረጋግተው የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ድጋፍ መጠቀምና መቆየት እንዲችሉ እንዲሁም በተሰጣቸው ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ የማድረግ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
ሁለተኛው ተግዳሮት በህብረተሰቡ አካባቢ በተባለው የጥንቃቄ መርህ አለመመራት ነው።ይህ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም ሁላችንንም የሚመለከት ነው።ስለቫይረሱ መከላከል እየተነገረ ስላለ መረጃና መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ ውሸት አይደለም፤ እውነት ነው።ምክንያቱም በአንድ አገር ብቻ እንኳ በአንዲት ቀን ብቻ እስከ ሁለት ሺ ሰው ሲሞት አይተናል።ስለዚህም ተገቢውን ጥንቃቄ መከተልና መተግበር ከማንም በላይ ራስን ማዳን ነው።ስለዚህም ራሳችንን ከአስከፊው በሽታ ለማዳን ቀላል የሆነውን ተግባር መፈጸም አለብን።
ሰው የግዴታ በፋብካሪካ የተመረተን የፊት መሸፈኛ ማድረግ አይጠበቅበትም።የአንገት ፎጣን፣ ነጠላንም ሆነ መሃረብን ጨምሮ ሌሎቹንም በመጠቀም አፍንና አፍንጫን መሸፈን ይቻላል።ይህንን ቀላል ተግባር ለመፈጸም መዘግየትና መፋዘዝ አግባብ አይሆንም።
ሦስተኛ ተግዳሮት ብለን ያየነው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የተመለከተ ነው።በተለይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ።ችግሩ ኢትዮጵያ ወስጥ እየተከሰተ ነው እየተባለ ከተባለው በላይ አትጫኑ ሲባሉ ጭራሽ ትርፍ የሚጭኑ መኖራቸውን አስተውለናል።አሳፋሪውም ሆነ ተሳፋሪው በተለይ በከተማው ውስጥ ያሉ ታክሲዎች በጣም ፈትነውናል።
አራተኛው የፈተነን የገበያ አካባቢ ነው፤ በተለይ አትክልት ተራ እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጦች የሚሸመቱባቸው አካባቢ ሰዎች መሸመታቸውንና ሸቀጦችን ማግኘታቸው እንጂ የሚደርስባቸውን የከፋ ነገር አለማስተዋላቸው ነው።ለአደጋ የተጋጡ ስለመሆናቸው ብዙዎቹ አያስተውሉም።ይህ ትንሽ ቀነሰ እንጂ ዛሬም ድረስ ያለተቀረፈ ጉዳይ ሆኖብናል።ሁሉን አስሮ እና ቀጥቶ አያቻልም።የመጀመሪያ ጉዳይ ሊይዘንና ሊቀጣን የሚችለው ህሊናችንና ማስተዋላችን ነው።ሌላው ደግሞ የአምልኮ አካባቢዎች የነበሩ ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን ትልቅ መሻሻሎችን ማየት ችለናል።ሰዎች ወደ እግዚአብሄር መቅረባቸው እንደ እምነታቸው እንዲሆንላቸው እጅግ በጣም እንደግፋለን።በዚህ ጉዳይ በምንም ዓይነት ሁኔታ መንግሥት ጣልቃ መግባት አይችልም።
ነገር ግን ደግሞ መንግሥት ያወጣውን ህግ ዜጎችን ለመታደግ እና ያንን አማኝ የሆነውን ህዝብ ለማትረፍ እንደሆነ መታሰብ አለበት።ትጋቱ እነሱ ለበሽታና ለችግር እንዳይጋለጡ መሆኑን በማስተዋል በያሉበት ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት መተሳሰሩ በየትኛውም በኩል የሚደገፍ ነው።የእምነት አባቶችም ይህንኑ ለማስተማር ሲተጉ አስተውለናል።ስለዚህ ይህ ሁሉ ለእኔ ነው በሚል መንፈስ አክብሮ መንቀሳቀሱ በጣም ወሳኝ ነው።መታዘዝ ደግሞ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ነው።ስለዚህም ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ ለመቀጠል ያስችላት ዘንድ የምታደርገውን ርብርብ ምንም ዓይነት ትርጉም መስጠት አያስፈልግም።በዚህ በሚደረገውም ርብርብ መጠነኛ መሻሻሎች የታዩ ሲሆን፣ የበለጠ መትጋት ደግሞ አስፈላጊ ነው።
ሌላው ተግዳሮት ነው የምንለው ንጽሕና የመጠበቅ ጉዳይ ነው።ልክ ተከሰተ የተባለ ጊዜ ያየነው ነገር በጣም የሚያስደስት ነበር፤ ሁሉም በየመስሪያ ቤቱ አካባቢ የንጽሕና መጠበቂያውን ሳሙና እና ውሃ በማስቀመጥ በኩል የነበረው መሯሯጥ ይበል የሚያሰኝ ነበር።የተያዘው ሰው ቁጥር አነስተኛ መሆኑና የተወሰነም ሰው አገገመ ሲባልና ሲሰማ የነበረውን ጥንቃቄ ለቀቅ የማድረግ አዝማሚያ እየታየባቸው ነው።መቋቋም በመቻላችን ደስ ሊለንና ጥንቃቄውን ይበልጥ መጨመር ነው ያለብን።በመጠንቀቃችን ወረርሽኙ ሊጎዳን አልቻለም የሚል መልዕክት አለው እንጂ ፈፅሞ ጥንቃቄያችንን እንድናላላ ምክንያት ሊሆነን አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- በህገ ወጥ መንገድ በየድንበሩ ወደ አገሪቱ ተገፍተው ከሚላኩ ዜጎች በተጨማሪ እርስዎም እንዳሉት ደግሞ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ዜጎች አሉና እነዚህም ዜጎች ደግሞ ምንም ዓይነት ምርመራ ሳይደረግላቸው ላኪ አገሮች ከአገራቸው ብቻ እንዲወጡ እያደረጓቸው ነውና ይህን ከሚያደርጉ አገራት ጋር ኢትዮጵያ በመነጋገሩ በኩል ያደረገችው ጥረት ይኖር ይሆን?
ወይዘሮ አዳነች፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለሚዲያ እንደተናገሩት በዲፕሎማቶቻች፣ በኤምባሲዎቻችን እንዲሁምበሚሲዮኖቻችን አማካይነት በተጨማሪም ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር ቀጥታ በስልክ እየተገናኙ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ትልቅ ሥራ እየተሠራ ነው ያለው።ያ ባይሆን ኖሮ ፈጽሞ ልንቋቋመው ከምንችለው በላይ እና ከምናስበውም በላይ ሊሆብን ይችል ነበር።በመጀመሪያ አካባቢ እንደ አጀማመሩ በምናይበት ሰዓት አይደለም አሁን ላይ ያለው፤ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው።በዚህም ምክንያት ያቆሙ አገሮች አሉ።
ድንበር አካባቢ ተገፍተው የሚመጡ ዜጎቻችንን በምናይበት ሰዓት ይህ እየሆነ ያለው ሁሉም ጎረቤት አገር ላይ አይደለም።አረብ አገራት ያሉ ዜጎቻችን ከህገ ወጥነታቸውም የተነሳ እንዲሁም በተለያዩ እስር ቤቶች ከመገኘታቸው የተነሳ የሚያያዝ ባህሪም ጭምር ነው ያለው።ዞሮ ዞሮ የዲፕሎማሲው ሥራ ከዚህ በላይ መጠናከር አለበት።በሰላሙ ጊዜ ይዘው እያሰሯቸው ችግር ሲመጣ ግን ወደ አገራችሁ የሚባልበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም።በእኛም አገር ብዙ የውጭ አገር ዜጎች አሉ።ያለምንም ችግር ሥራቸውን እያከናወኑ ነው የሚገኙት።ሌሎች አገሮች ላይ በጣም በርካታ ኢትዮጵያውን ደግሞ አሉ።ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ ነው። ያለምንም ነገር ዜጎቻችንን ወደአገራችን እየላኩ ያሉት አንዳንድ አገራት ናቸው።ስለዚህም በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።ደግሞም ውጤትም ተገኝቶባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በርካታ ተቋማት ሥራ በማቆም በቤት ውስጥ እንደየሥራቸው ባህሪ እንዲሠሩ ተደርገዋል፤ ነገር ግን ሚዲያን ጨምሮ በተለይ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሉና ለእነዚህ የሚሉት ነገር ካለ?
ወይዘሮ አዳነች፡- ችግር በሚመጣበት ሰዓት የሙያ ባህሪያቸው ሆኖ ለህዝብ ዋጋ በመክፈል አገልግሎትን የሚሰጡ ተቋማትና ባለሙያ ሠራተኞች አሉ።ከእነዚህ ውስጥ አንዱና የመጀመሪያው የጤና ባለሙያዎች ናቸው።ቀጥሎ ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የጸጥታና የደህንነት ባለሙያዎች እንዲሁም የባንክ፣ የአየር መንገድ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን።በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉ ሠራተኞችም የሚጠቀሱ ናቸው።
ለአገራቸውና ለህዝባቸው ሲሉ የህይወት ዋጋ የሚያስከፍልና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ስለወገናቸው የሚተጉ አሉ።
እንደዚህ ዓይነት ነገር በሚመጣበት ሰዓት እንደዚህ ዋጋ ከፍሎና ራስን ሰጥቶ ሌላውን ማዳን መቻል መታደል ነው። ይህ ትልቅ ሥራ በታሪካችንም ውስጥ በወርቃማ ቀለም መጻፍ ያለበት ትልቅ አስተዋጽዖ ነውና ሌላ ምንም ማለት አንችልም፤ እግዚአብሄር ዋጋቸውን ይክፈል ነው። እንደመንግሥት ደግሞ ለእነሱ ያለን ታላቅ አክብሮትና ፍቅር መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች ወረርሽኙ በኢትዮጵያ የተፈራውን ያህል አይደለም ይላሉና ለዚህ ምስጢሩ ምንድን ነው ይላሉ?
ወይዘሮ አዳነች፡- ሰዎች የተሳሳተ መረጃ እስከዛሬ ምንም ዓይነት የምርምርም ሆነ ሌላ የመረጃ ምንጭ ያልተደገፈ ነገር ሲያነሱ ይደመጣሉ፤ ቀለማችን ጥቁር ስለሆነ ነው፤ የመቋቋም ኃይላችን ከነጮች ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፤ እያሉ የተለያየ ትርጉም እየሰጡ ነው።ይህ ግን ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለው መላ ምት ነው።ይህ መላ ምት ደግሞ ለከፋ ችግር ያጋልጠናልና ስህተት ነው።ታድያ ምንድን ነው የተባለ እንደሆነና እንደ ኢትዮጵያ ለማንሳት ከሆነ ልክ ሌሎች ላይ ችግሩ ሲታይና መስፋፋቱ ሲበረታ በምናይበት ሰዓት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ወደእኛም ሊመጣ ስለሚችል ተብሎ ነው ኮሚቴ የተቋቋመው።ምናልባት የለይቶ ማቆያን አስገዳጅ ያደረግንበት ቀን ብንመለከት ምናልባትም ከዚያ በፊት ሦስት አሊያም ሁለት ሳምንት አስቀድመን ተግባራዊ ብናደረግ ኖሮ ትንሽም የመነካካት እድሉን ጭምር ልናስቆም እንችል እንደነበር ያሳያል።
ይሁንና ከዚያም በኋላ ቢሆን አንድ አሊያም ሁለት ሰው ብቻ ነው የተያዘው በሚል አላቃለልነውም።ወረርሽኙ ከገባ አቅማችንንና ኢኮኖሚያችን የቱ ላይ እንደሆነ አሳምረን እናውቃለን።የማህበራዊ አኗኗራችንንም ጭምር ጠንቅቀን እናውቀዋለን።አይደለም እኛ ‹‹ሰለጠኑ›› ስንላቸው የነበሩ አገራትም ስላልተቋቋሙት እኛ ያለን አማራጭ መጠንቀቅና መጠንቀቅ ብቻ ነው በሚል ሥራ መሠራቱ አንዱ ነው።
በግሌ እንደማምነው እግዚአብሄር ረድቶናል። ምክንያቱም የበሽታው ባህሪ ሲጤን ከሰው ልጅ አቅም በላይ ነው።ምርምርም ቢደረግና ቢጣር በባህሪው ዙሪያ የሚወጣው መረጃ ቀድሞ የወጣውን የሚያፋልስ ዓይነት ሆኖ ነው እየሰማን ያለነው።ይህን ስናስተውል ከእግዚአብሄር እርዳታ ጋር እዚህ ደርሰናል፤ እናመልጣለን ብዬም አምናለሁ።እስከአሁን ከታየው ምልክትም አኳያ ሲታይ ከኮሮና ቫይረስ ህዝባችንና አገራችን ኢትዮጵያ ታመልጣለች ብዬም አምናለሁ።ይህ የሚሆነው ግን ጥንቃቄያችንን ይበልጥ ካጠናከርንና ከዚህም በላይ እያጠበቅን ከሄድን ነው።ደግሞም ይህ እንዲሆን ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣው።አዋጁን ዓለም ስላወጀ አይደለም ያወጅነው የመጣብን አደጋ ክፉ በመሆኑም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጥቂት የማይባሉ አካላት በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር ማነስና ሞትም የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑን መሰረት አድርገው መንግሥት መረጃ ደብቆ እንጂ ከዚህም በላይ ነው ይላሉና ምላሽዎ ምንድን ነው?
ወይዘሮ አዳነች፡- መንግሥት ደብቋል እንበል፤ ለምን? ይህን ወረርሽኝ ያመጣው መንግሥት ነው እንዴ? ችግሩን መንግሥት አላመጣውም።በብዙ መለኪያ ከእኛ በብዙ እጥፍ ሰለጠኑ የተባለቱ አገራት ተወረዋል።ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በዛ ደረጃ ወረርሽኝ መኖሩ እውነት ከሆነ መንግሥት የሚያገኝበት ትርፍ ምንድን ነው? እንዲያውም እውነቱን አውጥቶ የተሻለ ገንዘብ ማሰባሰብ አለበት።ህዝቡም እንዲተባበርና ያለውን እንዲሰጥ ማድረግ አለበት።ስለዚህ ይህ ምንም መነሻ የሌለው እና ምክንያታዊ ያልሆነ ወቀሳ ነው።
ምናልባት ሊባል እንኳ ቢቻል ይህ ሳይሆን የመመርመር አቅማችን በየአካባቢው ባለመስፋፋቱ የተነሳ ሊሆን ይችላል።በዚህ ዙሪያ አቅማችን ደካማ ነው፤ ከዚህም ከዚያ ነው እያሰባሰብን ያለነው።ይህም ቢሆን የተገዛ እንኳ ቢሆን ወደ አገር ወስጥ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች ስለተገቱ ያለው ፈተና ከባድ ነው።እንዲያም ሆኖ የመመርመር አቅማችን በየጊዜው እያደገ ነው።በየክልሎችም ተጀምሯል።እንዲህ እንበል እንጂ ሁሉም ዘንድ በመድረስ መርምረናል ብለን ማለት አንችልም።ከታወቀ ግን መንግሥት የሚደብቅበት አንዳች ምክንያት አይኖረውም።የበሽታው ባህሪ በራሱ የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳ በመሆኑ ጊዜ ስለማይሰጥ ደብቆ ለማቆየት እድልን የሚሰጥ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ጥንቃቄን በተመለከተ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ወይዘሮ አዳነች፡- ወረርሽኙን መከላከል የምንችለው በመከላከልና በጥንቃቄ ነው።መድኃኒታችን ሁልጊዜ በልባችን እያሰብን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።መጪውም የዳግማዊ ትንሳዔ በዓል ነው፤ ኢትዮጵያውን ደግሞ በባህላችን አብረን መብላት እንወዳለን፤ አንድ መዓድ መጋራቱ በራሱ ለበሽታው መተላለፍ አንዱ መንገድ ነውና ፍቅራችንንና አብሮነታችንን በልባችን አድርገን ጥንቃቄው ላይ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል።ራሳችን መጠንቀቅ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ማስተማር እና ተግባራዊ እንዲደረግ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።ፖሊስም ሆነ መንግሥት ብቻውን አይችልም።ሁሉም በየበኩሉ ርብርብ እንዲያደርግ ነው ጥሪ የማቀርበው።ይህን ፈተናና የጭንቅ ጊዜ በጋራ እንለፈው ማለት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ አዳነች፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
አስቴር ኤልያስ