የኮሮና ቫይረስ ከወራቶች በፊት በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ሁዋን ከተማ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የስርጭት አድማሱን በማስፋትና በርካታ አገሮችን በማዳረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህዝቦችን አጥቅቷል። ከ165 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
ቫይረሱ በዓለም ህዝብ ላይ እያደረሰ ካለው ጥፋት ጎን ለጎን የበርካታ አገራት ኢኮኖሚንም አሽመድምዷል። በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል። የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን በረራዎችም ባሉበት ተገተዋል። ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችም ቆመዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ አገራት ከባድ የኢኮኖሚ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።
ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ አገራት ካጋጠማቸው የኢኮኖሚ ኪሳራ ባሻገር በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ከሚሠሩባቸው ድርጅቶች በመቀነሳቸው ሥራአጥ ሆነዋል። በቫይረሱ ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ መገደቡን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉም በከፍተኛ ደረጃ በመጎዳቱ፤ ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ የነበሩ አገራት በእጅጉ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።
በየዕለቱ የቫይረሱ ስርጭት እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር በዓለም ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳያስከትል እንደማይቀር በዘርፉ ያሉ ተንታኞች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። ይህ ቀውስ ሳይበርድ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለ ከዚህ የባሰ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ዓለማችን ልታስተናግድ እንደምትችልም እየተጠቆመ ነው።
በዚህ የጤና ቀውስ እጅግ ከተጎዱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንቨስትመንት ሲሆን፤ የኮሮና ቫይረስ የሰዎችን እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚገታ ከመሆኑ አኳያና እንደልብ ተንቀሳቀሶ የመሥራት ዕድልን ስለሚነፍግ አብዛኛዎቹ የዓለማችን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ባሉበት ቆመዋል። ከቀውሱ በኋላም ዳግም ለማንሰራራት ግዜያትን ይፈጃሉ። በዋናነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሚይዘው ከፍተኛ የሥራ ዕድልና ከሚያስገባው ገቢ አኳያ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል።
በኢትዮጵያም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንቅስቃሴው ቆሟል ማለት ይቻላል። በተለይ ኢንቨስትመንቱ ጥሬ ዕቃዎችን በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚፈልግ ከመሆኑ አኳያ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ተስኖታል። የቫይረሱ ስርጭት ተገቶ ሃገራት ድንበራቸውን ከፍተው የእርስ በእርስ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን እስኪጀምሩ ኢንቨስትመንቱ ባለበት ቆሞ ለመጠበቅ ይገደዳል።
የኮሮና ቫይረስ አሁንም በርካቶችን እያጠቃ በመሆኑና በርካቶችም ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን ተከትሎ የዓለም ኢኮኖሚ ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ከመጥፋቱ በፊት ምን ሊሆን እንደሚችልና ከጠፋም በኋላ ምን ዓይነት አቅጣጫ ሊይዝ እንደሚችል ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል። የኢኮኖሚው አንዱ አካል የሆነው ኢንቨስትመንትም ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል አስቀድሞ ለመተንበይ አስቸጋሪ መሆኑንም በርካታ ትንታኞች ከወዲሁ ይናገራሉ።
በዓለማችን በልዩ ልዩ ዘርፎች በርካታ ኢንቨስትመንቶች እየተካሄዱ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከእነዚህ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ውስጥ በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት አብዛኛዎቹ የተጎዱ መሆናቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ኢንቨስትመንት አጠራጣሪ ሁኔታ ላይ በወደቀበት ሰዓት እንኳን ሊጎዱ ቀርቶ ይልቁንም በቀጣይ ትርፋማ ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዳሉም ልብ ማለት ይገባል።
ኢንቨስቲንግ ዶት ኮም የተሰኘውና በኢንቨስትመንት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ማህበራዊ ትስስር ገፅ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መሰረት ከዚህ በፊት በአስተማማኝ ትርፍ ላይ የነበሩና አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ችግር ምክንያት ይበልጥ አትራፊና ውጤታም ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉ ሁለት የኢንቨስትመንት ካምፓኒዎች ጠቁሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትስስር ገፁ በኦንላይን ቴክኖ ሎጂ አማካኝነት የኤሌክተሮኒክ ግብይት በሰዎች ዘንድ በየዕለቱ እየጨመረ ቀጥሏል። ይህንኑ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ካምፓኒዎች እንደአሸን እየፈሉ መምጣቻውን ጠቅሷል። በቴክኖሎጂ ህዋ ውስጥ አሸናፊ የሚሆኑት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡና ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ይበልጥ የሚያፋጥኑ ካምፓኒዎች ናቸው ሲልም ትስስር ገፁ ያትታል።
ትስስር ገፁ እነዚሁ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ካምፓኒዎች በዚሁ የጤና ቀውስ ወቅት እንኳን ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ ተጨማሪና የግድ የሚሉ የንፅሕና ህጎችን በፍጥነት ወደ ኦንላይን ግብይት ሊቀይሩ ይችላሉ ይላል። አሁን ባለው ሁኔታም በተለይ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሥራ ይበልጥ የተለመደና ከቤት ሆኖ የመሥራት ልምድ በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ የገጠመው የጤና ቀውስ ካለፈ በኋላም የሚቀጥል ይሆናል ሲል ያብራራል።
ለእዚህም በዚህ ቀውስ ውስጥ ከፍተኛ የሽያጭ አገልግሎት ጫናን እያስተናገዱ የሚገኙትንና የምርትና አገልግሎታቸው ፍላጎት በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን ሁለት ጣራ የደረሱ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ካምፓኒዎችን በምሳሌነት ይጠቅሳል። ከእነዚህ የቴክኖ ሎጂ ኢንቨስትመነት ካምፓኒዎች ውስጥ አንዱ የኤሌ ክትሮኒክ ምርትና አገልግሎት ሽያጭን በማቀላጠፍ የሚታወቀው አማዞን መሆኑን የትስስር ገፁ የጠቀሰ ሲሆን ‹‹የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ አይነኬ ከተባሉ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ውስጥ አንዱ ነው›› ሲል ገልፆታል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተከሰተው የወቅቱ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ የዓለማችን ህዝቦች የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስረዓትን በብዛት እንዲጠቀሙ በማስገደዱ ሁኔታው አማዞንን ሌሎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከገቡ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ካምፓኒዎች መንጥቆ አውጥቶታል። በተለይ ደግሞ በዚህ ክስተት የዓለም ኢኮኖሚ ቁልቁል እየተንሸራተተ ባለበትና የሥራ አጥ ቁጥር ሰማይ በነካበት በአሁኑ ወቅት ብዛት ያላቸው ተጠቃሚዎች መሰረታዊ የጤናና የቤት ፍጆታ እቃዎችን ለመግዛት ወደ አማዞን ማማተራቸውን ተከትሎ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ አማዞን 175 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለመቅጠር ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁን የትስስር ገፁ መረጃ ያመለክታል። ከአንድ ወር በፊትም በተመሳሳይ 100 ሺህ የሚጠጉ ጊዜያዊና ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥሯል።
እያደገ ከመጣው የኤሌክሮኒክስ ግብይት ፍላጎት በተጨማሪ ወረርሽኙ አብዛኛዎቹን ሰዎች ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ የሚያስገድድ በመሆኑና ካምፓኒዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን እንዲያስፋፉ ጫና ውስጥ የሚከት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአማዞን ካምፓኒ የድረ ገፅ አገልግሎትም ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚኖረውም በመረጃው ተጠቁሟል።
ይህ አዲስ የኢኮኖሚ እውነታ አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ በአማዞን የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ስቶክ ካምፓኒ ኢንቨስተሮች በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህም በተለይ አማዞንን ከአስር ከፍተኛ ትርፍ ከሚያገኙ ካምፓኒዎች ውስጥ አንዱ ያደርገዋል። አማዞን እስከአሁን ባገኘው ገቢ ብቻ ገበያውን በአንድ ትሪሊየን ዶላር አሳድጎለታል። ባለፈው ሳምንትም የአማዞን የገበያ ድርሻ 2 ሺህ 333 በመሆን በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ከፍተኛ ለመሆነ በቅቷል።
ሌላው በዚህ የጤና ቀውስ ውስጥ በስኬት የሚቀጥልና ከቀውሱም በኋላ ስኬቱን ሊያስቀጥል የሚችልው የቴክኖሎጂ ኢንቨስትምንት ካምፓኒ ኔትፍሊክስ መሆኑን ትስስር ገፁ የጠቆመ ሲሆን፤ ካምፓኒው አሁን እያገኘ ያለው ገቢ በዚህ ቀውስ ውስጥ አሸናፊ ያደርጋዋል ብሏል። በዚህ ቀውስ ውስጥ ኔትፍሊክስን ለስኬት ያበቃው የኮቪድ 19 የተለመደ የመከላከያ ዘዴ የሆነውን የ‹‹እቤት ቆዩ›› ፅንሰ ሃሳብን በመከተል ሲሆን፤ ደምበኞች በዚህ የኤሌክትሮኒክ የገበያ ትስስር ገፅ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ምርትና አገልግሎቶችን ለመግዛት አጥፍተዋል።
በዚህ ዓመት አስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስም የኔትፍሊክስ የገበያ ድርሻ 34 ከመቶ የደረሰ መሆኑን ትስስር ገፁ አመልክቷል። ይህም ኔትፍሊክስን የሚገለገሉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል ሲልም ተስስር ገፁ አክሏል።
በኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት ምርቶችን እና አገልግሎቶችን የመጠቀም ባህል እምብዛም ያልዳበረ ቢሆንም፤ አሁን አሁን አንዳንድ የኦን ላይን ሽያጭ አገልግሎት የሚሰጡ ትስስር ገፆች እያቆጠቆጡ መጥተዋል። ስረዓቱን በተፈለገው መጠን ለማስኬድ የሚያስችል የቴሌኮም መሰረተ ልማት አለመገንባትና ህብረተሰቡ በዚሁ የኤሌክተሮኒክስ ግብይት ስረዓት የመጠቀም ባህሉ ዝቀተኛ መሆን ደግሞ በዚህ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ድርጅቶች እንዳይገቡ እያደረጓቸው ካሉ ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳል።
የሆነው ሆኖ ግን የአሊባባ ግሩፕ መስራችና ባለቤት ቢሊየነሩ ጃክማ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የተደረገላቸውን ጥሪ በመቀበል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የአይ ሲቲ ፓርክን ጎብኝተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ታዲያ ጃክማ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ይኸው ማዕከል ሲገነባም በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ተለያዩ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ሲፈፅሙ በቴክኖ ሎጂ የታገዘ የሎጀስቲክ አገልግሎትና የሰለጠነ ባለሞያ ለማግኘት ያስችላቸዋል ተብሎ ይገመታል።
በአሊባባና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተመሰረተው ይህ አዲስ አጋርነት በእስያ ቻይናና ማሌዢያ፣ በአውሮፓ ቤልጂየም እንዲሁም በአፍሪካ ሩዋንዳ ተመስርተው ስኬታማ ከሆኑት ማዕከላት በመነሳት መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከሩዋንዳ ቀጥሎ በኤሌክትሮኒክ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል ያላት ሁለተኛዋ አፍሪካዊ አገር ያደርጋታልም ተብሏል።
ዓለም በእንዲህ አይነት ቀውስ ውስጥ ስትዘፈቅ ኢንቨስትመንቱን ጨምሮ ኢኮኖሚውን ከጉድ ሊታደጉ የሚችሉት እንዲህ ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስረዓት በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱን ስርዓት በስፋት በመዘርጋት ተጠቃሚ ለመሆን በተለይ ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠውን የኔትወርክ አገልግሎት ማሻሻልና የኔትወርክ መሰረተ ልማቱን መስተካከል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
አስናቀ ፀጋዬ