ኢንጂነር ፎዚያ ሙህሲን ይባላሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፤ ለ10 ዓመታት ያህል በተለያዩ የምግብ ፋብሪካዎች ውስጥ ከጀማሪ ቴክኖሎጂስትነት እስከ ምርት ክፍል (ፕሮዳክሽን ዲቪዥን) ኃላፊነት ድረስ በተለያዩ የሙያ ድርሻዎች አገልግለዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት ደግሞ በምግብ ኢንጂነሪንግ ነው። በማሰልጠንና በማማከር ስራ ላይ ከአንድ ደርዘን በላይ ለሆኑ ዓመታት ሰርተዋል።
ኢንጂነር ፎዝያ በአሁኑ ወቅት የማነቃቂያ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃሉ። ምግብን ከሙያ አንጻር ያስተምራሉ፤ ያሰለጥናሉ፤ የምግብ ሳይንስን በሙያዊ አይን ይተነትናሉ፤ በዚህ ሂደትም ከ23 ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል።
አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር ተያይዞ ያልበሰሉ ምግቦችን አትመገቡ ሲባል ይሰማል። የኮሮና በሽታን መቋቋምን ጨምሮ በሽታ የመከላከል አቅምን ማሳደግ የሚችሉ ምግቦች ምን አይነት ናቸው? ከዚህ በተጨማሪ ወቅቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩበት እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ የረመዳን ጾም የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑ የማህበረሰቡን ጤና ሊጠብቅ የሚችለው የአመጋገብ ሂደት ምን መምሰል ይኖርበታል? ለሚሉት እና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢንጂነር ፎዚያ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉት፣ የኮሮና ቫይረስ በባህሪው ሕይወት የለውም፤ ቅርጹ(ስትራክቸሩ) ከላይ ያለው ሽፋኑ ስባማ(ፋት) ነው። መሐሉ ደግሞ ፕሮቲን ነው። ስለዚህ ስባማነቱን ሰባብሮ የሚያሟሟ ነገር መጠቀም ሲቻል ተሰባብሮ ይሞታል፤ በሳሙና ቶሎ ቶሎ ታጠቡ መባሉም ለዚህ ነው። የቫይረሱን የውጪውን ቅባታማነት በሳሙናው ሲታጠቡት ይፀዳል።
አልኮልም በባህሪው ቅባታማ የሆነን ነገር የማሟሟት አቅም አለው። በመሆኑም ቫይረሱን ሰባብሮና አሟሙቶ ያስወግዳል። በመሆኑም ሕብረተሰቡ አልኮሆልን ይጠቀም ዘንድ በባለሙያዎች የሚመከረው በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ ኢንጂነር ፎዚያ።
ለጤናማ ሕይወት ከአትክልትና ፍራፍሬ በላይ የሚመከር ሕክምና የለም። ጥንቃቄ ማድረጉ ለአትክልት ብቻ አይሰራም። ማንኛውም ነገር በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት አስረድተዋል።
ኮሮና ቫይረስ በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ አትክልትን ጨምሮ ሌሎች ነገሮች ተገዝተው ቤት ከደረሱ በኋላ ከመጡበት ፌስታል ጀምሮ በፈሣሽ ሳሙና መጽዳት አለባቸው። ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱን ነገር ለመንካት እጅን መታጠብ ተገቢነት እንዳለው ገልጸው፣ ይሄን ማድረግ ከኮሮናም በፊት በምግብ ፋብሪካዎች የሚተገበር አሰራር እንደሆነ ተናግረዋል። ይሄን አለማድረግም እንደኮሮና ሁሉ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የሰውነት በሽታ የመከላከልን አቅም ለማሳደግና ጤነኛ ሕይወት እንዲኖረው የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ያለ አትክልትና ፍራፍሬ የሚታሰብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለመመገብ ኮሮናን መፍራት አያስፈልግም። ማህበረሰቡ አሁን ከሞላ ጎደል እጅን በተገቢው አለመታጠብ እንዴት አደገኛ የሆነ ብክለትን ሊያመጣ እንደሚችል ግንዛቤውን እንዲያሳድግ አጋጣሚው ተፈጥሮለታል። ቀጥታ ሳይበስሉ ሊበሉ የሚችሉ አትክልቶች በፈሳሽ ሳሙና መታጠብ አለባቸው። ለዝግጅት የሚያስፈልግ እያንዳንዱ ቁሳቁስ ወዲያው እየታጠበና ንጽሕናው እየተጠበቀ ሰላጣም ይሁን ቆስጣ ሌሎች አትክልቶችም መመገብ ተገቢነት እንዳለው ተናግረዋል።
ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚመጣ የትኛውም በሽታ በረዥም ጊዜ የሚከሰት ነው። በመሆኑም አሲዳማነትን በሰውነት ውስጥ ሊጨምሩ ከሚችሉ የአመጋገብ ልምዶች መላቀቅ ያስፈልጋል። ሰዎች በመደበኛው የአመጋገብ ሂደት ከ80 በመቶ እስከ 90 በመቶ በሚደርስ ሁኔታ አትክልትና ፍራፍሬ በሰውነታቸው ውስጥ መኖር እንደሚገባ ይመከራል ብለዋል።
ኢንጂነር ፎዚያ ሲያብራሩ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ቀለማቸውን ሊያጡ አይገባም። ቀያዮች እንደ እንጆሪ፣ ሀባብ፣ ቲማቲም፣ ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው እንደ ካሮት፣ ዱባ ያሉ ወይን ጠጅ ከለር ያላቸው እንደ ጥቅል ጎመን፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ወይን፣ ነጭና የተለያዩ ቀለም ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች እንደቀለማቸው የያዙት ንጥረነገር ይለያያል። ቀለማቸውን እንደጠበቁ መሆናቸው የምግብ ይዘታቸውን እንደጠበቁ መሆናቸውን ያሳያል፤ አልተጎዱም ማለት ነው። ለብ ካለ ውሃ በላይ መብሰል አይገባቸውም።
የውስጥ አካልን በምግብ ማጽዳት ይቻላል፤ ሰውነት የራሱ ቋንቋ አለው፤ ኢነርጂ ይባላል። ሰዎች ሰውነታቸው ጉልበት የሚፈጅበት ምግብ በሚበሉበት ወቅት ማጽዳት ያዳግተዋል፤ ጊዜ የለውም። ለምሳሌ፡- ትልቅ ድግስ በቤት ውስጥ ኖሮ ሰዎች እስኪሸኙ ድረስ ቤትህን ከስር ከስር ማጽዳት አትችልም፤ ሰውነትም ልክ እንደዚህ ማለት ነው። ካልማቋረጥ ምግብ የሚበላ ከሆነ በዚያ ላይ ምግቡ ኃይል በጣም የሚወስድ እንደ ስጋ እና የበሰሉ ምግቦች ከሆኑ ሃይል ይፈጃሉ። አንድ ወፍጮ ጤፍና ባቄላ በእኩል ጉልበት መፍጨት አይችልም። አትክልቶች ሰውነት ለመፍጨት በጣም ቀላል ናቸው። ፍራፍሬዎች ደግሞ በጣም በቀላሉ ይፈጫሉ፤ ጁስ ሲሆኑ ደግሞ በጣም ይቀንሳል። ሰውነት የሚያወጣው ጉልበት እንደሚቀንስ አስረድተዋል።
ጾም ለጤና ምን ፋይዳ ይሰጣል?
ውሃ በሰውነት ውስጥ ለመፈጨት ምንም ጉልበት አያስፈልገውም። ጾምም እንደዚሁ ነው። በጾም ወቅት ሰውነት የሚያወጣው ጉልበት ባለመኖሩ ያለውን ጉልበት አሟጦ ለጽዳት እንደሚያውለው ያስረዳሉ።
ጾም መጾም ለመንፈሳዊ ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ለሰውነት ጤናማነት እጅግ አስፈላጊ ነው። ሰውነት በጽዳት ውስጥ ይሆናል። እያንዳንዱ የሆድ እቃ ለእድሳት ጊዜ ያገኛል፤ ይታደሳል ሌሎችም የዚህ አይነት ተግባራት ይከናወናሉ። በተጨማሪም በሰውነት ውስጥ የደም ዝውውር እንዳለ ሁሉ የፈሳሽ ዝውውርም አለ፤ (ሊፋቲክ ሲስተም) ይሰኛል፤ እያንዳንዱ ሴል የሚያወጣቸው አሲዳማ ቆሻሻዎች ይወገዳሉ፤ ከባድ ከባድ ምግቦች የሚያዘወትር ሰው እነዚህ አሲዳማ ፍሳሾች ወፍረው በመዝለግለግ ቶሎ ቶሎ እንዳይወገዱና አሲዱን ይዘው እንዲቀመጡ በማድረግ መሰናክል ይሆናሉ። በዚህ የተነሳ በሰውነት ላይ የመለብለብ ስሜት ይፈጠራል፤ ይሄ ደግሞ የበሽታ መነሻ ነው።
በተቃራኒውም አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚመገብ ሰው አሲዳማ የሆኑ ቆሻሻዎች በፍጥነት ከሰውነት እንዲወገዱ ያደርጋል። ሰውነትን ‹‹አልካላይዝድ›› ያደርጋል። ጤናማ ሰውነት ሊኖረው የሚገባው ደካማ ‹‹አልካላይዝድ›› ሲኖር ነው። በሰውነት ውስጥ አሲዳማነት በሚጨምርበት ጊዜ በሽታን የመከላከል አቅም አይኖርም፤ ከታመሙም ቶሎ ማገገም ያቅታቸዋል፤ በቀላሉ በጉንፋን ይጠቃሉ። አትክልትና ፍራፍሬዎች የማይመገብ ሰው በረዥም ጊዜ ሂደት አሲዳማነት ይገጥመዋል።
ሰዎች ጾማቸውን ውለው ስጋና መሰል ከባድ ምግቦች ሲበሉ ከባድ ድካም ይሰማቸዋል። ምክንያቱም ሰውነታቸው ለመፍጨት ሃይል ይወስዳል። ለዚህ ነው እንደ ቴምር፣ ውሃ፣ አትክልትና ሾርባ ያሉ ቀለል ያሉ ምግቦች መመገብ የሚያስፈልገው። ይሁን እንጂ ስጋ፣ ሩዝ፣ ወጥና የበሰሉ ምግቦች ወዲያው መመገብ አያስፈልግም። ሰዎች ከጾም በኋላ አመጋገባቸው ማስተካከል ካልቻሉ ያጸዱትን ሰውነት እንደገና ማቆሸሽ ነው የሚሆነው። ለዚህም ቀመሩ በጣም ቀላል ነው፤ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ ነው።
እንደማጠቃለያ
ኢንጂነር ፎዝያ እንደገለፁት መድሐኒት ላተገኘለት ኮሮና ወረርሽኝ መፍትሔው አትክልትና ፍራፍሬዎች አዘውትሮ መመገብ ነው። የሰውነት የመከላከል አቅም ያድጋል። ይህ ሲሆን በሽታን መቋቋም ይቻላል። ሰዎች ከጾም በኋላ አመጋገባቸው የሚቀየረው በድንገት ነው። በዚህ የተነሳ ሰውነት የበረዶ ዶፍ ዝናብ እንደወረደበት ይቆጥረዋል። አመጋገባቸውን ባስተካከሉ ቁጥር በጉበት፣ በኩላሊት፣ በጨጓራ እና በሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ላይ ያለው ጫና ይቀንሳል፤ ጤናማ ሆነው በተገቢው መስራት ይችላሉ። አሁን ላይ የሚስተዋሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደአሸን መፍላት ዋናው ምክንያት ከአመጋገባችን በሚፈጠሩ ስህተቶች ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ሙሐመድ ሁሴን