በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለውን የሀብት ክፍተት በዘላቂነት ለማጥበብ የሀገር ውስጥ ቁጠባን አጠናክሮ ማስቀጠልና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ቀጣይነት ላለው የቁጠባ ሥርዓት አለመዳበር ምክንያቱ ምንድነው? መፍትሄውስ?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ቁጠባ እድገቱ ብቻ ሳይሆን መጠኑም ዝቅተኛ ነው። እስካሁን ቁጠባ ሃያ አምስት በመቶ አልደረሰም። ይሄ ማለት ከ75 በመቶ በላይ ምርት ለፍጆታ ይውላል ማለት ነው።
በዓለም ላይ ሶስት አይነት የእድገት ደረጃዎች አሉ የሚሉት ዶክተር አጥናፉ በግብዓት፣ በውጤታማነትና በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት እድገት የተመሰረተው በግብዓት ላይ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ግብዓት የሰው ሃይልና ካፒታል ነው። በቂ የሰው ሀይል አለ፤ ካፒታል ግን የለም። ካፒታል ለመፍጠር እንደግብአት መጠቀም የሚቻለው ቁጠባን ቢሆንም ያለው ቁጠባ በሁለት ምክንያቶች የዳበረ አለመሆኑን ያብራራሉ።
የመጀመሪያው መሰረታዊ ፍላጎትን ያለማሟላት ችግር ምርትን ወደ ፍጆታ ስለሚወስደው ለመቆጠብ ፍላጎት ያለው ቢኖር እንኳ አይችልም። በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት ምርታማነትን መጨመር ቀዳሚው አማራጭ ይሆናል። ሁለተኛው በሀገሪቱ ያለው የቁጠባ ባህል ያልተገራ መሆን ነው። ይህንንም በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
አንደኛ በመንግስት ተቋማት ከፍተኛ አባካኝነት አለ። ለምሳሌ መንገድ የሚሰራው ተቋም ስራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለውሃ፣ ለመብራት ለሌላም በሚል የተሰራው መንገድ መልሶ እንዲፈርስ ይደረጋል። ይሄ ካፒታል የሚበላ በመሆኑ ተጨማሪ ወጪ በመጠየቅ ቁጠባውን እየሸረሸረው ይመጣል።
ሁለተኛ በመንግስት ተቋማት ያለው የሀብት አጠቃቀም የቁጠባ እንቅፋት ነው። ለስራ የሚያገለግሉ እቃዎች መሟላት ቢኖርባቸውም አርባና ሀምሳ ኢንች ቴሌቪዥንና ሌሎች የቢሮ እቃዎችን በውድ ዋጋ መሙላት፣ በጀት እንዳይመለስ በሰኔ መጨረሻ የሚፈጸሙ ግዢዎች፣ ለትናንሽ ስብሰባ የተጋነነ ወጪ፣ ባለስልጣናት የሚጠቀሟቸው መኪናዎች ውድ መሆንና አጠቃቀማቸው ሁሉ ቢፈተሽ በርካታ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው።
ለምሳሌ በጃፓን የቶዮታ ኩባንያ ትልቁ ሲሆን የአስተዳደሩ ቢሮ ግን ምንጣፍ የለውም። እዚህ ሹመት ሲሰጥ መኪናን ጨምሮ ለመደበኛ ስራ የሚሟሉት ቁሳቁሶች በጣም ብክነት ያለባቸው ናቸው። በዚህ የተነሳ ኢኮኖሚው ካፒታል የሚፈጥር ሳይሆን የሚበላ ይሆናል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሙስናውም ሌላ ቁጠባን የሚጎዳ ተግባር ነው። በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ወጪን በመቀነስ ቁጠባውን ማሳደግ መቻል አለበት።
በግለሰብ ደረጃም ቁጠባን መልመድና ከሚተርፈው ብቻ ሳይሆን ካለውም ላይ ቀንሶ የመቆጠብ ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል። በአርሶ አደሩ ዘንድ የምርት ብክነት፣ የሃይማኖትና ባህላዊ በአላት አስታኮ ስራ አለመስራት መቀነስ ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ መስራት ይጠበቃል።
በየቤታችን የውሃ፣ የመብራት ፍጆታችን አባካኝ ነው። በጀርመን የኤሌክትሪክ ሃይል ለመቆጠብ ለአንድ ሰአት ህዝቡ እንዲያጠፋ ይደረጋል። ከአንድ ሰአት በኋላ ተቋሙ ያዳነውን ብር በመግለጽ ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለም በተግባር እንዲታይ ይደረጋል። የዚህ አይነት ስራ መስራት ይጠበቃል። አዳዲስ ሃይል ማመንጫ ከመገንባት ሃይል በመቆጠብ ሌላ ማመንጫ የመገንባት ያህል ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ።
«የቁጠባ ባህላችን በአብዛኛው የተንተራሰው በባህላዊ መንገድ መሆኑ፣ የገቢ ማነስና የዋጋ ግሽበት ለቁጠባ አለማደግ ምክንያት ናቸው፤ ቁጠባ ሲያንስ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል» ያሉን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ኑረዲን ጁሀር ናቸው። አቶ ኑረዲን እንደሚያብራሩት እንደ እቁብ ያሉ ባህላዊ የቁጠባ ሥርዓቶች ወለድ የሌላቸውና ካፒታል ለማፍራት የሚጠቅሙ አይደሉም። በመሆኑም በባህላዊ መንገድ ያለውን ቁጠባ ወደ ዘመናዊ ማምጣት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ መንግስት እየተጠቀመባቸው ያለ የጋራ መኖሪያ ቤት ቁጠባና የቦንድ ግዢ የመሳሰሉትን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። አንድ ሰው በቆጠበው ገንዘብ ቤት ሊያገኝ እንደሚችል ካረጋገጠ የወለድ መጠኑ ዝቅተኛ ቢሆን እንኳ ቁጠባውን አያቋርጥም ፤ በልማትም ውጤቱን የሚያይ ከሆነ ተመሳሳይ ነው።
ሁለተኛው ለቁጠባ አለማደግ ምክንያት የወለድ መጠንና የኑሮ ውድነት አለመመጣጠን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የኑሮ ውድነቱ ለሚቆጥበው እንዲያተርፍ እድል አይሰጠውም። ለመቆጠብ የሚችል አልያም ካለው ላይ አብቃቅቶ እቆጥባለሁ የሚል ቢኖርም የኑሮ ውድነቱ ከወለዱ በላይ ስለሚሆን ተጠቃሚ አይሆንም። አሁን ያለው የወለድ ክፍያው ሰባት በመቶ አካባቢ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱ ግን እስከ አስራ አምስት በመቶ ይደርሷል። የወለዱን እጥፍ እንደማለት ነው። በዚህ ሂደት ገንዘቡ ቢቀመጥ የመግዛት አቅሙ በእጥፍ ይቀንሳል። በመሆኑም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድና ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ የዋጋ ማረጋጋት ስራ በመስራት ከወለዱ ጋር ተመጣጣኝ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል ቢኖርም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም መቀነስም አንዱ ለቁጠባ ተግዳሮት ነው። ይሄ ሲፈጠር አንዳንዱ በጥቁር ገበያ ገንዘቡን ለመያዝ ይሞክራል፤ ይሄ ገንዘብ በየግለሰቦች እጅ ስለሚኖር በባንክ የሚቀመጠውንና ለኢንቨስትመንት የሚውለውን ቁጠባ ይጎዳል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከወለድ ነጻ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልገውም ህብረተሰብ ብዙ ነው። ስለዚህ በባንኮች በተደራቢነት ከተጀመረው አገልግሎት በተጨማሪነት ራሱን የቻለ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ቢፈጠር፤ ከወለድ ጋር የተያያዘ ስራ መስራት የማይፈልግም ቀጥታ ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገባ ማድረግ የቁጠባ ባህልን ያበረታታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከፕላንና ልማት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 በጀት አመት የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 34 ነጥብ አንድ በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በበጀት አመቱ ይደረስበታል ተብሎ ከተተነበየው አመታዊ ግብ አንፃር ሲታይ የአምስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ያነሰ ነው። በአንጻሩ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ቁጠባ ምጣኔ በ2009 ከነበረበት የ22 ነጥብ አራት በመቶ በ2010 በጀት አመት ወደ 24 ነጥብ ሶስት በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም በቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው የሀብት ክፍተት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 10 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ካለፉት አመታት አፈጻጸሞች አኳያ ሲታይ የመጥበብ አዝማሚያ አሳይቷል።
ምሁራኑ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለው ቁጠባ ኢንቨስትመንቱን ሊሸከመው አይችልም። በመሆኑም መንግስት ወጪውን መቀነስ፣ ግለሰቦችም ከሚተርፋቸው ሳይሆን ካላቸው ላይ መቆጠብ፣ እንደ እቁብ አይነት ባህላዊ የቁጠባ ዘዴዎችን ወደ ዘመናዊነት መለወጥ እንዲሁም ህዝቡ ቆጥቦ የልማቱ ተጠቃሚ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባል። ይሄ ሲሆን ቁጠባ ያድጋል፤ ይበረታታል። በዚህ መልኩ እየቆጠብን በራሳችን ወጪ ኢንቨስትመንቱን እያስፋፋን ካልሄድን በየዓመቱ ከየትምህርት ተቋማቱ እየተመረቁ የሚወጡትን ማስተናገድ አይቻልም። ይሄ ማለት የሀገሪቱ ሀብት ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል። ይሄን ተከትሎ ፖለቲካዊ ቀውሶች መፈጠራቸው አይቀሬ ይሆናል ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ