ዓለም ለኛ ምቹ እንድትሆን ካልገራናት በቀር በራስዋ ምቹ ሆና አትገኝም። የሚገጥመንን መጥፎ አጋጣሚ ወደ ጥሩ የመለወጥ ልምድ ካለን፤ ችግር ወደኛ መቅረቡ እድል ነው። ችግሩ ሞርዶን፣ አስተካክሎና በፊት ከነበርንበት ሁናቴ ቀይሮ አዲስ ገፅታ እንድንላበስ አዲስ አስተሳሰብና ስብዕና እንድንወርስ ሊያደርገን ይችላል።አዎ የራሳችን ዝግጁነትና ችግሩ ወደ በጎ ለመለወጥ ያለን ፅናት እንጂ ችግሩ ስል ሆነን ወደምንፈልገው መወንጨፍ እንድንችል የሚያደርገን መሣሪያ ሊሆን ይችላል።
ስለቀረበን ችግር የምናይበት መነፅር ብሩህነትና ፀለምተኝነት ወይም የእኛ አተያይ እንጂ ችግሩ በራሱ የተለየ መፍትሄ እንድናፈልቅ የሚያደርገን መንስዔ ነው። ወዳጆቼ የምርምር ታሪኮችን መርምሩ ከዚያ ላይ ችግርን ወደ መፍትሄ የለወጡ ጠቢባን ተሞክሮ ታገኛላችሁ። ዓለም ላይ የተፈጠሩት ትልልቅ ግኝቶች መነሻቸው ችግር ነው። ምርምር ለማድረግ ችግር አስፈላጊና ዋንኛ ጉዳይ ነው። ያለ ችግር የሚጠነሰስ ጥናትና ምርምር የለም። የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚሰማ አልያም ደግሞ የሚያሰጋ ችግር ለምርምርና ለአዲስ ግኝት መነሻ መሰረት ነው።
በዓለም ላይ ለሰው ልጆች ስልጣኔ መሰረት የሆኑ ግኝቶች ምንጫቸው ችግር ነው። ጭለማን ስለፈራ የኤሌትሪካ አምፖልን የፈጠረው ቶማስ ኤድሰን እና በዘመኑ የተፈጠረ ወረርሽኝ እቤት አውሎት የመሬት ስበት ሕግን ተመራምሮ ያገኘው አይዛክ ኒውተን ለዚህ ትልቅ ማሳያዎች ናቸው። የመጣውን ክፉ ገጠመኝ መቀየርና ወደራሳችን ምቹ ገጠመኝ አድረጎ መጠቀሙ ባንወድ ግድ ነው። ምክንያቱም ክፉው ነገር ወደኛ መቅረቡ አልቀረም። አሁን ከኛ የሚጠበቀው ይሄን ወደ መልካም አጋጣሚ እንዴት ልቀይረው ብሎ ማሰብ ለዚያም መዘጋጀት ነው።
አሁን ብዙ መሮጥን የሚገታ አሳሪ ቀርቦናል። ብዙ ቦታ ላይ መድረስን እንዳሻ መምነሽነሽን የሚያቅብ ሁኔት ከፊታችን ተደቅኗል። ይህ ጊዜ በጥንቃቄ የምናልፈውና በብልሀት የምንሻገረው መሆኑ እርግጥ ነው። ለዚህም ነው የዓለም አንድ ሶስተኛው ህዝብ ከእንቅስቃሴው ተገቶ፤ ስራና ትምህርቱን አቋርጦ እቤቱ መቀመጥ ግድ የሆነበት። የሰው ልጅ ዛሬ ላይ የገጠመው ፈተና ሊያመልጥ እራሱን ነጥሏል። እናም ያለዕረፍት ወደፊት ሲገሰግስ ያለ ፋታ ሲተም የነበረበት ሁናቴው ተቀይሮ እራሱን በጥሞና የመመልከቻ ጊዜ ባይወድም አግኝቷል። አሁን ፈተናው ሆኖ የቀረበውን ገጠመኝ እንዴት በድል ልወጣው፤ ወደ መልካም አጋጣሚስ እንዴት ልለውጠው ብሎ ማሰብ ይኖርበታል።
መምህር ነህ ወዳጄ ታስተምርበት የነበሩ መንገዶች ስልቶችን ለውጦ እንደነበር መርምር። ብዙ ፍሬ አፍርተህ ከሆነ እሱን ለማሳደግ እራስህን አዘጋጅ። ማስተማርህ ግን ያለ ፍሬ የዘለቀ ከነበር እራስህን መርምር የተሻለ ሰው ለመሆን ጣር እራስህን ለውጠህ ሌሎችን ለመለወጥ ትጋ። የዓለምን ከንቱነት አይተህ የለ፤ አንተ ግን ውል ያለው ግዙፍ ሰው ሁን። አንድ በጎ ተፅዕኖ አሳድረህ ለማለፍ ሞክር።
ተማሪ ትሆን ይሆናል እቤትህ ቁጭ ብለህ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ መርምር፤ መጽሐፍትን አዘውትረህ አንብብ። ያሳለፍከው ከንቱ ጊዜ ከነበር አሁን አካክስ። ችግሩን ወደ በጎ ለውጠህ የተሻለ ለማደረግ ሞክር። ነጋዴ ከሆንክ የነገድከው ንግድ እራስህንና ማህበረሰብህ ጠቅሞ ከነበረ ውጤቱን ተመልከት። ለሀገርህ ኢኮኖሚ አዎንታዊ ሚና አበርክተህ ከነበር አብዝትህ ተደሰት። ይህ የእረፍት ጊዜህ ነውና ይበልጥ በመልካም መንገድ ለመበልፀግ እቅድህን አውጣ። አልያም ደግሞ ማህበረሰብህን ጎድተህ እራስህን ለመለወጥ ብዙዎችን አክስመህ ከነበረ አሁን ሊቆጭህ የሚገባ ጊዜ ነው። ወገን ማለት ምን እንደሆነ ስለወገን ብለው እራሳቸውን ከሰጡ ሰዎች ጋር እራስህን አነፃፅር ያኔ በውስጣዊ ስብዕናህ የጎደልክ መሆንህ ይገባሃል። በዚህ አጋጣሚ ራስህን አስተካክለህ በቀጣይ ህይወትህ ሰው ሆነህ ስለ ሰው ለመኖር አቅድ፤ ይህ ጊዜ እኔን ለመግራት የቀረበኝ ነው በል።
ሐኪም ነህ? ወዳጄ ይህ ጊዜ ላንተ መዝመቻ ነው። ከመጣው ጠላት ጋር ፊት ለፊት ሆነህ የምትጋፈጥበት ለወገንህ አለኝታነትህ የምታረጋግጥበት ተፋልመህ ድል የምትነሳበት ወሳኝ ዘመቻ። እራስህን ዝግጁ አድርግ። አንተ የምታደርገው አገርን የማዳን ህዝብን የመታደግ ጥረት ብዙዎች ዋጋ የሚሰጡት ተግባር ነውና ይህንን አጠንክር።
ሁሉም በየራሱ እራሱን መመልከት ማንነቱን መመርመር ያለበት የጥሞና ጊዜው ነው። እንደ ግለ ሰብ እራስን ለመለወጥ በግል ጥረት ማድረግ ይገባል። ከዚያ ባለፈ እንደ ማህበረሰብም አንድ አንድ አንድ ተገቢ ያልሆነ ልማድ ተፀናውቶናል ያ በዚህ አጋጣሚ መገራት ይኖርበታል። ይህ ልማድ እኛን በትክክል ወደፊት ሊያራምድ በአንድነትም ሊያቆም አይችልምና ሊታረም የሚገባ ነው። እኛ የሚለው ቋንቋችን በበጎውም በመጥፎውም የምንጋራው ሊሆን ይገባል። ጥሩ ጥሩው የኛ መጥፎው የእነሱ የማለት ክፉ አባዜያችን ሊቆም ይገባል።
ስለሚፈጠረው ችግር ሁሉ እራሳችንን አርቀን የምንኮንነው ሌላውን ነው። ጥፋት ሲሆን የእነሱ ውዳሴና ምስጋና ሲሆን የኛ የማድረግ አባዜ አልተላቀቀንም። ልምድ ሆኖብን ስለሚፈጠረው ችግር አልያም ጉዳት እኔ ምን አድረኩን ብለን እራሳችን ከመመርመር ይልቅ “ለምን አላደረጉም?” እናስቀድማለን። ለምንድነው እንደዚያ ያልተደረ ገው? ብለን ከመጠየቃችን በፊት እኛ ለንም እንደዚያ ለማድረግ አልሞከርንም ብለን እራሳችንን መጠየቁ ይከብደናል። ይህ ደግሞ ሁሌ ወቃሽና መፍትሄን ፈጣሪ ከመሆን የተዘናጋ ተቺ አድርጎናል።
የተገራ ተቃውሞና ትችት በምክንያት የተገራና መፍትሄ አመላካች ከሆነ መንገድ ነው። ጥሩ ነቀፋ ስህተትን ማቅኛ የተወላገደን መግሪያ ጥሩ መሳሪያ ነው። ነገር ግን መስመርን የሚያስት ምክንያት የሌለው ትችትና መፍትሄ አማላካች ያልሆነ ሽርደዳ እርባና ቢስ ነው። ጉዳዩ መስመር እንዲዝ ፈጽሞ ሊያደርግ አያችልም።
እራሳችንን ባነፃ መልኩ ሌላውን መኮነን እኛ ታዛቢ ሆነን ሌላው መተቸት ሻገር ብለን “እዲህ የሆነው እንደዚያ ስላልተደረገ ነው” የሚል የሁነትና ውጤታቸው ተንታኝም ሆነናል። ነገር ተቀባብሎ ያለ ምክንያት መፈረጅ እውነታን ትቶ ስሜትን መከተል ተላምደናል። ይሄ ደግሞ ከመፍትሄ ያርቃል። ስሚሆነው እያዩ እነዲህ አድርጉ ሁሌም እነዲህ እናድርግ ከሚለው ዝቅ ያለ ውጤት ያስገኛ። ትችታችን ልክ ሲኖረው ያንፃል፤ ይገራልም።
አዎን አስፈሪ ችግር ተጋርጦብናል። ነገር ግን ችግርን ወደ በጎ መለወጥ ፈተናን ወደ ስኬት መቀየር ግድ ይለናል። አተያያችንን ማስተካከል ከችግር መፍትሄን ለማፍለቅ መዘጋጀት ይኖርብናል። ካልሆነ ችግሩ ራሱ ተረማምዶብን ብዙ አጉድሎብን ያልፋል። እኛ የችሩ መፍትሄ አመላካችና ወደ በጎ ገጠመኝ ለውጠን ችግሩን ድል እናድርገው። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/ 2012
ተገኝ ብሩ