የኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም የፍርሃትና የጭንቀት ምንጭ ከሆነ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ወራትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጓል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ በበሽታው ተይዘው በበሽታው ከመሰቃየት ባለፈ እየተሰቃዩ ያለበት ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ እስካሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ለበሽታው መድሃኒትም ሆነ ክትባት ሊገኝለት እንደሚችል ተስፋ የመስጠት አመላካች ነገር አለመኖሩ ነው። ከዚህ ይልቅ በሽታው አድማሱን በመላው ዓለም እያሰፋ ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ መላውን ዓለም እየተፈታተነ መገኘቱ ነው።
ችግሩ ደግሞ እንደኛ ባሉ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ አቅማቸው በሽታውን ለመከላከል በራሱ ተግዳሮት ለሚሆንባቸው ሀገራት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የመሆኑ እውነታ ነው። እንደ አገር ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከነበርንበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመውጣት ያለንን አቅም አቀናጅተን መንቀሳቀስ በጀመርንበት ማግስት መከሰቱ ደግሞ እውነታውን ያከብደዋል። መንግስት በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ ቢገባ ሊደርስ የሚችለውን የከፋ አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
በአንድ በኩል በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩ ቢከሰት ሊመጣል የሚችለውን መጠነ ሰፊ ጥፋት መታደግ የሚያስችሉ አቅሞችን ለመፍጠር ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።መላውን ህዝብ ሰራዊት አድርጎ በማሰለፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሽታውን በመከላከል ሂደት ውስጥ አቅም ሆኖ እንዲሰለፍ የሚያስችሉ ስራዎችን በስፋት ለመስራት ሰፊ ሙከራ አድርጓል።
ሙከራዎቹ ግን በህዝባችን መዘናጋት የተጠበቀውን ያህል ወጤታማ መሆን አልቻሉም። በህዝቡ ዘንድ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው መዘናጋት ሀገርንና ህዝብን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ አጠያያቂ አልሆነም። አብዛኛው ህዝብ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከመንግስት ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ለሚተላለፍለት መልዕክትና ትእዛዝ ተገዥ መሆን አልቻለም። ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋም በአግባቡ ቢገነዘብም ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም።
አብዛኛው ህዝብ በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ ክልከላዎችን ከራሱ ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ያላቸውን ፋይዳ በአግባቡ በመረዳት በኃላፊነት መንቀሳቀስ ሳይችል ቀርቷል። ችግሩ በሀገርና በህዝብ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን አሰቃቂ አደጋ ከግምት ማስገባት አልቻለም ። ከዚህ የተነሳ መንግስት የህዝብን ሕይወት ከበሽታው ወረርሽኝ ለመታደግ በመላው ሀገሪቱ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል።
አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ የኮሮና ቫይረስ የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል የወረርሽኝ ስጋት ሆኗል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገር ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ አቅም ነው:: ስጋቱን ከተለመደው አሠራር ወጥቶ በልዩ ሁኔታ በመንቀሳቀስ መቀልበስ ካልተቻለ ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ አስደንጋጭና አስከፊ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ለአዋጁ ተፈፃሚነት ሙሉ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2012