ቸልተኝነትና አውቆ ማጥፋት ከስንፍና ይመጣል። ክፋትም መገለጫው ናት። ሲናገሩም ሆነ ሲሰሩና ሲያሰሩ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ከማስተዋል ውጪ የሆኑ ግለሰቦች አይጠፉም። እነዚህን ሰዎች ታላቁ መፅሐፍ ቅዱሱ እንዲህ ይላቸዋል ‹‹የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ።
አንድ ሰው ጥፋት ሲያጠፋ ይገሰፃል፤ ይቀጣልም። ደግሞ ቢያጠፋም እንዲሁ፤ አሁንም በእኩይ ስራው ቢቀጥልበት ግን…ጭርሱኑ ይተዋል። ለምን? ብትሉ አንድ ጥሩ መልስ ታገኛላችሁ። በእኛ በኢትዮጵያውያን ባህል አንድ ብሂል አለ ‹‹ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው›› ወይም ‹‹ጨው ለራስ ስትል ጣፍጥ›› የሚል። መካሪም ቀጭም ይሰለቻል ከአቅሙም በላይ ይሆናል። ‹‹እድሜ ይምከርህ!›› ወይም ‹‹መከራ›› ሊለውም ይችላል። መሰልቸቱን፣ መታከቱንና ተስፋ መቁረጡን የምናውቀው ኃላፊነቱን ለሌላ ኃይል አሳልፎ ሲሰጥ ነው።
ጎበዝ! አሁን እየገጠመን ያለው ጉዳይ ግን ከላይ ካነሳነው በላይ ነው። በቀላሉ የማንተወውና ለሌላ ኃይል አሳልፈን የማንሰጠው የጭን ቁስል። በዚህ አላዋቂነት ውስጥ ያሉትን ‹‹ምከሯቸው ምከሯቸው እንቢ ካሉ መከራ ይምከራቸው›› እንዳይባል ነገርየው የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ ነው። ቸልተኝነታቸው ለሌላው ጦስ ይሆናል። ለመሆኑ አውቆ አጥፊንስ እንዴት መምከርና መገሰጽ ይቻላል? ወጣቶች ብቻ ናቸው እንዳይባል አዋቂውም አለ፤ ሴቶች ናቸው እንዳንል ወንዶቹም ጭምር አሉበት። የጋራ ጥፋት፤ ‹‹የምን አገባኝ›› መንፈስ። በመንጋ አስበው በመንጋ ያጠፋሉ። የሚሰበር እቃ እንደተከለከለ ህጻን ልጅ ለጥፋት ይቸኩላሉ። ይህን ማሰብ በራሱ አንድ ሌላ ጭንቀት ነው። ከሚነገራቸው ይልቅ ውስጣቸውን ያደምጡታል። ከእውነታው ይልቅ ብዥታውን ያምኑታል። ዓለም በኮሮና ቫይረስ ተጨንቃለች። የህክምና ባለሙያዎች በየቀኑ ተገቢውን ምክረሃሳብ ይሰጣሉ። መንግስት፣ ተቋማትና ግለሰቦች በሚችሉት ሁሉ ዜጎች እንዲጠነቀቁ ይመክራሉ። ነገሩ ግን ወዲህ ነው።
‹‹የእርስዎ ጥንቃቄ ለወገንዎ መዳን ነው። የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ማህበራዊ ርቀትዎን ይጠብቁ ። ተራርቀው ይቀመጡ፣ ተራርቀው ተራዎን ይጠብቁ ፤ ሰዎች በሚበዙበት ቦታ አይገኙ። እጅዎን በሳሙናና በውሀ ደጋግመው ይታጠቡ። እጅዎን ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ…›› የሚሉ መልዕክቶችን ደጋግሞ መስማት በራሱ ያስጨንቃል። ‹‹ከእኔ ምን ይጠበቃል›› ብለው ከሚነገርዎ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄን አለመተግበር ለራስ ብቻም ሳይሆን ቀሪው ወገንንም ዋጋ ያስከፍላል። ‹‹ብልህ ከሰው ሞኝ ደግሞ ከራሱ ይማራል›› ይላል የአገሬ ሰው። ክፉው ጊዜ በራሳችን ደርሶ ማየት አይጠበቅብንም። በቻይና፣ በጣሊያን፣ በአሜሪካ፣ በስፔንና በኢራን የደረሰውን ማየት ብዙ ያስተምራል። ይህን ጉዳይ በምሬት ያነሳሁት የማየውና የምሰማው ነገር አስገድዶኝ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስቲ አንድ ገጠመኜን ላጫውታችሁ።
በታክሲ ውስጥ ጋቢና የተቀመጡ ሁለት ወጣቶች ናቸው። አንደኛው እጁን ሌላው ላይ ጣል አድርጎ ተቀምጧል። መስኮቱ ደግሞ ክፍት ነው። ‹‹ተራራቁ እንጂ ተቃቀፉ ተባለ እንዴ ?›› ስል መልዕክት አዘል ንግግሬን ጣል አደረኩ። ቀጠለ አንደኛው ተሳፋሪ ‹‹ምነው ቀናሽ እንዳውም አቅፌ እስመዋለሁ›› ብሎ ወደ ልጁ ጠጋ አለ። መብቱ ቢኖረኝ አደርገዋለሁ ብዬ ያሰብኩትን ከመናገር ተቆጠብኩ። ‹‹የሚሰሩትን አያቁምና ከኮሮና ጠብቃቸው›› ብዬ ዝምታን መረጥኩ።
ለገባው ሰው ዛሬ መተቃቀፍ ፍቅር ሳይሆን የጥላቻ መግለጫ ነው። ከአላዋቂነት ይሰውራችሁ። ወገንና አገራችሁን ከመጉዳትም እንደዛው። በታክሲው ውስጥ ያጋጠመኝ አላዋቂ ወይም ደግሞ አውቆ አጥፊ መድኃኒቱን ፈልጎ እንዳገኘ ተመራማሪ ነው የሚጀነነው። ቫይረሱ ‹‹ወጣትን አይነካም፤ ስፖርተኛን አይነካም›› የሚለው የተሳሳተ መረጃ ወጣቱ ልክ እንዳልሆነ ሊገነዘበው ይገባል። እሳቱ ሳያቃጥለን እሳት እንደሆነ ማወቁ መልካም ነው።
ወዲህ ደግሞ ሌላ አንድ አስገራሚ አጋጣሚ ሰማሁ። ልጁ የጤና ባለሙያ ነርስ ነው። የኮሮና ቫይረስ በተደጋገሚ በዓለም ላይ የሚያስከትለውን አደጋና ችግር በየዕለቱ በመገናኛ ብዙሀን በኢንተርኔት የሚከታተል ጭምር። በስራ ላይ እያለ አንዲት የስራ ባልደረባው ከእረፍት ስትመጣ ተጠምጥሞ ሳማት። ባልደረቦቹ ‹‹ተው እንጂ በኮረና ዘመን›› ሲሉ ይናገራል። እሱ ማንን ፈርቶ። የቅናት ወሬ ነው ብሎ ዳግም ተጠመጠመና ሰላምታውን ደገመው። አጋጣሚውን ተመልክታ ያጫወተችኝ ወደጄ ‹‹ቫይረሱ ሳይጨርሰን ይቀራል?›› ስትል ጠየቀችኝ። አዋቂ የተባለው ሰው ይህን ያህል የወረደ ተግባር ሲፈፅም ስታየው ምን ታድርግ።
ሰሞኑን የሃይማኖት አባቶች ተግሳፅ፣ መሪዎች የሚያስተላልፉት መልዕክትና ምክር አይደለም የሰውን ጭንቅላት ድንጋይ በስቶ አይገባምን? ታዲያ ለምን መመከር አቃተን? አንዳንድ ጊዜ እየሆነ ያለውን ስመለከት ከምድር ሳይሆን ከፈጣሪ የተላከ መቅሰፍት እየመሰለኝ ‹‹ኧረ! ምን ጉድ መጣብን›› እላለሁ። የተነገረንን ሳይሆን የምናስበውን ብቻ የምናደምጠው ለምን ይሆን? ቫይረሱ እንዳይሰራጭና ጉዳት እንዳያደርስ በሚል ‹‹ሰው በሚበዛበት ቦታ አትገኙ፣ አምልኳችሁን በቤታችሁ ወይም ራቅ ራቅ ብላችሁ አከናውኑ›› እናም ሌላም ሌላም…. ይባላል። ወደተለያየ ቦታ ብቅ ሲባል ግን የሚታየው የተለየ ነው። ከማሳሰቢያው በተቃራኒ። እናም የእኛ ህዝብ ከቤት አትውጣ ሲባል እስኪ እነማን ከቤታቸው እንደወጡ ወጥቼ ልመልከት ብሎ የሚወጣ ሆኖ ተሰማኝ።
‹‹የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲባል የመንግስት ሰራተኞች በየቤታቸው ሆነው ይስሩ›› በሚለው ዜና ያልተደሰተ የለም። አንዱም እኔ ነኝ። ምክንያቱም ትራንስፖርት ላይ የሚኖረውን ግፊያና የሰው ብዛት ይቀንሳል። በየቢሮው ያለውን መተፋፈግም እንደዚሁ። ይሄ ደግሞ በሽታውን ለመቆጣጠር ያግዛል። የተባለው ቤት ተቀምጣችሁ ስሩ ነው እንጂ እረፉ አይደለም። ለዙረት፣ ካፌ ለመቀመጥ እና በየመንገዱ ላይ ለመዘዋወርም አይደደለም። ነገር ግን ከቢሮ ቅሩ የተባሉ የመንግስት ሰራተኞች የመዝናኛ ቦታዎችን፣ ገበያና ትራንስፖርት ሲያጨናንቁ መንገድ ለመንገድ ሲታዩ እንደሚውሉ እንሰማለን። ይሄ ፍፁም ተቀባይነት የለውም።
በአጠቃላይ የምናስበውን ሳይሆን በባለሙያ የሚነገረንን እናድምጥ። ባወቅነው መጠንም ራሳችንን ጠብቀን ሌሎችን እናድን። ከዚህ ውጪ አውቀው በቸልተኝነት የሚባዝኑትን ብኩናንን አይተን ደግሞ እኛ እንዲህ እንላለን ‹‹የሚሰሩትን አያውቁምና እኛንም እነርሱንም ከኮሮና ጠብቀን›› ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር