
አለማችን ከሊዮናርዶ ዳቪንቺ እስከ ፓብሎ ፒካሶ ድንቅ ሰአሊያንን አፍርታለች። አሁንም በየሃገራቱ በተለያዩ የስነ ስዕል ዘርፎች የስዕል ጥበባቸውን ለዓለም የሚያሳዩ ዝነኛ አርቲስቶች አልጠፉም። ሃገራችንም ብትሆን ሰዓሊና ባለቅኔ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ጨምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት የስነ ስዕል ጥበበኞችን አፍርታለች።
ሰዓሊያን በተለያየ የስነ ስዕል ዘርፍ የየራሳቸውን የአሳሳል ዘይቤ በመከተል የስዕል ስራቸውን የሚሰሩ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ቀለም ነክረው በዘረጉት ሸራ ላይ የሚቀቡት በአንድ እጃቸው ብቻ ነው። ይሁንና አንዳንድ በተፈጥሮም ሆነ በአደጋ ሁለት እጃቸውን ያጡ ሰአሊያን በአንድ እጃቸው ብቻ ብሩሽ ወይም እርሳስ መጨበጥ ስለማይችሉ ስዕል ለመሳል ሁለቱንም እጆቻቸውን ይገለገላሉ። ኦዲቲ ሴንትራል ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ ይዞት ብቅ ያለው መረጃ ደግሞ ሁለት ጤነኛ እጆችን በአንድ ጊዜ በመጠቀም ስዕል መሳል እንደሚቻል ያረጋግጣል።
መክሊት ካልሆነና ከላይ ካልተሰጠ በቀር ስዕልን እንዲሁ በቀላሉ በአንድ እጅ እንኳን ለመሳል ያስቸግራል። በሁለት እጅ በአንድ ጊዜ ሲሆን ደግሞ ጭራሽ የማይታሰብ ይሆናል። ለአሜሪካዊው አማተር ሰአሊ ግን ይህ እጅግ የቀለለ ጉዳይ ነው ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
እንደ ዘገባው፤ በአሜሪካ ዴትሮይት ግዛት ጠበቃና አማተር ሰአሊው ኮሊን ዳርክ የተለያዩ ቀለሞችን በመጠቀም ጠለቅ ያሉ የስዕል ጥበብ ስራዎችን በሁለት እጆቹ በአንድ ጊዜ የመስራት ችሎታው ረፍዶም ቢሆን፣ የብዙሃንን ትኩረት ለመሳብ በቅቷል። የ42 አመቱ ይህ ጎልማሳ ከታዋቂ የፊልም አክተሮችና ታዋቂ ሰዎች ጀምሮ የተለያዩ እንስሳትንና ተፈጥሮን የሚያሳዩ ስዕሎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የስዕል ስራዎችን ሁለቱን እጆቹን በአንድ ጊዜ በመጠቀም ለማሳል ብዙ አልከበደውም።
ኮሊን ይህን በሁለት እጅ በአንድ ጊዜ የመሳል ጥበቡን ሚስጥር ለረጅም ጊዜ ደብቆ ካቆየው በኋላ በአነቃቂ ንግግር ተነሳስቶ የሚሰራቸውን ስዕሎች የሚያሳዩ ፎቶዎችና የቪዲዮ ክሊፖች በኢንስታግራም መልቀቅ ከጀመረ ወዲህ የብዙሃንን ትኩረት ለመሳብ ችሏል። ‹‹የተደረገልኝ ቀና ድጋፍ የስዕል ስራዎቼን ይበልጥ እንድሰራና ችሎታየን እንድጠቀምበት አነሳስቶኛል››ሲልም ተደምጧል። ‹‹በርግጥ የቀኝ እጄ ሲደክም ስዕል ለመስራት የግራ እጄን እጠቀማለሁም›› ብሏል።
በአምስት አመቱ ስዕል መሳል የጀመረው ኮሊን ይህን ችሎታውን በመጠቀም በሆሊውድ ፊልም የሚታወቀውን የሃሪ ፖተር ገፀባህሪ፣ ሊዮናርዶ ዳቪንቺን፣ ኮቤ ብሪያንትንና ሩድ ባድረ የተሰኙ ዝነኞችን ከሰራቸው የስዕል ስራዎቹ ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በእንዲህ አይነቱ ስዕል የመሳል ጥበብ ኮሊን የመጀመሪያው ሰው እንዳልሆነ ዘገባው ገልጾ፣ከዚህ በፊትም ራጃሴና የተሰኘች ኔዘርላዳዊት በሁለት እጆቿ በአንድ ጊዜ ስዕል እንደምትሰራ መዘገቡን አስታውሷል። የስዕል ስራዎቿ በአንዳንድ ወገኖች የውሸት ናቸው በሚል የተፈረጁ ቢሆንም፣ይህን የሚያረጋግጥ ትክለኛ ማስረጃ ግን እስካሁን እንዳልተገኘ ዘገባው አመልክቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
አስናቀ ፀጋዬ