
በሩሲያ በረዷማ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ደኖች ውስጥ ተኩላዎች በብዛት ይኖራሉ። እነዚህ ተኩላዎች ታዲያ በጫካ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች እንስሳትን ይመገባሉ እንጂ ለአካባቢው ነዋሪዎች ብዙም ስጋት አይሆኑም። በሩሲያ አንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግን በአንድ ግዙፍ ተኩላ ስጋት ገብቷቸው ሲቸገሩ ቆይተው ሰሞኑን እፎይ ብለዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ፅፏል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ በሩሲያ አሌክሳንደሮቭካ በተሰኘች አንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ሲያስጭንቃቸው የቆየው አንድ ተኩላ በአዳኞች መመታቱ ሪፖርት ይደረጋል።
እንዲህ መንደሪቷን ሲያምሳት የቆየው ተኩላ በአዳኞች መመታቱ ነዋሪዎችን እፎይ ያሰኘ ቢሆንም፣ ተኩላው ባለፉት አርባ አመታት በአካባቢው ውስጥ ያልታየ መሆኑና በዚህ የክረምት ወቅት ሰዎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ላይ መግባት መጀመሩ አነጋጋሪ ሆኗል።
ተኩላው ወደዚች መንደር መግባት ከጀመረ ወዲህ ብዙ ውሾች ቅርጥፍ ጥፍ ተደረገው ተብልተዋል። ከሃያ በላይ የሚሆኑ ላሞች፣ በጎችና ፈረሶችም የዚሁ ተኩላ ሲሳይ ሆነዋል። ተኩላዎች፣ መምጣታቸውን ለማንቃት በየቤቱ በጠባቂነት የተያዙ ውሾችም ይህንኑ ተኩላ በመፍራት ድምፃቸውን አጥፍተዋል። ከዚህ ሁሉ ውድመት በኋላም ተኩላው በአካባቢው አዳኞች በመከራ የተገደለ ሲሆን፣ አዳኞች ተኩላውን ከበው ለማንሳት ሲታገሉ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ትስስር መለቀቁን ተከትሎ ተኩላው በግዙፉነቱ ወደር ያልተገኘለት መሆኑ ብዙዎችን አስደንቋል።
‹‹ውሾች እንኳን ሊጮሁ ራሳቸውን ነው የደበቁት፤ ምንም አይነት የውሾች ጩኸትም አይሰማም። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ምን አልባት ውሾቹ ተኩላውን ፈርተው ሊሆን ይችላል›› ሲል አንድ የመንደሪቷ ነዋሪ ተኩላው ከመገደሉ በፊት የነበረውን ሁኔታ ገልጿዋል።
የአካባቢው አዳኞች በኋላ እግሩ ሲቆም መካከለኛ ቁመት ካለው ሰው ጋር እኩል የሚሆነውን ይህን ግዙፍ ተኩላ ለመግደል ሲዘጋጁ የመንደሪቷ ነዋሪዎች ፍርሃት ነግሶባቸው እንደነበር በዘገባው ተመላክቷል። ጉዳዩ በማህበራዊ ትስስር ገፅ መለቀቁን ተከትሎ ደግሞ በርካቶችን አስገርሟል።
የዚህ ግዙፍ ተኩላ መገደል በኢንተርኔት የብዙሃንን ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ቢሆንም፣የመንደሪቷ ነዋሪዎች ቤታቸውን በከበበው ደን ውስጥ አሁንም የዚሁ አይነት ግዙፍ ተኩላ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው በዘገባው ተመላክቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
አስናቀ ፀጋዬ