አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኤሌክትሮኒክ ፋይል መክፈትና መከታተያ ስርዓት (e-filing & follow up system) በመጠቀም ብቻ በ2011 በጀት ዓመት ስድስት ወር ውስጥ 12ሚሊየን 287ሺህ 949 ብር ወጪ ማዳኑን ገለጸ።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አማረ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቱ የዳኝነቱን አገልግሎት በኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ ተገልጋዮች በአነስተኛ ወጪ፣ እንግልትና መጉላላት ሳይደርስባቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየሠራ ሲሆን፤ ለዚህም የሚረዱ አራት መተግበሪያዎችን ይጠቀማል። ከእነዚህ አንዱ በሆነው በኢፋይሊንግ ወይም በኦንላይን ምዝገባ ካስተናገዳቸው 3ሺ311 መዝገቦች 12ሚሊየን 287ሺህ 949 ብር በላይ ወጪ ማዳን ችሏል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ፍርድ ቤቱ ይህን ስርዓት ጥቅም ላይ ለማዋል በቀጥታ (online) ከወኪሎች የሚላኩ የፋይል መክፈት ጥያቄዎችን ይቀበላል፤ መሟላት ያለባቸው ሰነዶች መሟላታቸውን ይከታተላል። መልስ ይሰጣል፣ ፋይል የሚከፍቱና የሬጂስትራር ሥራዎችን ያከናውናል። ይሁንና የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት ችግር ፈተና በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ለመሥራት አልተቻለም።
ባለሙያዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ ማሰማራት አሁንም ይጠበቃል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በየክልሉ ላሉ ፍርድ ቤቶች ወይም ወኪሎች ከባለ ጉዳይ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እየተቀበሉና ወደ ዲጂታል እየቀየሩ ወደ ኢ-ፋይሊንጉ የሚልኩ መልስ ተቀብሎም ለባለጉዳዩ የሚያቀርቡ ህጋዊ ፈቃድ ወይም ውክልና የሚሰጥበት መመሪያ በማውጣት ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢ-ፋይሊንግ የመረጃ ችሎት በተለይ የህዝብን እንግልት ከመቀነስ አንጻር የማይተካ ሚና እንዳለው የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ በጊዜ ቆይታቸው ከአራት ቀን ሳይበልጥ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተጨማሪም ለአንድ ሰው ይወጣ ከነበረው በአማካኝ ወጪ በቀን መቶ ስልሳ አምስት ብር ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል።
የኢ-ፋይሊንግ የዳኝነት አገልግሎት በ2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በ12ሺ37 መዝገቦች 44 ሚሊዬን 722ሺህ 368 ብር ወጪ የማዳን ሥራ ተሠርቶበታል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው