ሳንፈልግ የሚያስፈግጉን፤ ሳንወድ የሚያስቁን ብዙ ሁነቶች በሰሞኑ በውዝግብ ውስጥ አሳልፈናል። እርግጥ ነው እንደ ማህበረሰብ ለጉዳዮች ያለን ግንዛቤ እጅግ ያነሰ ነው። የኛ ያልሆኑ ነገሮች ደግሞ አዳዲስ ለሚፈጠሩ ጉዳዮች ማለቴ ነው። እንጂማ ስለኛ ከኛ በላይ የሚያውቅ እንደሌለ ዘንግቼው አይደለም። እናም ከሳምንት በፊት ወደ ሀገራች ገባ የተባለው የኮሮና ቫይረስ ብዙዎቻችንን በሀሳብ ኮርኩሮናል።
እጅግ ደጋጎችን አይተን “እናንተማ በርክቱልን፤ ስለኛ ህይወት ጣዕም ቅመሞች ናችሁና ጤናችሁ ይብዛልን” እንዳልነው ሁሉ፤ አንዳንድ ጉደኞች “ጉድ!” የሚያስብል ተግባር ውስጥ ገብተው መክረማቸውም ተሰምቷል። እርግጥ ተቆንጥጠዋል አሉ። ቁንጥጫው ተገቢ ነው ግን አይበቃቸውም። የምር በወገን ላይ ለጨከነ ቁንጥጫ ያረካል? በፍፁም። አቤት አቤት ጭካኔ! በወገን ላይ የምር ይደረጋል? ወይ ዘንድሮ!
ባይሆን ጥሩ ነበር ወገን፤ መሆን የሌለበት ግን ሆኗል። ባንሰማ ጥሩ ነበር፤ ግን ደግሞ ባንወድም ሰማን። ባይደረግ መልካም ነበር፤ ግን ደግሞ ተደረገ። ስናሳዝን ግን! መተዛዘንናችንንና መተሳሰባችንን ማን ቀምቶን ይሆን? ማንስ ለውጦብን ይሆን? ግን የእኛ የምንለውን እኛነታችንን በ“እኔ” ቀየረብን። “እኔ ከሞትኩ…..ን” ከኛ ጋር ያጋባው ግን ማን ነው? ከዚህ ጋርማ መፋታት አለብን። ጉድ ነው! ይሄ ለማመን ይከብዳል።
ወገን ስለወገን ሳይሆን ስለራስህ ብለህ ሰው ሰው ሽተት፤ ካልሆነ ኑሮህ ጣዕም ያጣል። በሰዎች ችግር ለመክበር መጣር ከባድ ነው። በሰዎች ስጋት ነግደህ፤ ለሽሮ የሚጋፋን ረግጠህ ቁርጥ ስጋ ለመብላት መስገብገብ የምር በጣም ያስተዛዝባል። ሰሞኑን የሆነው ይህ ነው። ምስኪኑ፤ የማያውቀው “መዓት መጣብህ” ተብሎ ወደአንተ ዘንድ ለመሸመት ደጅህ የመጣን አቅመ ቢስ ገፈተርክ አሉ።
በደህናው ጊዜ ለአንተ መለወጥ የተጋውን ሚስኪን በክፉ ቀኑ ክፉ ሆንክበት ሲባል ለሰሚው ግራ ሆኗል። ኧረ በፍጹም በዚህ ሰዎች በፍቅር በኖሩበት ሀገር ነጋዴ ህዝቡን በክፉ ቀን አይገፋም፤ ሰዎች በአንድነት ጠብቀው ባቆዩት ፍቅር እንዳይበጠስ ሆኖ በተጋመደበት ምድር ነጋዴ በህዝብ ላይ አይጨክንም፤ መነጠል በሚከብድበት፤ መነጠል በማይቻልበት ማህበረሰብ እንዲህ አይደረግም ተብሎ ሙግት ቢገጥሙም እውነቱ የተገላቢጦሽ መሆኑ አስፈርቷል።
አንዳንዴ ሳይፈልጉት የሚውጡት ሂስ አለ። ነጋዴ ሆይ “ዋጥ!” ተብለሀል ዋጠው። ይህን አድርገኸው ከሆነ ከባድ ነው። በወገንህ ላይ ጨክነህ ከነበር አጉል ነው። ይህ እውነት ሳይፈልጉትም የመረረ ነው።
ወዳጄ! እሰኪ አስበው ምንአልባት የዚህ ህዝብ ቀና መሆን አንተን ጠብቆሀል። የዚህ ህዝብ እያንዳንዱ ጥረት አንተን ጠቅሞሀል። አይንህን አስፍተህ ከተመለከትክ በምንም መልኩ በራስህ የያዝከው አንዳች ነገር እንኳን የለም። ስለራስህ ብታስብ ይህንን ለማድረግ ባላሰብክ፤
ሌላውን ተወው። ስለራስህ ምቾት፤ ስለራስህ ደስታና የተቃና ኑሮ ሌላውን ማኖር ግድ ይልሀል። ወዳጄ ደሀው እኮ ላንተ ውበት ነው። ከመሀሉ ስትቆም አንተን የሚያስጌጥ፤ ደፋ ቀና ብሎ፤ ብዙ አምርቶልህ ትንሽ ጎርሶ የሚያድር፤ ብሎኬት ተቀባብሎ ቤትህን የሚያንፅ፤ ቀለም አስቀስሞ ልጆችህን በእውቀት የሚያበለፅግ፤ ጠዋት ቤትህን አንኳኩቶ ቆሻሻህን የሚያፀዳ፤ የእርሱ መኖር ነው አንተን የሚያኖርህ!
እንዲያው ሌላው ይቅር፤ “ማነህ… “ እያልክ የፈለከውን የምታዝዘው፤ “እዚያ ጋ አምጣልኝ እንጂ!” እያልክ የምትጣራው “ሎሌ” ላንተ እንዴት ጠቃሚ መሆኑን ዘነጋህ? ያለ መስተንግዶ መኖር አይከብድህም፤ እንዲያው “ጌታው ምን ልታዘዝህ? ምን ጎደለህ?” የሚልህን አትወድድም? እና እንዴት ብለህ በዚህ ሰው ጨከንክ ታዲያ? ግን ካንተ ጋር በገቢው አነስ የሚል ከጎንህ ከሌለ በምን ትኮፈሳለህ? እንዲያው በሞቴ ወዳጄ ለአንተ ዛሬ እዚህ ላይ መቆም መሰረት ከእስርህ ያለው ያ ወገንህ መሆኑን እንዴት ዘነጋኸው?
ኮሮና የሚባል ጉድ መጣልህ ፤እራስህን ጠብቅ፤ መጠበቂያውም እኛውልህ ተብሎ የተነገረውና እራሱን ለማዳን ለሸመታ ወዳንተ የመጣን ምስኪን “አምጣ” እያልክ ስትነጥቀው የዋልከው ገንዘብ እኮ እረፍት አይሰጥህም። ጥረው ግረው የበሉት ነው የሚጣፍጠው፤ በእርግጥ ጣዕም የሚገባህ ከሆነ ያ ነው ትክክለኛ ጣዕም የሚፈጥር፤ ያ ነው የራስ ከሆነ ልፋት ተገኝቶ ሲበሉት የሚጥም፤
ከወገንህ መንጭቀህ የሰበሰብከውን ገንዘብ መሽቶ ጣትህን ከምላስህ ምራቅ እያስነካህ ስትቆጥረው ቫይረሱን ወደ ውስጥህ ብታዘልቀውስ? ከባድ ነው! የተያዝክበት መንገድ እንኳን አጉል ነው። ወዳጄ ትላንት የጨከንክበት ወገንህ መታመምህን ሰምቶ የሚጠይቅህ ይመስልሀል? በፍፁም! ሰው የእጁን ፍሬ ነው የሚበላ፤ ስለ መልካም ውለታህ መልካም ምላሽ ጠብቅ፤ ካልሆነ ግን በተቃራኒው ነው።
ሁሉም የተሰፈረ ልኬት አለው። ከዚያ ውልፍች አይልም። ስላግበሰበሰ ከተፈቀደልት አምልጦ ትርፍ አያሻምድም፤ ስለተወው የርሱ የሆነ ድርሻ በሌላ አይቀማም። ወገን ስለራስህ ምቾት ለሌሎችን ምቹ ሁን። ስለራሰህ መልካም ፍፃሜ ስትል መልካምነት ላይ አዘውትር!
ሰው በቁርጥ ቀን ይለያል፤ ሳንፈልግ የለየናችሁ እነአጅሬ፤ ያደረጋችሁትን ባናውቅ መልካም ነበር። እናንተም ይሄንን ባታደርጉ ምንኛ በወደድን፤ ተግባር እኮ ጥላ ነው በሄዱበት ሁሉ የሚከተል፤ ሲበርድ ፀሀይ ሆኖ የሚያሞቅ፤ ሲሞቅ ምቾትን የሚፈጥር በጭለማ የፋኖስን ያህል ብርሀን የሚፈነጥቅ፤ የምር መንገድ የሚገራው በበጎነት ነው።
ዛሬ ነገ ላይ ታሪክ ነው። ያ ታሪክ፤ ያ ትውስታ ነገ ላይ ሲገለፅ ሁለት መልክ አለው። አንዱ በተወሳ ቁጥር የሚያስፈግግ፤ ሌላኛው ደግሞ ምነው ባልተነሳ፤ አሁን የምር ይህንን የሰው ልጅ ያደርገዋል የሚያስብል፤ ከመጀመሪያው ማህደር ውስጥ እራስን ማስገኘት ነው። ቸር ያሰማን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ተገኝ ብሩ