ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል እንዲሉ አመለኛ ሌባ ያገኘውን ከመስረቅ ወደኋላ አይልም። ታዲያ ሌብነት ሁሌም አይቀናምና አንድም በሰዎች መደብደብን ባስ ሲልም በፖሊስ መያዝና ለአስር መዳረግን ያስከትላል።
ሌባ ከትንንሽ እቃዎች አንስቶ አስከ ከፍተኛ ውድ እቃዎች ድረስ ፤ ከትንሽ አስከ ከፍተኛ ገንዘብ ድረስ ይሰርቃል። አንዳንድ ሌባዎች የሚሰርቋቸው እቃዎች ግን እንግዳና ያልተለመዱ ሆነው ‹‹ምን ሊያደርግላቸው ነው?›› የሰረቁት ያሰኛሉ። ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል ይዞት የወጣው መረጃም ይህንኑ ያመለክታል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የ57 ዓመቱ ጃፓናዊ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ሂሮዋኪ ሱዳ ከወራት በፊት በአንድ የባቡር ጣቢያ በርካታ ብስክሌቶች በሚቆሙበት ቦታ ግምታቸው 8 ሺ የጃፓን የን ወይም 75 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ የሁለት ብስክሌቶች ኮርቻ ወይም መቀመጫ ሲሰርቅ በቅኝት ካሜራ በመታየቱ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ሱዳ ድርጊቱን መፈ ፀሙን ያመነ ሲሆን ባል ተለመደ ሁኔታ የብስ ክሌት ኮርቻዎችን ወይም መቀመጫዎችን ያውም ለሃያ አምስት ዓመታት ሲሰርቅ መቆየቱን ለፖሊስ አስታውቋል። የሚገርመው ደግሞ የሰረቃቸውን እቃዎች በሙሉ በአንድ ላይ በመሰብሰብ በሚ ማርክ መልኩ እንዳስቀ መጣቸውም ለፖሊስ መና ገሩ ግርምትን ፈጥ ሯል።
‹‹የብስክሌት ኮርቻ ዎችን መስረቅ የጀመርኩት ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በፊት በቶኪዮና ኦሳካ ነው። ስርቆቱን የጀመርኩትም በሥራ የሚገጥመኝን ውጥረት ለመቀነስ በሚል ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን ኮርቻዎቹን ሰርቄ መሰብሰብ ስጀምር ደስታን አጎናፅፎኛል›› ሲል ሶዳ ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።
የ57 ዓመቱ የከባድ መኪና አሽከርካሪ የሚሰርቃቸውን የብስክሌት ኮርቻዎች ተከራይቶ ወደሚያስቀምጥበት ቦታ ፖሊሶችን መርቶ አሳይቷል። በቦታው 5 ሺ 800 የሚሆኑና ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተሰረቁ ኮርቻዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል። የአሽርካሪነት ሞያውን በመጠቀም በጃፓን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የብስክሌት ኮርቻዎችን ሲስርቅ መቆየቱንም ለፖሊሶች አስረድቷል።
ከዚህ በፊትም ሌላ ጃፓናዊ በተመሳሳይ በአንድ ዓመት ውስጥ 159 የሚሆኑ የብስክሌት ኮርቻዎችን በመስረቅ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበርም መረጃው አስታውሷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
አስናቀ ፀጋዬ