
አዲስ አበባ፡- ሴቶች የሚፈጠሩ ዕድሎችን ሁሉ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ከራስ የጀመረ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ትናንት በመሥሪያ ቤቱ ባከበረበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፤ ሴቶች በአንድ ቀን ብቻ የሚታወሱ አይደሉም። ሥራቸው በየዕለቱ የሚታወስና ካለባቸው ጫና ማላቀቅን የሚጠይቅ ነው።
‹‹ከመጣንበት ባህልና ታሪክ ተሻግረን ሴቶችን የምናይበትን ሁኔታ መፍጠርም የየዕለት ሥራ መሆን አለበት። የመደገፉ ሥራም ከዚህ ቀደም የነበረውን ጫና ሊያካክስ በሚችል መልኩ መሆን ይኖርበታል።›› ሲሉ ገልፀዋል።
የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው፤ ሴቶች በሥራቸው ውጤታማ ስለመሆናቸው ተግባራቸው እንደሚመሰክር ጠቅሰው፣ ሴቶች የወንዶችን ያህል ፊት መስመር ላይ ልውጣ ስለማይሉ መግነን አለመቻላቸውን ገልፀዋል።
እንደ አቶ ወንድም ገለፃ፤ ሴቶች ማንኛውም ቦታ ላይ ከወንዶች በተሻለ እንደሚሠሩ አምኖ ዕድል መስጠት ይገባል። ሸብቧቸው የቆየውን ባህል በመስበር ወጥተው ኃያልነታቸውን እንዲያሳዩ ማድረግም ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ በአስተዳደግ ማረቅ ይቻላል።
በዕለቱ ሴቶች ቀን የክብር እንግዳ የ‹‹ነበሩ›› ቴሌቪዥን ጣቢያ መሥራችና ዳይሬክተር ወጣት ፊልሰን አብዱላሂ እንደተናገረችው፤ በገጠር አካባቢ ሴት ልጅ ለትዳሯ ምቹ እንድትሆን ብቻ ይደረጋል። ያም ሆኖ ግን ከዚያ ልቃ ሥትሠራ ትታያለች። እንዲያም ሆኖ ‹‹አትችይም›› ባይዋ ብዙ ነው። ስለሆነም ይህንን እንድታልፍ ለማድረግ ሴቶች በራሳቸው ሊያግዙ ይገባል። በተለይም ልቀው የወጡ ሰዎች ታች ላይ ያለችዋን ጠንካራ ሴት ማንሳት አለባቸው። ይህ ሲሆን ራሷን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ማላቀቅ ትችላለች።
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ወጥተን የምንመለከተው የድል ሐውልት ታሪክ እንጂ ቅኝ የተገዛንበት ታሪክ አይደለም።›› የምትለው ወጣት ፊልሰን፣ ‹‹ድህነት ታሪክ እንዲሆንብን ዕድል ልንሰጠው አይገባም። ሴቶች ሥራ ፈጣሪና ኢኮኖሚ አበልፃጊ እንዲሆኑ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ሴቶች ህይወትን የያዘ ማህፀን ባለቤት ናቸው። ስለዚህም አገር የሚያድን ሥራን በልጃቸውም በራሳቸውም ይሠራሉና የዘርፉ ባለሟል ሁኑ ልንላቸው ይገባል።›› ብላለች።
የድርጅቱ የሥርዓተ ጾታ ማህበራዊ ጉዳዮች ተወካይ ወይዘሮ ብርሃኔ ደመቀ በበኩላቸው፤ ሴቶችን በሚመለከት በአገር ደረጃ የተሻሉ አሠራሮች ተዘርግተው ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው፣ አሁንም ከችግር ተላቀዋል ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል። መታገትና መደፈር አሁንም እንደበረታባቸው መሆናቸውን ተናግረው፣ መንግሥት ይህንን ችግር ተመልክቶ ለመፍትሄው መረባረብ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። ህብረተሰቡም ቢሆን ሴት ልጅ እናት፣ ልጅና ሚስት መሆኗን አምኖ ትኩረት ሊሰጣትና የፈለገችበት ቦታ ላይ እንድትደርስ ሊያግዛት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሴቶች በሰላም እጦት ምክንያት የመጀመሪያ ተጠቂዎች እንደሆኑ የሚገልፁት ወይዘሮ ብርሃኔ፣ ‹‹የድርጅታችን ሥራ በብዕሩ እየከተበ ህዝብን ማስተማር ነውና የሰላምን ጉዳይ በአንክሮ በማየት ለህዝቡ የሰላምን ዋጋ ማሳየት ላይ መሥራትም ያስፈልጋል።›› ብለዋል። በዕለቱ በድርጅቱ ከ30 ዓመታት በላይ ላገለገሉና ጡረታ ለወጡ ሴት ሠራተኞች የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው