ተሰልፈን ቆመናል አምባሳደር አካባቢ ታክሲ ተራ።ታክሲዎች ተሳፋሪውን ተራ በተራ እየጫኑ ወደ መድረሻቸው ይጓዛሉ።ተሳፋሪው ሌላ ታክሲ እስኪመጣ ይጠብቃል።አንድ ከፍ የለ ድምፅ በሰልፍ የቆመውን ተሳፋሪ ትኩረት ስቧል።ሁሉም ወደ ተሰማው ድምፅ አማተረ።አንድ ወጣት አንዲት ህፃን ልጅ አቅፎ ተሳፋሪውን ቀረበና በእጁ የያዘውን በፕላስቲክ ማሸጊያ የተለበጠ ወረቀት ላይ የተፃፈ ጽሁፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነባል፡፡
የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚሰማ ምልዕክት አይነት የመሰለው አይንና ጆሮው መለሰ። ልጁ ቀጥሏል፤ ወረቀቶችን ይዞ ድመፁን ከፍ አድርጎ ያነባል። “ከተፋቀርን አባይ ይገደባል እኛም እንጠግባለን። እባካችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርስ ተፋቀሩ ያኔ ኢትዮጵያ ከፍ ትላለች፡፡” ሰውየው ከፍ ባለ ድምፅ ይናገራል። ይሄን እዚያ ለመሳፈር የቆመው ሁሉ ጆሮ ሰጥቶ ይሰማው ጀምር፡፡
ከሰውየው አንደበት የሚፈልቁ ቃላት የተመጠኑና ሁሉም ሰው ሊያዳምጣቸው የሚገቡ በመሆናቸው እንዲቀጥሉ ተመኘሁ።ታክሲ ለመያዝ ተጣድፌ የነበርኩትን ያህል፤ ታክሲ እንዲዘገይ ተመኘሁ።ሰውየው በፈገግታ ተሞልቶ ስለ ፍቅር ታላቅነት ይሰብካል።“እባካችሁ ተዋደዱ ያኔ ለውጥ ይመጣል ተከባበሩ ያኔ ድል ይመጣል….” ስለ ፍቅርና መዋደድ ስለ አብሮነትና ፍቅር በማይጠገብ አንደበቱ ያስረዳል። እናንተዬ ፍቅርን የሚሰብክ አንደበት፣ እድገት የሚያፀና ምክር፣ ህብረትን የሚሰብክ ንግግር ምንኛ ይጥማል።
ታክሲ መጣና ተሳፈርኩ። ስራ ረፍዶብኝ ነበረና ቦታውን ሳልወድ ለቀኩ።ሰውየው ግን ከአይምሮዬ አልጠፋም ደጋግሞ ይታሰበኛል።ይህ ሰው ስለዚህ ጉዳይ እንዲናገር ምን አነሳስቶት ይሆን? የጎደለን ፍቅር መሆኑ ከኛ ከፍ ባለ ሁኔታ ገብቶት መንገርስ ላይ ያደረሰው ምን ይሆን? ብዙ አሰብኩ፤ እዚያው ቦታ ሆኜ የጎደለን ፍቅርና መተሳሰብ እንጂ እውነትም አባይ አይደለም ችግርና መከራችንም መገደብ እንችላለን የምር!!።ስለ ፍቅር ብለን እርስ በርስ ብንተጋገዝ ስለ ሀገር ፍቅር ብለን ለሀገራችን በጎ ካበረከትን ምን ሊጎለን ይችላል?ምንም! ለራሴ መልስ ሰጠሁ፡፡
ታክሲ ውስጥ ረዳቱ ሒሳብ ሲለኝ ከሄድኩበት ሰመመን ተመለስኩ።አውጥቼ ሁለት ብር ሰጠሁት።“አምስት ብር ነው፡፡” እ…ከሁለት ወደ አምስት ብር ያደገው ከመቼ ጀምሮ ነው? አትነጫነጭ ሁሉም ከፍሏል። “በአቋራጭ ነው የምሄደው ጨምር።” ሹፌሩ በመሀል ረዳቱን ለማገዝ ቃላት መወርወር ጀመረ። “አንተ ሰው ስራ አይደል እንዴ ምን እያልክ ነው ለምን ገባህ እየተናገርን አይደል የጫንክ”
ተሳፋሪውን ዞር ብዬ አየሁ ፊቱን ሁሉም ቅጭም ሲያደርግብኝ መኪናው ሙሉ በኔ ያኩረፈ መሰለኝ፤ አውጥቼ ሰጠሁ።እስክሰጠው ድረስ በስድብ እያጥረገረገኝ ነበር። ኦህ! አምላኬ ትግስቱን ስጠኝ ትርፍ ከፍዬም ተሰድቤም ከባድ ነው።ሰልፉ ቦታ ወደነበረው ሰው በሀሳብ ተመለስኩ።“ እርስ በርስ እንከባበር እንዋደድ፣ ፍቅር አተን ነው የተቸገርነው እባካችሁ እንፋቀር፡፡” ንዴቴ ረገበ።ስለፍቅር ብዬ ዝም አልኩ።
እኛ ግን ምን ነካን።ፍቅራችን የት ገባ።ረዳቱና ሹፌሩ ግን ያንን ሰው ሰምተውት ይሆን ሲጭኑ እዚያ ቦታ ነበሩና ሳይሰሙት አይቀሩም።ችግሩ አያደምጡትም…። ወዳጄ ስላለን ብቻ የፈለግነው አንበላም እኮ አረ እንዋደድ ተዉ…። አብዝቶ መስገብገብ ምንድነው እንዴ? ሆድ ልክ አልባ ይመስል ሰውን መበደል፣ ሰውን መግፋት የሰውን መሰብሰብ አስጭኖና ቋጥሮ መቃብር ይዞ ላይሄዱት ነገር ኧረ ነውር ነው…!!።
ሰው ከተዋደደ በደህነቱ ንፁህ ህሊናውን ይዞ ሊሰፈር የማይችል ደስታን ይጎናፀፋል።ህሊና ቢስ ከሆነ ግን ሰው ከሚለው ስብዕና የራቀ ክፉ አውሬ ከመሆን አይድንም። በክፉ ስራው ሰዎችን ክፉኛ ያቆስላል፣ ከሚታሰበው በላይ ክፋትን ይለምድና ለሰዎች ሴራን ይጎነጉናል ስለሌላው አይጨንቀውም ስለማንም አይገደውም።ይህ ሰው እያደረ ‹‹ሰው ጤፉ›› ነው።
ሰውየው ግን አይቶናል ፍቅር በማጣታችን መቸገራችን ከኛ በላይ ገብቶት ጎዳና ላይ መስበክ ተያይዞታል… እንደው በዚህ በጎ ተግባሩ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን? ታድሎ።ውስጡ የሚሰማው ሰላምስ ምን ያህል ይሆን? እኔ ምለው ሰላም ግን ይሰፈራል። ምን ያህል ነው ክብደቱ? ኦህ! ይከብዳል አቻ የሌለው ነገር በምን ሊሰፈር ይችላል።ሰውየው ውስጡ ያ ሰላም ሳስበው ቀናው።
ወዳጄ ደስታህ ከእጅህ እንዳይወጣ ባንተ ሰው እንዲደሰት ትፈልጋለህን? ውስጥህ ሰላም ከሆነ ባትበላ ረሀቡ አይቀፈድድህም፣ ባትለብስ የሰው ፍቅር ትሞቃለህ፣ በሰው ክብር ምቾት ይሰማሀል።የትም ጋደም ብትል ለሽ… ብለህ የሚያስቀና እንቅልፍ ትተኛለህ።ሰዎች ብዙ ጊዜ ስግብግብ የሚሆኑት ፈፅሞ ቢያገኙም በማይጠቀሙበት አግኝተውም በማይደሰቱበት መሻታቸው ላይ ነው። ይሰበስባል፣ ላይ በላይ ደራርቦ ከምሮም ከልክ በላይ ያደልባል እድሜውን ሙሉ ያለ እረፍት የሱ ያልሆነን የማይገባውን የሌሎችን እየነጠቀ ባለው ላይ እየጨመረ ቀዶ እንኳን የማይጨርሰው ሀብት ያከማችና ሰላሙን ያጣል።
ሰውየው ግን ከየት ተልኮልን ይሆን “ተፋቀሩ ተዋደዱ” ያለው ፍቅር ከኛ መንጠፉ ምን ያህል ቢገባው ነው።ፍቅር አተን እንጂ ምን ይጎለን ነበር።በተጓዘበት በደረሰበት ሁሉ የሚሰብከው መልካም ነገር ስንቶቻችን ይሆን ጆሮ ሰጥነት የምንሰማው ምን ያህሎቻችንስ ነን ከልብ የምናዳምጠው።
ዛሬ ላይ የምነሰማው መልካም ነገር ጎሎ ሳንፈልግ የሚቀርበን መጥፎ ዜና በተበራከተበት ለሁሉ ጉዳት መፍትሄ የሚሆነው ፍቅር ማጣታችን ዋንኛው ምክንያ ነው።ፍቅር ውስጥ የማይፈታ ችግር የማይታለፍ ፈተና የለም።መከባበር ውስጥ የማያስችል ጉዳይ የማያግባባ ሀሳብ አይኖርም ግን በተቃራኒው ከኛ ፍቀር ከራቀ ጥላቻ ቦታውን ይወርስና የማያርቅብን ጉዳይ አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
ተገኝ ብሩ