የአይቻልምን መንፈስ የደፈሩ፣ ‹‹ሴት ናት አትችልም…›› በሚል በሰፊው ተንሰራፍቶ የቆየውን የተሳሳተ አመለካከት ሰብረው ሴትነት ፆታ እንጂ የመቻልና ያለመቻል ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አለመሆኑን ያስመሰከሩ እናትና እህቶቻችን ከፆታ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ልዩነቶች ውድቅ መሆናቸውን ያስመሰከሩ ሕያው ምስክሮች ናቸው። እኛም ለዛሬ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትምህርት ሚኒስቴር በሪፎርም፣ በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር፣ በሥነምግባርና በመምህራን ልማት ላይ የሚሠሩ ዳይሬክቶሬቶችን እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉን አነጋረን ያሰናዳነውን ዘገባ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የት ተወለዱ? የት አደጉ የልጅነት ጊዜዎስ ምን ይመስል ነበር?
ወይዘሮ ጽዮን፡- የተወለድኩት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፤ ትምህርቴን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ሊሴ ገብረማርያም ተከታትያለሁ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በትብብር በኢትዮጵያ በሚሰጠው የትምህርት ዕድል በሊደርሺፕ አግኝቻለሁ።
በአገራችን ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር አቆራኝተው በመሆኑ ሁልጊዜም ለሰዎች ማካፈል መስጠት አስፈላጊ ነው የሚለውን ሐሳብ ያሰርጻሉ። እኔም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊት ከልጅነቴ ጀምሮ በዚህ ውስጥ ስላለፍኩ ሌሎችን መደገፍ ብሎም አስተሳሰብ ቀረፃ ላይ መሥራት ደስታን ይሰጠኛል።
በነገራችን ላይ የሁለት ሴት ልጆች እናት ነኝ። አንደኛዋ በቅርቡ በኮሪያ ከሚገኝ ጋቹን ከተባለ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃለች። ሁለተኛዋ ደግሞ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነች። ልጆቼም የተማሩበት ትምህርት ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን የሚያበረታታ ስለነበር በተለያዩ በጎ ፍቃድ ሥራዎች ተሳታፊ ሊሆኑ ችለዋል።
ከትምህርት ቤት ከወጣሁ በኋላ በተለይ በሥራ ዓለም እያለሁ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናት ያሉበት አካባቢ ውሎዬን ማድረግ ያስደስተኝ ነበር። ሌሎችን ስለ መደገፍ ስናስብ ብዙ ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን የሚመጣው ቁሳዊ ነገር ቢሆንም ዕውነታው ግን ይህ አይደለም፤ ትንሽም ነው። ነገር ግን መገኘት፣ ለሕፃናት መጻሕፍት ማንበብ፣ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። ልጆቼም በክረምት ወራት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ አብረውኝ ይሳተፋሉ። በትምህርት ቤታቸው ደግሞ ነህምያ ኦቲስቲክ ሴንተር (የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ሕክምና ማዕከል) የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ካለባቸው ልጆች ጋር አብረው ጊዜ ያሳልፉ ነበር። ለእኛ የበለጠ ደስታን የሚሰጠውም ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማህበረሰባችን በተለይ ለሴቶች በፆታቸው ብቻ የሚሰጣቸው ቦታ እንዳለ ይታወቃል። እርስዎ በዚህ መሰል ጫና ውስጥ አላለፉም?
ወይዘሮ ጽዮን፡- እኔ ፆታዬን ተከትሎ ጫና ተደርጎብኝ አላደኩም። ነገር ግን ውልደቴ አዲስ አበባ ይሁን እንጂ አባቴ የተወለደው በገጠር የአገሪቱ ክፍል በመሆኑ ቋሚ ኑሯችን በዛው ባይሆንም ገጠር እንሄድ ነበር፤ ይህም የሕብረተሰቡን በተለይም የሴቶችን ችግር በቅርብ ለመረዳት ዕድሉን ሰጥቶኛል።
በአጠቃላይ ስለ ሴቶችና ወንዶች ሲወራ አንዳንዴ ጽንፍ ይዞ መጓዝም ይታያል። በሴቶችና በወንዶች መካከል ልዩነት አይደረግም ብዬ አላምንም፤ ይደረጋል። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ወንዶች ለሴቶች ድል ትልቁን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፤ የሚታይ ዕውነታም ነው። በጣም ገጠር በሆነ የአገሪቱ ክፍል ላይ ሴቶች ልጆቻቸውን መማር እንዲችሉ ብቻ ሳይሆን የተሻለ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ብዙ አባቶች እንዳሉም አይካድም። በመሆኑም ችግሮቹን ከፆታ ጋር ከማያይዘው ይልቅ ከሠው ልጅ ስብዕና ጋር ባያይዘው ይቀለኛል።
ሚስታቸውን የሚያሰቃዩና የሚደበድቡ ወንዶች ወይንም ሌሎች ሴቶችን የሚያስቸግሩ ወንዶችን የኋላ ታሪክ ለመፈተሽ ቢሞከር በማህበራዊ ሕይወታቸው ይህን መሠል ሠዎች ናቸው። ይህም በሁለቱም ፆታ ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል። ከጉልበት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው አቅም ያላቸው ላይ ነገሩ ሊስተዋል ይችላል እንጂ የስብዕና ችግር ፆታ አይለይም።
ከጉልበት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ነገሮች ቢኖሩም በአስተሳሰብ ግን ሴቶች የንቃተ ሕሊና ደረጃቸው በጣም ፈጣን ነው። በአገሪቱ ተረትም ሴት ልጅ መለኛ ናት ይባላል። አካላዊ አቅም ሲታይ ደግሞ ወንዶች ጥንካሬ አላቸው። በዚህም የነበረውን ትርክት ተጠቅሞ ሴቶችን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ወንዶች አሉ። ይህን መሠል ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሠቦች የኋላ ታሪካቸው ቢፈተሽ ብዙ ችግር እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል።
ከሥርዓተ ፆታ ጋር ተደጋግመው የሚደመጡ ነገሮች ዕውነት እየመሰሉ ሁሉን ችግር ‹‹ሴት ስለሆንኩ ነው›› በሚል ማያያዝ ይታያል። ስለሆነም ችግሩ ከየት እንደመጣ በተገቢው መንገድ ማጤኑ ተመሳሳይ ፍረጃ ከመስጠት በማዳን ትክክለኛ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል። ለአብነት እኔ በራሴ ሕይወት እህት ሳይኖረኝ በወንዶች መሐል ነው ያደኩት። ነገር ግን ሴትነት ጉድለት ሳይሆን በረከት መሆኑን ተገንዝቤ ስላደግኩ ችግር ሲያጋጥመኝ ሴት በመሆኔ ነው ብዬ ሁለት ጊዜ እንኳ አስቤ አላውቅም።
በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ሴቶች በሕይወታቸው ደርሶ የሚታዩ ችግሮች አሉ። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሥራ አጋጣሚዎች የማገኛቸው ሠዎችም ለእኔ የሚሰጡኝን ቦታ ስመለከት ለሴቶች የሚሰጡ ያልተገቡ አመለካከቶች ምን ያህል በማሕበረሰቡ ውስጥ እንደ ዘለቁ ያሳየኛል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ኃላፊነት ተረክቤ መሥራት ከጀመርኩ በኋላም ውሳኔ ላይ ስደርስ ሴት ስለሆንኩ ኃላፊነት የሌለኝ የሚመስላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ያጋጥሙኛል። ይህን መሠል አመለካከት የሚያራምዱ ግለሰቦች በአቅሜ እበልጣለሁ ወይም ደግሞ በተለያየ መንገድ አሸንፋለሁ በሚል በተሳሳተ መንገድ የመሄድ ልምድ አላቸው። ይልቁንም ሠውን በሠውነቱ የሚያከብር ሁሉ ግን ችግሩ አይስተዋልበትም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ሴት በመሆናችን ቅድሚያ የምናገኛቸው ጥቅሞች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለሴቶች የሚደረጉ አዎንታዊ ድጋፎች ተገቢ ናቸው ብለው ያምናሉ
ወይዘሮ ጽዮን፡- አዎንታዊ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ያለንበት የማሕበረሰብ ንቃተ ሕሊና ደረጃ ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ እስኪደርስ በትክክል ከተሠራበት ይጠቅማል። ሴቶች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲገቡ ውጤታቸው ቢቀንስም ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ማስገባቱ ነው ትክክል ወይንስ ብዙ ልጆች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚሆን የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ መሥራት ነው የሚገባው? የሚለውን ማጤንም ያስፈልጋል። ለምሳሌ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ብዙዎቹ ሴቶች በቤት ውስጥ በማጀት ሥራ ስለሚጠመዱ ለትምህርታቸው ተገቢውን ጊዜ ለመስጠት ስለሚቸገሩ ማካካሻ ክፍሎችን በመስጠት በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ማድረግ ነው የሚሻለው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት።
ሴት ተማሪዎችን በዚህ መልኩ በመደገፍ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ማድረግ ወይንስ ውጤታቸውን ቀንሶ በማስገባት በኋላ ሲቸገሩ ማየቱ ይሻላል? በሚል መመልከት ትክክለኛ አዎንታዊ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል። በወንዶችና በሴቶች መካከል የሚደረጉ ውድድሮች አካላዊ ካልሆኑ በቀር ከጭንቅላት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ እኩል ዕድል የተሰጣቸው ሠዎች እኩል መወዳደር ይችላሉ። በዓለም ላይ አደጉ በተባሉ አገራትም ቢሆን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ የሚደረገው በውጤት ተወዳድረው እንጂ ሴቶች ስለሆኑ በሚል አይደለም። በአሁኑ ወቅት ችግሩ ደግሞ እኩል ዕድል የለም የሚል ነው።
አንዲት ሴት ልጅ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ቤተሰቧን ማገዟ በመልካም የሚታይ ነው። ሴቶች በኋላ ላይም ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ስኬታማ ከሚያደርጋቸው ነገር አንዱም በሥራ ቦታ ሲዝል የዋለ ጉልበታቸው ሳይበግራቸው ቤታቸውን ማስተዳደራቸው ነው። ይህም የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ ያስችላቸዋል። አገር የተሻለች የምትሆነውም ሴቶች የተለያየ ተደራራቢ ኃላፊነቶችን ተሸክመው መወጣት ሲችሉ ነው፤ ይህን መሠል ክህሎት ማዳበራቸው ለአገር የተሻለ ትውልድ እንዲቀርጹ ያስችላቸዋል። መሆን ያለበትም ሴት ልጅ ቤት ውስጥ ሥራ እንዳትሠራ ማድረግ ሳይሆን ወንዱም ቤት ውስጥ እንዲሠራ በማድረግ እኩል እድል መፍጠር ነው። በዚህ መልኩም በሒደት ድጋፉ የማሕበረሰብ ንቃተ ሕሊና ሲያድግ መቆም አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በሴትነቴ ተጋርጦብኝ የነበረ ፈተና ነው የሚለት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?
ወይዘሮ ጽዮን፡- እኔ አለመታደል ሆኖ ልጆቼን ለብቻዬ ነው ያሳደኳቸው። ከባለቤቴ ጋር በትዳር ለተወሰነ ጊዜ ከቆየን በኋላ በመለያየታችን ልጆቼን በትክክል ማሳደግ ስለነበረብኝ መወሰን ነበረብኝ። ልጅን ለብቻ ማሳደግ ከባድ ቢሆንም ለእኔ ብዙ ጠቅሞኛል። ፈታኝ የሕይወቴ ምዕራፍ ብለውም ውጣ ውረዱን ማለፉ በአሁኑ ወቅት ላለኝ ጥንካሬ ትልቅ መሠረት ጥሎልኛል። በዚህ ሒደት ውስጥ ቤተሠብ በጣም ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ማዕቀፍ እንደሆነ ለመገንዘብ ችያለሁ።
ከሥርዓተ ፆታ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ፍቺን ሲያበረታቱ አስተውላለሁ። ይህ ግን ትክክል አይደለም። በርግጥ ሠዎች በተለያየ ሁኔታ ይህን መሰል ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ነገር ግን ልጆች ማደግ ያለባቸው በእናትና በአባት ነው። ይህም በአንድ በኩል ጫና የሚቀንስ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች በሕይወታቸው የተሻሉ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል። በመሆኑም ቤተሠብን ከመበተን በፊት በደንብ ማሰብ፣ በጋራ ማሳደግና የልጆችም መብት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በዚህም አንዳንዴ ከመጥፎ ነገሮች መካከል የተሻለውን መጥፎ ለመምረጥ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉና እኔም ሴት ሆኜ በእናትነቴ ያሳለፍኩት ፈተና ይህ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ልጅነትዎ ልመልስዎትና ልጅ ሆነው ከነበርዎት ሕልም አንፃር በአሁኑ ወቅት የደረሱበትን ደረጃ እንዴት ይገመግሙታል?
ወይዘሮ ጽዮን፡- ከልጅነቴም ጀምሮ ነገሮችን ቀለል አድርጌ የመመልከት ልማድ አለኝ። እናም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ስወስድ ምንም እንኳ በወቅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ቀላል ባይሆንም እኔ ግን እንደምገባና ኢኮኖሚክስ እንደማጠና አውቅ ነበር፤ እርግጠኛም ነበርኩ። ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ከወጣሁ በኋላም ስለ ሥራ ዓለም ሳስብ ራሴን የማገኘው ሠዎችን በመርዳትና ስብዕና ቀረጻ ላይ ስለነበር በዛው ዙሪያ መሥራት ያስደስተኝ ነበር።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቆይታዬን ጨርሴ ስወጣም በአንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ ለረጅም ዓመታት ሠራሁ። ወደ ሥራ ዓለም ከገባሁ የተወሰነ ዓመት ቆይታ በኋላ ሁለተኛ ዲግሪዬን ሠራሁ። ከዛም ከመደበኛ ሥራዬ ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመርኩ። ለዚህም ያነሳሳኝ በውስጤ ያለው ስብዕና ቀረፃ ሲሆን፤ ሥልጠና ከመስጠት ይልቅ የአገር ተረካቢ ከሆኑ ትውልዶች ጋር በቅርበት ለመገናኘትና የተሻሉ ዜጎችን ለማፍራት ዕድል ስለሚፈጥር ነው።
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ፣ ኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ እያስተማርኩኝ በተጨማሪነት ሁለተኛ ዲግሪዬን በሰራሁበት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በቅድመ እና በድህረ ምረቃ ክፍል አስተምር ነበር። በዚህም በሥልጠና በትምህርት በኩል ያለውን ሥነምግባርና የትምህርት ሥርዓት የተረዳሁበት ትውልድን የመቅረጽ መልካም አጋጣሚ አግኝቻለሁ። በኋላም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችን ለተወሰነ ጊዜ አስተምሬያለሁ።
በመጨረሻም ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ የመሆን ዕድል አገኘሁ። የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ መሥራት ጥሩ ያደርጋል ብዬ የማስበውም ብዙዎቻችን በውጪ ሆነን ከመፍረድ በቅርብ ሆኖ ለመሥራት ብሎም የመፍትሔ አካል ለመሆን ስለሚያስችል ነው። በተያያዘም በግል የሚደረገውን ጥረትና መልካም ተግባሮች በአገር ደረጃ ለማስፋትና ለማሳደግ ዕድል ሰጪም ይሆናል። በሕይወቴ አጥብቄ ከምሻው ነገር አንዱ አገሬን በሆነ መንገድ ማገልገል ነበር።
በአሁኑ ወቅት ከተቀበልኩት የመንግሥትና የሕዝብ ኃላፊነት በፊትም በምክረ ሐሳብ ለጋሽ የምሁራን ቡድኖች ውስጥ በመሳተፍ በአገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ጥናቶችን በማካሄድ ተሳታፊ መሆን ችያለሁ። በዚህኛው መንገድ ደግሞ ውሳኔ ሰጪ የምሆንበት ኃላፊነት መረከቤ የተሻለ መረዳት በመፍጠር በውጪ ሆኖ እንዲህ ቢሆን ብሎ ከመናገር ባሻገር ውስጥ ገብቶ መሥራት ማሳየቱ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የወጣትነት የፖለቲካ ተሳትፎዎ ምን ይመስል ነበር?
ወይዘሮ ጽዮን፡- እኔ እስካሁን ድረስ የየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም። ነገር ግን ፖለቲካ በጣም ደስ የሚል ነገር እንደሆነ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ ሠዎች ፖለቲካን ከውሸት፣ አቋም አልባነት ጋር ያስተሳስሩታል። በተቃራኒው ግን ጥበብ ነው። አስደናቂ የሀገራችን መሪዎችም ይህንኑ አሳይተውን አልፈዋል። ለዚህም ትልቅ ምሳሌ መሆን የሚችለው በቅርቡ የተከበረው የአድዋ ድል በዓል ነው። ይህንን ሳስብ አንዳንዶች ስለ ፖለቲካ በተሳሳተ መልኩ ስያሜ መስጠታቸው ቢያሳስበኝም ዜጎች ለአገራቸው ውጤት ለማስመዝገብ ግን ግዴታ በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ አለባቸው ብዬ ደግሞ አላስብም።
ዜጎች በተሠማሩበት የሙያ መስክ ለአገር የሚጠቅም ተግባር አበርክተው ማለፍ ፖለቲከኞችም ደግሞ ሕዝቡን አስተባብረው በውስጥም በውጪም አገሪቱን ገናና ማድረግ ወሳኙና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። በዚህ ሒደት ደግሞ በአንድም በሌላም መንገድ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አይቀሬ ነው። እኔ ግን በሙያዬ ስለምሠራ ተሳታፊ መሆኔ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ከዚህ ውጪም የሚያሳስቡኝ ማሕበራዊ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ጎዳና ላይ የወደቁ ልጆች ጉዳይ አንዱ ነው።
በግሌም ‹‹ጎዳና ልጅ የለውም›› የሚል እንቅስቃሴ አደርጋለሁ። በዚህም በወር አንድ ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር 200 የሚደርሱ የጎዳና ልጆች ጋር እንበላለን። ይህም በማሕበረሰቡ ውስጥ የፈጠርነውን ‹‹እነሱ እና እኛ›› የሚል ትክክል ያልሆነ ዕይታ ለመቀየር አንድ እርምጃ ነው ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ምንም እንኳ በቤት ውስጥ የሚኖረው ማሕበረሰብ ያልተገባ ስዕል ቢፈጥርም እያንዳንዱ ጎዳና ላይ የወደቀ ዜጋ ግን ወደ ጎዳና የወጣበት ምክንያት ለእኛ አሳማኝ ቢሆንም ባይሆንም የራሱ ታሪክ ግን አለው፤ እኛ ግን የማናውቀውን ታሪክ ፈጥረን ሥያሜ ሰጥተናቸዋል።
ጎዳና ልጅ መውደቁ የእኛ መውደቅ ነው። እኔ ባልወድቅ ኖሮ ጎዳና ላይ ልጆች መውደቅ አልነበረባቸውም። ይህ ደግሞ የእኔ ኃላፊነት ነው። ነገር ግን በእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስብዕና ቀረጻ ላይ ሲሠራም ታሪኩን እኛ ነግረነው ሳይሆን እንደ ዕቃ ሳይሆን የምቀይረው መጀመሪያ እንደ ሠው ተቀራርበን ሊሆን ይገባል። ልጆቹም ጎዳና የሚሰጣቸውን የተለየ ነፃነት በሚጠቀሙበት ወቅት ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዳይወጡ የሚያደርጉ አስቸጋሪ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንገድ ላይ ራሳቸውን ገላቸውን በመሸጥ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ዕድሜያቸው እስከ 14 ዓመት የሚሆኑ አሉ። በመሆኑም መደጋገፉ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።
መርዳት ማለት ወደ መኖሪያ ቤት መውሰድ ላይሆን ይችላል። ይልቁንም መጀመሪያ የተሰጣቸውን ስያሜ ማሻሻል ሲሆን፤ እኛም በሚኖረን የግንኙነት ጊዜ ከልጆቹ ጋር ግንኙነቶችን የሚፈጥሩ ግለሰቦች ይኖራሉ። ለዚህ የሚያግዘን በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው ብራይት ስታር የተሰኘ ድርጅት ነው። በዚህም ምግብ ይዘጋጃል፣ ገላቸውን መታጠብ ይችላሉ፣ ፀጉራቸውን ይስተካከላሉ በዚህ ውስጥም በርካቶችም ያልፋሉ። በሚፈጠሩ ግንኙነቶችም ጎዳና ላይ የወደቁ ልጆች የነገ ሕይወታቸው የተሻለ እንዲሆን የሚሠሩም አሉ።
ከዚህ ባሻገር ሌላ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ሥራ አጥነት ነው። አንዱ ሥራ የማግኛ መንገድ በጎ ፈቃድ ላይ መሳተፍ እንደሆነ አምናሁ። በዚህም በትምህርት ሚኒስቴር በዘርፌ ሥር የተጀመረ አምስት ወራት ያስቆጠረ ‹‹እኛ ለእኛ›› የተሰኘ የበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ስንሠራ ቆይተናል። ለተጎዱ ብሎም ለተፈናቀሉ ዜጎች የትምህርት ቁሳቁስ በማሰባሰብ ብዙ ወጣቶች በዚህ ላይ ተሠማርተው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ለበጎ ተግባራቸውም የምስጋናና ዕውቅና ሠርተፍኬት ሰጥተናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- እነዚን መልካም ተግባራት የተሰጥዎትን ኃላፊነት በመጠቀም እንዴት ሊያሳድጓቸው አስበዋል? ሕዝቡስ ምን ይጠብቅ?
ወይዘሮ ጽዮን፡- በግሌ ሳደርጋቸው የነበሩ ትንንሽ ነገሮች ከሌሎች ሠዎች ጋር በመተባበር የተከናወኑ ናቸው። ሁሉንም ነገር እኔ ብቻ መሥራት አለብኝ ብዬ አላስብም። መንገድ ማሳየቱ ግን ብዙዎችን በመልካም ተግባር ላይ እንዲጓዙ ለማድረግ ያስችላል። ሴቶችን በተመለከተ አርዓያ በመሆን፣ በራስ መተማመን የሚያመጡ ተግባራትን ማከናወን ይገባል፤ ማንም ሠው በሕይወቱ በመጥፎ ጎዳና ሊያልፍ ይችላል፤ ነገር ግን ጎትቶ እንዳያስቀረው መጣሩ ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች ይህንን ተገንዝበው ወደ ፊት እንዲጓዙ ማድረግ፣ በየትኛውም አጋጣሚ የሥራ ዕድሎች ሲፈጠሩ ለማገናኘትና መሠል ተግባራትን ለማከናወን አቅጃለሁ።
በተጨማሪም ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ልጆች እንዴት የዕውቀት ማዕድ ሊቋደሱ ይችላሉ? በሚል ይሠራል፣ የካንሠር ሕሙማን የሆኑ ተማሪዎችም ሕክምናቸው ተፅዕኖ ሳይፈጥርባቸው ትምህርታቸውን ሊከታተሉ በሚችሉባው ሁኔታዎች ላይ፣ የንባብ ባሕል ማዳበር እንዲሁም ሌሎች በርካታ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ለማከናወን በዕቅዴ አካትቻለሁ። ሕዝቡም ከእኔ በትምህርት ዘርፉ ለውጥ ይጠብቅ። በተለይም በአገሪቱ እንዲሁም ከባህር ማዶ የሚገኙ በርካታ ለትምህርት ዘርፉ ልባቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ለትምህርት ጥራት የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸውን አሰራር በመዘርጋት ረገድ የራሴን ድርሻ እወጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በማሕበረሰቡ ዘንድ በፆታ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች አንድም ሴቶች ለራሳቸው ከሚሰጡት የተሳሳተ ቦታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም ትክክለኛ መፍትሔ ለማበጀት ችግሩን ማወቅና መለየት አስፈላጊ ነውና ምንጮቹ ምንድን ናቸው? መፍትሔዎቹስ ምን መሆን አለባቸው ይላሉ?
ወይዘሮ ጽዮን፡- ችግሮቹ የሚመነጩት ከሥብዕና በመሆኑ በሴቶች ላይ ግንባታ መሥራት ይገባል። ሴቶች በራስ መተማመንን ማጎልበት አለባቸው። ችግሮቹን መፍታት የሚቻለውም በመጣላት ሳይሆን በመልካም መንገድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በመልካሙም መንገድ ጋሬጣዎችን ማንሳት የሚቻለው ሴቶች በራስ መተማመን ሲኖራቸው ነው። አልያ ግን ከመጀመሪያው ሴቶች ራሳቸውን ተጠቂ እንደሆኑ ካሰቡ ቶሎ ለችግሮች ይጋለጣሉ።
ሴት ስለሆንኩ ሌሎች አይቀበሉኝም በሚል መጮህ አልያም መሳደብ ሳይሆን በምክንያት ማስረዳት መቻል ተቀባይነት እንደሚያስገኝ ማመን ይገባል። ብዙ ጊዜ ሴቶች ኃላፊነት ቦታ ላይ ሲቀመጡ ወንድ መሆን ያለባቸው ይመስላቸዋል። በዚህም ገና ለገና እጠቃለሁ በሚል እሳቤ አመራር ሰጪነት ላይ ያሉ ወንዶች ሲሳደቡ ከሰሙ እነርሱም ይሳደባሉ አልያም ሌሎች ያልተገቡ ባህርያትን ያሳያሉ። ያልነበረ ፀባይን ለማምጣት የሚደረገው ጥረትም ጎልቶ ይስተዋላል። በዚህም ሴቶች ትልቅ የአመራር ሰጪነት ቦታ ላይ ሲቀመጡ ላይቀበሉኝ ይችላሉ ከሚል ስጋት ወንድ መሆን አለብኝ በማለት ነገሮችን ከሚገባው በላይ መከላከልና ኃይለኛ ለመሆን መሞከር አስፈላጊ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ብሳሳትስ ከማለት ይልቅ ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮች በመጋፈጥ ብሎም ፍላጎታችንን በግልጽ በማሳወቅ መንገዳችንን ማቅናት ይኖርብናል።
በኃላፊነት ላይ ሴቷ የምታሳርፈውን ውሳኔ የማይቀበሉት ወንዶች ብቻ ተደርጎ መወሰድም የለባቸውም። ምክንያቱም የማይቀበሉት ሴቶችም ናቸውና። ይህም ራሳችን ለራሳችን የምንሠጠውን ቦታ ሌሎች ላይ እንደምናንፀባርቅ ማሳያ ይሆናል። በተያያዘ ሴቶች ላይ የሚያጋጥሙ ጥቃቶችም የሚደርሱት በወንዶች ብቻ ሳይሆን በራሳቸው በሴቶችም ጭምር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚገኙ ዕድሜያቸው ለተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ያልደረሱ ሴቶችን አደራድረው ለወንዶች የሚያቀርቡት ሴቶች ናቸው። በመሆኑም ሴቶች ለሴቶች ኃላፊነት እንዳለብን ተረድተን ደራሽ መሆን አለብን።
ራዕይ፣ ሐሳብና አቋም ፆታ የላቸውም። ባለ ራዕይ ዜጋን ሌሎች ይከተሉታል። ማንም ይሁን ማን አሸናፊና ገዢ የሆነ ነገር ይዞ ሲቀርብ ማስረዳት ሲችልም ሁሉም ወደ መስመሩ ይገባል። በመሆኑም ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ማወቅ ይገባል። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች በውጭ የሚኖሩ ሴቶች በሚጓዙበት መንገድ መሄድ ውጤት አያመጣልንም። ባደጉት አገራት የሰለጠኑ ሴቶች ያደርጉታል ብለን እንደምናስበው ቤተሠብን መበተን እንደ ኩራት የሚመለከቱ ሴቶች አሉ። ይህ ደግሞ የተሳሳተ አመለካከት ነው። በመሆኑም በተፈጥሮ የተቸሩንን ነገሮችን ረጋ ብሎ መመልከት አገናዝቦ መጓዝ የበታችነት አይደለም፤ ሠዎች ይህንን ለማዳበር ሠዎች ትምህርት ቤት ገብተው እንደሚማሩ መረዳትና ያሰብንበትን ዓላማ እንዴት መድረስ እንደምንችል ማጤን ይገባል። በሌላ በኩል ሥራ ባለመቻሏ ለመባረሯ ፆታዋን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ሠርቶ በማሳየት የሚፈጠሩትን ጎራዎች መስበር ትችላለች። ችግሩን ብቻ ከማውራት በጎ ጎኑንም ማጉላት የመፍትሔው አንዱ አካል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሴቶች በሰፊው ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በፖለቲካውም ተሳታፊ ሆነው ይታያሉና ይህ በቂ ነው ብለው ያስባሉ?
ወይዘሮ ጽዮን፡- በፌዴራል ደረጃ በሚኒስትርነት ማዕረግ ሴቶች ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እየሰሩ ቢሆንም፣ ታች ሲኬድስ ብሎ መጠየቅ ግን ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶች ላይ ቢፈተሸ ሴቶች የሚመሯቸው ተቋማት ውጤታማ ሆነው ይታያሉ። ይህም ሴቶች ከመኖሪያ ቤታቸው ጀምሮ የአመራር ቦታን ሲይዙ፣ በትምህርት ሲታገዙና ውሳኔ ሰጪ ሲሆኑ የተሻሉ ውጤቶችን ማየት እንችላለን።
ሴት ልጅን ማስተማር ቤተሠብን በሙሉ እንደማስተማር ነው። የተማረች ሴት መፍጠር ለተሻለ ዜጋ የሚኖረው ድርሻም የላቀ መሆኑ መዘንጋት አይገባም። ይህም መልካም ብቃታቸው በየቦታው ይታያል። በመሆኑም እኩል ዕድል ማመቻቸትና ከታች ጀምሮ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረጉ ላይ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉትና ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ወይዘሮ ጽዮን፡- ሴቶችም ወንዶችም ልጆች ይበርቱ። ትውልድ ለዚህች ምድር ለራሱ ሲል ጥሩ ውሳኔ ላይ የሚደርስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ በግራም በቀኝም ስንዞር የምንመለከታቸውን ትክክል ያልሆኑ ነገሮች ለማስተካክል ሁላችንም ብንሠራ በሌሎች አገሮች መቅናትና ስደት አቁመን ስለ ኢትዮጵያ ብዙ የምንናገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ስለሆነም ሁላችንም ስለ ትውልዱና አገራችን ኃላፊነት እንዳለብን ተገንዝበን ለዕድገታችን መትጋት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ሆነው ጊዜዎትን ስለሰጡን እናመሰግናለን!
ወይዘሮ ጽዮን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
ፍዮሪ ተወልደ