
ዓለም በኮርኖ ቫይረስ (ኮቪድ–19) ተላላፊ በሽታ ምክንያት ችግር ውስጥ ገብታለች ሲል የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል:: ድርጅቱ ለኮርኖ ቫይረሱ ኮቪድ–19 የሚል ስያሜ ሰጥቷል::
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ቫይረሱ የተለየ ቢሆንም ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የሟቾች ቁጥር ከ3000 በላይ ያለፈ ሲሆን አብዛኛው ከቻይና ነው:: ባለፉት ቀናት ቻይና ውስጥ ካለው ይልቅ በውጭ ሀገራት ዘጠኝ እጥፍ አዲስ ኢንፌክሽኖች መታየታቸው ተገልጿል::.
ዶክተር ቴዎድሮስ ይህን ቫይረስ መክተን መመለስ አለብን፤ ከበሽታው የበለጠ ደግሞ አደገኛው መገለል ነው ብለዋል:: ዋና ዳይሬክተሩ የዓለም የጤና ድርጅት ለቫይረሱ ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ የሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮርኖ ቫይረስ የአንድ ቀጥተኛ መንገድ ጉዞ አይደለም:: ሀገሮች እጅግ በጣም ፈጥነው ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተንቀሳቀሱ አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰዱ ቫይረሱን መዋጋት ይቻላል:: አሁኑኑ እርምጃ ከመውሰድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል:: ከቻይና ውጭ አንዷ ክፉኛ የተጎዳችው ሀገር ኢጣሊያ ስትሆን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ34 -52 ደርሷል::
ዶክተር ቴዎድሮስ እያንዳንዱ ሀገር የየራሱን ሁኔታ በተለይ መመልከት ያለበት መሆኑን ወረርሽኙን ለመግታት ያለው መንገድ አንድ አይነት መንገድ ብቻ አለመሆኑን ተናግረዋል:: እያንዳንዱ ሀገር የየራሱ አቀራረብ ሊኖረው ይገባል መጀመር ያለበት ግን የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠርና የግድ ከመግታት ነው ብለዋል:: ይህ ቫይረስ የተለየና የተለየም ምልክቶች ያሉት መሆኑን ገልጸው፤ የዓለም ጤና ድርጅት በስፋት ይዛመታል ብሎ የጠበቀ ቢሆንም የመከላከያ እርምጃዎቹ እየሰሩ ነው ብለዋል::
የቫይረሱ ወረርሽኝ መገኘት ሪፖርት ከተደረገባቸው 62 ሀገራት ውስጥ 38 ያህሉ 10 እና ከዛም ያነሰ ነው የታየባቸው:: ስምንት ሀገራት ቫይረሱን በተመለከተ ለ2 ሳምንታት አዲስ ሪፖርት አላቀረቡም:: የተዛመተውን የኮርኖ ቫይረስ ወረርሽኝ መግታት ችለዋል:: በቻይና ወረርሽኙ በከፍተኛ ቁጥር የሚገኝ ቢሆንም መቆጣጠር እንደሚቻል አሳይታለች ብለዋል – ዶክተር ቴዎድሮስ::
የዓለም ጤና ድርጅት ይህ በሽታ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተብሎ ይጠራ አይጠራ ብሎ ለመወሰን በቅርበት እየተከታተለና እየተቆጣጠረ መሆኑን ዋናው ዳይሬክተር መግለጻቸውን ቢቢሲ በዘገባው ገልጿል::
ደቡብ ኮሪያ፤ ኢጣሊያ፤ ኢራን፤ ጃፓን በትልቁ የቫይረሱ አደጋ የተጋረጠባቸውና አሳሳቢ ሀገራት ሆነዋል:: በኢራን የዓለም ጤና ድርጅት አባል የሆነ ሰው ተመርምሮ በሽታው ተገኝቶበታል፤ ምልክቶቹም ከባድ ናቸው ብለዋል-ዶክተር ቴዎድሮስ:: አክለውም ማግለል እውነቱን ለመናገር ከበሽታውም የበለጠ አደገኛ ነው:: ይህንን እናስምርበት ማግለል እጅግ በጣም አደገኛ ጠላት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ሲታይ በ70 ሀገራት ውስጥ ከ90ሺ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተመዘገቡ ሲሆን ዋናው ከ90 በመቶ በታች ያለው ቻይና ውስጥ ነው:: አብዛኛዎቹ ሁቤይ ግዛት ውስጥ ሲሆኑ ቫይረሱ ባለፈው ዓመት የተገኘበት ዋናው ቦታ ነው:: ወደ 8ሺ800 በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ከቻይና ውጭ ሲሆኑ 81 በመቶው በአራት ሀገራት ውስጥ ነው:: እነሱም ኢራን፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ኢጣሊያና ጃፓን ናቸው::
በኢጣሊያ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠባቸው አንድ ሺ 835 ሰዎች ውስጥ 18 ሞተዋል:: አብዛኛዎቹ በሰሜን የሎምባርዲና የቬንቶ አካባቢ ነዋሪ ናቸው:: ኢራን ተጨማሪ 12 ሰው በቫይረሱ መሞቱን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን፤ የሟቾቹን ቁጥር 66 አድርሶታል:: በኢራን ከሞቱት ውስጥ የሀገሪቱ መሪ የሆኑት አሊ ኮሚኒ አማካሪ የሆነው ሞሀመድ ሚር ሞሀመዲን እንደሚገኝበት የኢራን ሚዲያ ሪፖርት አድርጓል::
በዋሽንግተን የሚገኙ የአሜሪካ መንግስት የጤና ባለስልጣናት ተጨማሪ አራት ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል:: በአሜሪካ በቫይረሱ የሞቱትን ቁጥር 6 አድርሶታል::
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፋርማሲዩቲካል ኩባንያዎች በአስቸኳይ ለቫይረሱ መድኃኒት የሚሆን ክትባት ለማግኘት ስራቸውን እንዲያፋጥኑ የነገሯቸው መሆኑን ገልጸዋል:: የኒውዬርኩ ገዢ አንድሪው ኩሞ በከተማዋ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ፖዘቲቭ ሆነው መመዝገባቸውን በመናገር አሳሳቢነቱን አስጠንቅቀዋል:: በእንግሊዝ 39 በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች አሉ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮብራ ኮሚቴን አስቸኳይ ስብሰባ መርተው ከጨረሱ በኋላ ቫይረሱ ወደፊት ባሉት ቀናትና ሳምንታት አሳሳቢ እየሆነ ይሄዳል ሲሉ ተናግረዋል::
ፖርቹጋል፤ አይስላንድ፤ ጆርዳን፤ ቱኒዚያ፤ አርመኒያ፤ ላቲቫ፤ ሴኔጋልና አንዶራ ባለፈው ሰኞ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ግዜ መኖሩን ማረጋገጣቸውን ሪፖርት አድርገዋል:: የአውሮፓ የበሽታዎች መከላከያ ማእከል የበሽታው አሳሳቢነትና የአደጋው ደረጃ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አረጋግጧል:: ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ከ2009 (እኤአ) ጀምሮ የቫይረሱ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ማደጉን የኢኮኖሚ ትብብር ለእድገት የተባለው ድርጅት በመግለጽ አስጠንቅቋል:: ገበያዎች በአውሮፓ ተቀዛቅዘዋል:: ኳታር፤ ኢኳዶር፤ ሉክዘምበርግ፤ ቼክ ሪፐብሊክና አየርላንድ ላይ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የቫይረሱ የመጀመሪያ ምልክት ተመዝግቧል::
በደቡብ ኮሪያ በቫይረሱ የሞቱት ቁጥር 28 ደርሷል:: ከሀገሪቱ 60 በመቶ ከአራት ሺ በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ የተያዙት ሺንቺኦኒጂ የጂሰስ ቤተክርስቲያን የኃይማኖት ክፍል አባላት ናቸው:: አባላቱ አንዱ ሌላውን እንዳስያዘውና በሀገሪቱ አካባቢ ሳይታወቅ ይዘዋወሩ ስለነበር መዛመቱ ይታመናል::
ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን ብዙ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ሲሉ የ88 ዓመት እድሜ ያላቸው መሪ ተናግረዋል:: ለመከላከል የመጨረሻውን ጥረት ያደረግን ቢሆንም አልቻልንም ብለዋል:: የደቡብ ኮሪያ አቃቤ ሕግ የቤተክርስቲያኑ መሪ የሆኑት ሚስተር ሊ በቫይረሱ ዙሪያ ግዴለሽነትና ቸልተኝነት በማሳየታቸው ክስ እንዲመሰርትባቸው ጥያቄ ቀርቦለታል::
በቻይና ተጨማሪ 42 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል:: የሞቱት በሙሉ ከሁቢ ግዛት ነው:: ግዛቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ በዓለም ደረጃ 90 በመቶ ሞት የተመዘገበበት ነው:: በቻይና አዲስ የተመዘገቡት ስምንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከሁባይ ግዛት ውጭ ሲሆኑ መቆጣጠር ተችሏል:: ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ቫይረስ በዓለም ዙሪያ እየተሰራጨ ሲሆን ሳይንቲስቶች አፋጣኝ ክትባት(መድኃኒት) ለማግኘት ስርጭቱንና ቫይረሱን ለማስቆም ያለእረፍት እየሰሩ ይገኛሉ:: ይህ እጅግ አስደንጋጭና አስፈሪ በሆነ ደረጃ በዓለም ዙሪያ እየተዛመተ የሚገኘው ኮቪድ-19 የተባለው ቫይረስ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚውን የንግድ ልውውጥና የግብይት ስርአቱን አናግቶታል:: ድፍን ዓለምን ግራ ያጋባና ያስጨነቀ መድኃኒት አልባ ቫይረስ ሆኖ ቀጥሏል::
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2012
ወንድወሰን መኮንን