.የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም መያዙ ተጠቆመ
- ረቡዕ የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፡- የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) በሚል በአገሪቱ የሚስተዋለው ቁማር እንዲቆም ከስምምነት መደረሱን የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሲገልፅ፤ የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ግን በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም መያዙ ተጠቁሟል፡፡
በሚኒስቴሩ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ሠይድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የስፖርት ውርርድ በሚል የሚካሄደው የቁማር ጨዋታ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አጀንዳ ካደረገው ጀምሮ ለሁለት ወራት በተሠራው ተከታታይ ሥራ የቁማር ጨዋታው እንዲቆም ተወስኗል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ 26 አባላትን ያቀፈ የፌዴራል የአሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ኃይልና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ የሆኑበት መድረክ በማዘጋጀት የስፖርት ውርርድ ቁማር በዜጎች ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አጠቃላይ ችግሮች ላይ የሚያደርሰው ችግር ተፈትሿል፡፡
ዳይሬክተሩ ‹‹በወቅቱ በተደረገው መድረክ የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጣንለት አዲስ የመዝናኛ ቴክኖሎጂ ነው›› ማለቱን አስታውሰው፤ ግብረ ኃይሉና በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ድርጊቱ ቁማር እንደሆነ ለአገር ፀር መሆኑን አምነው እንዲቆም መግባባት ላይ ቢደርሱም፤ አስተዳደሩ ግን ለሕዝቡ መዝናኛ ቴክኖሎጂ ነው በሚል በአቋሙ መፅናቱን ገልፀዋል፡፡
ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ያለውን ገደብ የሕግ ማሻሻያ እንደሚደረግና ውርርዱ ግን ሊቀጥል እንደሚገባ አቋሙን እንዳራመደ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ የስፖርት ውርርድ ቁማር እንጂ ቴክኖሎጂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ሕዝቡ እንደማይጠቅመው እየተናገረ ብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ይህን መሰል አቋም መያዙ ለሕዝብ የተቋቋመ ድርጅት ቢሆንም እንኳ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን የሕዝብ ውግንናው አጠራጣሪ ነው፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ዝግጁ አይደለም›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሻው በርካታ ቴክኖሎጂ መኖሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዜጎች መንግሥትን የሚጠይቁት የዳቦ፣ የዘይት፣ የወጣቱን ዕውቀትና ክህሎት የሚያዳብሩና ሥነ ምግባራቸውን ሊገነባ የሚችል እንዲሁም መሰል ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበትን ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ ውርርዱ ግን ጭርሱን የዜጎችን ዳቦ መግዣ የሚቀማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ዜጎች ወር ጠብቀው የሚያገኙትን ደመወዛቸውን የሚቀማ በሚሊየኖች ኪሣራ ጥቂቶች የሚከብሩበት፣ ዜጎች ከፈጣሪነት ይልቅ ሳይሠሩ መክበርን የሚያስተምረውን ይህን የቁማር ተግባር ምንም እንኳ አስተዳደሩ መዝናኛ ነው ቢልም ቁማር ግን መዝናኛ ሊሆን እንደማይችል፤ ይልቁንም ከቤተሰብ አልፎ ለአገር ፀጥታም ሥጋት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በተከናወኑ ጥናቶች ጉዳዩ በጣም አሳሳቢና በተለይ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን የሚጎዳ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ በተመሳሳይ ለአገሪቱ የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ያልሆነው ይህ ቁማር ባህልን፣ እሴትን እንዲሁም ሃይማኖትንም የሚፃረር ነው፡፡ በዚህም የሃይማኖት አባቶች ያወገዙት፣ ተጠቂ የሆኑ ሚስቶች እንዲሁም ወጣቶች ሱሰኛ እንደሆኑና መንግሥት እንዲያስቆምላቸው እየጠየቁ አስከፊነቱን እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ዳይሬክተሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ባለመረዳት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ እንደሚስተዋሉ በመጠቆም፤ ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታች ወረዳ ድረስ የሚገኙ መዋቅሮችን በመጠቀም ሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በጥናት የተደገፈ መረጃ እየተደራጀ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ፈቃድ ሰጪ ሆኖ በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ቀርቦ ጉዳዩ እንዲታይና ሕጉ ማሻሻያ እንዲደረግበት እንደሚቀርብ፤ ማሻሻያ የሚደረገው ግን ሚኒስቴሩና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሙሉ በሙሉ እንደማያስፈልግ ባሳዩት ዕምነት መሠረት የሕዝቡን ጥቅም ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በጥር ወር ውስጥ ለስፖርት ውርርድ በሚል ይሰጥ የነበረው ፈቃድ የቆመ ሲሆን፤ አይጠቅምም ተብሎ ከተወሰነ በሥራ ላይ የሚገኙት አቋማሪ ድርጅቶች የውላቸው ጊዜ እስኪጠናቀቅ ብቻ ሊቆዩ እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሷል፡፡ በዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በተለይ ወጣቶችና ሕፃናቶችን የሚጎዳ ድርጊት እንደሆነም ምክር ቤቱ አምኗል፡፡ ስለሆነም ሂደቱ ተጠብቆ የሚመለከታቸው አካላት ደረጃ በደረጃ ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሣይንሳዊና ሌሎች አገራትም እንደ መነሻ ሊወስዱት የሚችሉት አገር አቀፍ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ በሁለት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በችግሩ ተጠቂ የሆኑ አካላት የተካተቱበት ጥናታዊ ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) እየተሠራ ነው፡፡
በክልል የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ፈቃድ አሰጣጡን እንዲመረምሩ፣ ያልጀመሩት ደግሞ ከክልል ፕሬዚዳንቶች ጀምሮ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ፈቃድ አሰጣጡን እንዲያጤኑና ፍቃድ እንዳይሰጥ መግባባት ላይ መደረሱን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት በመጀመሩ ይዋል ይደር እንጂ ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ፍዮሪ ተወልደ