እኛን ኢትዮጵያውያንን ለዓለም ህዝብ በሰፊው ካስተዋወቁን ክስተቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአድዋ ድል ነው። ይህ ላይደበዝዝ የደመቀው የኛ ታሪክ አንተ ባትፈልገውም በወርቃማ ቀለም የተፃፈ ማንነትህን የሚያፈካልህ ጌጥ ነው። ይህ በውብ ቀለም ተፅፎ ጥቁሮችን ያደመቀ ብርሃን ነው። የአድዋ ድል “የኔ አይደለም” ብትልም ማለት እንዳትችል የሚያደርግህ ብዙ ሁነቶችን አምቆ የያዘ ታሪክህ ነው። አድዋ ህልም የመሰለ የደመቀ ድል የተዋበ እውናዊ ክስተት ነው። አዎ የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ መኩሪያና መመኪያ የሆነ ታላቅና ዘመን የማይሽረው ጀብድ ውጤት ነው።
አድዋ አባቶችህ በደማቸው የፃፉት የዘመኑ ትንግርት፤ የዚያን ወቅት ተዓምር፤ የእኔና የአንተ ዘመን ትንግርት ነው። ልንገርህ “አድዋ በሆነ ዘመን እንዲህ ሆኖ ነበር “ተብሎ የሚወራ ተረት አይደለም። በእውን የታየ ታላቅ ገድል፤ ስለ ሀገር በተሰጠ ህይወት የተጠበቀ ክብር፤ የሰው ልጅ ደምና አጥንት ትሩት እንጂ፤ አድዋን ያለመለመው፤ ያ ምድር ያበቀለው አንተም ዘርተህ የቃምክበትን፤ ወልደህ የሳምክበትን ሀገር ያቆመው ያ ታሪክ ነው።
አድዋ ፈጠራ አይደለም። ሲነገር የሚደንቅ፤ ሲወራ የሚያስገርም የጥቁሮች ቋሚ የነፃነት በር የሀገር ፍቅር መስዋትነት ውጤት እንጂ! ዛሬ የተዛባ ትርክት ለውጦህ አሊያም ትላንትን የማያይ ስሜት አስክሮህ “የኔ አይደለም” ብትልም አንተን ዛሬ ላይ የሚያኮራህ የአያትህ ገድል ነው። ማያህ ተነጥቆብህ “አያገባኝም፤ ምኔ ነው” ብትለውም ቅድመ አያቶችህ ብዙ የሆኑበት የአንተ ብዙ ነገር ነው።
መቼም ወገን ከዚህች ምድር መብቀልህን አትክድም አይደል? አዎን! የዚህች ሀገር ፍሬ መሆንህን ካመንክ ለዚህ ምድር የተዋደቁ ጀግኖች፤ አልደፈር ባይ አባቶች ደምና አጥንት የተቀላቀለበት በመሰዋዕትነት የፀና መሆኑን ሳትወድም የምትቀበለው እውነት ነው። “ስለ አድዋ ምን ገዶኝ” ያልከው ባይገባህ እንጂ ላንተ የተገባ ብዙ ገቢር መሆኑ በተገለፀልህ ነበር። አድዋ ማለት “ማን ነህ?” ስትባል በኩራት የምትናገረው የማንነትህ ልዩ ታሪክህ ነው።
ይህቺ ሀገር የሚዋደቁላትን ብዙ ልጆቿን ያህል ባይሆኑም ከማህፀንዋ የፈሩ ጠላቶችም በየዘመናቱ አላጣችም። ከስዋዊ ተፈጥሮ እሷን የሚያጠቃ ከርሷው ተገኝቶ የእርሷን መኖር የማይወድ ጉደኛ ልጅም ታቅፋለች። እነዚህን ከጠላት ጋር አብረው የወጓት፤ ከሌላ ጋር ሆነው የተጫኗት በትጉህ ልጆቿ መክነው ቀርተዋል። ስለ ኢትዮጵያ በተዋደቁ፤ ስለ ሀገራቸው በተጋደሉ፤ እራሳቸውን በሰጡ የበዙ ፍሬዎቿ እንክርዳዶቹ ከስመዋል። ያኔም አድዋ ላይ ከጠላት ወገን ሆነው የወጓት አርበኞችን የተፈታተኑ ባንዳዎች አልጠፉም ነበር።
እርግጥም ሀገርህ ያኔም እንደዛሬው እዚህም እዚያም የሚከሰቱ አለመግባባትና ንትርኮች ላይ ነበረች። ነገር ግን ሁሉም ስለ ሀገሩ መወረር ሲሰማ፤ ስለ ኢትዮጵያ መጠቃት ሲነገረው ከመሪው ሲደርሰው ከራስ ፍላጎት ሀገርን አስበልጦ፤ ከግል ጥቅም ይልቅ ኢትዮጵያን ብሎ በአንድነት ለድል ዘምቷል። ሀገሩን ካስቀደመ የውስጥ ችግሩ በቀላሉ ሊቋጭ የሚችል መሆኑ ገብቶት የሚቀድመውን አስቀድሞ እራሱን ከፍሏል።
መዛግብትን አገላብጥ ወዳጄ! በውስጥ ጠላት የተፈተነው አያትህ ስለ አገርህ ብዙ ሆኗል። ትላንትን ተመልከት ወገንህ ስለዚህች ምድር እራሱን ገብሯል። ቁጥሩ ውስን የሆነ ኢትዮጵያዊም ከጠላት ጋር ተሰልፎ መዋጋቱን ሳንፈልግም የተጋትነው አሳፋሪ ዜና ነበር። እነዚህ አገርን የካዱ፤ የግል ወገናቸውን ያጠቁ መጨረሻቸው ሽንፈት ነበር።
አድዋ ላይ ከጠላት ጎን ተሰልፎ ወገኑን ለመውጋት የተዘጋጀ ተው ሀገርህን አስብ ካልሆነ ግን አይቀጡ ቅጣት ትቀጣለህ ተብሎ ታውጆ ነበር። አዋጁን ያከበረ ቢበዛም ከጠላት ጋር የተሰለፈ የጠላት እጣ ገጥሞታል። ሀገራዊውን ጥሪ ትተው ከጠላት ወገን ሆነው የተዋጉ የተወሰኑ ሱዳኖችን ጨምሮ ቁጥራቸው እስከ 6000 (ስድስት ሺህ ) እንደሚደርስ በበርካታ መፅሀፍት ላይ ተገልፆ እንደሚገኝ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መፅሐፋቸው ስለዚህ መራራ እውነት ይተርካሉ።
እነዚህ ከኢትዮጵያ አብራክ የወጡ ሀገራቸውን በጥቅም የካዱ ግለሰቦች በጦርነቱ ተዋግተው ብዙ ኢትዮጵያንን ፈጅተዋል። የነጩ ወታደር በመንገድ፤ በረሀብና በውሃ ጥም እየደከመ ውጊያ ላይ ሲደክም እነርሱ በብርታት እየተዋጉ በብዙ ወገኖቻቸው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሰዋል። በመጨረሻ ድሉ የኢትዮጵያን ስለሆነ ከሞቱት ውጪ የተማረኩት ዳግም ሞት ሞተዋል ሊያውም ከፍ ያለውን የመንፈስ ሞት፤
ስለ ሀገር ተብሎ ምንም ይተዋል፡፡ ሀገር እንድትቆም ሰው ይወድቃል። ለዚህ ደግሞ አድዋ ምስክር ነው። ዛሬ ሀገርህ እድትቆም የራስህን ስሜት ግዛና የወገንህን ፍላጎት ኑር። ኢትዮጵያዊ ዛሬ የራበው ፍቅር፤ የጠማው አንድነት ነው። የበዛ መለያህ ላይ በራስህ ባህልና እምነት እያደርክ አንድ አድርጎ የሚያቆምህን ፍቅርህን በሚያፀናልህ ሀገራዊ አንድነት ላይ ጠንክር።
በአድዋ የተገኘው ድል አንድ የመሆን ውጤት ነው። መለያየት አቅምን ያለሽባል፤ መነጣጠል ጉልብትን ያብረከርካል፤ እልፍ ዘመናትን አንድነቷን የጠበቀች ሀገር ምክንያት አልባ በሆነና ውሀ በማይቋጥር እንዲሁ ዘራፍ በሚያሰኝ ጊዜያዊ ስሜት ላፍርስ ማለት ጤናማነት አይደለም። በአንድነት ጥላ ስር የጋራ ቤታችንን ማነፅ ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ይለናል። ከየትም የሚመጣን ጠላት ድል ማድረግ የምንችለው በህብረት መቆም ስንችል ብቻ ነው።
ወገን አድዋን እየዘመርክ አንድነትህን ብታፀና መልካም ነው። ዳሩ ግን፤ “አድዋ ምኔ ነው” እያልክ እውነቱን ብትክድም አድዋ ማለት ቅድመ አያትህ ስለሀገርህ ሲል የተዋደቀበትና እራሱን የሰጠበት መሆኑን መካድ አትችልም። ይልቅ ወገን ዛሬ አንድነትህን አጠንክረህ ከወገንህ ጋር ተከባብረህ በመኖር በላቀ ፍቅር ጀግን! አድዋ የአንድነት ማሳያ ድል ነውና አንድነታችንን አፅንተን የጋራ ጉዳያችን ላይ ተነጋግረን፤ ተቻችለን ሀገራችንን እንጠብቅ አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ተገኝ ብሩ