በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ሀገራቸው በእውቀት እንድትመራ ብዙ የለፉ ናቸው። ፖሊሲ በማውጣት፣ የምርምር ሥራ በመስራት፣ የጠቅላይ ሚንስትሮች ልዩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል። በሰው ሀብት አቅም ግንባታ ስራ ላይ ብዙዎችን አስተምረው በማብቃት በዘርፉ አንቱታን ያተረፈ አሻራቸውን አኑረው አልፈዋል – አቶ ነዋይ ገብረአብ።
ክፉ ነገር ከአፋቸው የማይወጣ፣ በፍቅርና በማግባባት ስራን የሚሰሩና የሚያሰሩ አመራር እንደነበሩም አብረዋቸው ያሳለፉ የስራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ። አቶ ነዋይ በህይወት ዘመናቸው ለሶስት ዘመን በሙያና እውቀታቸው የሰሩትን ስራ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አንስተን ለዛሬው የ‹‹ህይወት እንዲህ ናት አምድ››እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ!
ከውልደት እስከ ዕድገት
ምድሪቱ በተፈጥሮ አበባ እና ልምላሜ ደምቃና ተንቆጥቁጣ በምትታይበት ወር ለቤተሰቡ ልዩ አበባ በመሆን ይህችን ዓለም የተቀላቀሉት አቶ ነዋይ ገብረአብ ጥቅምት 17 ቀን 1934 ዓ.ም ነው። በቀድሞው የትግራይ ጠቅላይ ግዛት በአድዋ አውራጃ ልዩ ስሙ ማይምሻም በተባለ ስፍራ ከአባታቸው ከአቶ ገብርአብ ቢያድግልኝ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ኢሌኒ መንገሻ አብራክ ተገኝተዋል። በህጻኑ መወለድ የተደሰቱት ቤተሰቦችም አንተ ልዩ የፈጣሪ ስጦታ ሀብታችን ነህ ሲሉ ነዋይ ብለው ስም ሰጧቸው። እንኳን ለቤተሰባቸው ለሀገራቸውም በምጣኔ ሀብት ባለሙያነታቸው ሀብት ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ነዋይ በገጠር ይወለዱ እንጂ እድገታቸው ግን የተመሰረተው በአዲስ አበባ ነው። ከወላጆቻቸው ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ጋር ተያይዞ የእሳቸውም ዕድገት በዚሁ ከተማ ላይ ተመሰረተ።ትምህርታቸውን “ ሀ “ ያሉት በአባታቸው እጅ ፊደል ቆጥረው ነው። ከዚያ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስፋወሰን ትምህርት ቤት አደረጉ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ደግሞ በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት በኋላም ኮተቤ ተብሎ በተሰየመው ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረዋል። ይህንን የክፍል ደረጃ በጥሩ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ።
በ1954 ዓ.ም በምጣኔ ሀብት የዲግሪ ፕሮግራም ከመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች አንዱ ነበሩ። ባገኙት የትምህርት እውቀት ሀገራቸውን እያገለገሉም የትምህርት ጥማታቸውን ለማርካት ሌሎች መንገዶችን ማማተር ቀጠሉ። ዕድል አግኝተውም በቀጥታ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አመሩ። በ1958 ዓ.ም ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በምጣኔ ሀብት በድህረምረቃ በዲፕሎማ ተመረቁ። ቀጥለውም በ1975 ዓ.ም ከታዋቂው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አገኙ። ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና አለምአቀፍ ተቋማት ዲፕሎማዎችና ሰርተፍኬቶችንም አግኝተዋል።
የስራ ላይ ቆይታ
ከ1954 እስከ 1958 ዓ.ም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ባለሙያ በመሆን ሥራቸውን ሀ ብለው እንደጀመሩ የሚነገርላቸው አቶ ነዋይ፤ በፕላን ኮሚሽን የእርሻ ክፍል ተጠባባቂ ሀላፊ ሆነውም አገልግለዋል። ከዚያ ቀጥሎም ‹‹የመካከለኛው ምስራቅ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ/MEED/ በተባለ የመካከለኛው ምስራቅ የገበያ የውል ጉዳዮችን የሚተነትን በለንደን የሚታተም ወርሃዊ መጽሔት ዝግጅት ክፍል አማካሪ በመሆን ሰርተዋል።
አቶ ነዋይ በ1972 ዓ.ም ደግሞ ‹‹UNCTAD›› በተባለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚክስ ኦፊሰር በመሆን ሰርተዋል። በተመሳሳይ ከ1972 እስከ 1975 ዓ.ም ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት ወይም ዩኔስኮ ተቀጥረው በሌሴቶ የትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የትምህርት እቅድ አማካሪ በመሆንም ነው ያገለገሉት። ከ1976 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አማካሪ በመሆን የሰሩት እንግዳችን፤ ከ1980 እስከ 1981 ዓ.ም የአለም ምግብ ድርጅት ኒው ጊኒ በነበረው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት የግብርና የሰው ሃይል ልማት ስልጠና ቡድን መሪም ነበሩ።
ሥራ ሰለቸኝ ደከመኝ የማያውቁት አቶ ነዋይ ፤ ከ1982 እስከ 1983 ዓ.ም ደግሞ ወደ ጣሊያን ተጉዘው ሮም በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት የግብርና ፖሊሲ ፕሮጀክት አስተባባሪ በመሆን በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል።
አቶ ነዋይ ለአገራቸውና ለሙያቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው በመሆናቸው ከደርግ መውደቅ በኋላ ሙያቸው አይገድባቸውምና አገራቸውን ለማገልገል ከውጪ አገር ጓዛቸውን ጠቅልለው በመግባት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ሀገራቸውን አገልግለዋል። ስለዚህም ከሽግግር መንግስቱ በኋላ ከ1984 በጡረታ እስከተሰናበቱበት ግንቦት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ በምጣኔ ሀብት ያላቸውን እውቀት አካፍለዋል። በሽግግር መንግስቱ ወቅት በሚኒስቴር ማዕረግ የፕሬዚዳንቱ የኢኮኖሚ አማካሪ ነበሩ። ከዚያ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሚኒስቴር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪና የአማካሪዎች ቡድን መሪ በመሆን ከፍተኛ ሚናን ተጫውተዋል።
በዚህ የረጅም ዘመን የአገልግሎታቸው የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የልማት እቅዶችን ማውጣት፤ ስትራቴጂዎችን መቅረጽ፣ መገምገም፣ ምዘና ማድረግና የማስተግበር ትልቅ ሚና የነበራቸው አቶ ነዋይ፤ በተለይ ኢትዮጵያ የነበረባትን የእዳ ክምችት ለመቀነስ ከአበዳሪ አገራት ጋር በመደራደር ብዙ ሥራዎችን ማከናወናቸውን በቀብር ስነስርዓቱ ወቅት በተነበበው የህይወት ታሪካቸው ላይ ተገልጿል ።
አቶ ነዋይ ኢትዮጵያ የእዳ ስረዛ እድል/ HIPIC/ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ሀላፊነት የተሰጣቸው ቡድን አባል በመሆንም ሰርተዋል። በዚህም አገሪቱን ካለባት የእዳ ጫና ለማለቀቅ የሰሩ ናቸው። ከዚያ ባሻገር በወሳኝ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ለመወሰን የተቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት በሚመራው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግም አገልግለዋል። በዚህም አቶ ነዋይ አገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ እንድታመጣ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችና ስትራቴጂዎች በመቅረጽ፣ ተግባራዊ በማድረግና በመከታተል እንዲመራና እንዲያስተባብር ሀላፊነት የተሰጠው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቡድን አባልም በመሆን አሻራቸውን ካሳረፉት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ከ1986 እስከ 1992 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ አባል በመሆን ሰርተዋል። ደረጃቸው እያደገ በመሄዱም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው አገልግዋል። እንዲሁም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ በምርምር እንዲታገዝ በሚያደርገው የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት በሚኒስቴር ማዕረግና በዋና ዳይሬክተርነት ሰርተዋል።
አቶ ነዋይ ኢንስቲትዩቱን ከመጀመሪያ ጀምሮ በማቋቋም፣ በማደራጀትና በመምራት በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ ቀዳሚ የምርምር እና ጥናት ተቋማት አንዱ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል። በተለይም በዚህ ተቋም የሰው ሀብት ልማት ዙሪያ የሰሩት ሥራ አንቱታን ያተረፈላቸው እንደነበር የታሪክ ማህደራቸው ያትታል። በተቋሙ በአገሪቱ ከነበሩት ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች የላቀ ውጤት አምጥተው የጨረሱ ወጣቶች ያለሥራ እንዳይቀመጡ ለማድረግ አወዳድረው በመምረጥ በአውሮፓና ኢስያ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲማሩና ለአገራቸው እንዲተርፉ በማድረግ በሰው ሀብት ልማት ግንባታ ስራ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው የህይወት ታሪክ ድርሳናቸው ያትታል።
ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም አስተምረው ብዙ ተመራማሪዎችንና ምሁራንን ያፈሩት አቶ ነዋይ፤ ሥራ በቃኝ ባህሪያቸው አይደለምና ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ውድድር ኮሚሽን አባል በመሆን አገልግለዋል። በተጨማሪም ከ1996 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በአፍሪካ መንግስታት የእርስ በእርስ መገማገሚያ ዘዴ /APRM/ የኮሚቴ አባልና ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል።
የሥራ ቦታቸው ተዘርዝሮ የማያልቀው አቶ ነዋይ፤ ሙያቸው ብዙ ቦታ ይከታቸዋልና ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በአፍሪካ ህብረት በኩል በቡድን 20 ስብሰባዎች ላይ በመገኘት አፍሪካን ወክለው ተሳትፈዋል። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲገኝ ያደረገ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። ሌላው የሰሩት ሥራ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀረጻ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ።
ከ1995 እስከ 2002ዓ.ም የመንግስትና የለጋሾች ድርጅት ኮሚቴ ውስጥ በእርዳታ አፈጻጸም የቁጥጥርና የአስተዳደር ማሻሻያ ሥራ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ነዋይ፤ ከ2002 እስከ 2003ዓ.ም ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ በሰየሙትና የኖርዌና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጋራ ይሰበስቡት በነበረው የፋይናንስ አማካሪ ቡድን ውስጥ አባል ሆነው አገልግለዋል።
በጡረታ ከተሰናበቱ
በኋላም ባላቸው ልምድና እውቀት ሀገርና ህዝብን በተለያየ መልኩ ከማገልገል አልቦዘኑም። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሚመለከት በርካታ
ጹሑፎችን አዘጋጅተው ለንባብ ከማብቃታቸውም በላይ የታዳጊ አገሮች ኢኮኖሚን በሚመለከት ከአራት ያላነሱ ጹሑፎችን አዘጋጅተዋል። ‹‹ከዚህ
በኋላ አገሬን መጥቀም የምችለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አፈጻጸም
አቅጣጫን በሚመለከት መጽሐፍ አዘጋጅቼ ሳደርስ ነው›› በማለትም ሰነዱን ሙሉ ለሙሉ አዘጋጅተው በመጨረስ ከአለም አቀፍ አታሚዎች ጋር በመነጋገር ላይ እያሉ ነበር እቅዳቸው ግብ ላይ ሳደርስ ለህልፈት የተዳረጉት።
በስራ መታወቅ
አቶ ነዋይ ገብረአብ ‹‹African Peer Review Mechanism (APRM)›› የሚባል ማዕከልን ሲመሩ በሚገባ የታላላቅ አፍሪካውያን ምሁራን ክለብ በማድረግ ዙሪያ እየሰሩ ነበር። በዚህም እንዳሉት ያደረጉ ናቸው።
የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ኮሚሽነር ለመሆን የኢትዮጵያ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ቢቀርቡም በመጨረሻው ዙር በካሜሩን እጩዋ ቬራ ሶንግዊ ተሸንፈው ፕሬዚዳንት ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁንና ከዚያ ያልተናነሰ ለአገራቸውም ሆነ ለአፍሪካ ሰርተው ያሳዩ ሥለመሆናቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
አቶ ነዋይ እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ የኢትዮ- ጃፓን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክርን ሲመሩ ቆይተዋል። ይህም በጃፓን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ የጠለቀ ዕውቀት እንዲያካብቱ አድርጓቸዋል። ያንን ልምዳቸውን አገራቸው ላይ እንዲተገብሩትና ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ችለዋል ። የጃፓናውያን የአሰራር ፍልስፍና የሆነው ካይዘን በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲደረግም ያደረጉት እርሳቸው እንደነበሩ ይነገራል።
በሥራቸው ርህሩህና ፈሪሃ-እግዚአብሄር ያደረባቸው አስገራሚ ሰው እንደነበሩ፤ ከመናገር ይልቅ መጻፍ የሚቀናቸው የምጣኔ ኃብት ሊቅም እንደሆኑም ይወራላቸዋል።
የኢትዮጵያን የዕድገት ስትራቴጂን ቀይሰው ሲያበቁ ስለ አፍሪካም የሚገዳቸው መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ አስመስግኗቸዋል። ለአብነት በእርሳቸው ሥራ በ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያን ብድሮች ላይ እንዲመከር አማካሪ ሆነው የተሾሙ ጊዜ ኢትዮጵያ በብድር ለሰሯቻቸው መንገዶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ሆስፒታሎች ፣ባቡር ሀዲዶችና ሀይል ማመንጫ እንዲሁም ግድቦች የአቶ ነዋይ ምክረ ሀሳቦች ከፍተኛ ሚናን ተጫውቶ እንደነበር ይገለጻል።
‹‹የአፍሪካውያን የምጣኔ ሃብት ልሂቃን የሚመክሩበት ፓናል ነዋይ ገብረአብ በዛ ለስለስ ባለ ልሳናቸው ስብሰባውን ሲመሩ ላየ ሰው ከመደመም በስተቀር ምንም ማድረግ አይቻለውም›› ይላሉ የሚያውቋቸው ሰዎች። በተለይም ከአፋቸው ሁልጊዜ የማይነጥሏት ድህነትን የመግታት ነገር በሰው ልብ ውስጥም እንዲታተም ይፈልጋሉ። በዚህም ዘወትር ‹‹ጠላታችን አንድ እና አንድ ነው እርሱም “ ድህነት” ብቻ›› ይላሉ። ቀጥለውም እንዴት እናሸንፈው ብለው እቅድ ያወጣሉ። ሲተገበርላቸው ደግሞ ይደሰታሉ።
ነዋይ እና መለስ ዜናዊ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ እንደነበሩ የሚገለጽላቸው አቶ ነዋይ ፣ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF)፣ ከአለም ባንክ ለተበደረቻቸው ብድሮች እርሳቸውን ሳያማክሩ የሚያደርጉት ምንም ነገር እንደሌለ ይነገራል። በአቶ መለስ ልቡ ከልብ የሚታመኑ እንደነበሩም ብዙዎች ይስማማሉ። በኢኮኖሚው ዘርፍ ብዙ አስተዋጽኦ ለሀገር ያበረከቱ ሰው እንደነበሩም ብዙዎች ይመሰክራሉ።
እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከቻይና፣ ከእንግሊዝና ከሌሎች ያደጉ አገራት የሚመጡ ብድሮች የነዋይን ጠረጴዛ ሳይነኩ የማያልፉትም አቶ መለስ የእርሳቸውን ምልከታ ሳያካትቱና ሳይመረምር ወደ ትግበራ መግባት አይፈቅዱም። በዚህም ስራቸው ሀገርን ከችግር በማውጣት እና መሪውንም ከስህተት በማዳን ብልህ አስተዋይ የሚል ስሞች እንዲጎናጸፉ አድርገዋል። ምክንያቱም ብድሮቹን አንደ ድርሰት መፅሀፍ አንብበው የመገምገምና ምን ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የማወቅ ትልቅ እውቀት ያላቸው እርሳቸው ናቸው።
ያደጉት አገራት ለሚለቁት በካይ ጭስ ለአፍሪካ ካሳ መከፈል እንዳለባቸው ሁልጊዜ ያሳስቡ ነበር። ‹‹The New Partnership for Africa’s Development (NEPAD)›› ሲመሰርት አቶ ነዋይ በርካታ ሳይንሳዊ የጥናት ጽሁፎች በግብአትነት ያቀርቡ እንደነበር የታሪክ ማህደራቸው ያስረዳል።
ከስራ ባልደረቦች አንደበት
አምባሳደር ዶክተር ኃይለሚካኤል አበራ ስለ አቶ ነዋይ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉን። ‹‹በመሰረቱት የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት አጥኚዎችን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምረው መልምለው፣ ትምህርት እንዲማሩ፣ በአግባቡ ከተማሩ እገዛ ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳስቡ ሊቅ ናቸው። ኢንስቲትዩቱን ሲያቋቁሙት አላማዬ ብለው የያዙትም ጠንካራ የሰው ኃይል ማፍራትና ያንን ተጠቅሞ አገሪቷን በፖሊሲ፣ በምርምር መርዳት መቻል እንደሆነ አስታውሳለሁ። ያንንም በሚገባ እንዳደረጉት አይቻለሁ። ስለዚህም የአገር ባለውለታ ስለመሆናቸው ማንም አይጠራጠርም።››
‹‹ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ተቋሞች በጥናትና ምርምር ዘርፍ በሚያወጡት የደረጃ ሰንጠረዥ ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ከአንድ እስከ አስር ደረጃ እንደሚያገኝም አምነው ሰርተዋል። አድርገውታልም›› የሚሉት አምባሳደር ዶክተር ሀይለሚካኤል፤ ትውውቃቸው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በሚሰሩበት ጊዜ ነው። እናም ኢኮኖሚው ላይ ያላቸው እውቀት ጥልቅ በመሆኑ በቻሉት መጠን ለተማሪም ሆነ ለአገር እንዳዋሉት ማየት ችያለሁ” ሲሊ አድናቆታቸውን ችረዋቸዋል።
“ወጣት ሆነው የመለመሏቸው የእርሳቸው ፍሬ የሆኑ ልጆች የተለያየ ቦታ አሉ። በዚህ በጣም ደስ እንደሚላቸው ይሰማኛል” የሚሉት አምባሳደር ዶክተር ሀይለሚካኤል፤አቶ ነዋይ ከሥራ ውጪ ባለ ሕይወታቸው መጻሕፍት ማንበብ እንደሚያዘወትሩ፤ከተለያዩ አገራት ልምድ ለመቅሰም ስለሚሹ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረኮችን መከታተልም ይወዱ እንደነበር አጫውተውናል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ስለ አቶ ነዋይ እንዲህ ይላሉ ‹‹በአህጉሪቱ ጠንካራ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ እንዲኖር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚካሄዱ ድርድሮችን በበቂ ሁኔታ ለመምራት (እኩል ተደራዳሪ ለመሆን) በቂ አገር በቀል የተማረ ኃይል ሊኖር እንደሚገባ ያምናሉ። ይህ ደግሞ በሰው ሀይል ልማት ላይ በስፋት እንዲሰሩ አድርጓቸዋል››
አቶ ነዋይ ከኢኮኖሚክስን ንድፈሀሳብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አስተሳስረውም የማስረዳት አቅም እንዳላቸው ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ። በተገኙባቸው መድረኮችና በተሳተፋባቸው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይም ቢሆን ሀሳባቸውን ቀለለ ባለና በሚያሳምን መንገድ ያቀርባሉ። በዚህም ስራዎቻቸው የእርሳቸውን ሃሳብ የሚጻረር ብዙም እንዳልተመለከቱ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደለ ፈረደ በበኩላቸው፤ አቶ ነዋይን በተለያየ አጋጣሚ እንዳወቋቸውና ከእርሳቸውም ጋር በስራ ላይ ቆይታ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። በትውውቃቸው ወቅት የታዘቡትም አቶ ነዋይ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በንግግርም አስተዋይ መሆናቸውን ተረድተዋል። ከእርሳቸው ያነሱ ልጆችን ሲመክሩም በፍቅርና ሊለወጡ በሚችሉበት መልኩ መሆኑን በራሳቸው እንዳዩትም አጫውተውናል። እንደ ማህበር ደግሞ የክብር ተሸላሚ መሆናቸውንና ለአገሪቱ ባበረከቱት አስተዋዕጾ የክብር አባል እንደሆኑ ነግረውናል።
ዶክተር ታደለ እንደሚያስረዱት፤ ከአገር ውጪ ከእርሳቸው ጋር የመጓዝ እድሉም ነበረራቸው። በዚህም ማህበራዊ ችሎታ ያላቸው መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። በተለይ ከራሳቸው ይልቅ ለሰዎች ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸውን ስመለከት ይገርመኝ ነበር ብለዋል።
የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሃም ተከስተ እንዲህ ሲሉ ምስክርነት ይሰጣሉ፤” የኢትዯጵያ ኢኮኖሚ በደርግ ጊዜ በ80ዎቹ መጀመሪያ በተለይ ኢኮኖሚው የተሽመደመደበትና ቀውስ ውስጥ የወደቀበት ጊዜ ነበር። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣና እርሳቸው በአማካሪነት ሥራ ሲጀምሩ ግን ትልቁ ፈተና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ነበር። እርሳቸው ይህንን በማድረግ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል››ይላሉ።
የወጪ ንግድ፣ የመንግሥት በጀት የነበረውን ክፍተት፣ ትልልቅ የአገሪቱ የኢኮኖሚው ችግሮችንና የውጭ እዳን ጭምር ሥርዓት እንዲይዝ ያደረጉም ናቸው ሲሉም ውለታቸውን ያስታውሳሉ። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጀት (አይ ኤም ኤፍ) እና ዓለም ባንክ ጋር በነበረ ድርድር ከፊት ሆነው ይደራደሩ የነበሩትም እርሳቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ። የኢትዯጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ።
“አቶ ነዋይ አገሩቱን የሚጠቅሙ ወሳኝ ፖሊሲዎችን ተክለዋል። በአገሪቱ ይመዘገቡ ለነበሩ የኢኮኖሚ እድገቶችም መንግስትን በማማከር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል” የሚሉት ዶክተር አብረሃም፤ ከሰው ጋር ተረዳድቶ መስራት የሚችሉ፣ ሰፊ እውቀት እና ልምድ ይዘው እጅግ ትሁት የሆኑ፣ሰው እንዲማርና እንዲያድግ የሚጥሩ ቀና ሰው መሆናቸውንም ይገልጻሉ። መንግሥት የራሱ የፖሊሲ ነፃነት እንዲኖረው ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም አያይዘው ያነሳሉ። ዶክተር ግሩም አበበ በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ሲሆኑ ስለ አቶ ነዋይ የሚሉት ነገር አላቸው። አቶ ንዋይን ላለፉት 13 ዓመታት በቅርብ ያውቋቸዋል። መጀመሪያ ሲተዋወቁ ያስተዋሉት እጅግ ረጋ ያሉ፣ ለምንም ነገር የማይቸኩሉ፣ በጥሞና አስተውለው የሚናገሩ ሰው እንደሆኑ ነው።የሚናገሩት ነገር ጠንካራ፣ ፍሬያማና አስተማሪ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ጠንከር ያለ መልዕክት ማስተላለፍ እንኳን ሲፈልጉ ረጋ ብለው፣ የተመረጡ ቃላት ተጠቅመው፣ መልዕክቱ ሌላ ይዘት እንዳይኖው አድርገው ነበር ሲሉም ይገልጽዋቸዋል ።
ዶክተር ፍሬው በቀለ ትውውቃቸው የጀመረው ተመርቀው የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩትን ሲቀላቀሉ ሲሆን፤ በወቅቱም አቶ ነዋይ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ነበሩ። በወቅቱ ለትምህርት ተልከው ስለነበር የመስሪያ ቤቱ ድጋፍም አልተለያቸውም። ግንኙነታቸውም የቀጠለው በዚያ መልኩ ነው። ተምረው ከመጡ ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት ወቅት ድረስ አብረው ሰርተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ከስራ ጋር በተገናኘ በተለይም ከምጣኔ ሃብት ጋር በተያያዘ ውይይትም አድርገዋል። አቶ ንዋይን “በጣም ለስላሳ ሰው፣ ረጋ ያሉ፣ ባለራዕይ፣ ነገሮችን ራቅ ብለው ማየት የሚችሉ” ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል።
ለአምስት ዓመታትም ያህል ከአቶ ንዋይ ጋር በቅርበት የመስራት እድሉን አግኝተዋል። ለዚህም የሚያነሱት ተማሪዎችን በሚመለምሉበት ወቅት ከአስር እስከ ሃያ ዓመት ወደፊት የሚሆነውንም በማሰብ ነበር። በተለይም ለምርምሮች ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለውይይቶች ክፍት ነበሩ ይላሉ።
አቶ ነዋይ በተደጋጋሚ አፍሪካውያን ከውጭ የሚመጡ ጫናዎችን ተቋቁመው የራሳቸውን የምጣኔ ኃብትም ሆነ ሌሎች ፖሊሲዎቻቸውን ለእነርሱ በሚመጥን መልኩ ሊቀርፁ ይገባል› በማለት በተደጋጋሚ ይሟገቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አቶ ነዋይ ባለ ራዕይ ናቸው። ይህንን ያልኩት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚደረገው የእለት ተእለትና አጣዳፊ ለሆኑ ጉዳዮች ቢሆንም እርሳቸው ግን የቀጣዩን የአገር እጣ ፋንታ አይተው ጭምር ነው ፖሊሲ እንዲቀረጽ የሚያደርጉትም ሆነ የሚመራመሩት። ስለዚህም እሳቸው ከባለራዕይነታቸው ባለፈ ወደፊቱን የሚሆነውንም አርቀው የሚያልሙ ናቸው።
በ27 ዓመታት የምጣኔ ኃብት ግስጋሴ ዘመን ታላቁ ሰው ነዋይ ገብረአብ የምጣኔ ሃብቱ ስትራቴጂ ፊትአውራሪ ሆነው ሃገራቸውን ከልብ አገልግለዋል። እሳቸውም በወጣት የምጣኔ ኃብት ልሂቃን የተደራጀው የምጣኔ ኃብት አማካሪዎች ማዕከልን ይመሩ ነበር። ከዚያም ባሻገር በማዕከሉ ውስጥ ብዙ ሥራዎችን ሲሰሩ ላስተዋላቸው የእውቀት ውቅያኖስ እንደገቡ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ።
ሽልማት
አቶ ነዋይ ኢትዮጵያ እና ጃፓን በልማት ትስስር ዙርያ በስድስት ወር አንዴ የምክክር መድረክ እንዲኖራቸው በማድረግ ለአስር ዓመት ያህል ለፍተዋል። በዚህም ‹‹ኦርደር ኦፍ ዘ ራይዚንግ ሰን ጎልድ ኤንድ ሲልቨር ስታር›› የተባለውን በጃፓን ለአንድ ሲቪሊያን ሊሰጥ የሚችለውን ከፍተኛ ሽልማት ከጃፓን ንጉስ ተበርክቶላቸዋል።
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ላይም ላቅ ያለ ተሳትፎ ነበራቸውና በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት ተበርክቶላቸዋል። ከዚህም ባሻገር ወርክ ሾፕ ላይ ተጋብዘው ጥናት ሲያቀርቡም ሆነ ሲናገሩ ባላቸው ብቃት ሽልማት አግኝተዋል።
ስራን እንደ ልጅ
በቀለም አባትነታቸው ተማሪዎችን አስተምረው ቢተኩም የአብራካቸው ክፋይ ልጅ አልነበራቸውም። እናም እርሳቸውን መስሎ የሚቀጥለው ትውልድ በመምህርነታቸው ያፈሯቸው የቀለም ልጆቻቸው ብቻ ናቸው። ለሀገር የሰራ ስራው ከመቃብር በላይ ነውና አቶ ነዋይም የካቲት 16ን ማለፍ ባይችሉም ስማቸው ከመቃብር በላይ ነው ።
የካቲት 16 ቀን 2012 ከዚህ አለም በሞት የተለዩት አቶ ነዋይ ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን
ታላላቅ ምሁራንና የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ተፈጽሟል። የዝግጅት ክፍላችንም በህልፈታቸው የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣
ለሥራ አጋሮቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012