‹‹እውቀቴን ወደ መቃብር ይዤ መውረድ አልፈልግም›› ደራሲ ጌታቸው በለጠ (ዳግላስ ጴጥሮስ)

የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን ላለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ገበታ ላይ አሻራው በጉልህ የታየ ደራሲ ነው። ከሥነ ፅሁፍ ሕይወቱ ባሻገር በኮሙኒኬሽን እና በኮንሰልታንት ሙያ አሰልጣኝ ነው። ዳግላስ ጴጥሮስ በሚል የብዕር ስሙ በአዲስ ዘመን እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከሶሰት አስርት ዓመታት በላይ በአምደኝነት ተሳትፎ አድርጓል። ለዓመታት የሁነት ዝግጅቶችን በማሰናዳትና የኮሙኒኬሽን ሥራዎቸን በማስተናበር ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተሳትፎ አለው።

በርካታ መፅሀፍትን በመድረስ ለአንባቢያን አቅርቧል። ከሰሞኑ ‹‹የትዝታዬ ማሕደር ግለ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ መፅሀፍ አበርክቶልናል። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል በመሆኑ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን ለሁለት የሥልጣን ዘመን በመምራት ለሥነ ፅሁፍ እድገት የድርሻውን አበርክቷል። ይህ ሰው ደራሲ ጌታቸው በለጠ ነው። የዝግጅት ክፍላችንን የእንግዳችንን የዛሬውን ማንነት የገነቡ ትናንቶች እና የሕይወት ምዕራፎቹ ትውልድን ያስተምራል ብለን በማሰባችን እነሆ እንግዳችን አድርገነዋል።

የደራሲው- የትዝታ ማሕደር

ደራሲ ጌታቸው የትዝታ ማሕደሩን አየቀሰቀሰ ኮራና ጀነን ብሎ ‹‹የወታደር ልጅ ነኝ›› ይላል። ወላጅ አባቱ እጩ መኮንን በለጠ በቀለ ኢትዮጵያ በሆለታ ገነት የ15ተኛ ባች ምሩቅ እንደነበሩ እየተናገረ። ይህ ቡድን ሀገሪቱ ካሏት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል የሚጠቀስ ነው። እርሳቸው በ1951 ዓ.ም ነበር በእጩ መኮንንነት የተመረቁት። ከንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ ጋር በቅርበት የሚሠሩና በተለያዩ የጦር አካዳሚዎችም በአሰልጣኝነት ያገለገሉ ነበሩ።

ታዲያ የዛሬው የሥነ ፅሁፍ ፈርጥ፣ ባንዲራውን እና ኢትዮጵያዊነቱን ከፊት የሚያስቀድመው ጋሽ ጌታቸው ከቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ ሆኖ በታህሣሥ 7 ቀን 1953 ዓ.ም ከመወለዱ አስቀድሞ አባቱ ‹‹ልጄ ናፖሊዮን ሲወለድ ጋዜጠኛና ደራሲ ይሆናል›› በማለት ማስታወሻ እንደፃፉለት፤ ይህንን አደራ ከእናቱ እጅ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት መቀበሉን ይገልፃል። ጋሽ በለጠ ቃለ በቃል እርሳቸው በሚጠሩት የስስት ስም ‹‹ወንዱ ልጄ ናፖሊዮን›› ቀድመው የሥነ ፅሁፍ አድባር እንደሚቀርበው ተንብየው ነበር። መፅሀፍትን መውደዳቸው፣ ለቀለም እና ሙያ ትምህርት የቀረቡ መሆናቸው እና ሀገራቸውን በፍፁም ወታደራዊ ወኔ ማገልገላቸው ለልጃቸው አደራ ለማስቀመጣቸው ምክንያት እንደሚሆን ይገምታል።

ይህንን ታላቅ አደራ የተቀበለው የያኔው ታዳጊ ታዲያ በልጅነት አዕምሮው ነበር የቄስ ትምህርት ቤት ሳለ በሥነ ፅሁፍ ውስጥ የገዘፈ ድርሻ አንደሚኖረው ያመነው። በኑሮ አለመመቻቸት እና አንዳንድ ሳንካ ገጠመኞች ምክንያት የትውልድ መንደሩን ለጥቂት ዓመታት ለቅቆ የነበረ ቢሆንም ሰፊውን ግዜውን ያሳደገው ባደገበት ኮልፌ ነው።

ከቄስ ትምህርት ተሻግሮ መደበኛ ትምህርት በብርሀነ ዩኒቨርሳል ሥነ ጥበባት ትምህርት ቤት ሲገባ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ ጋሽ ጌታቸው ደምሴ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለ የትምህርት ቤቱ ጋዜጠኛ አንደሆነ ነገሩት። የእርሳቸው ይህንን ኃላፊነት መስጠት ከአባቱ ማስታወሻ ጋር ተደምሮ የደራሲና ጋዜጠኘነት ሙያ ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲያደርግ እረዳው። በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚደረጉ የክበባት እንቅስቃሴ ውስጥ ቀዳሚ ተሰላፊ፣ ሀሳቦችን የሚሞግት፣ ለአዳዲስ ሀሳቦች ክፍት የሆነ ትጉህ ታዳጊ ሆነ። አባቱ ጋሽ በለጠ ‹‹ለልጅ ቅርስ መተው ሳይሆን አስተምሮና በእውቀት አንፆ ማሳደግ ይገባል›› የሚል ፍልስፍና ነበራቸው። በእርሱም ላይ የሆነው ይህ ነው። የእውቀትን ጭራ እንዲይዝ የዞም አንዳይለቅ በልቡ ውስጥ እውቀትን እንዲያከብርና እንዲሻት ሆኖ ተቀረፀ።

ደራሲ ጌታቸው ባደገበት ኮልፌ አካባቢ ከትምህርት ባሻገር በትዝታ ወደ ኋላ የሚጎትቱ የልጅነት የሰፈር ትዝታዎች አንዳሉት ይናገራል። ቡሄ ጨፍሮ፣ በእንቁጣጣሽ የእንኳን አደረሳችሁ ስዕል ለጎረቤቶቹ አዙሮ ፤ ጢቢኛ ገምጦ ማደጉን ይገልፃል። አነዚህ የልጅነት ትውስታዎቹን በትዝታ ማሕደር ግለታሪክ መፅሀፉ ላይ በስል ብዕሮቹ በተብራራ ሁኔታ አስፍሯቸዋል። ከወላጅ አባቱ ከወረሳቸው ጥልቅ ሀገራዊ እውቀትና ስሜቶች ውስጥም ሰንደቅ ዓላማን ማክበር፣ ለዚያም እራስን አሳልፎ መስጠትን ነው። ዛሬ የተገነባው የደራሲው ስብእና የተማሪ ቤት፣ የአባቱ ትጋት እና የጎረቤቶቹ ተፅእኖ እጅ አለበት። ለዓመታት በድርሰትና በዓምደኝነት እነዚህን ስሜቶቹን የሚያንፀባርቁ የሥነ ፅሁፍ ውጤቶችን በኢትዮጵያ ፕሬሰ ደርጅትና በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ሲፅፍ የቆየበት መነሻ ምክንያትም ይህ ነው።

የቤተሰብ ፈተናን መጋፈጥ

ደራሲ ጌታቸው ዛሬ ለደረሰበት የሕይወት ምዕራፍ ብዙ መሰናክሎችን ተሻግሯል። የበቃ የነቃ ደራሲ ለመሆን በልጅነቱ የገጠሙትን ሳንካዎች በፅናት ማለፍ ይጠበቅበት ነበር። ከእነዚህ ውጣ ውረዶች መካከል አባቱን ገና በታዳጊነቱ በአደጋ በማጣቱ ምክንያት የተከሰተውን የቤተሰብ መበተን በልጅነት ጫንቃው የመቋቋም ግዴታ ወድቆበተ ነበር። ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሰዋል።

አባቱ ግዳጅ ላይ እያለ እርሱና ሌሎች ስምንት መኮንኖች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያልፋል። በዚህ ምክንያት ‹‹ያ የተከበረ የምንለው፣ ያ በወግና ሥርዓት ልጆቼን አስተምራለሁ የሚለው አባታችን መስዋዕት ሆኖ ሲያልፍ ሰማይ ተደፋብን›› በማለት እናቱ የቤት እመቤት ሆነው ልጆቻቸውን ከማሳደግ ያለፈ ሙያና ትምህርት ስላልነበረቻው ለጆቻቸውን የግዴታ ወደ ዘመዶቻቸው መላክ ስለነበረባቸው ታዳጊው ጌታቸውም የዚህ ሰለባ ሆኖ ወደ ምዕራብ ሸዋ አጎቱ ቤት ለመሄድ ተገድዶ ነበር። በዚያ ትምህርቱን አቋርጦ (በአካባቢው ወግ ደረባ እየተባለ በሚታወቅ) እረኛ ሊያደርገው ሲሞክር ሌላኛዋ አክስቱ በሁኔታው ባለመስማማት ከዚያ አውጥታ ዳግም እርሷ በምትኖርበት ሽኩቴ በምትባል መንደር ትምህርት ጀመረ። በዚያም ትንሽ አንደቆየ ሊጎበኙት ወደዚያው ያቀኑ እናት የልጃቸው ያልተመቻቸ ሁኔታ በመመልከት ሁኔታው ስላሳዘናቸው መልሰው ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ዳግም ትምህርቱን በኮልፌ ከእርሳቸው ጋር ሆኖ እንዲቀጥል አደረጉ።

ታዳጊው ጌታቸው በኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የፖሊስ ሠራዊት አባላት በመጠነኛ ክፍያ የሚማሩበት በተለምዶ ሙሉጌታ ትምህርት ቤት ውስጥ ገባ። የትዝታዬ ማህደር ግለ ታሪክ መፅሀፉ ላይም ይህንን አጋጣሚ እንዲህ በማለት አስፍሮታል፤ ጊዜ ሳላጠፋ የምዝገባና ወርሃዊ ክፍያውን አጠናቅቄ አንድ ዓመት በመቀነስ ትምህርቴን ከአራተኛ ክፍል ጀመርኩኝ። ከዚያ በኋላማ ምኑ ይጠየቃል በከፍተኛ ሞራልና በቁጭት ድህነትንና ትምህርቴን በአሸናፊነት ለመወጣት ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትምህርት ቤቱ ኮከብ ተማሪ የሚል ቅጽል ለማትረፍ በቃሁኝ። በዓመቱ የትምህርት ፍፃሜ ላይም በክፍላችን ውስጥ ይገኙ ከነበሩ 45 ተማሪዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ ሆንኩኝ።

ከዚያን ግዜ ጀምሮ ደራሲ ጌታቸው በትምህርቱ የላቀ ውጤትን እያስመዘገበና ተሸላሚ እየሆነ ቀጥሏል። ኑሮውን ለማሸነፍ እና የአባቱን በልጁ ላይ ሊያጋባ የሚሻውን ርዕይ እውን ለማድረግ ግን ጠንካራ፣ ብልህና ለፈተናዎች የማይበገር መሆን ነበረበት።

እራስን የማሸነፍ ትግል- ያልታሰበው አጋጣሚ

ከክፍለ ሀገር ተመልሶ ዳግም በኮልፌ ትምህርቱን በተሳካ ሁኔታ የቀጠለው የያኔው ታዳጊ ጌታቸው ኑሮን አሸንፎ የሰነቀውን ሕልም ከዳር ለማድረስ ትንቅንቅ ውስጥ ገብቷል። ‹‹በጊዜው እናቴ ምን ተስፋ አላት?፤ ልረዳት የሚገባው እኔ ነኝ በማለት መርካቶ ከአከስቴ ልጅ ጋር በመሆን በርኖስ፣ ሳሙናና ፌስታል በትርፍ ግዜዬ እየሸጥኩ ኑራችንን መደጎም ጀመርን። በቆሎ ፈልፍዬም እሸጥ ነበር›› ይላል፤ ከትምህርቱ ባሻገር ንግድ ውስጥ መግባት የግድ ብሎት አንደነበር እየገለፀ።

በዚህ የኑሮ ትግል ውስጥ እራሱን ለማሸነፍ ከላይ እታች ደፋ ቀና ሲል የቆየው ታዳጊ በፈጥኖ ደራሽ ግቢ ውስጥ ለአንድ ዓመት በስኬት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ አንድ ያልታሰበ እድል ጋር ተገጣጠመ። ሁኔታው እንዲህ ነው የንጉሱ ሥርዓት በወቅቱ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የላቀ አፈፃፀም ያላቸውን ተማሪዎች በማወዳደር በልዩ ፕሮጀክት በአራት ኪሎ ወወክማ (ወጣቶች ወንዶች ከርስቲያናዊ ማህበር) ውስጥ የትምህርት ስልጠና ለመስጠት ማስታወቂያ ይወጣል። በውድድሩ ላይ በአዲስ አበባ ካሉ አስሩም ወረዳዎች (በቀድሞ አወቃቀር) እጀግ በርካታ ተማሪዎች ተመዝግበው ይፈተናሉ። ታዳጊው ጌታቸው ይህንን ፈተና በብቃት በአንደኛ ደረጃ ላይ ማለፉን ውጤት ሲወጣ ያውቃል። ሁኔታውን ሲያስታውስ ‹‹እኔም ጓደኞቼም የትምህርት እድሉን እናገኛለን የሚል ሀሳብ አልነበረንም፤ ውጤቱ ሲለጠፍ ግን አንደኛ መውጣቴን ተመለከትኩ›› ይላል።

የነገይቱን የኢትዮጵያ መሪዎች ለመቅረፅ ባለመው በንጉሱ ሥርዓት በተቀረፀው በወወክማ በሚሰጠው ትምህርት ላይ አዕምሮን በሚያንፅ ሥርዓት መማር ጀመሩ። ‹‹የነገ ሀገር ተረካቢ ናችሁ በሚል በአረንጓዴ ምንጣፍና ሶፋ ላይ ተቀምጠን ነው የተማርነው። ትምህርቱ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ጨምር ይሰጠን ነበር›› በማለት ግዜውን ያስታውሳል። የንጉሱ የቅርብ ከትትል ሳይለያቸው አንዳንዴም በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው እየጎበኟቸው ነበር። ደራሲ ጌታቸውም በዚህ ሁኔታ ነበር የስድስተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ትምህርቱን በላቀ ውጤት አጠናቅቆ ወደ ቀዳማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ገባ። በዚህ ሂደት ውስጥ ከኮልፌ እየተመላለሰ ከመማር በተጨማሪ መርካቶ ከአክስቱ ልጅ ጋር የጀመሩትን ንግድ አላቆመም ነበር።

ፈተና የማይለየው የደራሲው ሕይወት በሚኒሊክ ትምህርት ቤት ሳለም ከአንድ አጋጣሚ ጋር ተጋፍጦ ነበር። ትምህርቱን ለመማርና ኑሮውን ለመደጎም በሌሊት መነሳቱ ለሳንባ ሕመም ዳረገው። አጋጣሚውም ለሶስት ወራት ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ታሞ ተኝቶ ነበር። ይሁን አንጂ በትምህርቱ ሳይሰንፍ የ8ተኛ ክፍል ሚኒስትሪን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ነበር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የጨረሰው። በትምህርት ቆይታውም በሥነ ፅሁፍ፣ ግጥምን በማንበብና በጋዜጠኝነት የማይረሱ ትዝታዎችን አሳልፏል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በኮልፌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቋል።

የከፍተኛ ትምህርትና የሙያ ስኬቶች

ደራሲ ጌታቸው በለጠ የከፍተኛ ትምህርት ምርጫውን ያደረገው የልጅነት ሕልሙን ሊያሳካ በወጠነበት የሥነ ፅሁ ዘርፍ ነው። በዚህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንዎችና ሥነ ፅሁፍ ክፍል በ1973 ዓ.ም በመግባት 1976 ዓ.ም ተመርቆ የመጀመሪያ ድግሪውን ሰርቷል። ግዜው በነበረው የአብዮት ስሜትና በሚከተለው የክርስትና እምነት ምክንያት አስቸጋሪ የሚባሉ ወቅቶችንም አሳልፏል። በተለይ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ፍልስፍና በእምነቱ ምክንያት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎችን እስር እና ማሰቃየት ደርሶበታል። ይህንን የታሪኩን ክፍል በየትዝታዬ ማሕደር ግለ ታሪክ መፅሀፉ ላይ በስፋት እንደተረከውም አጫውቶናል።

‹‹የአባቴ ትምቢት ከእኔ ፍላጎትና ጥረት ጋር እኩል እየተፈፀመ ነበር›› የሚለው አንጋፋው ደራሲ ጌታቸው፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንዎችና ሥነ ፅሁፍ እንደተመረቀ በግዜው ሥራ የሚደለድለው የማዕከላዊ ፕላን፤ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር (በማተሚያ ኮርፖሬሽን ጥያቄ መሰረት) ተመደበ።

1977 ዓ.ም መስከረም ሁለት የኢሠፓ ምስረታ ነበር። ደራሲ ጌታቸው ደግሞ በማተሚያ ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ለአንድ ትልቅ የሥራ ዘርፍ ታጭቶ ነበር። የደራሲዎችን የሥነ ፅሁፍ ውጤት በተሻለ ጥራትና ብዛት ለማሳተም ፅህፈት ቤት ለማቋቋም እቅድ የነበራቸው ሥራ አስኪያጁ ፅህፈት ቤቱን አንዲመራላቸው መርጠውት ነበር። ይሁን አንጂ ይህ እቅድ በኢሠፓ ፓርቲ ሰዎች ስላልተወደደ (የኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን ይፎካከራል በሚል) እቅዱ አንዲከሽፍ ሥራ አስኪያጁም በተፅእኖ ሀገር ጥለው አንዲሰደዱ ሆነ። ሙያውን አሀዱ ብሎ የጀመረው ደራሲ ጌታቸውም ተንሳፎ በኋላ ወደ አንጋፋው የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በእርም ከፍል ባልደረባነት እንዲመደብ ተደረገ። የዚያን ግዜ ደራሲው የዘወተረር የሥነ ፅሁፍ ሕልም ተወለደ። በግዜው ከአንጋፋ ደራሲና እውቅ ጋዜጠኛ መሀል አንዱ ከሆነው ብርሀኑ ዘሪሁን ከመሳሰሉ የሥነ ፅሁፍ ሰዎች ጋር ተዋወቀ።

አንጋፋው ደራሲ ጌታቸው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ መጣጥፎችን መፃፍና ዓምደኛ መሆን የጀመረው በዚህ አጋጣሚ ነበር። በቤተሰቡ ላይ የደረሰው መበታተን፣ የኢኮኖሚ ጫና፣ የአባትና እናቱ በልጅነቱ (አባቱ ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለ እናቱ ደግሞ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ አልፈዋል) ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ሳይበግረው የልጅነት ሕልሙን ለማሳካት የሥነ ፅሁፍ ሥራውን ተያያዘው።

የመጀመሪያ ፅሁፉ ‹‹ሀ በፅጌሬዳ ብዕር›› በኪለው መፅሀፍ ላይ የፃፈው ሂስ ቀመስ አርቲክል ነው። በዛሬይቱ ላይም ‹‹ግጥም ወይም ሥነ ግጥም›› የሚል የፃፈው ይጠቀሳል። በጊዜው ከደራሲ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ (የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ)፣ ከነ አሸናፊ ዘደቡብ፣ ዳንዴው ሰርቤሎ፣ ከሻለቃ ክፍሌ አቡቸር፣ ከመሳሰሉ ፀሀፊያን ጋር ሂሰ ቀመስ ፅሁፎችን በማንሳትና በሥነ ፅሁፋዊ ወግና ዘይቤ በጋዜጦቹ ላይ የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በማስቀመጥ ቀጥታ የሥነ ፅሁፍ ዓለሙን ተቀላቀለ። ከዚያን ገዜ ጀምሮ ደራሲ ጌታቸው ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ እጅግ በርካታ ፅሁፎቸን ሲከተብ ቆይቷል።

ከብርሀንና ሰላም የማተሚያ ድርጅትት ከአራሚ ክፍል ሲለቅ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ከርስቲያን የሥነ ፅሁፍና ኮሙኒኬሽን መምሪያ መምራት ጀመረ። በመምሪያ እየሠራም የፅሁፍ ሥራዎቹን ማሳተሙንና ሂሳዊ ምልከታዎቹን ማጋራቱን አላቆመም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር ለተጨማሪ ትምህርት በአሜሪካን ሀገር በመሄድ በሜኖሶታ ስቴት በቤቴል ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ድግሪውን በኮሙኒኬሽን መሥራት የቻለው። ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ በዚያው በአሜሪካን ሀገር ሀዋይ በአጭር ሥልጠና ሊደርሺፕ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያነት ሰርቲፋይድ ሆኖ ነበር።

ወደ ኢትዮጵያ

ሙያና የትምህርት ጉዞው ብዙ ውጣ ውረዶችን አሻግረውት አሜሪካን ሀገር ሜኖሶታ አድርሰውታል። በቤቴል ዩኒቨርሲቲ የነበረው የትምህርት ውጤት አጅግ አጥጋቢ በመሆኑ በዚያው እንዲቀር ብዙ ጉትጎታዎችን አስተናግዶ ነበር። እርሱ ግን በሰለጠነና የተሻለ የሥራ እድል ባለበት ከባቢ ከመቆየት ይልቅ ምርጫው ወደ እናት ሀገሩ ተመልሶ መሥራትን ነበር። ‹‹የአባቴንና የሀገሬን አደራ መብላት አልፈለኩም›› የሚለው ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ዳግላስ ጴጥሮስ በሚል የብዕር ስም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዓምደኛ የነበረው አንጋፋው ደራሲ ጌታቸው፤ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ከምንም በላይ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ይናገራል።

ኢትዮጵያ አንደገባ መፅሀፍቶችን ከማሳተም፣ በዓምደኝነት ፅሁፎችን በጋዜጦች ከማሳተም ባሻገር ልዩ ልዩ የግል ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ነበር። ከዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው በሙያው ለግል ድርጅቶች ኮንሰልታንት በመሆን የሠራበት ነው። በተለይ ዮቤግ ኮሙኒኬሽን ሚዲያና ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር የሚል ስያሜ ያለው ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር በጋራ በመሆን የመሰረተው ድርጅት ይጠቀሳል። በዚህ ድርጅቱ በስልጠና፣ በማማከር እና ሁነት ላይ የሚሠራ ነበር። በዚህ ድርጅት ሥር የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በዓል፤ የ13ተኛ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል፤ ዓለም አቀፍ የቡና ጉባኤ፤ 75ተኛውን የድል በዓል፣ የባንቡ ኢንተርናሽናል ጉባኤ እና ሌሎችም ትላልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሁነቶችን አዘጋጅቶ ነበር።

ሰንደቅ ዓላማ እና ሀገራዊ ተልዕኮዎች

የደራሲው አባት ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት በመኖሪያ ቤታቸው ለነበረ ሰንደቅ ሁሌም ሰላምታ በመስጠት ልጆቻቸው የሀገርና የባንዲራ ፍቅር በውስጣቸው እንዲሰርፅ ያደርጉ ነበር። ይህ የልጅነት ትዝታ በጋሽ ጌታቸው እዕምሮ ውስጥ ለዓመታት ተቀርፆ ቆይቷል። በሀገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ብሔራዊ ስሜትን የሚያጭሩ ሥነ ፅሁፍ እና ተግባራት ላይ እንዲሳተፍ ምክንያት ነበሩ።

ይህንን ተከትሎ የሚሊኒየም ክብረ በዓል ወቅት ‹‹የብሔራዊ ሚሊኒየም ምክር ቤት›› አባል በመሆን ተሳትፏል። የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አከባበር ፅህፈት ቤት የሁነት ዝግጅቱ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን አገልግሏል። ይህ አጋጣሚ ነበር ከአንድ ጉዳይ ጋር ያገጣጠመው። ነገሩ እንዲህ ነው ከእርሱ ጋር ይሠሩ ከነበሩ የኮሚቴ አባላቶች ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ፣ አርቲስት ደበሽ ተመስገን፣ ሰራዊት ፍቅሬ እና ሌሎችም ጋር በጋራ በመሆን በመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ስለሚከናወኑ ሁነቶች ውይይት ያደርጋሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር መነሻ ሀሳብ ውይይት በምናደርግበት ወቅት ሰንደቅ ዓላማን የተመለከተ ሁነት ለማካሄድ ውይይት አደረግን›› የሚለው እንግዳችን ሁነቱ በጊነስ ቡክ ሊመዘገብ የሚችል ሰንደቅ ዓላማ ከማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሀር (በቸርቸር ጎዳና ልክ) የማዘጋጀት ሀሳብ አንደነበረ ይናገራሉ። ይህ ሀሳባቸው በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ አንደነበር በማንሳትም ከዚያን ግዜ ጀምሮ የባንዲራ ቀን መከበር መጀመሩን ያስረዳል። እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ የተቀረፀውን የሀገር ፍቅርና የሰንደቅ ስሜት በተግባር የተወጣበት መሆኑን ያነሳል።

ደራሲ ጌታቸው በለጠ ከሥነ ፅሁፍ ሥራዎቹ ባሻገር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነው። ለዚህ ማሳያው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የነበረው ተሳትፎ ነው። በዚህም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በተቋቋመው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ውስጥ አባል ነበር። በሂደቱም ወደ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ በመጓዝ ‹‹ኢትዮጵያ አትጎዳችሁም በዓባይ ተፋሰስ ጉዳይ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ነው የምትከተለው›› የሚለውን መልእክት ሕዝብና ሀገራቸውን ወክለው መልእክቶችን ያስተላልፉ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆኑ እንደሚያኮራውና የአገረ ፍቅር ስሜቱን የገለፀበት አንዱ መንገድ መሆኑን ይናገራል።

ስምንት ዓመታትን በደራሲያን ማሕበር

ደራሲ ጌታቸው በለጠ በሥነ ፅሁፍ ሥራዎቹ ልህቀት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለው ተሳትፎና በአመራር ጥበብ ክህሎት በወሰዳቸው ስልጠናዎች ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ አንጋፋ ከሆኑ ማሕበራት አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር ለሁለት የስልጣን ዘመናት መርቷል።

‹‹አንዱ ወርቃማ ዘመናችን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር የደረሰበት ነው›› ይላል ደራሲ ጌታቸው በእርሱ እርሱና ሌሎች ማህበሩን የመሩ ባልደረቦቹ ውጤታማ ሥራ እንደሠሩ እየገለፀ። በተለይ ማሕበሩ 50 ዓመት በዓሉን ሲያከብር በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ስመጥር ያደረገውን የአፍሪካ ደራሲያን ማሕበር ጉባኤ በኢትዮጵያ በማዘጋጀት፣ የፍቅር አስከመቃብር፣ ከቡስካው በስተጀርባ እና ሌሎች ድርሰቶችና ደራሲያኑን የሚዘክር፣ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ‹‹ሕያው የጥበብ ጉዞ›› በሚል መሰናዶዎችን በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ሕትመቶችን አሳትሞ በማሰራጨት፣ የደራሲያን የአዕምሮ ውጤት የሆኑ ሥራዎችን በግልና በጋራ በማሳተም፣ የማሕበሩ ፅህፈት ቤት የሚገነባበት መሬት እንዲገኝ በማድረግ መሥራታቸውን ይናገራል።

ደራሲ ጌታቸው ማሕበሩን ከመምራት ባሻገር 13 መፅሀፍትን ለተደራሲያኑ አቅርቧል። ስድስት የሕፃናት መፅሀፍትን ጨምሮ፣ የልቦለድ ሥራዎች፣ የአመራር ጥበብ መፅሀፍ፣ የተማሪዎች መርጃ መፅሀፍት አበርክቷል። በአርትኦት ሥራው እንዲሁ ተመሳሳይ ተፅእኖ በስነ ፅሁፉ ላይ አለው።

‹‹ባዶህን ሙት›› የደራሲው ፍልስፍና

ደራሲ ጌታቸው የጸሀፊ ቶድ ሄነሪ አድናቂ ነው። ከእርሱ ከወረሳቸው አመለካከቶች አንዱ ያለህን እውቀት በሙሉ ለሀገርህ እና ለወገንህ ሰጥተህ ተሰናበት (ወደመቃብር ይዘህው አትውረድ) የሚለውን መርህ እንደሚወደው ይገልፃል። ከተፅእኖዎቹ ውስጥ ‹‹ቂም፣ በቀል፣ ጥላቻ እና ክፋት አዕምሮ ውስጥ ካለ እርሱንም አራግፈህ ሙት›› የሚል ነው። እርሱም በዚህ እሳቤ መመራት ምርጫው ነው። ሀገሩና ወገኑን በዚህ ልክ ማገለገል የሕይወት ፍልስፍናው ነው።

በኢትዮጵያ በምርመራ ጋዜጠኝነት ታዋቂ የሆኑት አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ ተፈራ እምሩ (ዶ/ር) ደራሲ ጌታቸው ከሰሞኑ ባሳተመው ‹‹የትዝታዬ ማሕደር ግለ ታሪክ›› መፅሀፍ ላይ ምስክርነት ሲሰጡ የሕይወት ፍልስፍናው እና መርሁን የሚያሳይ ሀሳብ አስፍረው ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት ደራሲው በግለ ታሪኩ ውስጥ አብራርቶ የተረካቸው እውነታዎች ለረዥም ዓመታት በሥነ ጽሑፍ ሙያው፤ በተለይም በሚዲያው ዙሪያ፤ ያከናወናቸው ተጨባጭ አበርክቶዎች ለትውልድ ሊተላለፉ የሚችሉ ቅርሶች ለመሆናቸው ቋሚ ማሳያዎች ናቸው። ደራሲው በሚጠቀምባቸው የብዕር ስሞች አማካይነት ለሕዝብ ያቀረባቸው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውና በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ትምህርታዊና መረጃ ሰጭ ትንታኔዎች በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመንና በተለያዩ መጽሔቶችና የሕትመት ውጤቶች ስናነብና እንዲሁም በኢትዮጵያ ሬድዮ በየጊዜው ስናደምጥ መኖራችን የሚዘነጋ አይደለም።

ቤተሰብ

በሕይወቴ ላይ ላሳካኋቸው ጥረቶቼ ባለቤቴ ወየዘሮ ሰናይት ኃ/ማሪያም ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች ይላል። ባለቤቱ የእግዚአብሄር ስጦታ መሆኗን እየተናገረ በሥራዎቹ ሁሉ ከጎኑ በመሆን የምታግዘው አጋሩ አንደሆነች ይናገራል።

ያሳደጉት ልጃቸው ሲድራቅ በለጠ በ2011 መጋቢት 1 ቀን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በቢሾፍቱ አካባቢ በደረሰውና አደጋ ምክንያት ሕይወቱን ማጣቱን በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሆኖ ይናገራል። የትዝታዬ ማሕደር በሚል ርዕስ ያሳተመውን የሕይወት ጉዞውን በመታሰቢያነት ለልጁ እንዳበረከተም ይገልፃል። ‹‹ባለቤቴ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አብራኝ የቆየች የሕይወት አጋሬ ናት። ፈተናዎችን በእግዚአብሄር አርዳታ ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚቻልም አምናለሁ›› በማለት ለሕይወቱ መቃናትና መሰረት መያዝ የቤተሰቡ ደርሻ ጉልህ አንደሆነ አጫውቶናል። ሀሳቡን ሲያጠቃልልም በቀጣይ በሥነ ፅሁፍና በማማከር፣ አንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የድርሻውን በማበርከት የሕይወት ዘመኑን እንደሚያገለግል በመግለፅ የነበረውን ቆይታ ቋጭቷል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You