ኢትዮጵያዊያን ረሀብ ሲፈራረቅብን መኖሩ እርግጥ ነው፡፡ በበለፀጉ አገራት ስንረዳ መቆየታችንም አይካድም፡፡ አሁን አሁን ከዕርዳታ ተላቅቀናል ቢባልም “ከውጭ የምናስገባው ስንዴ ምንዛሪያችንን እንክት አድርጎ እየበላው ይገኛል፡፡” እየተባለ ነው፡፡ ሌላውም ሆነ እኛ እንደምናውቀው የዚህ ሁሉ መከራ መነሻና የችግሩ ምንጭ የገንዘብ እጥረትና ስንፍናችን እንጂ ሌላ አይደለም፡፡
ተፈጥሮ የሰጠችን ፀጋዎች ከዚህ በመለስ የሚባሉ አይደሉም፡፡ አሁን አሁን እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር (70 በመቶ ወጣት) ሲጨመርበት ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ከራሳችን አልፈን ለሌላውም መትረፍ ስንችል ሳይሆን መቅረቱን ስናስብ ከመቆጨትም አልፎ ያሳዝናል፤ ለትዝብትም ይዳርጋል፡፡ ከዚሁ ትዝብት ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው አቢይ ጉዳይ ቢኖር በ1966 ዓ.ም በአገራችን ተከስቶ የነበረውን አስከፊ ረሀብ ያጋለጠው የቢቢሲ “አረንጓዴው ረሀብ”(The Green Drought) ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡
ይህ ፊልም፣ ሰብአዊ ገፅታውና አስተዋጽኦው እንዳለ ሆኖ፣ ስለማንነታችን ያስተላለፈው ሚስጢራዊ ቋጠሮ ርእሱ ላይ ተደብቆ መገኘቱ ነው፤ “አረንጓዴው ረሀብ”፡፡ ጉዳዩ እውነት ሲሆን ከዚህ በላይ ምንም አይነት ስላቅ እንደሌለም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ዘጋቢ ፊልሙ ዓለምን እምባ ያራጨ፣ ኪስ ያስዳበሰና ፈጥነው ይደርሱልን ዘንድም ያጣደፈ ይሁን እንጂ ስንፍናችንን፣ የተሰጠንን ፀጋ መጠቀም አለመቻላችንን፣ ረሀቡ ፈልጎን ሳይሆን ፈልገን ያመጣነው መሆኑን፣ ተፈጥሮ አንድ፣ ሁለት … በማለት ከማንም በላይ ቆጥራ ያስረከበችንን በረከት መጠቀም አለመቻላችንን፣ ኋላ ቀርነታችንን፣ ሰነፎች መሆናችንን፣ ጠባቂነታችንን ወዘተ ወዘተ የገለፀ ሸንቋጭ ርዕስ መሆኑን አዘጋጁ በ”አረንጋዴው ረሀብ” አማካኝነት ቁልጭ አድርጎ ገልጾአል፡፡ (የዳኛቸው ወርቁ “እምቧ በሉ ሰዎች” የሽፋን ስዕልም ሆነ የአሁኑ ዘመን “አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ ፤ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ” ዜማ የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡)
በፈንታሌ ሰሞኑን በተደረገ የስንዴ መስኖ ልማት የመስክ ጉብኝት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴንም ያሉት ይሄንኑ ነው፤ “መሬቱም እዚሁ ነው፣ ውሃውም እዚሁ ነው፤ ሰውም እዚሁ ነው፡፡ ነገር ግን ባለመሥራታችን ብቻ ስንቸገርና ለድህነት ተጋልጠን ስንራብ ኖረናል፡፡ ባለመሥራታችን ብቻ ስንዴ ከውጭ ስንለምን ኖርን፤ በሌለን የውጭ ምንዛሪ ስንዴ ከውጭ በሚሊዮን ዶላሮች እየገዛን ነው፡፡ አሁን መንግሥትና ህዝቡ በጋራ እየሠሩ ያሉት በጥቂት ዓመታት ውስጥ እራሳችንን በመቻል ስንዴን ከውጭ ማስመጣቱን ለማስቀረት ነው፡፡” ይህ ከሆነ እየተሸጋገርን ነው ማለት ነው፡፡
ሌላውና ወገብን ጠፍሮ መሥራትን የሚጠይቀው ጉዳይ የህዝብ ቁጥር መጨመር ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋ.ኦ) እ.ኤ.አ “በ2050 የዓለማችን የህዝብ ቁጥር ወደ ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ከፍ የሚል ሲሆን፤ የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት ደግሞ የስንዴ ምርት ላይ 60 በመቶ ጭማሪ መደረግ አለበት፡፡” የሚል መረጃ ወጥቶ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ስንዴ ላይ አተኩራ መሥራቷ የራሷን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተገቢ ነው ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ በስንዴ አምራችነት ከአራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ኑሯቸውን የመሰረቱበት መሆኑ የሚነገርለት ነው፡፡ በሄክታር ሁለት ነጥብ ሰባት ቶን የሚገኝበት ስንዴ ከ90 በመቶ በላይ ምርቱ ግን በአነስተኛ ገበሬዎችና በአነስተኛ የእርሻ ይዞታ የሚመረት ከመሆኑም ባሻገር ምንም አይነት መስኖ የማያውቀው በመሆኑ ለምርታማነቱ መውረድ በምክንያትነት ሲጠቀስ ኖሯል፡፡ አሁን ግን ይህን ታሪክ ለመቀየር እየተሠራ ስለመሆኑ ነው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የሚናገሩት፡፡ በኦሮሚያ፣ አፋርና ሱማሌ ክልሎች የሚታየውም ይሄው ነው (ጉዳዩ “ከዓይን ያውጣሽ” የሚለው ላይ ነው እንጂ)፡፡
የባለፈው ዓመት የአሜሪካው ጌይን ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ከስድስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ የስንዴ ፍላጎት ይኖራል፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ ያለው ዕድል ወይ መለመን፤ አልያም ጠንክሮ መሥራት ሲሆን እንደ ግብርና ሚኒስቴር ወቅታዊ መረጃ መፍትሄው ጠንክሮ መሥራት በመሆኑ “እየተሠራ ይገኛል”፡፡
ባለፈው ዓመት በአርሲ ዞን ኩታ ገጠም መሬቶችን በማዋሀድ(Cluster approach) እየተከናወነ ያለው ተግባር ይህንን ሁሉ ችግር ለመቋቋምና የተሻለ ለማምረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በትግራይ ክልል የታየው ተሞክሮም ሌላውና ተጠቃሽ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በመስኖ ልማት ስንዴን ማልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው፤ በቦታው ተገኝተንም ተመልክተናል፡፡ ደስ ይላል፤ አንድን ወቅት (ክረምት) ብቻ ጠብቆ ከማምረት ወደ መስኖ ልማትም እየተሸጋገርን ነው ማለት ነው፡፡
በእርግጥ በምርጥ ዘሩም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ እየተነገረ ነው፡፡ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከሰጠው መረጃ እ.ኤ.አ እስከ 2017 መስከረም ወር ድረስ 72ሺህ 634 የሰብል፣ የአበባ፣ የአትክልና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) ዝርያዎች ናሙና በጂን ባንኩ ውስጥ” መኖራቸው ተነግሮናል፡፡ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ካለው የአፈርና አየር ጠባይ ሁኔታ ጋር ተስማሚነታቸውን አጥንቶ ተግባር ላይ የማዋሉን ጉዳይ በተመለከተ ግን አሁንም ችግሮች መኖራቸውን ኢንስቲቲዩቱ አልሸሸገም፡፡
ከእነዚህ 72ሺህ 634 ናሙናዎች ውስጥ በ2003 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ደጀኔ ካሳሁን አማካኝነት ተወስዶና ከአካባቢው ሁኔታ ጋር ተጠንቶ ወደ ሥራ ተገብቶበት ውጤታማ የሆነው “ዱረም” የተባለው የስንዴ ዝርያ ይገኛል፡፡ 60 አርሶ አደሮችን በማካተት የተጀመረው ይህ ሙከራ በአሁኑ ጊዜ ከ900 በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፈ በመሆኑ ሰፊ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ሌሎች ክልሎችስ ይህን ማድረግ ስላለማድረጋቸው መረጃ አለ?
በተለያዩ ጊዜያት ሲገለፅ እንደሚሰማው በኢትዮጵያ ለምርትና ምርታማነት ዝቅተኛነት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች “የተሻሻሉ ዝርያዎች አጠቃቀም አነስተኛ መሆን፤ የስንዴ በሽታዎች የሚያስከትሉት ጉዳት፤ አነስተኛ የምርት ግብዓት አጠቃቀም (ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ማዳበሪያ፤ ምርጥ ዘር)፤ ኋላ ቀር የአመራረት ዘዴ፤ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነ አመራረት፤ የአረም ፤ የአፈር ለምነት መከላት፤ ደካማ የገበያ ትስስርና ሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች (ድርቅ፣ ውርጭ)” ይጠቀሳሉ፡፡ ኃላፊዎቹ እንደሚሉት አሁን እነዚህ ችግሮች እየተወገዱና ዘርፉን በማዘመን ለተሻለ ምርትና ምርታማነት እየተሠራ ሲሆን፤ ከ”በዓመት ከአንድ ጊዜ ወደ በዓመት ሁለቴ” ማምረት ደረጃ ታሪካዊ ሽግግር እየተደረገ ነው፡፡
ይህ እውነት ከሆነ ልክ እንደነ እንግሊዝ በሄክታር 16 ነጥብ አምስት ቶን የማናመርትበት ምክንያት የለምና በዚሁ ልክ ብንቀሳቀስ፤ የተጀመሩ ሥራዎችም ቢቀጥሉ መልካም ነው እንላለን፡፡ የግል ባለሀብቶችም በዘርፉ እንዲሰማሩ እየተጋበዙ እንደሆነ ሰምተናል። ስለዚህ ባለሀብቶቹ ከከተማ መውጣቱን ቢለምዱት ይጠቀማሉና ቢያስቡበት ጥሩ ነው እንላለን፡፡ ሁላችንም የረሀብ ምንቸት ወጥቶ የጥጋብ ምንቸት ገብቶ ለማየት እንጓጓለን፡፡
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ግርማ መንግሥቴ