የካቲት የታሪክ ወር ነው ማለት ይቻላል። የቅርቡን ጨምሮ በዚህ ወር ብዙ ታሪኮች ተፈጽመዋል። የካቲት 12ቀን 2012 ዓ.ም ታስቦ የዋለው 83ኛው የሰማዕታት ቀን ይጠቀሳል። ቀኑ ከአድዋ የድል በዓል ጋር ግንኙነት ስላለው ነው አይረሴ ያደረገው። ዘመናዊ መሣሪያ እስከአፍንጫው ታጥቆ ኢትዮጵያን በግፍ ለመውረር የመጣውን ጣሊያንን ጀግኖች አባቶችና እናቶች አድዋ ላይ ሽንፈት አከናንበው አሳፍረው በመመለሳቸው ነበር ፋሽስት ጣሊያን ቂም ቋጥሮ አጸፋውን በንጹሀን ሕዝብ ላይ ለመመለስ ባካሄደው ጭፍጨፋ የ30ሺ ንጹሀን ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው።
የካቲት 23ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካውያን ኩራት የሆነው የአድዋ ድል በዓል ይከበራል። በበዓሉ ሰማዕታቱን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ የታሪክ ገድሎች ይነገራሉ። ይዘከራሉ። ታሪኩ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥልም መልዕክት ይተላለፋል።
የድሉን ተምሳሌት ለመልካም ነገር ማዋሉ ጥቅም እንዳለው ብዙዎች ይናገራሉ። ወጣቱ የትናንት ማንነቱን ሳይረሳ ሀገሩን ከጠላት በመከላከልና በልማት በማሳደግ ታሪክ የማቆየት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል የሚሉም ጥቂት አይደሉም። ጀግኖች አባቶችና እናቶች አንድ ሆነው ፋሽስት ጣሊያንን ድል እንዳደረጉት ሁሉ ድህነትንም ማጥፋት የሚቻለው፣ ህብረትና መተሳሰብ ሲኖር ነው። ይሁን እንጂ ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ ከማወቅ ጀምሮ ሀገራዊ አንድነቱን አጠናክሮ በልማቱ ያለው ተሳትፎ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ይታማል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ታደለ ቤዛ ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ በማወቅም ሆነ ከታሪኩ ትምህርት በመውሰድ በኩል የሚያደርገው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ነው ብሎ አያምንም። እርሱ እንደታዘበው ወጣቱ አዕምሮውን አስፍቶ የተለያዩ ነገሮችን ለማወቅ ከመጓጓትና ለመስራትም ከመነሳሳት ይልቅ በአንድ ነገር ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይስተዋልበታል። ይልቁንም የራስን ታሪክ አውቆና አክብሮ ሕዝብን በሚጠቅም ነገር ላይ ማዋሉ እንደሚጠቅም ይመክራል። የተለያየ ግንዛቤ ያለው ሰው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ነገሮች ለመፍጠር ከመርዳቱም በላይ አኩሪ ታሪኮችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ ክፍተት ያለባቸውን ደግሞ ለማረምና ለማስተካከል ያግዛል ብሎ ያምናል። እንደ እግር ኳስና አንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ታሪክን በተለይም እንደ አድዋ የድል በዓል ያሉትን አጀንዳ አድርጎ እርስ በርስ ውይይት የሚያደርግ ሰው አላጋጠመውም። መገናኛ ብዙኃንም በዓሉ ሲደርስ ብቻ መረባረባቸው ለትኩረቱ ማነስ መንስኤ እንደሆነ ይገምታል።
ወጣት ታደለ ‹የዓድዋ ድል ታላቅ ኩራታችን ነው። ዓለምም ያደነቀው ነው› ሲል ይገልጻል። ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ለሀገር ፍቅር ሲባል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት እንዲሁም ህብረትና የሀገር ፍቅር እስካለ ድረስም ድል ማድረግ እንደሚቻል ከዓድዋ ድል መማሩን ይናገራል። ወጣቱ እንዳለው ትውልዱ ታሪክን ማወቁና ካለፈው ትምህርት መውሰዱ ሌላ ታሪክ ለመስራት መንገድ ይከፍትለታል። ታሪክ መስራት በጦርነት ብቻ ላይሆን ይችላል። እራስን በተለያየ መንገድ ከመለወጥ ጀምሮ በሀገር ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራትን በማከናወን ይገለጻል።
ወጣት ታደለ ስለ አድዋ ድል ስላለው ግንዛቤም ወራሪዎች የቅኝ ግዛት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያደረጉት ነው ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ‹ኩሩ ሕዝቦች ነን፣ አንገዛም› ብለው ጠላትን በመጣበት አሳፍረው በመመለስ ሀገራቸውን ከወራሪው ተከላክለው ዳር ድንበራቸውን በመጠበቅ እንዳቆዩዋት ይናገራል። የአድዋ ላይ ጦርነት መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል ስምምነት እንደሆነም ከታሪክ ማወቁን ይገልጻል።
አራት ኪሎ አካባቢ ያገኘናት ወጣት ቤዛዊት ቸሩ የድል በዓሉን አስመልክቶ የመወያየት ልምዱ አናሳ እንደሆነ የወጣት ታደለን ሀሳብ ትጋራለች። በየካቲት ወር የሚከበር አንድ ታላቅ በዓል ስለመኖሩ እንድትነግረኝ ጠየኳት፤ ለማስታወስ ተቸገረች። ሳስታውሳት ግን ይሄማ አይጠፋኝም በሚል ስሜት ጀገኖች አባቶች ኢትዮጵያን በኃይል ሊወር የመጣውን ጣሊያን ድል ያደረጉበት ቀን እንደሆነ ነበር የነገረችኝ። በዓሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚወክል እንደሆነና ሁሉም በእኩል ሊያከብረው እንደሚገባ ትገልጻለች።
‹‹ጀግኖች አባቶች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስከበሩት በብሔር ሳይከፋፈሉ አንድ ሆነው ነው›› የምትለው ወጣት ቤዛዊት፤ ከዚህ አንድነት፣ መከባበርና መተሳሰብን እንደተማረችም ትናገራለች። በተለይም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አንተ የእከሌ ዘር ነህ የሚለውን በማስታወስ ጀግኖች አባቶችና እናቶች በዘር ቢከፋፈሉ ኖሮ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ጠብቀው አያቆዩም ነበር በማለት ታስረዳለች። የካቲት 23 የአድዋ ድልን በጊዮርጊስ አደባባይ ተገኝታ ለማክበር መዘጋጀቷን ነግራኛለች።
ሌላው ሀሳቡን የሰጠኝ ወጣት ፊሊጶስ ወንድወሰን ይባላል። በሲፒዩ ኮሌጅ የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ነው። በሚማረው ትምህርት ላይ መረጃ ለማግኘት እንጂ ታሪክ ለማወቅ ጥረት እንደማያደርግ ነው የገለጸልኝ። እርሱ እንዳለው ወጣቶች ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እንደ ቀልድ የሚያነሷቸው ነገሮች አይጠፉም። የሚያውቁትን ነገር ለመጠያየቅ ይሞክራሉ። ግን ስለጉዳዩ በጥልቀት ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ግን ዝቅተኛ ነው። ከጀግኖች አባቶችና እናቶች አልገዛም ባይነታቸውን ያስታውሳል። ኢትዮጵያ በቅኝ እንዳትገዛ አስተዋጽኦአቸውም ከፍተኛ እንደሆነ ይገነዘባል። እርሱን ጨምሮ ይህን ትልቅ ታሪክ ከማወቅ ጀምሮ ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት ያምናል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ማህበሩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ አድዋ ላይ የተገኘውን ድል መሠረት በማድረግ ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል። ማሳወቅ ብቻም ሳይሆን እንዲኮሩበትና በየተሰማሩበት መስክም ለሀገራቸው ታሪክ እንዲሰሩ ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችው ጀግኖቿ ከራሳቸው በላይ ሀገራቸውን በመውደዳቸው እንደሆነ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በአኩሪ ታሪካቸው ዳር ድንበር ያስከበሩ ጀግኖች በወጣቱ ትውልድ ሊታወሱና ሊወደሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2012
ለምለም መንግሥቱ