ሳብሪና ኦርጂኖ ትባላለች። ለበጎ አድራጊነት ቅን ልብ ያላት ወጣት ነች። ደግሞ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ። በእነዚህ ስራዎቿ በዓመት ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ትታወቃለች። ለተቸገሩ ሰዎች መድረስ የሁልጊዜም ተግባሯ ነው። በአሁኑ ወቅት 104 ልጆችን በመርዳት ላይ ትገኛለች። 20 ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው ህጻናትን ደግሞ ማቆያ ማዕከል በመክፈት ታግዛለች።
ይህን ስኬቷን በቀላሉ አላገኘችውም። እዚህ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። ይሄም በብዙዎች ዘንድ ምሳሌ ለመሆን አስችሏታል። ሰው ለሰው እጁን እንዲዘረጋ፤ ቅን ልብ እንዲኖረው በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር ትታወቃለች። እኛም የሳብሪናን የህይወት ዶሴ በመግለጥ በጎነቷን፤ እዚህ ስኬት ላይ ለመድረስ የከፈለችውን መስዋእትነትና ያጋጠማትን ፈተና ለማለፍ የወጣች የወረደችውን መንገድ በመቃኘት ለዛሬው የ‹‹ህይወት እንዲህ ናት›› አምዳችን እንግዳ አድርገናታል።
የሰው ስሙ ተግባሩ
ትውልዷ አሰላ ቢሆንም የአሰላን ውሃ ብዙም ጠጥታ አላደገችም። ምክንያቱም አባቷ የህክምና ባለሙያ በመሆናቸው ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የሚሰሩ ናቸው። በዚህ የተነሳ ቤተሰቡ የልጃቸው መንገላታት ስላሳሰባቸው ከእናቷ ጋር ሆሳዕና እንድትኖር አደረጉ። ከዚያች እለት ጀምሮ ሳብሪና የሆሳዕና ልጅነቷን አረጋግጣ እድገቷን በዚያ አደረገች። ይህም ቢሆን ከእድሜ እኩዮቿ ጋር የመጫወት እድሉን አላገኘችም።
ምክንያቱ ደግሞ ከቤት ወጥታ ከሰፈር ልጆች ጋር ለመጫወት የቤተሰብ ፍቃድ ስለማታገኝ ነበር። ስለዚህ በጭቃ ከምትሰራቸው አሻንጉሊቶች ጋር ወዳጅነት እንድትመሰርት ተገዳለች።
ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ሳብሪና በትምህርቷ ጎበዝ እና ጠንካራ አይነት ልጅ ባለመሆኗ ይበሳጩባት ነበር። ሆኖም በተቃራኒው የውሸት ባህሪ ስላልነበራት ይደሰቱባት እንደነበር ታነሳለች።
እንግዳችን መጀመሪያ ሮማን የሚል መጠሪያ ነበራት። ይህ ስም የወጣላትም በቀለሟ ነጮችን ስለምትመስል “ከጣሊያን የመጣች” ሲሉ እንደነበር ትናገራለች። ቀጥሎ ደግሞ ፍሬህይወት ተብላለች። ይህ መጠሪያ የተሰጣት ደግሞ እናትና አባት ተለያይተው ቆይተው ስለነበር የመገናኘታቸው ምስጢር በመሆኗ ነበር። በሦስተኛ ትግዕስት ተብላም ተጠርታለች። ዳግመኛ በትዕግስት መገናኘታቸውን አብነት በማድረግ አውጥተውላታል። ይሁንና ይህ ስም ብዙ መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱም የአባቷ የእህት ልጅ መጠሪያ ትዕግስት በመሆኑ ስሙ ለታላቅ ይለቀቅ በመባሉ እርሷን የቤቱ እመቤት ነሽ ሲሉ እመቤት አሏት።
እመቤት የሚለው መጠሪያ ስም ግን ለእርሷ ምቹ እንዳልሆነ የምታነሳው ሳብሪና፤ በሰፈራቸው ወይዘሮ እመቤት የተባሉ ትልቅ ሴት ስለነበሩ ትልቅ ላለመባል በራሷ ፈቃድ ስሟን እንደቀየረችና ሰብለወንጌል እንዳስባለችው አጫውታናለች።
ውጪ አገር ከሄደች በኋላም ስሟ እንዳልጸና የምትገልጸው ባለታሪኳ፤ ብዙዎች ቃሉን መጥራት ስለሚከብዳቸው” ሰብለ ወንጀል” እያሉ ስላስቸገሯት ወንጀለኛ አይደለሁም በማለት ወንጌልን በመተው ሳብሪና ብላ ቀይራዋለች።
ሳብሪና በልጅነቷ አንድ ህልም ብቻ ነበራት። ይኸውም በጣም ሀብታም መሆንና ሰዎችን ከችግራቸው ማላቀቅ፤ በዚህም ከቤተሰቧ ሳንቲም እየወሰደች ገንዘብ አጠራቅማ ለችግረኛ ልጆች ጫማ ትገዛ እንደነበር ታስታውሳለች። የራሷን ጫማ አንድ እግር ደብቃ ጠፋ በማለት ከተረሳላት በኋላ ጫማውን ለተቸገሩት ታድል እንደነበርም አትረሳውም። ይህ ደግሞ የተቀደደ ኮንጎ (ላስቲክ ጫማ) እስከመልበስ አድርሷት እንደነበርም ትናገራለች።
እንግዳችን በልጅነቷ ሰዎችን አክባሪ ናት። የይቻላል መንፈስን ያነገበች፤ የምትፈልገውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማትል፤ በቆራጥነት መንፈስ የምትሰራም ነች። ሽንፈትን አጥብቃ የምትጠላ እንደነበረችም አጫውታናለች።
ከሆሳዕና እስከ ሮም
እናቷ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረው በማቋረጣቸው ቁጭት ነበረባቸው። በዚህ ምክንያት ልጆቻቸው ተምረው ቁጭታቸውን እንዲወጡላቸው ይፈልጉ ነበር። ዘወትር ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ይጎተጉታሉ። አልፎ ተርፎም የቻሉትን ያህል ያስጠናሉ። ያም ሆኖ ግን ሳብሪና የምትማረው ስለማይገባት ማጥናትም ሆነ ትምህርት ቤት መሄድ አትወድም። ይህ ባህሪዋ በቤተሰቧ ዘንድ ትምህርት የማይገባት ልጅ አስብሏታል። እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ይጨነቁ ነበር።
ሆኖም ሳብሪና ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ይልቅ የተግባሩ ቶሎ ይገባታል። ስለዚህም የተሻለ ተማሪ እንድትሆንላቸው ለማድረግ የሙያ ትምህርት በግል እየተከፈለላት በሆሳዕና ካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት እንድትገባ ተደረገ። እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማረች በኋላ የትምህርት ፍላጎቷ ይባስ እየተዳከመ መጣ። ትምህርት ወዳድ እንዳትሆን ያደረጋትን ምክንያት የተረዳት አልነበረም። የድሃና የሀብታም ልጆች በአለባበስ ያላቸው ልዩነት ያናድዳት ነበር። በተለይም የኢኮኖሚ አቅም ያለው ሰው ለተቸገሩ መድረስ አለመቻሉ ቤተሰቧንና ጓደኞቿን ጭምር እንድትጠላቸው እንዳደረጋት ትናገራለች።
በዚህም ልዩ ትኩረቷን ለሰዎች በተለይ ጫማ ለሌላቸው ልጆች እንዴት መድረስ እንደምትችል ማሰብ ላይ በማድረጓ ለትምህርቷ ትኩረት እንዳትሰጥ አድርጓታል። ቤተሰቧ የእርሷ እንዲህ መሆን ያሳስባቸዋልና በትርፍ ጊዜ የምትማርበትን ሁኔታ አመቻቹላት። እርሷ በዛን ወቅት በካቶሊክ ትምህርት ቤት መማሯ ሰውን ለመርዳት ያላትን ፍላጎት ይበልጥ ጨመረው፤ ከቤተሰቦቿ ጠፍታ አዲስ አበባ እስከመግባት አድርሷታል። የሁለተኛ ምዕራፍ ትምህርቷም የቀጠለው እዚሁ አዲስ አበባ ከገባች በኋላ ነበር።
መነን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 7ኛ ክፍልን እንደተማረች የምትናገረው እንግዳችን፤ ከስምንት እስከ ዘጠኝ የተከታተለችው ደግሞ በካቴድራል ትምህርት ቤት ነው። ይህ ጊዜ ሌላ የትምህርት ምህዋሯን ቀይሮት ኖሮ ወደጣሊያን እንድታቀና ምክንያት ሆናት።
ከብዙ ድካምና እንግልት በኋላም የሚያስተምራትን አሳዳጊ ቤተሰብ በማግኘቷ የግል ኮሌጅ በመግባት ቋንቋ ተማረች። የአገሩ የትምህርት ሥርዓት ከኢትዮጵያ የሚለይ በመሆኑ ውጤታማ ካልሆኑ በስተቀር በቋሚነት ዘመናዊ ትምህርት አይፈቀድም። እርሷ ግን በብዙ ትግል ተፈቀደላት። በእርግጥ ለዚህ መነሻው በቋንቋ ትምህርቱ የተሻለ ውጤት ማምጣቷ እንደነበር ታስታውሳለች።
ስምንተኛ ክፍልን በሴና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ እንድትማር ተፈቀደላት። ይህም የሆነው አሳዳጊዎቿ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለውላት እንደነበር ትናገራለች። ቀጣዩ የትምህርት ክትትሏ የሚወስደን ወደ ሮም ሲሆን፤ የመማር ፍላጎቷ የተገለጠበት ጊዜ ነበር። በዚህም ልዩ ፍላጎት ከሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ሆና በ‹‹ግራንድ›› ትምህርት ቤት ገብታ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ተማረች።
ሳብሪና፤ የ12ኛ ክፍል ውጤቷ ዩኒቨርሲቲ ባያስገባትም ወደ ሙያ ትምህርት አዘንብላለች። የልዩ ፍላጎት የትምህርት መስክን መርጣም በ‹‹ሎጎስ›› የግል ኮሌጅ በመማር ድግሪዋን ይዛለች። ቀጥላ የህግ ትምህርት የተማረች ሲሆን፤ በቼፑ ዩኒቨርሲቲ በርቀት ትምህርት ዲግሪዋን አግኝታለች።
‹‹የምማረው የትምህርት ርሀብ ኖሮብኝ ሳይሆን ለበጎ ተግባር ስራዬ የሚረዳ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው።›› የምትለው ባለታሪኳ፤ የህግ ትምህርትን የተማረችው የህግ ከለላ የሚያስፈልጋቸው አፍሪካውያን ለማገዝ በማሰብ ነው። በተለይም ኢትዮጵያዊያን በጣሊያን አገር መንገድ ዳር ሲለምኑ ማየቷ ልዩ ቁጭት ፈጥሮባታል።
የልዩ ፍላጎት ትምህርትን የተማረችው እርሷን መሰል ዜጎች በአገራችን በርካቶች በመሆናቸው እነርሱን ከዚህ ችግር ለማውጣት እንደሆነ የምትናገረው ሳብሪና፤ አሁንም ለመማር እንደምትፈልግ አጫውታናለች። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ያለፈችው እስከዘጠነኛ ክፍል በመሆኑ ይህንን ጠልቃ ካልተረዳች በሥራዋ ስኬታማ መሆን እንደማትችል ታምናለች። እናም በርቀት ትምህርት ለመማር ራሷን እያዘጋጀች መሆኑን አውግታናለች።
ሳብሪና በሌሎች አገራት የትምህርት ጉዞ ውስጥ 46 በመቶ ልዩ ፍላጎት የሚስፈልጋት ተማሪ በመሆኗ ይህንን የተመለከተ ትምህርት ለመማርም ነው የምትፈልገው። “ይህ ደግሞ ለእኔ ተሳክቶልኝ ከተጓዘ ወደፊት አስፍቼ ለምሰራበት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተስፋ ይሰጣልም” ብላለች።
የደስታ ምንጭ
‹‹እኔ ለአገሬ ልጆች መፍትሄ እስከሆንኩ ድረስ የምሸሽገው ማንነት የለኝም›› የምትለው ባለታሪኳ፤ ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችን የምታገለግልበት ትምህርት ቤት ከፍታ ትሰራለች። ይህም ከመዝናናት፣ ስፖርት ከመስራትና ከሰዎች ጋር ከመጫወት በላይ እፎይታን ይሰጣታል። የደስታዋ የመጨረሻ ጥግ የሚሆነው ሰዎች በእርሷ ስራ ሲደሰቱና ችግራቸው ሲፈታ ስታይ ነው። ለአብነት እስካሁን ከሰራቻቸው ውስጥ የአምስቱ ልጆችን ታሪክና ያላቸው ለውጥ እንደሚያስደስታት ትናገራለች። የነበሩበት ህይወት ከሳምንት በላይ አስለቅሷታል። ዛሬ ግን ተምረው ከችግራቸው በመውጣታቸው ደስተኛ እንድትሆንና በተስፋ እንድትሰራ እንዳስቻላት ታስረዳለች።
ሳብሪና በመስጠት የደስታ ምንጯን ፍለጋ የጀመረችው ገና በልጅነቷ ነበር። ለዚህ ደግሞ መንስኤዋ የአንድ በባዶ እግሩ የሚሄድ ልጅ እንቅፋት መመታት ነው። እናም ‹‹ለምን?›› በማለት ለእርሱ አይነት ልጆች ለመድረስ የሚሰጣትን ሳንቲም ማጠራቀም ጀመረች። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንዲት በባዶ እግር የምትሄድ ልጅን ከእንቅፋት ታደገቻት። ይህ ደግሞ ጉዞዋ በበጎነት እንዲሞላ አደረገው። ምክንያቱም የልጅቷ የዛን ቀን ፈገግታ ከአዕምሮዋ እንዳይጠፋ ሆኗል።
ማንም ይህንን ፍላጎቷን ተረድቷት እንደማያውቅ እንደውም ‹‹አትችይም›› የሚላት ብዙ ሰው እንደነበር የምትናገረው እንግዳችን፤ ‹‹እኔ ለድሃ መኖር ነው የምፈልገውም››› ያለቻት አንዲት እማሆይ ካቶሊክ ግን ህልሟን ለማሳካት ብርታት እንደሆነቻት አጫውታናለች። በተለይ ቤተሰብ ጋር እያለች የነበረባት ፈተና ከባድ እንደነበርም አትረሳውም። ምክንያቱም ደስታዋን እየፈለገች እንደሆነ አልተረዱምና፤ እርሷ ደግሞ ችዬ አሳያችኋለሁ የሚል እልህ ነበራት። በጥረቷም የዛሬውን ስኬት አገኘች።
ያልተጠበቀ ህይወት
የደስታ ምንጯን ፍለጋ በምትዋትትበት ጊዜ ነበር ከቤተሰብ ጠፍታ አዲስ አበባ ከገባች በኋላ ሥራን ሀ ብላ የጀመረችው። በአዲስ አበባ ‹‹ማዘር ቴሬዛ ገዳም›› በመግባት በኤች አይ ቪ ከተያዙ ህመምተኞች ጋር በማቆያው ዓመታትን ስታሳልፍ አንዳንድ ሥራዎችን ትሰራ ነበር።
ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ደግሞ መካኒሳ ‹‹ሳሊዢያን ወይም ዶንቦስኮ ›› የተባለ ገዳም ውስጥ ገብታም እየተማረች የተለያዩ ሥራዎችን ታከናውን ነበር። ይሁንና መሀል ላይ ታመመች። በዚህም ከማህበሩ ለመውጣት ተገደደች። ይህ ደግሞ ማንም እንደሌላት እንዲሰማት አደረገ። ሆኖም ግን ካቴደራል ስትማር የምታውቃቸው የንስሀ አባቷ ነበሩና ወደ እርሳቸው ሄደች። ችግሯንም ነገረቻቸው። እርሳቸውም እንደሚረዷት ቃል ገቡላት። በዚህም ተስፋዋ ዳግመኛ ለምልሞ ወደ ሥራ ገባች።
ከእዚህ ቀደም የሚያውቋት ሌላ አባት አገኝዋትናም በስልክ ኦፕሬተርነት ቀጠሯት። ስድስት ወር ሲሞላት ወደጣሊያን የምትሄድበት ሁኔታ ተፈጠረ። አዲስ ህይወት በጣሊያን አገር ጀመረ። በእርግጥ ገና ከአገሯ ስትነሳ ሦስት አላማዎችን በልቧ ላይ አትማ ነው የተጓዘችው። ይኸውም የመጀመሪያው እናትና አባቷን ይቅርታ መጠየቅና ለምን እንዲህ እንዳደረገች ማስረዳት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቤት መግዛት ሲሆን፤ ሶስተኛው ልጆቹን ሰብስቦ ማሳደግ የሚል ነው። ይህም ውጥኗ በብዙ እንግልት እንደተሳካላት ትናገራለች።
ጣሊያን የሚቀበላት ሰው ጋር ብታርፍም ያለሥራ መቀመጥ ግን አልተመቻትም። እናም በሰው አገር የቤት ሰራተኝነት ተቀጠረች። ህልሟ የሰው ቤት ሰራተኛ መሆን አልነበረምና ቶሎ ሰርታ የምትለወጥበትን መንገድም ማመቻቸት ጀመረች። በአንዴ ስለማይሳካ ልፋቷን ቀጠለች። ለጊዜው ግን በጣም ተጨነቀች።
በሰው አገር ተያዥ ጭንቅ ነው፤ የሚያሰራም ማግኘት እንዲሁ። አንድ ቀን ጥሩ ሥራ ያሲዛል የሚባል ደላላ ጋር ሄደች። ብዙ ነገር ባይጠይቅም ሴቶችን በጾታቸው መጠቀም የለመደ ነው። እናም ይህንን የሰማችው ሳብሪና አንድ መላ ዘየደች።
የሱማሌ አለባበስ በመልበስ ባለትዳርና የልጆች እናት መስላ ቀረበችው። የአጎቶቿን ልጆች በማሳየትም ባሏ ሞቶባት ከኤርትራ ተሰዳ እንደመጣችም ገለጸችለት። ለጊዜው አመናት፤ የምትፈልገውን ሥራ አስቀጠራት። የጠበቀችው ባይሆንም መጀመሪያ ከነበረችበት የተሻለ ደመወዝ ስለሚከፈላት ተደሰተች።
‹‹ሥራው አንዲት አረጋዊ መንከባከብ ብቻ ነበር›› የምትለው ሳብሪና፤ ብዙ የምታነብበትና ራሷን የምትፈልግበትን ጊዜ እንደሰጣት ትናገራለች። እያንዳንዱን ነገር ስታከናውንም በእውቀት መሆን እንዳለበት የተረዳችው በዚህ ስራ ነበር። ዓመት እንኳን በዚህ ቤት ሳትቆይ ግን ሌላ አማራጭ የምታገኝበትን መንገድ አመቻቸች። ወደ አንድ ቀጣሪ ድርጅትም በመሄድ በ2600 ዩሮ አዲስ ስራ መቀጠር ቻለች። ይህም ቢሆን አዛውንቶች ከመጠበቅ ያለፈ አይደለም። በዚያ ላይ ለአንድ ወር የሙከራ ጊዜ ነው የገባችው። ግን ለእርሷ የተመቻቸ እድል አለና ወራት ወራትን ወልደው ዓመታት ተተኩ።
በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን መንከባከብ ደግሞ ብዙ ፈተና ነበረበት። እሷ ግን ጠንካራ መሆኗ ለውጤት አብቅቷታል። አዛውንቶቹ ሁለቱም ታማሚዎች ናቸው። በተለይ ወንድዬው ከአንድ ወር በላይ ሊቆዩ እንደማይችሉ ለልጆቹ ተነግሯቸዋል። እናም ይህንን ተቀብላ ነበር ስታስታምምና ስትንከባከብ የቆየችው። እርሳቸውን ለማዳንም መፍትሄ ያለችውን አገርቤት ሳይቀር እየደወለች ሀሳብ ትቀበል እንደነበር አትረሳውም። ልፋቷን አምላክ ቆጥሮላት የአንድ ወር ዕድሜ አላቸው የተባሉት አዛውንት በከዘራ መራመድ ጀመሩ።
ለአንድ መድሃኒት መግዢያ 10 ዩሮ ቢያስፈልግም 500 ዩሮ፤ ወርቃቸውንም አውልቀው ‹‹ይህ ለአንቺ ነው›› እያሉ የሚሰጧት ባለቤታቸውም ቢሆኑ ብዙ ያለፏት ነበር። ሆኖም እርሷ በሌብነት ማንነት አልተገነባችምና ይህንን ሁሉ ለልጆቻቸው ታስረዳ ጀመር። ገንዘቡንም ሆነ ወርቁን በማስቀመጥ ታስረክባለች። ሆኖም ልጆቹ ግን እርሷ ባሰበችበት ሁኔታ አልተረዷትም። ይልቁንም ወላጆቻችንን እየተንከባከበችልን አይደለም ብለው ይጠረጥሯት ገቡ። አልፈው ተርፈው የመከታተያ ድብቅ ካሜራ ቤቱ ውስጥ ገጠሙ። ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ሳብሪና አታውቅም ነበር። የተለመደ ስራዋን ከመስራት ውጪ።
‹‹ምንም ሰው በዚያ አገር የሚረዳኝ የለም። የሚመክረኝም እንዲሁ። ስለዚህ መካሪም፣ አቅጣጫ ጠቋሚም ራሴን አድርጌ ነበር የታመሙ እናትና አባታቸውን ለመንከባከብ የገባሁት›› የምትለው ሳብሪና፤ አንድ ቀን የተለየ ተአምር እንደተፈጠረ ታነሳለች። ይኸውም በድብቅ ካሜራ ሲከታተላት የቆየው ቤተሰብ የባንክ ስቴትመንት ይዞ መጥቶ ያመሰግናት ጀመር።
‹‹አንቺ ሰራተኛችን ሳትሆኚ እህታችን ነሽ። እኛ ቤት አንቺን የላከሽ ፈጣሪ ነው።›› አሏት። ግራ የገባት ሳብሪናም ‹‹ምን ማለት ነው›› አለች። እነርሱም ‹‹አንቺ ከገባሽ በኋላ ለምግብም ሆነ ለመድሀኒት የሚወጣው 500 ዩሮ ብቻ ነው። ስለዚህም ከዚህ ቀደም የነበሩ ሰራተኞች እያታለሉ እንደሆነ ተረድተናል። የአገርሽን ሰው አምጪና አንቺም እድሜሽ ለሥራ ስላልደረሰ ተማሪ›› አሏት። እድለኝነቷን በማመስገን የተባለችውን አደረገች።
መማር ጀመረችና ሁለት ዲግሪዎችን በሁለት የትምህርት መስክ ከያዘች በኋላ በመምህርነት ለዓመት ያህል ማገልገል ግዴታዋ ነበርና አስተማረች። ከዚያ የራሷን ሥራ ከፍታ መስራት ቀጠለች። ምክንያቱም ያገኘቻቸው ቤተሰቦች አሳድገው ለቁምነገር አብቅተው ብቻ አልተዋትም። የውርስም ተካፋይ አድርገዋታል። ስለዚህ ‹‹ቪታጁዬዛ›› የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ከፍታ የሰብአዊ መብት ጥብቅና መቆም ጀመረች።
ህልሟን እውን ለማድረግ አገሯ መጥታ በጎ አድራጎት ድርጅት ከፍታ ለመስራት ስትሞክር በአንዳንድ ሀሰተኞች ምክንያት እንዳቋረጠችው የምትናገረው እንግዳችን፤ የእነርሱ ፈተና የሲኦልን ጥግ አሳይቷት እንደነበር ትገልጻለች። ሆኖም ግን በአገር ተስፋ አይቆረጥምና ዳግም ሰውን ለመርዳት እንደመጣች ትናገራለች።
አንዲት ፓስተር ልጆቹን ትተሸ መሄድ አትችይም ያለቻትና ቼክ የሰጠቻት ነገር መቼም እንደማይረሳት የምታነሳው ሳብሪና፤ በጎ ማድረግ ከአገር ያሰደደኝ ነው። እናም ያንን መተው አልችልም ትላለች። ስለዚህም በጣሊያን እያለች በጆይፉል ድርጅቷ ተመዝግባ ህጋዊ እውቅና ኖሯት የምትሰራበትን ድርጅት አገሯ ላይም እንድትሰራበት የሆነው ለዚያ እንደሆነ ትናገራለች።
‹‹ጆይፉል›› እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የመመስረት እቅድ እንዳልነበራት የምትናገረው እንግዳችን፤ ሀብታም እያለ ደሀ መቸገር የለበትም ስትል በመንፈሳዊ ቅናት እንደጀመረችው ታስረዳለች። ይህ ደግሞ ውጤታማ የሚሆነው በህጋዊ መንገድ መስራት ሲቻል መሆኑን አምና ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ኤልሻዳ›› በሚል እኤአ በ2005 ተመዝግባ ለሁለት ዓመት ሰርታለች። በዚህ ደግሞ ለ16 ልጆች መድረስ ችላለች። በህጻናት ስም የመለመኑ ሁኔታ ሰፍቶ ለራስ ጥቅም ብቻ የሚሰራ በአገሪቱ ላይ መበራከቱና በልጆቹ ስም መንግስትንም አገርንም የሚያጭበረብር መብዛቱን ማስተዋሏ ሥራውን ጠልታ ድርጅቱን እንድትዘጋው እንዳደረጋት አጫውታናለች።
እኤአ በ2012 ዳግም በጎ ሥራዋን ለማስቀጠል ‹‹ኤልሮኤ›› ብላ ድርጅት እንደከፈተች ያጫወተችን ባለታሪኳ፤ በዚህ ሥራዋ ለ60 ልጆች ደርሳለች። ፈተና እየበዛባትም ቢሆን ሳታቋርጥ ስሙ ተግባሯን በደንብ እየገለጸላት እንዳልሆነ በመረዳቷ ‹‹ጆይፉል›› በሚል ሰይማ መስራቷን ቀጠለች። ሰው ሁሉ ደስታውን ሸጦ መለመን የለበትም ስትልም ደስተኛ ህይወት እንዲኖሩ በሚል ስሙን ሰይማ 104 ልጆችን በመርዳት ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ ውስጥ 20 ህጻናት ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑም ትናገራለች። ይህንን ሥራ በሦስት ክፍለ ከተሞች ላይ እየሰራች መሆኗን አጫውታናለች።
‹‹በብዙ ችግር ውስጥ ባልፍም እኔን አንድ የውጪ ዜጋ እረዳኝ። ለአገሬ የምሰራበትን ምቹ ሁኔታም ፈጠረልኝ። የአገሬ ልጆች ግን ማንም የላቸውም። ስለዚህም አንድ ጡብ መወርወሬ ግዴታ እንደሆነ ሥለሚሰማኝ ነው የምሰራው›› የምትለው ባለታሪኳ፤ ከ2017 ጀምሮ ልዩ ፍላጎት ተጠቃሚዎች ላይ በስፋት መስራት እንደጀመረችና አሁን ላሉት 20 ልጆች ኮተቤ አካባቢ የህጻናት ማቆያ ከፍታ እየሰራች መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይም ይህንኑ ማስፋት እንደምትፈልግ ነግራናለች።
ልጅ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ማደግ የለበትም ብላ የምታምነው ሳብሪና፤ ጆይፉል የኳስ ቡድንም አቋቁማ ደስተኛ የሚሆኑበትንና ልዩ ፍላጎታቸውን የሚያወጡበትን መድረክ ፈጥራለች። ከዚያም አለፍ ሲል በየዓመቱ ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ተማሪዎች ከልዩ ፍላጎት ትምህርት ወጥተው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ታደርጋለች። በቀጣይ አቅም ከፈቀደላት ደግሞ ይህንን ሥራ በየሰፈሩ ለመስራት አቅዳለች።
ቀጣዩ ውጥን
ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው ልጆች ብዙዎቹ የሚወጡት አነስተኛ ኑሮ ካላቸው ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ የምታስረዳው ሳብሪና፤ መተጋገዝ ያስፈልገዋልና መንግስት ቢያንስ በየሰፈሩ ያሉ የተዘጉ የቀበሌ ቤቶችን ቢያዘጋጅልኝ ለብዙዎች መድረስ እችል ነበር ትላለች። ይህ ደግሞ ቤተሰብ ልጁን ይዞ ከመቀመጥ እንዲድን፤ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቅና ልጆችም የፈለጉት ስኬት ላይ እንዲደርሱ እንደሚያስችል ታስረዳለች።
በቀጣይ እቅዷ ያካተተችው ነገር እንዳለ የምትናገረው እንግዳችን፤ በማይክሮ ፋይናንስ በማደራጀት የልጆቹ ቤተሰቦች የሚታገዙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስባለች። በዚህም በልጆቻቸው ምክንያት እየተጉላሉ ያሉትን እናቶች እንደምታሳርፍ እምነት አላት። አሁን ያላት የገቢ ምንጭ ውስን በመሆኑም መንግስት እንዲደግፋት ትሻለች። በተለይ ዕቅዷን የምታሳካበት የመስሪያ ቦታ ከመንግስት እንዲመቻችላት ትፈልጋለች።
የሁልጊዜ ህልሟ በልመና ሰውን መርዳት ሳይሆን ሰርታ እያሰራች በምታገኘው ገቢ ሰዎችን መለወጥ ነው። የገቢ ምንጯን ለማሳደግ ‹‹አንድ ቡና ለአንድ ልጅ›› የሚል ፕሮጀክት ነድፋ ገቢ ማሰባሰብ እንደቻለች ትናገራለች። በዚህም ይህንንም ልትቀጥልበት እንደምትፈልግ አጫውታናለች። ከዚያ ባሻገር ቋሚ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ ለመስራትም አቅዳለች።
ሌላው ውጥኗ ደግሞ ሎጅ መስራት ሲሆን፤ ሙሉ ወጪውን የሚሸፍንላት በጎ አድራጊ አካል እንዳገኘችና መሬት ብቻ እንደምትፈልግ አውግታናለች። ቦታውን መንግስት ከሰጣትም ልጆቹ ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ሰው የሚጠቀምበት ብዙ ነገር እንደምትሰራም ነው የነገረችን።
ሳብሪና የበጎ አድራጎት ሥራዋ ልጆች በመርዳት ብቻ የተገደበ አይደለም። ባደገችበት አካባቢ በመሄድ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሱ አድርጋለች። አሁንም ለሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን መድረስ እንዳለባት ታምናለችና ‹‹አሁን ጉልበት ባለኝ ጊዜ እንድሰራ አግዙኝ ›› ትላለች።
የሀብታም ልጆችን የልዩ ፍላጎት ትምህርት በትርፍ ጊዜዋ በማስተማር እስከ ስድስት ሺ ዩሮ ታገኝ እንደነበርና አሁንም አጫጭር ኮንትራቶችን በመፈራረም ወደ ውጪ አገር በማምራት ይህንን ስራዋን በማከናወን ገቢ እንደምታገኝ ነግራናለች።
መልዕክት
‹‹ በህይወቴ በጣም የምጠላው መለመንን ነው። ነገር ግን ልጆቹን ለማገዝ ደግሞ ይህንን ማድረግ ግዴታ ነው›› የምትለው ባለታሪኳ፤ 14 ዓመት የሞላው ድርጅቷ ብዙ ለውጥ እንዳያመጣ የሆነው በአቅሟ ልክ እንዳትሰራ ባደረጓት አንዳንድ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች። እናም የመጀመሪያ መልዕክቷ ለሀገርና ለወገን የሚሰሩ ሰዎችን የሚያደክሙ ሰዎች ከመጥፎ ተግባራቸው ይታረሙ የሚል ነው። በየደረጃው አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ነገ አሁን ባሉበት ቦታ እንደማይቆዩ አውቀው በተሰጣቸው የሀላፊነት ጊዜ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል አለባቸው ትላለች።
‹‹የማግዛቸው ልጆች የእኔ አይደሉም። የሁላችንም ናቸው። ተምረውና ተመርቀው ሲወጡም ለአገራቸው፣ ለቤተሰባቸው እንዲሁም ለወገናቸው የሚደርሱ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። እናም በድህነት የምንታወቅበትን ነገር ለማጥፋት በጎነታችን ያሸንፈንና ከግል ጥቅም ይልቅ ለአገራችንና ለወገናችን ቅድሚያ እንስጥ›› ።
ሰውን መርዳት የሚፈልግ ሁሉ ኢኮኖሚው ከፍ እስኪል ድረስ መጠበቅ የለበትም፤ ዛሬ ፍላጎቱን ገትቶ ካለው መቀነስ መልመድ ካልቻለ እያለውም መስጠት አይችልም። እናም ለመስጠት ቆራጥ ውሳኔ መወሰንም እንደሚያስፈልግ ትመክራለች። 50 ብር እያለ 10 ብር ለመስጠት መወሰን እንጂ ቢኖረኝ ኖሮ አድርገው ነበር ማለት እንደማይገባም ትናገራለች።
‹‹በተለይ 10 ብር ምን ያደርጋል፤ ይህን ሰጥቼ ወር እንዴት እደርሳለሁ›› የሚሉ ከሆነ የመርዳት ፍላጎቱ የሌላቸው መሆናቸውን ማመን አለባቸው። ካለን ትንሿ ላይ ቀንሰን መስጠትን መለማመድ ይገባል የሚለው እምነቷ ጠንካራ ነው። በጎነት ይዞት የሚመጣ በረከት ስላለ ‹‹ተጠቀሙበት›› የሚለው የማሳረጊያ መልዕክቷ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 15/ 2012
ጽጌረዳ ጫንያለው