«እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም። አሁንም አገርን የሚያጠፋ፥ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።
ያገሬ ሰው! ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለሚሽትህ፣ ለሃይማኖትህ፣ ለሀገርህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጠላኛለህ ፣ አልተውህም ! ማርያምን ! ለዚህ አማላጅ የለኝም ! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና እስከ ጥቅምት እኩሌታ የሸዋ ሰው ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።» ዳግማዊ አፄ ምኒልክ
ታላቁ የጥቁር ህዝብ ድል ዓድዋ የጀመረው ከጦርነቱ በፊት ህዝቡ የንጉሠ ነገስቱን ጥሪ ሰምቶ ከጫፍ ጫፍ በተመመበት ዕለት ነው። አዋጁም ገና ከመነሻው ላይ የድል አድራጊነት መንፈስ እንደረበበበት የሚያመላክት ያስተላለፉበት የክተት አዋጅ ነው። ሁሌም አልሸነፍ ባይና ኩሩው ኢትዮጵያዊም ጥሪውን በሚገባ ተግብሮ ጣሊያንን ዶግ አመድ አድርጎ ዳር ድንበሩን ማስከበር ችሏል።
ይህ ሁሉ ከሆነ ዛሬ 124 ዓመት ሞላው። ሆኖም ድሉ እንደተዘከረና በጥቁር ህዝቦች ልብ ውስጥ እንደተወደሰ ይኖራል። አኩሪው ገድል በተለያየ አውድና ሁነት ቀኑን ሊመጥን በሚችል መልኩ እየተከበረ ከአንድ ምእተ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ዛሬ የድል ወር እየተባለ በሚጠራበት የካቲት ወር ውስጥ እንደመገኘታችን ይህንን ድል በልዩ ሁኔታ ለማሰብ ወደናል። ይህ አምድ የኪነ ጥበብ አምድ እንደመሆኑም ድሉንና ኪነ ጥበብን የሚያስተሳስር ርእስ ነው ይዘንላችሁ ለመቅረብ የፈለግነው። ከዚያ አስቀድመን ግን ስለ ስእል እና ስነ ጥበብ ጥቂት ልንላችሁ ወደድን።
አድዋና ስነ ጥበብ
በተለያዩ የኪነ-ጥበብና ስነ ጥበብ ዘርፎች ድሉ እየተዋዛ ለትውልድ ህያው በሆነ መንገድ እየቀረበ ቆይቷል። በተለይ በስነ-ጥበብ አውድ ግዙፉን ታሪክ ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት ታላቅ አቅምን መፍጠር ይቻላል። ይህም በጥቂት ስነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ፍቃደኞች እየተከናወነ ነው። ሁሉም ይህን ታሪካዊ ቀን ለመዘከር ፍቃዱን ሲያሳይ ደግሞ ከዚህም በበለጠ ጎልቶና ደምቆ እንደሚከበር እሙን ነው። የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ማሳያዎች አንዱን ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የህብር ሰዓሊያን ቡድንን እናስታውሳለን። ስብስቡ አድዋን በተመለከተ የተለያዩ ስራዎችን በማቅረብ ድሉን ለማጉላትና ለማወደስ ጥረት አድርገዋል። በውጤቱም ስኬት አስመዝግበዋል።
የአድዋ ጦርነት የኋላ ታሪክ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አኩሪ ድል የሁሉ አፍሪካዊ ደማቅ ታሪክ ነው። ይህንን ሀቅ መላው ዓለም የማይዘነጋው ስለመሆኑ ደግሞ በብሩሾቻቸውና በቀለማቸው አሳምረው ማስቀመጥ ችለዋል። ህብር የሰዓሊያን ቡድን ከአድዋ ተራሮች ጥግ የወደቁት ጀግኖች፣ የዛሬው ትውልድ ህያው ምስክሮች ስለመሆናቸው በሸራዎቻቸው ላይ አስቀምጠዋል። በአድዋ የረገፈው አጽም፣ የፈሰሰው ደምና ስለ ሀገር ሲባል የተከፈለው መስዋዕትነት ሁሌም በትንሳኤ አዲስ ሆኖ እንደሚወሳ ምሳሌ መሆን ችለዋል።
ዛሬም እንደ ጥንቱ
ሰዓሊ አብዱልቃድር መሀመድ የህብር ሰዓሊያን ቡድን አባል ነው። እርሱ እንደሚለው በስነ ጥበብ አድዋን ለመዘከር የተጠራው የክተት አዋጅ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸው ከስክሰው ያቆዩንን ሀገር ፈጣሪ የቸረንን ጥበብ ተጠቅመን ታሪካቸውን ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ጥሪ ነው ይላል።
‹‹የካቲት ታላላቅ ገድሎች የተፈጸሙበትና አንፀባራቂ ድሎች የተመዘገቡበት ወር ነው›› በማለትም የካቲት ለኢትዮጵያውያን፣ ለመላው አፍሪቃ ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል በደማቁ የታተመበት የዓድዋ ድል የተበሰረበት ወር መሆኑን ይናገራል። በመሆኑም በተለያዩ ሙያ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በስራዎቻቸው የዓድዋን ድል ክንውኖች በድምቀት ሲያከብሩት 124ኛው ዓመት ላይ ደርሰዋል ይለናል።
አብዱልቃድር እንደሚናገረው ህብር የሰዓሊያን ቡድን ከዛሬ ዓመት በፊት የተቋቋመ ማህበር በ14 ሰዓሊያን የተመሰረተ ነው። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ «ዝክረ ዓድዋና የነፃነት ገድል አድዋ» በሚል መሪ ሃሳብ ታሪክን አጉልቶ የሚታይበት የስነ ጥበብ ሥራዎች ለተመልካች በማቅረብ የክተት አዋጃቸውን እንደጀመሩ ገልፀዋል። በተጨማሪም ‹‹ውብ ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሀሳብም የኢትዮጵያን ውብ ገጽታ በማሳየት ረገድ የስእል አውደ ርእይ ሕዳር ወር ላይ ለተመልካች እንዳቀረቡ ያነሳል። አሁን ደግሞ ከየካቲት 19 ቀን 2012 ጀምሮ ‹‹የነፃነት ገድል አድዋ- ፪›› የስእል አውደ ርእይ በአዲስ አበባ ሙዚየም ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል።
የሰአሊያን ቡድኑ ሊቀመንበር የሆነው ሳሙኤል እንዳለማው በበኩሉ ስለ ሁነቱ በተጨማሪ ሲያስረዳ እንደገለፀው፤ የስእል አውደ ርዕይው ለተከታታይ አስር ቀናት 14 ሰዓሊያን ሥራቸውን የሚያቀርቡበት ነው። ስራዎቹ በሙሉ የአድዋን ጦርነትና ድል አጠቃላይ ታሪክ የሚያሳዩ ይሆናሉ።
ሊቀ መንበሩ ‹‹ ይህ ታላቅ አውደ ርእይ በስኬት እንዲጠናቀቅና ሳይቋረጥ ዘመናትን እንዲሻገር ፤ የጥበብ የክተት አዋጆችን እንዲሳካ የዓላማችን ደጋፊ የሆኑ የጥበብ ወዳጆችን አብዝተን እንፈልጋለን›› በማለት አላማውን እነርሱ ይጀምሩት እንጂ ከጎናቸው ተጨማሪ ደጋፊ እንደሚፈልጉ ይናገራል።
በዋናነት ደጋፊ የሚያስፈልጋቸውም ከዚህ እንደሚከተለው ለተቀመጠው ዓላማ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ያስረዳል። የመጀመሪያው ህብር የሰዓሊያን ቡድን ‹‹የነፃነት ገድል አድዋ›› የስእል አውደርእይ ተተኪው ትውልድ የአባቶችን ገድልና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በጥበብ እየተዝናና እንዲያውቅ ማድረግ እንደሆነም ይገልጻል። በተጨማሪም የአድዋ ድል በተለያዩ መስኮች ከሚተረከው በተጨማሪ በስዕል አማካኝነት ያልተዘመረላቸውን ኢትዮጵያዊ ጀግኖች ማወደስ፣ታሪካቸው ቋሚ ቅርስ ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማስቻል መሆኑንም ያስረዳል። ይህ ሁነት ቀጣይነት ኖሮት ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ለትውልድ ለማሻገር ከአስቀመጡት ግብ ውስጥ እንደሚካተትም ይገልፃል። በተለየ መልኩ ደግሞ ህብር የስነ ጥበብ ማእከል በማቋቋምና ኢትዮጵያዊነት ሁሌም እንዲዘመርለት ቀለሙን ፣ማንነቱን፣ ባህሉን ብሎም ወጉን ጠብቆ የትውልድ መኩሪያና መመኪያ እንዲሆን ለማስቻል እየሰሩ እንደሆነም ይናገራል።
የዝግጅት ክፍላችን ህብር የሰአሊያን ቡድን የአድዋ ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ በመሆኑ በስእል አማካኝነት ተተኪው ትውልድ ገድሉን በሚገባው እንዲረዳው ማስቻል፤ ታሪኩም በስዕል ለመጭው ትውልድ በቋሚ ቅርስነት እንዲተላለፍ የማድረግ አላማን አንግበው እንደተነሱ መረዳት ችሏል። ይህ ተግባር በሌሎችም የጥበብ ዘርፎች ላይ ጎልቶ መታየት እንዳለበትም እምነቱን ለማስቀመጥ ይወዳል። ኪነ ጥበብ፣ ስነ ጥበብ እና ስነ ፅሁፍ በአገር ግንባታ፣ በታሪክ አስተምሮት፣ በባህል እና የሞራል ልእልና ግንባታ ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም ሊታወቅ እንደሚገባ መልዕክቱን ያስተላልፋል። ከዚህ መነሻ እነዚህን የሰዓሊያን ቡድን ዓላማ መደገፍ ትውልድን ማነፅ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ይግባ እያልን ዳሰሳችንን በዚሁ ቋጨን።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/ 2012
ዳግም ከበደ