ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የምርምርና የፈጠራ ክህሎት ያለው፤ የሰለጠነና ብቃቱ የተረጋገጠ የሰው ሃይል በማፍራት የካበተ ልምድ የላትም። ያም ሆኖ ግን በተለያዩ ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ምሁራን መፍለቂያ ናት። አሁንም ቢሆን በየዩኒቨርሲቲዎቿ ለከፍተኛ ደረጃ የሚበቁ ወጣቶች ይዛለች። እነዚህ ተማሪዎች ለዘርፉ መጠንከር መሰረት ናቸውና ማበረታታትና መደገፍ ተገቢ ነው።
በመስኩ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የኢትዮጵያ ፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር፤ ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል፤ ለፈጠራና ለምርምር ሥራዎች መሠረት የሚል ድጋፍና ማበረታቻ ያደርጋል። ባለፉት ስምንት ዓመታትም በየዓመቱ ለዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ተማሪዎች ውድድር በማዘጋጀት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ።
የኢትዮጵያ ፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ከ20 ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፤ ዶክተር ተስገራ በዳሳ ደግሞ የኢትዮጵያ ፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። ማህበሩ ሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ የፊዚክስ ማህበራት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ፤ በፊዚክስ ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡና ለህብረተሰቡ አጋዥ የሆኑ የምርምር ስራዎች ለሰሩ፤ የቅድመና የድህረምረቃ ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ የማበረታቻ ሽልማት እየሰጠ ይገኛል።
ማህበሩ ሁለት አይነት ሽልማቶች ይሰጣል። አንደኛው፤ ከሰሜን አሜሪካ የፊዚክስ ማህበራት ጋር በመተባባር የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተጠሪ በነበሩት ህንዳዊ ፕሮፌሰር ኤ.ቪ ጎላፕ ስም የተሰየመ ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታት በየዓመቱ አንድ ሴት የድህረ ምረቃ ተማሪ የምትሸለምበት ነው። በዚህ ዘርፍ በዘንድሮው ሽልማት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሴት ተማሪ ተሸላሚ መሆኗን ዶክተር ተስገራ ገልጸውልናል።
እንደ ዶክተር ተስገራ፤ በዘንድሮው ዓመት በሰሜን አሜሪካ የፊዚክስ ማህበራት የስኮላርሽፕ ሽልማት ያገኙት የቅድመና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከሐሮማያ፤ ከአዳማ፤ ከአምቦ፤ ከጂንካና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ተማሪዎች ናቸው። ሆኖም ስኮላርሽፕ ሲባል ነጻ የትምህርት እድል ሳይሆን ትምህርት ላይ ያሉትን ለማበረታታት የእውቅና ሰርተፊኬትና የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥበት ነው። ሽልማቱ የትምህርት ውጤትን፤ የምርምር ስራዎችንና የማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎን፤ እንዲሁም ሌሎች የድጋፍ ማረጋገጫዎችን በመስፈርትነት በማስቀመጥ የሚሰጥ መሆኑን ይናገራሉ።
ፊዚክስ ለማናቸውም የህዋ ሳይንስ፤ ለኢንጂነሪንግና ለጤናም የሚያገለግል የትምህርት መስክ ነው የሚሉት ዶክተር ተስገራ የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ግን በብዙዎች ዘንድ አይወደድም ይላሉ። የፊዚክስን ትምህርት ተማሪዎች እንዲወድዱት ለማድረግ በርካታ ስራዎቸ እየተሰሩ መሆኑን በመጠቆምም በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ፊዚክስ ሁሉም የሚማሩት የወል ትምህርት/ ኮመን ኮርስ/ ሆኖ ተካትቷል። ብለዋል።
ለአብዛኛው ሴቶች የማይደፈር የሚመስለውን የፊዚክስ ትምህርት በመድፈር ዘንድሮ ለሽልማት ከበቁ የፊዚክስ ተሸላሚዎች መካከል ሃና ተሾመ አንዷ ናት። ሃና የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የድህረምረቃ ተማሪ ስትሆን፤ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚያመጡ ነገሮችን በመለየት ሁለት ምርምሮች በማከናወንና በፊዚክስ ክበባት ውስጥ ባደረገችው ተሳትፎ ለሽልማት መታጨቷን ትናገራለች ።
በተለያዩ ጊዜያት በፊዚክስ መስክ በሰራቻቸው ስራዎች የተለያዩ ሽልማቶች መውሰዷን የምትናገረው ሃና፤ ሽልማቱ ለስራዎቿ እውቅና የሚያስገኝላትና የሚያበረታታት መሆኑን ትገልጻለች። በዘርፉ ልቆ ለመውጣት፤ ይበልጥ ኃላፊነት በመውሰድ በርካታ ስራዎች ለመስራት አቅም እንደሚፈጥርላትና በተለይ በምርምር ስራ እንድትገፋ የተስፋ ብርሃን ያሳያት መሆኑን ትናገራለች።
ሃና፤ በዘርፉ ያሉ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የተሻለ ኃላፊነት በመውሰድ መስራት እንደሚችሉ ማሳያ ነው። “አብዛኛው ተማሪ ከውጪ ሆኖ የሚያስበው ፊዚክስ እንደሚያስፈራና ከባድ እንደሆነ ነው። ነገር ግን፤ ውስጡ ሲገቡ ይለያል። ማንኛውም ነገር ውስጥን አሳምኖ እችላለሁ፤ እወጣዋለሁ ተብሎ ከተገባበት የሚከብድ ምንም ነገር የለውም። በማለት የሚያስፈልገው ፍላጎት ብቻ መሆኑን ትገልጻለች።
“ፊዚክስ እጅግ በጣም ደስ የሚል ትምህርት ከመሆኑም በላይ ከምናየው ነገር ከተፈጥሮ ጋር በማገናኘት ወደ መልካም ነገር በመለወጥ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ መስክ ነው። አብዛኛውን ሴቶች ብዙ ጊዜ ፊዚክስን ደፍረው አይማሩትም።” የምትለውና ደፍረው ቢማሩት ግን የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ በማለት የምትናገረው ሌላኛዋ ተሸላሚ ብርቁ ታምሩ ናት።
ብርቁ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የፊዚክስ ተማሪ ናት። ለሽልማት ያበቃትም በፊዚክስ ትምህርት ባስመዘገበችው ውጤትና በአካባቢ ላይ ያሉ ነገሮችን በመጠቀም ችግሮች በምታደርገው እንቅስቃሴ መሆኑን ትናገራለች። ሽልማቱ ለወደፊቱ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ በያዘችው እቅድ የበለጠ ለመስራት ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርላትና እንደሚያተጋት ገልጻ፤ በዘርፉ ምርምሮች ላይ በኃላፊነት ስሜት እንድትሳተፍ የሚያደርጋት መሆኑን ትናገራለች።
ሌላኛው ተሸላሚ ጌታቸው አንክሽ ይባላል። የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሦሰተኛ ዓመት የፊዚክስ ተማሪ ነው። ለሽልማት የበቃውም በፊዚክስ ትምህርት ባስመዘገበው ውጤትና በትርፍ ጊዜው የአንደኛና የሁለተኛ ዓመት የፊዚክስ ተማሪዎችን በመረዳት በሚሰጠው አገልግሎት፤ እንዲሁም ከተማሪዎች ህብረት አባላት ጋር አብሮ በመሳተፉ ባበረከተው አስተዎጽኦ እንደሆነ ይናገራል።
ጌታቸው ሽልማቱ አበረታች በመሆኑ የበለጠ እንዲተጋ ተነሳሽነትን እንደፈጠረለት ይናገራል። በፊዚክስ ዘርፍ የሚደረጉ ማበረታቻዎች እምብዛም በመሆናቸው ምክንያት አብዛኛው ተማሪ ከወጪ በመፍራት ቀርቷል። ይህ ማበረታቻ ወደፊት በትጋት በመስራት ዘርፉን አንድ እርምጃ ለማራመድ የሚያግዝ መሆኑንም ይጠቁማል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16 / 2012 ዓ.ም
ወርቅነሽ ደምሰው