አካባቢው በርከት ባሉ ሰዎች ተጨናንቋል፡፡ አብዛኞቹ ኀዘንና ትካዜ ይነበብባቸዋል። ጥቂት የማይባሉትም ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ይጮሀሉ። በርከት ከሚሉት ገሚሶቹ በሰፊው መስክ ላይ የተሠራውን ግንባታ በማፍረስ እንጨቱን ይከምራሉ። ከእነርሱ መካከልም የውስጣቸውን ኀዘን አውጥተው የሚያለቅሱና በተለየ ቁጭት የሚበሽቁ ጥቂቶች አይደሉም። ጀሞ አንድና አካባቢው በተለየ የኀዘን ስሜት ተውጧል።
ሕፃን ያዘሉ እናቶች፣ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች፣ክንዳቸው የፈረጠመ ወጣቶች ሁሉ ስሜታቸው አንድ ሆኗል። ሁሉም ስለመበደልና ትኩረት ማጣት ያወራሉ። ሁሉም ስለ ትናንትናው ችግርና ስለነገው ተስፋ ማጣት ይናገራሉ። «ዛሬም እንደ ዜጋ አልተቆጠርንም» የሚሉት እነዚህ ወገኖች ከቀናት በፊት በተፈቀደላቸው የንግድ ቦታ ላይ የገነቡትን የገበያ ማዕከል እንዲያፈርሱ መገደዳቸው በከፍተኛ ብሶትና ኀዘን ውስጥ ጥሏቸዋል።
የስምንት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ አስካለ ለዓመታት በህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ቆይታለች። ይህ መሆኑ ብቻ ግን ህይወትን ለእሷ ምቹ አላደርገውም። ዕጣንና ጌጣጌጥ ለመሸጥ የሚያስችል ቋሚ ቦታ የላትምና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መሯሯጥና መጋጨት ግድ ሲላት ቆይቷል።
የእርሷን እጅ ዓይተው የሚያድሩት ስምንት ልጆቿን ለማስተማርና በወጉ ለማሳደግ ስትል ያልሆነችው የለም። ከሁሉም ግን በአንድ ወቅት የያዘችውን ዕቃ ከደንብ አስከባሪዎች ለማስጣል ስትል የደረሰባትን ችግር ዛሬ በተለየ ኀዘን ታስታውሰዋለች። የዛኔ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። በዕለቱ እየደካከማት ከቤቷ ወጥታ ከለመደችው መንገድ ዳር ትቀመጣለች። ወዲያው ግን አንድ ደንብ አስከባሪ በድንገት ደርሶ በእርግጫ ይመታታል። ይህን መቋቋም ያቃታት ወይዘሮም ከአስፓልት ወድቃ ትዘረራለች። በዚህ ምክንያትም ያረገዘችው ጽንስ ተጨናግፎ ለከፍተኛ ህመም ትዳረጋለች።
ወይዘሮዋ ከዚህ ክፉ አጋጣሚ በኋላ በጤና ውሎ ለማደር ስትቸገር ቆይታለች። ይሁን እንጂ ሌላ መተዳደሪያ ስለሌላት ከዚህ ውሎ መራቅ አልተቻላትም። ዛሬም የምትሸጠውን ይዛ ከመንገድ ዳር ትውላለች። አሁንም ከደንቦች ጋር ትሯሯጣለች። ይህች እናት አቅም ስላነሳትና ጉልበት ስላጣች ራሷን የምትስትበት ጊዜ ይበረክታል።
አስካለ ይህ መሰሉ ታሪክ የእርሷ ብቻ እንዳልሆነ ትናገራለች። እንደ እርሷ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የሆኑ በርካቶች በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ ይገኛሉ። ከቀናት በፊት ግን ከዚህ አስቸጋሪ ህይወት የሚታደግ የምሥራች በመስማታቸው የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ምዝገባ እንዳካሄዱ ትገልጻለች። እነርሱ እንደሚያውቁትና እንደተነገራቸው ከሆነ ከዚህ በኋላ በጎዳና ላይ መነገድ አግባብ ያለመሆኑን ነው። ይህን እውነትም ተከትሎ ከወረዳው ጽህፈት ቤት በተገኙ አመራሮች ተሸንሽኖ በተሰጣቸው መሬት ላይ የድርሻቸውን ለመውሰድ እያንዳንዳቸው አንድ ሺ ብር እንዲከፍሉና ስለ ህጋዊ ነጋዴነታቸውም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በስማቸው እንዲወጣ ይደረጋል። ይህ በሆነ ጊዜም የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች የሆኑ ሁሉ ዕንባቸው የሚታበስበት ጊዜ መድረሱን አስበው ይደሰታሉ። ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መሯሯጥና ንብረታቸውን መነጠቁ፣በስጋት መኖርና መሳቀቁ እንደሚቀር አስበውም በተሰጣቸው ቦታ ላይ የንግድ ቤቶቹን መሥራት ይጀምራሉ።
ይህ በሆነ ማግስት ግን ፈቃዱን ከሰጧቸው አካላት ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል። የጀመሩትን ግንባታ እንዲያፈርሱና ቦታውን ነፃ እንዲያደርጉም ተገደድን ይላሉ። ነጋዴዎቹ ይህን ችግራቸውን አቤት ለማለት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ድረስ ለመሄድ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ጉዳዩን የያዘው አካል ምላሽ ይስጣችሁ ከማለት የዘለለ መፍትሔ ያለማግኘታቸውን በኀዘኔታ ይናገራሉ።
ወጣት አዲሱ ፀሐይ በጀሞና አካባቢው በህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ዓመታትን አሳልፏል። ይህን ቦታ ለማግኘት ከወረዳው ጋር ስምምነት መደረሱንና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነትን በሚያረጋግጥ መታወቂያም ምዝገባ ሲደረግ መቆየቱን ይናገራል። እርሱና መሰሎቹ ቦታውን ለክተው ከተረከቡ በኋላ ለህጋዊነታቸው መለያ (ባጅ) ተቀብለዋል።
አዲሱ እንደሚለው ከዚህ ሂደት በኋላ ወደሥራው ለመግባት የጓጉ ነጋዴዎች የተለካውን ቦታ መነሻ በማድረግና ገንዘብ በማዋጣት ግንባታውን ይጀምራሉ። ላስቲክ ለማልበስና ሥራውን ለመጀመር በተዘጋጁበት አጋጣሚ ግን ድርጊታቸውን ከተቃወሙ የወረዳው ጽህፈት ቤት አካላት ግንባታውን እንዲያቆሙ ይነገራቸዋል።
እንደ ወጣቱ ነጋዴ አገላለጽ ከእያንዳንዱ አባል የተሰበሰበ ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ ለግንባታው ሥራ ውሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአናጺነት የእጅ ዋጋ ክፍያ አልተጠናቀቀም። በዚህም ምክንያት ለተጨማሪ ዕዳና ኪሳራ ተዳርገዋል። «ህጋዊ ለመሆን ስንሞክር በህገወጥነት ስያሜ ወደነበርንበት ህይወት እንድንመለስ ተገደናል» የሚለው አዲሱ በመንግሥት ፍላጎትና ስምምነት መሰረት መንቀሳቀሳችን ላልታሰበ ወጪ ስለዳረገን ከሚመለከተው አካል መፍትሔን እንሻለን ይላል።
ወይዘሮ ገነት ታደሰ ህይወታቸውን ለመምራት ዕንቁላል፣ ለውዝና ዕጣን በመሸጥ ቆይተዋል። ወይዘሮዋ ዓመታትን በገፉበት የንግድ ሥራ ህጋዊ አለመሆናቸው በስጋት እንዲኖሩ ምክንያት ነበር። ከጥቂት ጊዚያት በፊት በአካባቢው ሊጀመር በታሰበው አደረጃጀት መታቀፋቸው ግን ተስፋ እንደሆናቸው ይናገራሉ። ለተጠየቁት መዋጮም ከወንድማቸው ብድር በመውሰድ የድርሻቸውን አበርክተዋል። አሁን ግን ግንባታው ሲፈርስ በማየታቸው ከልብ አዝነው እያለቀሱ ነው። መንግሥት እሳቸውን ለመሰሉ አቅመ ደካሞች አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥም ይማጸናሉ።
ወይዘሮ ሲሳይ ንጉሴ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የጀሞና አካባቢው ወረዳ አንድ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ኢ- መደበኛ የሚባሉ ነጋዴዎችን ወደህጋዊ ስርዓት ለማስገባት እንቅስቃሴው ተጀምሯል። የአካባቢው ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴዎችም በዚሁ ሂደት ስር የሚካተቱ ናቸው።
እንደ ወይዘሮ ሲሳይ አገላለጽ፤ በከተማዋ በተያዘው ዕቅድ መሰረት የአካባቢውን ነጋዴዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊ ምዝገባ ሲካሄድ ቆይቷል። ምዝገባው የተለየ ማጣራትና ክትትል የተደረገበት ሲሆን፤ ትክክለኞቹን ለመምረጥም የተለየ ጥንቃቄ ነበረው። ኃላፊዋ እንደሚሉት ግን በቢሮው የተሟላ ባለሙያ ያለመኖሩ ለኢ- መደበኛ ነገዴዎች ምን እንደሚፈቀድና እንደሚከለከል በቂ ግንዛቤ እንዳይኖር አድርጓል።
በባለሙያው ልክ የሚመዘን የዕውቀት ክፍተት መፈጠሩም ሌላ ቦታ የተሠሩትን ከማየት የዘለለ ግንዛቤ እንዳይኖር ማስገደዱን ኃላፊዋ ያምናሉ። ለቦታው የሚሆነውን ባለሙያ ተክቶና ወክሎ በመሥራት ሂደት ጽህፈት ቤቱ የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል የሚሉት ወይዘሮ ሲሳይ፤ በህገወጥ ንግዱ ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ለመለየት የነበረው ጥረትም ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ ሲሳይ ኢ- መደበኛ ነጋዴዎችን ወደህጋዊነት ማምጣት ተቀዳሚ ዓላማ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ እውነታም ለቦታው እንጂ ለግንባታው ሂደት ትኩረት እንዳይሰጥ አድርጓል። ኃላፊዋ እንደሚሉት አዋጅና መመሪያው ለኢ- መደበኛ ግንባታ እንዲካሄድ አይፈቅድም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግን ባልተገባ መንገድ ግንባታውን አካሂደዋል። ነጋዴዎቹ እንደሚሉት ሳይሆን ጽህፈት ቤቱ ለቦታው እንጂ ለግንባታው ፈቃድ የመስጠት መብት የለውም።
የንግድ ቦታው በቋሚነት የሚያገለግል ሳይሆን መንግሥት በፈለገው ጊዜ የሚረከበውና ለቀን ንግድ ብቻ ግልጋሎት እንዲሰጥ የታሰበ ነው። ነጋዴዎቹ በራሳቸው ፍላጎትና አቅም ሌላ ቦታ ያዩትን ለመገንባት መሞከራቸው ለችግር ዳርጓቸዋል የሚሉት ኃላፊዋ አሁንም በግንባታው እንጂ በቦታው ላይ ችግር ባለመኖሩ መታወቂያ የወሰዱ ከ400 በላይ ሰዎች ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በተዘጋጀው ቦታ ላይ የመነገድ መብታቸው የተጠበቀ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ