ለውጡ ከባተ የፊታችን መጋቢት ሁለተኛ ዓመቱን ይደፍናል። በዚህ አጭር ጊዜ በሀገሪቱ ታሪክ ታይተው ተሰምተው የማያውቁ ፤ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ለውጦች፣ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥ ፖለቲካዊ ምህዳሩን የሚያሰፉ፤ ለውጡን ተቋማዊ የሚያደርጉ፤ ሰላምን እርቅን የሚያጠናክሩ፤ የውጭ ግንኙነቱን የሚያሻሽሉ፤ የኢኮኖሚውን ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮች የሚፈቱ ሀገር በቀል ማሻሻያዎች፤ በኢፌዴሪ ካቢኔ የሴቶችን ተሳትፎ ወደ 50 በመቶ ያሳደገ፤ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በሀቀኛ ውስጠ ዴሞክራሲ ሳይቀር የተካ፤ በአባልና በአጋር ድርጅቶች የነበረን ቀይ መጋረጃ የቀደደ፤ ሁሉንም ፍትሐዊ በሆነ አግባብ የሚያሳትፍ ውህድ ፓርቲ ምስረታ፤ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን የሚያጠና እና የእርቀ ሰላም ኮሚሽኖችን ማቋቋም፤ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው የሰላም ሚኒስቴር መቋቋም፤ የዜጎች ክብርን ከግምት ያስገባ ዜጋ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዝግጅት፤ ስንዴንና ዘይትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት መደረጉ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል እንቅስቃሴዎች መጀመር፤ ኢትዮጵያ የራሷን ሳታላይት ማምጠቋ፤ በአረንጓዴ አሻራ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከል፤ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፤ የአንድነት ፓርክ እውን መሆን፤ ወዘተ … ይገኙበታል።
ከዚህ ለውጥ በፊት የተከናወኑ ሶስቱም ለውጦች ስልጣን ላይ ለመቆየትና ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የለውጡን አጋፋሪዎች ጥቅሞች ያስቀደሙ ነበሩ። ልዑል አልጋ ወራሹ ያመጡት ለውጥ እሳቸውንና ባለሟሎቻቸውን ለ50 ዓመት ያህል ዙፋናቸው ላይ ያደላደለ ነበር። በቁሙ እየበሰበሰና በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተነቃንቆ የነበረውን መንበር በቀላሉ የተረከበው ደርግም የተማሪው ጥያቄዎች ከነበሩት የመሬት ላራሹና ! ሕዝባዊ መንግስት ይመስረት ! ለሕዝባዊ ተቀባይነት ሲል የመጀመሪያውን ይመልስና ሁለተኛውን ጥያቄ ግን አዳፈነው። በዚህ የተነሳ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ምሁራን በግፍ ተገደሉ፣ ተጋዙ፣ ታሰሩ፣ ተሰደዱ። ሀገሪቱም ባለብሩህ አእምሮና ሀገር ወዳድ የነበረ አንድ ትውልድ አጣች። እናት የወላድ መካን ሆነች። ምድሯም የደም መሬት ሆነች። በትህነግ/ኢህአዴግ አፈሙዝ ተገዶ ከስልጣን እስኪወርድ ድረስ ለ17 ዓመት አገዛዝ ላይ ቆየ። በእሱ እግር የተተካው ትህነግ በትጥቅ ትግሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሰውቶ ፤ ከዚህ ያልተናነሱትን አካል ጉዳተኛ አድርጎ ፤ በእርስ በርስ ጦርነቱ የተነሳ የሀገር ኢኮኖሚ ደቆ እጁ የገባውን ስልጣን ሌላ ዙር ግፍ መፈጸሚያ፣ የግል ጥቅም ማሳደጃ፣ የስልጣን ጥቅም ማርኪያ በማድረጉ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ዳር እስከዳር በተካሄደ ሕዝባዊ ተቃውሞና ከውስጡ በፈለቁ የለውጥ ኃይሎች ለ27 ዓመታት ጨብጦት የኖረውን የዘረፋና የግፍ ስልጣን ለቆ ተዋርዶ መማፀኛ ከተማው ለመደበቅ ተገዷል።
የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ በእጅጉ ይወስናሉ ብዬ ከማምንባቸው የለውጡ ትሩፋቶች ትህነግ ለቀደሙት 27 ዓመታት በብረት በር ከርችሞባቸው የነበሩት የፖለቲካ ምህዳሩ እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተቋማት በርገድ ብለው መከፈታቸው ነው። በሀገራችን ሰማይ ላይ ‘ረብቦ የነበረው የፍርሀት፣ የጭንቀት፣ የአፈና፣ ተስፋ ቢስነት፣… መንፈስ ተገፎ በምትኩ ከእነ ፈተናዎቹ ተስፋ ያሰነቀ በአልማዝ ወይም በቀይ እንቁ የማይተመን፣ የማይገዛ ድል መቀዳጀት ሌላው ትሩፋት ነው። አንድ ጊዜ ብቻ በምንኖርባት፣ በማትደገም ወይም በፈለግን ጊዜ ወደኋላ በማንመልሳት፣ በማናጠነጥናት rewind በማናደርጋት ህይወት በነጻነት ሀሳብን ከመግለፅ በነጻነት ከማሰብ በላይ ምን አለ ! ?። ሰው በመሆናችን የተጎናጸፍነውን የነጻነት መጎናጸፊያ ከማስመለስ በላይ ምን አለ ! ?
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለውጡን፣ ሀገረ መንግስቱን ከግለሰቦች መዳፍ ፈልቅቆ አውጥቶ ተቋማዊ ለማድረግ የተሄደበት እርቀት ተስፋን ያጫረ ነው። ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፍትሕ ተቋማትን ለመፍጠር፤ አፋኝ ሕጎችን አዋጆችን ለማሻሻል፣ አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በመደበኛም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሰዎች የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የነበረበት በዚህ ሁለት ዓመት በለውጡ የተገኙ ውጤቶች እና በዜጎች ዘንድ የፈነጠቀው የተስፋ ጮራ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ይሁንና የለውጥ ኃይሉ ያስመዘገባቸውን ዘርፈ ብዙ ስኬቶች በአግባቡ ባለማስተዋወቁ ፤ የተግባቦት ስትራቴጂ ነድፎ ቀጣይነትና ወጥነት ባለው አግባብ ባለመስራቱ የለውጡን ተረክ ፣ ትርክት በሴራ /በደባ/ ፖለቲካ ፣ በውሸት ወሬ fake news እና በማንነት ፖለቲካ ጡዘት ተነጥቋል።
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ ሁለት ተጻራሪ ትርክቶች አሉ። ከለውጡ ጎን የተሰለፉ እና ከለውጡ በተቃራኒው የቆሙ ተረኮች። የሚቆጠር፣ የሚዳሰስ፣ የሚለካ ሀቀኛ ለውጥ ተረክ በአንድ በኩል በነጭ ውሸት፣ በሴራ ኀልዮት የሚመራ የፈጠራ ፣ የማንነት ጥላቻ እና የመጠራጠር ተረክ በሌላ በኩል። የሚያሳዝነው ይህ የፈጠራ፣ የሀሰትና የጥላቻ ታሪክ ለጊዜውም ቢሆን አየሩን መቆጣጠሩና በለውጡ ላይ ብዥታን መፍጠር መቻሉ ነው። ይህ ለውጡን ጥላሸት የሚቀባ፣ የሀገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚፈታተን አደገኛ አዝማሚያ ስለሆነ ነገ ዛሬ ሳይባል ሊቀለበስ ይገባል። የለውጥ ኃይሉ የተነጠቀውን ትርክት ሊያስመልስ ይገባል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያ ሀገራችንን እና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !
አሜን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ሞሼ ዳይን