ሥራ ፈላጊን ሥራ ለማስቀጠር የሚከናወን ማንኛውም ተግባር፤ የቃል ወይም የጽሑፍ ማስታወቂያ፣ የምዝገባ፣ የምልመላና የምደባን ተግባራት የሚያጠቃልል ሁሉ ‹‹ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት›› ተብሎ እንደሚጠራ አዋጅ ቁጥር 632/2001 በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ፈላጊን ከተፈላጊ ጋር በማገናኘት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በሠራተኛውና በአሠሪው ድርጅት በኩል የሚባክን ጊዜን በማስቀረት ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ ውጤታማነ ትንም በእጥፍ ያሳድጋሉ፡፡
በኢትዮጵያ በኤጀንሲዎች በኩል ሥራና ሠራተኛን የማገናኘት አሠራር ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በርካታ የአሠራር ክፍተቶች እንደሚታዩ ይነገራል፡፡ ለእዚህ ወጣት ጠይባ ሀሰን አንድ ምስክር ነች፡፡ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ አካባቢ ነበር ያገኘናት፡፡ የመጣችው ከሰሜን ወሎ ሲሆን፤ ሳዑዲ አረቢያ በህጋዊ መንገድ ለሥራ የሚኬድበት ዕድል መመቻቸቱን ሰምታ ነው ወደ ስፍራው የመጣችው፡፡
ለሥራ ወደ ውጭ ለመሄድ አዲስ አለመሆኗንና የአሁኑ ሦስተኛ ጊዜዋ መሆኑን አልደበቀችም፡፡ በሥራና ሠራተኛ አገናኞች በኩል የገጠማትን እንድትነግረን ጠየቅናት፤ ገንዘብ ተቀብሎ መጥፋት፣ ፓስፖርት መደበቅ፣ በተደጋጋሚ ውሸት መናገር፣ የሚነገረው የሥራ ዓይነትና የገንዘብ መጠን የተለያየ መሆን ከገጠሟት ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው።
ወጣት እንድሪስ ጸጋዬ ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በጂኦሎጂ የትምህርት ዘርፍ ክፍል 3 ነጥብ ሥድስት አራት አስመዝግቦ 2008 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ሁለት ዓመታትን ያለ ሥራ አሳልፏል፡፡ ያገኘነው በለገሃር አካባቢ የሥራ ማስታወቂያ ሲያነብ ነበር፡፡ ሥራ ለመያዝ ያልደወልኩለት ኤጀንሲ የለም ይላል ወጣት ጀማል፡፡ በየቦታው ሥራ እናስቀጥራችኋለን የሚሉ ሌቦች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡
ሕጋዊ ይሁኑ ሕገ ወጥ መለየት አይቻልም፡፡ የትምህርት ማስረጃህን ኮፒ ሲቀበሉህ ጀምሮ ሥራ ተገኝቶልሃል በሚል እየጠሩ ገንዘብ እንድትከፍል ይጠይቁሃል ሲል ይገልጻል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሣ ሥዩም እንደገለጹት፤ በሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋሉት ችግሮች አያሌ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኞች በችግር የተተበተቡ ናቸው፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎች ከሕብረተሰቡ፣ ከመገናኛ ብዙሃን አካላት፣ ከተቀጣ ሪው ሠራተኛና ከኤጀንሲዎች ጭምር ይነሳሉ ብለዋል፡፡
ሠራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የዳሰሳ ጥናት መሰረት ችግሮቹ በሁለት ይመደባሉ፡፡ የመጀመሪያው በአገልግሎት አሰጣጡና በሥራ ሥምሪት ዙሪያ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኤጀንሲዎች ከሦስተኛ ወገን ሥራን ተረክበው ሠራተኛ ራሣቸው ቀጣሪ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ከአሠሪና ሠራተኛ መብትና ግዴታ የሚመነጩ ችግሮች መሆናቸውን ተለይቷል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ የአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጎች ምን እንደሚመስሉ መፈተሽ ተገቢ መሆኑን ዳይሬክተሩ አቶ ካሣ አንስተዋል፡፡
የመጨረሻው መረጃና ጥናት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በመሆኑም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ መረጃ መሰብሰብ፣ ጥናቶችን ማካሄድ፣ ትንበያዎችን ማድረግና መረጃ ማሰራጨት ላይ የሚያተኩር መሆኑ በመመሪያው ተመላክቷል፡፡ ይህ የተጠቀሰው ለአብነት ያህል እንጂ አገራችን ያፀደቀቻቸው ወይም የምታፀድቃቸው ኮንቬንሽኖች የአገሪቱ የሕግ አካል እንደሆኑ/እንደሚሆኑ ሕገ-መንግሥቱ ሕጋዊ መሠረት አስቀምጧል።
በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ በዓለም ሥራ ድርጅት የወጡ 21 ስምምነቶች ፀድቀው የአገሪቱ የሕግ አካል ሆነው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ ካሣ ሥዩም ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በዚች አገር ላይ እንዲኖሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ከእነዚህ ሥምምነቶች የሚመነጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 632/2001 እንደተመለከተው፤ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ መንግሥታዊ አካል ያልሆነ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሠራተኛው ገንዘብ ሳይቀበል የሥራ ውል ተዋዋይ ወገን ባለመሆን በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ወይም ከሠራተኛው ጋር የሥራ ውል ስምምነት በማድረግ ሠራተኛን በአገር ውስጥ ወይም በውጭ አገር ለሥራ ለሦስተኛ ሰው የማቅረብ ወይም ሁለቱንም አገልግሎቶች አጣምሮ የሚሰጥ የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው በማለት አስቀምጧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ መብራቴ በበኩላቸው በከተማዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኤጀንሲ ፈቃድ አውጥተው በአገልግሎቱ ዘርፍ የተሰማሩት 454 ተቋማት መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ በተደረገ ክትትልም ከተፈቀደላቸው ሕጋዊ ተግባርና ኃላፊነት ውጪ የተለያዩ ጥፋቶች መፈጸማቸውን በማረጋገጥ የእርምት ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ በመሆኑም 128 ኤጀንሲዎች ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡ 23 ኤጀንሲዎች ፈቃድ መልሰዋል፡፡
303 ኤጀንሲዎች አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል 116 ኤጀንሲዎች ፈቃዳቸው የሥራ ውል በማዋዋል ሲሆን፤ 187 በማገናኘት ብቻ ፈቃድ ያወጡ ናቸው፡፡ በሕጋዊ ሽፋን ሕገ ወጥ ተግባር የሚሠሩ አሉ የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በ222 ኤጀንሲዎች ላይ ክትትል ተደርጓል፡፡ በመሆኑም 81 ኤጀንሲዎች ፈቃድ ባወጡበት የመስሪያ ቦታ አለመገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት ብቻ የተሰማሩ 28 ኤጀንሲዎች በሕገ ወጥነት በርካታ ገንዘብ ከሥራ ፈላጊዎች ሰብስበው የተገኙ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከድግሪ ምሩቃን ሥራ ፈላጊዎች ከአራት ሺህ ብር እስከ ሥምንት ሺህ ብር በሰው ሲያስከፍሉ እንደነበረ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ካሣ ሥዩም የሥራ ውል ተዋዋይ ወገን በመሆን ለሦስተኛ ወገን ሥራ የሚያሠሩ ሕጋዊ ፈቃድ ያወጡ 116 ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕግና መመሪያን ተከትሎ የመሥራት ችግር ያለባቸው መሆኑን በክትትልና ቁጥጥር ከታች የተዘረዘሩት ችግሮች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሠራተኞች የሥራ ላይ አደጋ ሲደረስባቸው የህክምና ወጪ አለመሸፈን ፣ በህዝብ በዓላት ቀን በሥራ ላይ ለሚሰማሩ ሠራተኞች በህጉ መሠረት ክፍያ አስልቶ አለመፈፀም፣ በማህበር የመደራጀት መብት አስቸጋሪና ፈታኝ መሆኑ፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ ቦነስና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሠራተኞች እንዲያገኙ ለማድረግ ትኩረት ያለመስጠት፤የሥራ አልባሳትና መጫሚያዎች በወቅቱ ያለመስጠት፤ሥራ ሲለቁ የተሰጠ የግል አልባስትና መጫሚያዎች ካልመለሳችሁ የሥራ ልምድና መልቀቂያ አንሰጥም በማለት በመያዥነት የመያዝ፤ በአንዳንድ የሥራ ዘርፎች በኤጀንሲ ተቀጥረው በሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ከአንድ በላይ ለሆኑ አሠሪዎች ክትትልና ቁጥጥር የተዳረጉ ሆነውም ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ አሰፋ መብራቴ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲዎች ከነችግራቸውም ቢሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት 54‚624 (ወንድ 34‚548 እና ሴት 20‚076) ሥራ ፈላጊዎችን ለሥራ ማብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ 995 ሕገወጥ ኤጀንሲዎች ሥራ ፈላጊውን ማህበረሰብ በማታለል መሰማራታቸው በክትትል ተደርሶበታል፡፡ ሕጋዊ ዕርምጃም ተወስዷል፤በመወሰድ ላይም ይገኛል ብለዋል፡፡
አዲሰ ዘመን ጥር 2/2011
መሀመድ ሁሴን